ምሁር ሆድ አደር ሲሆን …! (ይገረም አለሙ)


(Admin) #1

ይገረም አለሙ

የተማረ ሆኖ እውነቱን የማይገልጽ ፣
ባለ ጸጋ ሆኖ ገንዘቡን የማይሰጥ፣
ደሃ ሆኖ መስራት የማይሻ ልቡ፣
ሶስቱም ፍሬ ቢሶች፣
ለምንም አይረቡ።

(ከበደ ሚካኤል የእውቀት ብልጭታ)

ለዚህች ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ ጉዳይ በአጭሩ አንዲህ ነው፡፡ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩና አዲስ አበባ ላይ ሆስፒታል ለማቋቋም በሚል የተሰባሰቡ ሁለት መቶ ሀምሳ የሚሆኑ የህክምና ዶክተሮችን አስመልክቶ ከወር በፊት የተሰማው ዜና ነው፡፡ የስብስቡ አመራሮች ዶ/ር ቴዎድሮስ ለአለም የጤና ድርጅት መሪነት ለመመረጥ የሚያደርጉትን ዘመቻ ደግፈው መግለጫ አወጡ፡፡ በዚሁ ሰሞን አባላቱ ሲሰበሰቡ አንድ አባል የተፈጸመው ድርጊት ከስብስቡ ዓላማ
ውጪ መሆኑን በመግለጽ አንሰራዋለን ለምንለው ሆስፒታል መሰረት ያልጣልን ሰዎች ለመግለጫ መሮጣችን ተገቢ አይደለም በማለት ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡በስብሰባው ቦታ ድጋፍ ለመስጠት ያልቻለ ዶ/ር (ምሁር ) ሁሉ ከስብሰባ ሲወጡ ልክ ነህ የእኛን ሀሳብ ነው የገለጽከው ወዘተ በማለት አድናቆቱን ገለጸላቸው፡፡ ይህ ግን ከተፈጸመው ድርጊት ከሰብሳቢዎችም ከተሰጣቸው ምላሽ በላይ ያበሳጫው እንደሆነ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገለጹ ፡፡ አሳዛኝ አሳፋሪ!

በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚተላለፍ ሃምሳ ሎሚ የሚባል ፕሮግራም ነበር፡፡አዘጋጆቹ አሜሪካ ሄደው በአርቲስት ዓለም ጸይ ወዳጆ ጣይቱ የባህል ማእከል መድረክ ላይ ተገኝተው የቀረጹትን ልከው አሳዩንና አነርሱ ወደ ሀገር ከመመለሳቸው በፊት ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዝን ተሰሰናበተ፡፡አነሳሴ ስለ ፕሮግራሙ የምለው ኖሮኝ ሳይሆን በዛ ፕሮግራም የቀረቡ አንድ ምሁር የተናገሩት ለርእሰ ጉዳዬ መንደርደሪያ ለመጠቀስ አንጂ፡፡ ምሁሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው፣ የርሳቸውን ስምና የእለቱን ፕሮግራም ርዕስ ባላስታወስም የተናሩት የሚረሳ አይደለም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ምሁር የሚለው መጠሪያ አይገባንም አሉና ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት እስከ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ የሚደረስው እያንዳንዱን እርከን ለማለፍ ሲባል ብቻ በሚደረግ ንባብ መሆኑን ገልጸው ከዚህ ያለፈ ለሀገር ለወገን ምን ሰራን በማለት ጠየቁና እኛ ምሁራን ሳይሆን የፊደል ሐዋሪያ ነው መባል ያለብን አሉ፡፡

አንዳንድ ሰዎች ምሁር የሚለውን የወል መጠሪያ ይዘው ህብረተሰቡም በዚሁ ጥሮ ግሮ በሚገኝ መጠረያ እያከበራቸው በተግባር ግን ለመጠሪያው የማይመጥኑ ለተሰጣቸው ክብር የማይበቁ ሆነው ሲገኙ ያሳዝናል፡፡ በሙያቸው ሕዝብን ማገልገሉ በእውቀታቸው ሀገር መጥቀሙ ቢቀር እውነት ለመናገር ድፍረቱ የጎደላቸው ወይንም ተፈጥሮአቸው ለዛ ያላደላቸው ቢሆኑ እንኳን ምሁርነታቸውን መኖሪያ ብቻ አድርገውት ህይወታቸውን ቢገፉ ጥሩም ባይሆን ባልከፋ ነበር፡፡

ነገር ግን ለሆዳቸው አድረው ሎሌ ሲሆኑ ፤በጥቅም ተሸንፈው ወይ በዘር ወግነው በእውነት ላይ ሲያምጹ፤ አባይ ምስክር ሆነው አደባባይ ሲወጡ፤ ለገዢዎች አጨብጫቢ ሆነው ሲሰለፉ ወዘተ ማየት የመማርን ትርጉም ያሳጣል፡፡ አንዲህ አይነቶቹ ምሁራን ለራሳቸው ከመኖር ባለፈ (በዚህ መልኩ መኖር ኑሮ ከተባለ) ከበደ ሚካኤል አንዳሉት ለምንም የማይረቡ ናቸውና የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲትው መምህር ያወጡት መጠሪያም (የፊደል ሐዋሪያ ) ይበዛባቸዋል፡፡ ፊደል መቁጠር ክፉና ደጉን ለመለየት ካላስቻለ፤የህሊናና የሆድን ሚና ካላሳወቀ፤ ምነው ሸዋ ካላስባለና ጎመን በጤና እያሉ ኗሪ ካደረገ ወዘተ ምኑን ፊደል ተቆጠረ ምኑንስ ምሁር ተሆነ?

እናት አባቶቾቻን ብሎም አያት ቅድመ አያቶችችን የትምህርት ቤት ደጃፍ ያረገጡቱ፤ፊደል አይተው የማያውቁት ተማርኩ በሚለና መማሩ ከሆድ አደርነት ባላወጣው ወገን ኋላ ቀር የሚባሉት፤ በእውነት ላይ አያሸምቁም፤አማራጭ በማጣት ካልሆነ በስተቀር ለሆዳቸው ብለው በሎሌነት አያድሩም ፣ቃላቸውን አያብሉም፤አምነታቸውን አይሽሩም፡፡

የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ የሚለው ብሂላቸው ቃል አክባሪነታቸውን የእምነት ጽናታቸውን ያሳያል፡፡ አይገፉት ባላጋራ ገጥሟቸው፣ግዜ ፊቱን አዙሮባቸው ለመኖር ብለው ህሊናቸው ያለፈቀደውን ነገር ሲፈጽሙ ደግሞ፤ ልጅ አሳድግ ብዬ በሀገር እኖር ብዬ፤ ሚስቴን ለሹም ሰጠሁ እህቴ ናት ብዬ በማለት ቁጭታቸውን ይገልጻሉ ተልፈስፋሽ የሆነ ህሊናውን ገሎ በሆዱ የሚመራ፣ለራሱ ጌታ ሆኖ መኖር እየተቻለው ልበ ሙት ሆኖ በሎሌነት የሚያድር ሲያጋጥማቸው ደግሞ እሱም አይደል ልቡ ነው እውሩ፣ ጥንድ በሬ እያለው ለጌታ ማደሩ ፡ ይሉታል፡፡

የዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆኑት ምሁራን ( የፊደል ሐዋርያት) ጥንድ በሬ እያለው ለጌታ ያደረው ገበሬ አይነት ናቸው፡፡ከላይ አንደገለጽኩት ለሀገር ለህዝብ የሚለው ቢቀር በቀሰሙት እውቀት በያዙት ሙያ ሰርተው ለራሳቸው መኖር የሚያቅታቸው አይደሉም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ በድሎት የሚንቀባረሩ፤አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አይቶት አይደለም ሰምቶት የማያውቅ ብር የሚቆጥሩ ናው፡፡ በዚህ ሁኔታ እየኖሩ ግን ለተጨማሪ ጥቅም ሎሌነት ሲያምራቸው፤ መስሎ ለማደር ከእውነትጋር ሲጣሉ፣ በጥቅሉ የምሁር ሆድ አደር ሊያስብላቸው የሚበቃ ተግባር ሲፈጽሙ ማየትና መስማት ያሳዝናል
ያሳፍራል፡፡

በተለይ ደግሞ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ድርብ ዜግነት ወይንም የመኖሪያ ፈቃድ ኖሮአቸው በሙያቸው ስራ ፈጥረው ድርጅት መስረተው የሚኖሩ ከመንግሥት ተሞዳሙደው ሀገር ውስጥ ሊያገኙት ስለሚችሉት ጥቅም በማሰብ ከእውነት ጋር እየተጣሉ በሎሌነት ሲያገለግሉ በሀገር ውስጥ የመንግሥት ጥገኛ ሆኖ የሚኖረውና ከስራ ቢወጣ የእለት ጉርስ የሚቸገረው ወገን ምንም ቢያደርግ ምን እንዴት ይፈረድበታል?

ህሊና የበላይነቱን ወሳኝና አዛዥነቱን ጠብቆ ሆድም ተገቢ ድርሻውን እየከወነ ኖሮ ሰው ከነክብሩ ለህልፈት ሲበቃ ራሱን ብቻ ሳይሆን ባለቤቱን ልጆቹን ቤተሰቡን ወዳጅ ዘመዱን ሁሉ ያኮራል፡፡ የእገሌ ናቸው ያስብላል፡፡ ምሁር ተብሎ ለሀገር የሚበጅ ለወገን የሚጠቅም ተግባር መከወን ቢያቅት ልጆች የሚመኩበት ወዳጅ ዘመድ የሚኮራበት መሆን ቢቸግር ከአሳፋሪ ተግባር በመራቅ፣ አኩሪ መሆን ባይቻል አሳፋሪ ላለመሆን መጠንቀቁ የሚገድ አይሆን ነበር፡፡ መማር ምሁር መባል ለዚህ ካላበቃ …

የዛሬን አያድርገውና አበው የተማረ ሰው አያብልም፣ለጥቅም አያድርም፣ሀቅ አያዛንፍም ድሀ አይበድልም፤ለጌታ አያጎበድድም ወዘ ብለው ያምኑ ስለነበር የተማረ ይግደለኝ ይሉ ነበር፡፡ ዛሪስ? ይሄ ስንን ምላሽ ይሰጠን ይሆን!

አባባ ገድልህን ለምን ነው የነገርከኝ?
ለትናንት አሻቅለህ ዛሬ አስጠላኸኝ
ብትከፍተው ገለባ
ሕይወት ትግል አልባ፣ ትግሉም ሕይወት አልባ

የተማረ ይግደለኝ ብለህ አጓግተኸኝ
ፊደል ከቆጠረ ቁጥርን ከደመረ ለሆዱ ካደረ
መንጋ መሀል ጣልከኝ
እኔም ተማከርኩልህ” ተመራመርኩልህ
የመብት አቡጊዳ ትግሌን ጀመርኩልህ
መብሌን አትንኳት ብዬ ፎከርኩልህ

ኧረ በሞትኩልህ
ይልቅስ ልንገርህ” ሞትክን በተማረ መመኘትክን እርሳው
ጽድቁን ከፈለከው
ፊደል ያልቆጠረው ያገሬ ገበሬ ተኩሶ ይጣልህ፣ ይግደልህ ከማሳው፡፡

(ቼበለው መኩሪያ፣ ማለዳ፣ 1993)