ያልዘሩት አይበቅልም ~ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ


(Admin) #1

ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ

የብሔር ፖለቲካን እጅግ ከፋፋይና አደገኛ በሆነ ቅርጹ ተቁዋማዊ እንዲሆን፥ ሰዎች ከሁሉም በላይ በብሔር ማንነታቸው ብቻ እንዲተዋወቁና እንዲፈራረዱ ሲደረግ ዘር እየተዘራ ነበር። መታወቂያ ላይ የብሔረሰብ ማንነት እንዲጻፍ የተደረገው የትራፊክ ሕግ ለማስከበር ስለሚረዳ ነበር ወይስ የግብርና ምርትን ለማሳደግ ስለሚጠቅም?

የኢንተርሃሙዌን ትርክት፥ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ከሩዋንዳ ተጎትቶ በአደባባይ ወደ አገሪቱ የፖለቲካ ተዋስዖ ሲገባ ዘር እየተዘራ ነበር። የኢንተርሃሙዌ ትርክት በብሔረሰብ ማንነት ተከፋፍሎ የመጋደል ትርክት ነው፤ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የማስተማሪያ ትርክት ኢንተርሃሙዌ አልነበረም። የፖለቲካ ነጋዴዎቹ የዚህ ትምህርት መዘዝ የተውሰኑ ዛፎችን እየመረጠ ሳይሆን ጫካውን እንዳለ እንደሚያቃጥለው እንዳይረዱት እብሪትና ድንቁርና ከለከላችው ።

ለኢትዮጵያ ፥ ዩጎዝላቪያንና ሩዋንዳን የመምሰል አሳዛኝ ዕድሉዋ ከ1983 ይልቅ ዛሬ እጅግ የሰፋ ነው። ሊመጣ ካለው እሳት ራሳችንንና ወገኖቻችንን የምናድነው ኢትዮጵያን በማዳን ብቻ ነው። የፖለቲካ ሃይሎች ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማዳን ከሌላው ጋራ ተባብራችሁ ካልሰራችሁ፥ “ብሔራችንን ነጥለን ከእሳቱ እናድናለን” ብላችሁ አትሞኙ።

በዚህ ሂደት የሚተርፈን፥ ብሔር ያለው በብሔሩ፥ ብሔር ‘የሌለው’ በፍጥርጥሩ ተሰልፎ የሞቱና የጠፉ ወገኖቹን መቁጠር ብቻ ነው። ከዚያ በየዓመቱ ቀን እየቆጠሩ “ሰማእታት ወዘተርፈ” እያሉ ደረት መድቃት፥ አጥንት መልቀም እና መቃብር ማሳመር ብቻ ነው። እርግጥ ይኼ ለፖለቲካ ነጋዴዎች ትልቅ እድል ነው፤ በሄዱበት፥ በዋሉበት ባደሩበት አይቅናቸውና!

እልህና ቂም ጊዜያዊ ስሜትን ከማርካት አልፈው ለዘላቂ ሰላም መሠረት አይሆኑም። ክፉ ዘር በማስተዋልና በትእግስት እንጂ በእልህ አይጠፋም። አለዚያ ከማን ወገን ምን ያህል ሰው እንደሚሞት ሒሳብ የመስራት ጨዋታ ላይ ነን ማለት ነው። ለዝርዝሩ ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማሻርን መጠየቅ።