የባንክ ሥራና ቤተ ክርስቲያን

bank
orthodox

(Admin) #1

ሪፖርተርና ፎርቹን ደጋግመው ቤተ ክህነት በመሥራችነት የሚሳተፍበት ‹‹ዳሎል ባንክ›› በመቋቋም ላይ መሆኑን ጽፈው አንብበናል፡፡ የባንኩ የአዋጭነት ጥናትና መሥራቾቹ/ አስተዋዋቂዎቹ/ (ፋውንደርስ/ ፕሮሞተርስ) በይፋ ለሕዝብ ግልጽ ባይደረጉም በግለሰብ ተቋማት ደረጃ ለአንዳንድ የአዲስ አበባ አጥቢያዎች የአክሲዮን ግዙ ግብዣው መድረሱን ሰምተናል፡፡ በዚህ ሒደት እንደ ባለሙያ ከታየ ግልጽ ሆኖ ሳለ ባለማወቅም፣ ሆን ተብሎ ተዛብቶ የሚቀርብ መረጃም አለ፡፡ በመሥራቾቹ ድክመት የግድ ምሥጢራዊ የመስሎ የታየ ጉዳይም ይታየኛል፡፡ በሁለቱም ላይ እንደ አንድ ምዕመን የተሰማኝን ለመናገር ያህል ጥቂት ልበል፡፡

1. ግልጽ ሆኖ ሳለ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ የተዛባው መረጃ

ሀ) የባንክ ሥራን እንደ አራጣ ማየት፡-

  1. ‹‹የባንክ ሥራ›› ማለት ብሔራዊ ባንክ በፈቀደው የገንዘብ አሰባሰብ ዘዴ መሠረት ከሕዝብ ተቀማጭ ገንዘብ መቀበል፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ማበደር ወይም ለኢንቨስትመንት ማዋል፣ እንክብል (በሳንቲምነት ያልተቀረጸ) ወርቅና ብር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ መግዛትና መሸጥ፣ ገንዘብን ከላኪ ወደ ተቀባይ ማስተላለፍና ሌሎችንም የባንክነት ተግባራት ማከናወን ነው፡፡ ይህም በባንክ አዋጅ ቁጥር 592/2000 በግልጽ የተመለከተ ነው፡፡

  2. ‹‹አራጣ›› ማለት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሳይዙ የተበዳሪን ችግረኛነት፣ የበታችነት፣ መንፈሰ ደካማነት፣ የልምድና የችሎታ ጉድለት ተጠቅሞ በሕግ ከተፈቀደው የወለድ ተመን በላይ ማበደር ወይም ጥቂት አበድሮ ካበደሩት ገንዘብ ጋር የማይመጣጠን የንብረት ማያዣ ከተበዳሪው መቀበል ነው፡፡ ባጭሩ አራጣ ማለት የባንክ ሥራ ፈቃድ ሳይኖር አበዳሪነትን እንደ መደበኛ ሥራ ይዞ በሕጉ ከተተመነው የወለድ መጠን በላይ የማበደር ተግባር ነው፡፡ ይህም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 712 በእስራትና በገንዘብ የሚያስቀጣ ነው፡፡ በነፍስም ‹‹ወዘኢለቅሀ፡ ወርቆ በርዴ›› መሰኘት እንጂ ‹‹ልቃህ፡ በርዴ - በአራጣ ማበደር›› ብፅዕና አያስገኝም፡፡ አራጣ በዓለማዊውም በመንፈሳዊውም ሕግ የተነቀፈ ነው፡፡

  3. እዚህ ላይ #ወለድና (interest) #አራጣን (usury) መለየት ያስፈልጋል፡፡ በፍትሐ ብሔር (የውል) ሕጋችን (አንቀጽ 1751) 9 በመቶ (9%) ላልተከፈለ ዕድ ሕጉ ያስቀመጠው ሕጋዊ ወለድ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 5(4) ደግሞ የወለድ ተመንን በመመሪያ የመወሰን ሥልጣን ለብሔራዊ ባንክ ተሰጥቷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በዚሁ ድንጋጌ መሠረት በየጊዜው ይህንኑ የሚገዛ መመሪያ ያወጣል፡፡ ዘንድሮም ይኸው ከዚህ አውጥቷል፡፡ ስለዚህ አራጣ ማለት ከዚህ መመሪያ ውጪ ሆኖ መሥራት እንጂ በዚህ መመሪያ ስር ሆኖ መሥራት አይደለም፡፡

ለ) ታሪክና ተመክሮን አለማገናዘብ

  1. ታሪክ፡- ከባንክ ጋር መሥራት ለቤተ ክርስቲያናችን አዲስ አይደለም፡፡ ቤ/ክ ሕንጻዎችን፣ ት/ቤቶችን፣ ሌላው ቀርቶ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻም በብድር የሠራችበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህን ለማረጋገጥ አንድም ከመንበረ ፓትርያርክ በታች በዘመነ ቅዱሳን አበው ባስልዮስ ወቴዎፍሎስ የተሠሩና በደርግ ተወረሱ ሕንጻዎችን ግንባታ ሪከርድ መጠየቅ ነው፤ አለዚያም ጎፋ ወርዶ የመካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤልን የሕንጻ ቤ/ክ ግንባታ የወጪ መዘርዝር ከታሪክ መዛግብት ማጣራት ነው፡፡

  2. ተመክሮ፡- በአሁን ሰዓት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የባንክ አካውንት አላቸው፡፡ የሚጠቀሙት አካውንት ከወለድ ነጻ የሚባል እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ የኛም የምዕመናን የየግል አካውንት ከወለድ ነጻ የሚባለው ምድብ ውስጥ አይደለም፡፡ ባንኩ በኛ ይጠቀማል፤ እኛም በባንኩ፡፡ ስለዚህ ቤ/ክ በዚህ ተቋም አባል ስትሆን ‹‹አራጣ ጀመርሽ!›› ማለት የራስን ከመቶ ሰባት የሚገኝ ወለድ የጽድቅ ማስመሰል ነውና ያስተዛዝባል፡፡ ቤ/ክ ያለባትን የፋይናንስ አያያዝ ድክመትና የአምስቱን መረን ከለባት (አለቃ፣ ጸሀፊ፣ ቁጥጥር፣ ሒሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥ) አስነዋሪ ተግባር ብንጸየፍም እንደ ሌሎቹ ሃይማኖት ውጫዊ የጡት አባትና ሞግዚት ለሌላት ቤ/ክናችን አሁንም ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ማስፈለጉ ችላ መባል የለበትም፡፡ የባንክ አክሲዮን አለመግዛት እነዚህን እምነት ያላቸው ስለመሆናቸው ይቅርና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ስር ማለፋቸው የሚያጠያይቅ በፍቅረ ንዋይ የናወዙ ቀሳጥያን ጸያፍ ተግባር የሚገድብልን አይደለምና ሐሳቡን በእነሱ ቀሳጢነት ሰበብ ማጣጣልም ለቤ/ክ የረዥም ጊዜ ጥም ማስከበሪያ አይሆንም፡፡ ይህን ራሱን በሙዳየ ምጽዋት ግጥገጣና በቤ/ክ ይዞታ ችርቸራ የተሠማራ አዲስ ውልድ ጥገኛ የ5 ሰዎች አክሲዮን የግልገል ቡርዠዋ ቡድን ለብቻው ለማየት እመለስበታለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን ከረዥሙ የቤ/ክ ጥቅም አንጻር ከአዋሽ ባንክ ድርሻ እስከ 10 በመቶ የመካነ ኢየሱስ ድርሻ መሆኑን፣ ብርሃን ባንክ በገቢር (de facto) የፕሮቴስታንቶች ድርሻ ያየለበት መሆኑን የምንሰማ፣ የምናየው መሆኑን በመገንዘብ ሒደቱን በበጎ ማየትን እመርጣለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ያለቦታው መግደርደርና መ’ገበዝ አዋጪ አይመስለኝም፡፡

2. በአደራጆችና በቤተ ክህነት ድክመት የተፈጠረ ብዥታ

ባንኩ የምሥረታ ይሁንታውን በተዘዋዋሪ ከብሔራዊ ባንክ እንዳገኘና ሒደቱም በቤተ ክህነቱ የበላይነት ስር ሆኖ በዘርፉ ባለፉ ባለሙያዎችና ባለ ሀብቶች እንደሚመራ ፎርቹን ከነሰዎቹ ስም ጠቅሶ እንዲህ ነግሮናል፡፡ በምስረታ ላይ ያለው ባንክ ቢሮውን አራት ኪሎ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ላይ ማድረጉንም ሰምተናል፡፡ እንዲህም ሆኖ ዛሬም ድረስ ስለ ምስረታ ሒደቱ፣ ቤተ ክህነቱ ያለው ሚና በማዕከል ደረጃ ብቻ ወይስ በአጥቢያም ደረጃ፣ የቤ/ክ ተሳትፎ ሚና፣ ቤተ ክህነቱን የወከሉት አካላት ማንነት፣ … የነገረን የለም፡፡ የገዛ ቤታችንን ጉዳይ በጓሮ በርና በጋዜጣ ብቻ ማየት እጣችን እየሆነ ይመስላል፡፡ እስከ መቼ በመረጃ ደባቂነት (information asymmetry) ውስጥ ሆኖ ራሱን በራሱ እየነጠለ በሒደቱ የጋዜጣ ማሻሻጫና የብሎግ ማናበቢያ በሚሆን ድኩም ቤተ ክህነታዊ አደረጃጀት እንደምንማቅቅ አላውቅም፡፡ ያሳዝናል! በበኩሌ እንደ አንድ የአጥቢያ ተመዝጋቢና የሰበካ ጉባኤ አባል ምዕመን በዚህ ጉዳይ ኦፊሴላዊ መረጃ ቢሰጠኝ ደስ ይለኛል፡፡ ምዕመናንና ቀሳውስት ቤ/ክ የምትሳተፍባቸውን የተጓዳኝ ገቢ ማስገኛ መሰማሪያ መስኮች የማወቅ መብት አለኝ፤ አለንና፡፡