የዓርብ ጨዋታ፡- ቴዎድሮስን ጥበቃ /ዝክረ መቅደላ ፩፻፶/


(በአማን ነጸረ) #1

ትንቢት፣ ራዕይ፣ ጥንቈላ፣ ኮከብ ቆጠራ፣ ሲኒ ምልከታ… ማኅበረሰባችን እንደየዕምነቱ ስለ ነገ ፍንጭ አገኝባቸዋለሁ የሚላቸው መንገዶች ናቸው፡፡ በእርግጥ መንገዱና መንገደኞቹ ይለያያሉ፡፡ ትንቢትና ራዕይ ክቡራንና መንፈሳውያን ሲሆን ጥንቆላ፣ ኮከብ ቆጠራና የመሳሰሉት ኅሡራንና መናፍስታውያን ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተናጋሪው ያልተለየ ትንቢት ከትውልድ ወደ ትውልድ ባፍም በመጣፍም እየተላለፈ በማኅበረሰቡ መካከል ይሽከረከራል፡፡ ንግርት የሚባለው እሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ባገራችን በትንቢትና በንግርት መካከል ሆነው ከደረሱን ታሪኮች ውስጥ የምጽአተ ቴዎድሮስ ታሪክ ይጠቀሳል፡፡ የንግርቱ ምንጭ ከአንድ በላይ ነው፡፡ የበዛ ነው፡፡ ንግርቶቹ ‹በዘመነ መሣፍት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ደባትር የተፈጠሩ› ነበሩ ሲባሉ ኑረዋል፡፡ እውነታው ግን እንዲያ ብቻ አይመስልም፡፡ ወዲያ፣ ወዲያ ይሻገራል - እስከ ዘመነ ገላውዴዎስ ሳይደርስ አይቀርም፡፡ እስከ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ ይጠረጠራል፡፡ ከፖርቱጋሎች ጋር ከመጡት ኢየሱሳውያን ጋር የሚያያዝ የነገር ሰበዝም አለው፡፡

ንግርቱ የተሠራባቸው ሰበዞች ከ፡-

 1. ከመጽሐፈ ዝክሪ ወጳውሊ፣
 2. ፍጻሜ መንግሥት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዜና መዋዕል ፣
 3. ፍካሬ ኢየሱስ እና
 4. ልሳነ-ኦሮሞ ቀዳምያን ሥነ ቃሎች

ለመቅደላ 150ኛ ዓመት መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ (አለላ እየገባ) እንደሚከተለው ተሰፍተዋል፡፡ እንያቸው፡፡

ትንቢት በእንተ ቴዎድሮስ እመጽሐፈ ዝክሪ ወጳውሊ

በነገረ ቅብዓት ወተዋሕዶ ማንበብ ከጀማመርኩ ሰነባበትኩ፡፡ በጉዳዩ ካነበብኳቸው ውስጥ ‹‹ምሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢት ዘዝክሪ ወጳውሊ›› የሚል መጽሐፍ አለበት፡፡ መጽሐፉን መ/ብ አድማሱ ጀምበሬ ከእኛ ወገን (ከተዋሕዶ) ነው ይላሉ፡፡ ቅብዓቶችም የኛ ነው ብለው አሳትመውታል፡፡ ለጊዜው፣ የኔ ጉዳይ እሱ አይደለም፡፡ ጉዳዬ ከትንቢቱ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ስለ መጪው ቴዎድሮስ 3 ጊዜ ተነስቷል፡፡

 1. በመግቢያው፡- በአፄ ገላውዴዎስ ዘመን ከቤርሙዴዝ ጋር የተከራከሩት ዝክሪና ጳውሊ ‹‹ደጉ ቴዎድሮስ እስኪመጣ ኃይማኖታችን አይቀናም›› ስለማለታቸው ተጽፏል፡፡

 2. በመጽሐፉ ገጽ 22 ደግሞ የአባ ዝክሪ (ዝክረ ማርያም) ቃል እንደወረደ፡- ‹‹ተመይጦሰ፡ ትትመየጥ፡ ሃይማኖተ፡ እስክንድርያ፡ ወኢትረክብ፡ ጥዒና፡ ሃይማኖተ፡ ኢትዮጵያ፡ እስከ፡ ይመጽእ፡ ቴዎድሮስ፡ ንጉሥ - መመለሱንስ የእስክንድርያ ሃይማኖት ትመለሳለች፤ ሆኖም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ንጉሥ ቴዎድሮስ እስኪነሳ ጤና አታገኝም፤›› በሚል የቤተ ክርስቲያን ድኅረ-ሱስንዮስ ትንሣኤ ዘበምክንያተ ቴዎድሮስ ትንበያ ተቀምጡዋል፡፡

 3. ግንቦት 7 ቀን ከመስፍኑ ዮልዮስና ከጳጳሱ አቡነ ስምዖን ጋር 1275 ኦርቶዶክሳውያን ማዕትነት ሲቀበሉ አብሮ ሰማዕትነት የተቀበለው ዲዮስቆሮስ እንዲሁ ሀገሩን፡- ‹‹ወይ፡ ለኪ! አሌ፡ ለኪ!›› እያለ፣ በካቶሊኮቹ ኢየሱሳውያን ከኢትዮጵያውያን ቈነጃጅት መዋለድ ሲያዝን ከቆየ በኋላ፣ ተስፋውን በቴዎድሮስ ትንሣኤ ላይ ጥሎ ሀገሩን፡ ‹‹እምይዕዜሰ፡ ሃይማኖተ፡ እስክንድርያ፡ ኀቤኪ፡ ኢይረትዕ፡ እስከ፡ ይመጽእ፡ ቴዎድሮስ፡ ንጉሥ - ከእንግዲህስ ንጉሥ ቴዎድሮስ እስኪመጣ ድረስ ባንቺ ዘንድ የእስክንድርያ ሃይማኖት አይቀናም፤›› ይላታል፡፡

እና መጥቶ ይሆን? በቅብዓት ዓይን ካየነው መምጣቱን እንጃ! የቅብዓቶች ሌላኛው መጽሐፍ ‹‹ወልደ አብ›› (ውጉዝ) መግቢያ፣ ቅብዓቶች በመቅደላው አፄ ቴዎድሮስና በዝክሪ እና በዲዮስቆሮስ ትንቢት በተነገረለት መጻኢው ቴዎድሮስ መካከል ልዩነት እንዳላቸው ያስረዳል፡፡ የመቅደላው ቴዎድሮስ የአምባ ጫራ የ1846 ዓ.ም. ጉባኤም የመቅደላውን ቴዎድሮስና በቅብዓት ወንድሞቻችን ምናብ ያለውን ቴዎድሮስ የሚያቀራርብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ያለን አማራጭ ወይ ሌላ ቴዎድሮስ መጠበቅ፣ ወይም ዝክሪና ጳውሊን ከተዋሕዶ ወገን አድርገን የመቅደላውን ቴዎድሮስ እንደ ፈጻሜ ትንቢት መቀበል ነው፡፡ በበኩሌ ቤተ ክርስቲያንን ከንግሥናው በፊት አንድ ለማድረግ በአቡነ ሰላማ ሣልሳይ መሪነት ካደረገው ጉባኤና በአንጻረ ሚሲዮናውያን ከተከተለው ፖሊሲ አንጻር ሌላ ቴዎድሮስ አልጠበቅም፡፡

ነገር በእንተ ቴዎድሮስ እምዜና መንግሥቱ ለተክለ ጊዮርጊስ

የእነ ዝክሪ ትንቢት ‹‹ቴዎድሮስ ይነሣል›› ከማለት በቀር ጊዜ ወስኖ አላኖረም ነበር፡፡ ኋላ ትንቢቱ ወደ ንግርትነት ዞረና ዓለም በተፈጠረ በ7268 ዓመት (በ1768 ዓ.ም) ተቀብቶ የሚነግሥ መሢህ ንጉሥ አለ ተብሎ ተነገረ፡፡ በዚህ ጊዜ የነበረው ንጉሥ ደግሞ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ፈጻሜ መንግሥት) ነበር፡፡ እሱ በየቦታው ዘመቻውን አጦፈው፡፡ ከዘመተባቸው ቦታዎች የወሎዋ ውጫሌ፣ መቅደላ፣ ቤተ አምሐራ (ሳይንት) ይጠቀሳሉ፡፡ በዚያ አካባቢ ኦሮሞዎች ገንነው ነበር፡፡ እነሱን አሳምኖና አጥምቆ ግብር ተቀመጠ፡፡ ደስታ ሆነ፡፡ ያን ጌዜ ከደባትሩ አለቃ ገብሩ እና ሊቀ ጉባኤ ዜና የተባሉቱ ጠረጠሩት፡፡ ‹‹ይሄ ሰው የምንጠብቀው ቴዎድሮስ መሆን አለበት›› ብለው ጠረጠሩ፡፡ ይህንንም በቅኔያቸው ገለጡ፡፡ ከሥላሴ ቅኔያቶቻቸው እንቀንጭብ፡፡

ሥላሴ ቅኔ ዘአለቃ ገብሩ
ካህናት፡ ሠመርዎ፤
ለዕንቈ-ሥምከ፡ ቴዎድሮስ፤
በውሳጤ፡ መዝገብ፡ ሥምከ፥ አፍአዊ፥ ተክለ፡ ጊዮርጊስ፡ ዘይት፣
ዘቀደስከ፥ አሕዛበ-ምድር፥ ለዛቲ፡ ዕለት፡፡…

ትርጓሜና ምሥጢሩ ሲጠቃለል፡-

‹‹በዚያች ቀን የአሕዛብን ምድር የቀደስክ (ኢጥሙቃን እንዲጠመቁ ያደረግህ)፣ በውጫዊ አጠራር ተክለ ጊዮርጊስ የተባልክ ምዑዘ ስም ሆይ፣ በውስጣዊ አጠራር ቴዎድሮስ የተባለ ስምህን ካህናት ወደውታል››

የሚል መልእክት አለው፡፡ ካህናቱ ቴዎድሮስን መጠበቅ ቢታክታቸው ንጉሣቸውን ቴዎድሮስ ብለው ለፈጽሞ ትንቢት ተቻኮሉ፡፡ የተከታዩ ሥላሴ ቅኔ ምሥጢርም ያው ነው፡፡

ሥላሴ ዘሊቀ ጉባኤ ዜና
እግዚእነ፡ ሶበ-አይድዓ፤
ለስመ-ነገሥት፡ ጥንተ-ፊደሉ፤
ተክለ-ጊዮርጊስ፡ እምይበል፥ ጸሐፊ፥ መንገለ፡ ቴዎድሮስ፡ ሖረ፣
ወእመ-ሰማዒ፤ በዝንቱ፡ አንከረ፣
አመ፡ጸሀፊ፡ ወንጌለ ፥ድኅረዝ፥ በወይነ-ዝንጋኤ፡ ዘሰክረ፣
ጥንተ-ሥም፡ ክልኤተ፡ አመ-አኅበረ፣
እንዘ-ደኃራዌ፡ ያቀድም፤ ኀበ-ኢያዕመረ፣
ቀዳማዌ፤ ኢጽሕፈ፡ ድኅረ፡፡

ትርጓሜና ምሥጢር ባጭሩ፡- በታሪክ ‹‹ዘ›› ይነግሥ፣ ‹‹በ›› ይነግሥ፣ … እየተባለች የምትነገር ትንቢት ትሁን ንግርት ወይም ኵሸት አለች፡፡ ‹‹ዘ›› ይነግሥ ከተባለ ‹‹ዘርዓ ያዕቆብ ይነግሣል›› ማለት ነው፤ ‹‹በ›› ከሆነ በዕደ ማርያም ይጠበቃል፡፡ እንዲያ ያለ አነጋገር በድርሳናት አይጠፋም፡፡ ነገርዬዋ በጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ‹‹ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ››ም ተጠቅሳለች፡፡ ባለቅኔያችንም ‹‹ቴ ይነግሥ›› የምትል ንግርት ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ያለው ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ነው፡፡ ሥሙ በ‹‹ተ›› እንጅ በ‹‹ቴ›› አይጀምርም፡፡ እሳቸው ደግሞ በ‹‹ቴ›› ጀምሮ ‹‹ቴዎድሮስ›› እንዲባል ፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ያን ትንቢት ተናጋሪ ወይም ባለንግርት ወይም ኳሽ የመጻእያን ነገሥታት ጠቋሚ ‹‹ተ›› ሳይል ‹‹ቴ›› ምን አሰኘው? እያሉ፣ ጥንተ ፊደልን መነሻ አድርገው በቅኔያቸው ይሞግቱታል፤ ይወርፉታል - ‹‹በወይነ ዝንጋኤ ዘሰክረ›› እያሉ ጭምር፡፡ ፍካሬ ትንቢት፣ ፍካሬ ኢየሱስ አልደርስ ቢላቸው በቅኔ ፈከሩ፤ ፎከሩ፡፡

ቴዎድሮስ በፍካሬ ኢየሱስ

‹‹ፍካሬ›› ማለት በቁሙ ‹‹ትርጓሜ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ትንቢት ተናገረ›› ቢልም ይ’ሰዳል፡፡ ‹‹ፍካሬ ኢየሱስ›› ታዋቂ መጽሐፍ ናት፡፡ በገጠር ‹‹ፍ››ን ወደ ‹‹ፉ›› ቀይረው ‹‹ፉካሬ ኢየሱስ›› ይሏታል፡፡ (በወንድ አንቀጽ እንጥራውና) መጽሐፉ የተዘጋጀው (እንደ ፕ/ር ሥርገው መረጃና ኢንሳይክሎፖዲያ ኢትዮፒካ አነጋገር) ከ1395-1397 ዓ.ም እንደነገሡ በሚታመነው ቀዳማዊ ቴዎድሮስ ዘመን ነው፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀዳማዊ ኅልፈት በኋላ ግን መጽሐፉ በተቀዳና በተባዛ ቁጥር ውላጤ፣ ድማሬ ሳያገኘው አይቀርም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከፍካሬ ኢየሱስ በተጨማሪ ካሏቸው መለያዎች ውስጥ፡-

 1. በአንድ ሚስት የተወሰኑ መሆናቸው፤ ‹‹ወኢያውሰበ፡ ዘእንበለ፡ አሀቲ፡ ብእሲት›› እንዲል ስንክሳሩ፣

 2. የቤተ ክህነት ይዞታ በሚባል የሚታወቁ መሬቶች ላይ ዳግም ድልደላ መወጠናቸው፣

 3. በቤ/ክ በቅድስና ደረጃ መጠራታቸው (ሰኔ 29 ስንክሳር ተመልከት፤ ከንጽህናቸውና ከምግባራቸው በተጨማሪ ምናልባት በሙስሊሞች እጅ ስላለፉ ሳይሆን አይቀርም ቅድስናው፤ ጄምስ ብሩስ ግን ኅልፈታቸውን ከደባትር ሴራ ጋር ያይዘዋል)፣

 4. ዳግም ተነሥተው ሺህ ዓመት ይነግሣሉ የሚል ንግርት እንደነበረም ጄምስ ብሩስ ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የፍካሬ ኢየሱስ ትንቢት፣ በትዳር (በንጽህና) መወሰንና የቤተ ክህነት (ተብዬ ቶፋ መሳይ) ይዞታዎችን የመደልደል ውጥን ቀዳማዊ ቴዎድሮስን ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ያዛምዳሉ፡፡ በእርግጥ ከተዋበች ኅልፈት ወዲህ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ‹‹ሳይሄዱ›› እንዳልቀሩ የሚጠቁሙ ፍንጮች አሉ፡፡

ወደ ቴዎድሮስ ጥበቃ ትንቢትና ንግርቶች ስንመለስ፣ ፍካሬ ኢየሱስ ከ29 ዓመታ ስቃይ በኋላ ስለሚነሳው ቴዎድሮስ እንዲህ ይላል፤

‹‹ወአመጽእ፡ ድኅሬሁ፡ ንጉሠ፡ እምነ፡ ምሥራቅ፡ ዘሥሙ፡ ቴዎድሮስ፡ ዘያስተጋብዖሙ፡ ለእለ፡ አትረፍክምዎሙ፡ … ወይመጽእ፡ ጳጳስ፡ ዘይቄድሳ፡ ለምድር፡ ወይትነሥአ፡ ኩሉ፡ አብያተ፡ ክርስቲያናት፡ እለ፡ ተነስታ - ከእሱም (ከስቃዩም) በኋላ ያተረፍኳቸውን የሚሰበስብ ሥሙ ቴዎድሮስ የተባለ ንጉሥን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤ … ምድሪቷን የሚባርክ ጳጳስ ይመጣል፤ የፈረሱ አብያተ (ዳግም) ይታነፃሉ፡፡››

የዚህ ትንቢት ወይም ንግርት ፍጻሜ በዘመነ መሣፍንት እጅጉን ተናፍቆ ሳለ፣ ካሳ ተነሳ፡፡ ጳጳሱ ሰላማ መጣ፤ ‹‹ወይመጽእ፡ ጳጳስ፡ ዘይቄድሳ፡ ለምድር›› ተባለ (ብቻ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንዳይሰሙን፤ ለሰላማ ሣልሳይና ለዳግማይ ቴዎድሮስ ብዕራቸው አትራራምና፡፡) ካሳ ‹‹ሥሜን ሰሜን እነግርሃለሁ›› እንዳለ በደረስጌ ‹‹ዳግማዌ ቴዎድሮስ›› ተባለ፡፡ ‹ሚሲዮን ባገሬ እንዳላይ› አለ - Catholic missionaries were expelled፡፡ በዚህ ረገድ ትንቢት ዝክሪና ትንቢተ ዴዎስቆሮስ ፍጻሜ አገኘ፡፡ በትንቢቶቹ የተነገሩትን የንግሥና ዓመታት ግን ቴዎድሮስ አልታደላቸውም፡፡ በእርግጥ ከትንቢቱም በላይ 490 ዓመት ያኑርህ ተብሎ ነበር፡፡ አካልዬ፣ ‹‹ይማሯል እንደ አካልዬ …›› ያሰኙት መምህር አካለ ወልድ በአጭር ዘይዕዜአቸው (ሣህልከ)፡-

ሥላሴ፡ ነገሥት፡ እስከ-ዐርብዐ፤
ተቀሥፎ፡ ዘመነ፤ ዘአመ-ሙሴ፡ ተሠርዐ፣
ይፍትሑ፡ ብከ፤ ቴዎድሮስ፤
ወይኩን፥ ንስሐ-ዕድሜከ ፥ በበስብዕ፡ ስብዐ፡፡

ሲሉ 40 የንግሥና ዘመንን ከሙሴ የ40 ግርፋት ድንጋጌ ወስደው፣ ዕድሜውን ከጌታ የ7 ጊዜ 70 (በበስብዕ ስብዐ) የይቅር መባባል ትእዛዝ ጋር እያገናኙ ቅድስት ሥላሴ አፄ ቴዎድሮስን 490 እንዲያኖሩላቸው ለምነው ነበር፡፡ ከውጥን ራዕዩ ዘላቂ መሆን በቀር ልመናውም፣ ከብራና እስከ ኦሮሞ ሥነ ቃል የዘለቁት ንግርትና ትንቢትም ዕድሜውን ለማሰንበት አልቻሉም፡፡

ቴዎድሮስን ጥበቃ በኦሮሞ ንግርቶች

ንግርት ለኦሮሚያ ባህል አዲስ አይመስልም፡፡ የአፄ በካፋን ንግሥና አንድ የጊቤ ኦሮሞ አስቀድሞ ተንብዮት እንደነበር ዜና መዋዕሉ ይመሰክራል፡፡ ስለሚመጣው ቴዎድሮስም በ19ኛው ክ/ዘ የነበሩ ኦሮሞዎች ከፍካሬ ኢየሱስ ጋር የሚመሳሰል ንግርት ኖሯቸዋል፡፡ “The Folk Literature of Ga***” ከተሰኘው መጽሐፍ ቆንጥረን በእነሱው እንዝጋ፡፡ የትንቢቱ / ንግርቱ/ ባለቤት ‹‹አባ ረጊ (አበ ትንቢት- የትንቢት አባት)›› የሚል ማዕረግ ያላቸውና ጊጆ ባኮ - Abba Raggi [literally, “father of prophecy”]. His name was Giggo Bacco - የተባሉ ሰው ናቸው፡፡ ከንግርቱ ትርጓሜ ውስጥ ፡-

‹‹Motumma wagga kudalama moeti sarde Bokkaha qabe indu a. Ilma Tiewodros kan gedamu dalca. Fardi Tiewodros lafa kiessa baa, ebon Tiewodros inni tti naggasu suni waqada dufa. Gafa Tiewodros dalate wagga torba, nigusa Gondar ya-Galla negu gedame, … The horse of Theodore will come forth from the earth; the lance, with which this Theodore will reign, will come from heaven. Seven years after the birth of Theodore, the king of Gondar will be called Ya-Galla negus (“king of the Galla” in Amharic),. … የቴዎድሮስ ፈረስ ከምድሪቱ ይነሳል፤ ከሰማይ ወርዶ የሚነግሥበት ሠይፉ በእጁ ነው፤ ቴዎድሮስ በተወለደ በሰባት ዓመቱ የጎንደር ንጉሥ ‹‹የጋ* ንጉሥ› ይባላል፤ …››

እያለ ይቀጥላል፡፡ እኒህ ባለንግርት የሸዋ የምስፍና አልጋ በቴዎድሮስ እንደሚፈርስም ተንብየዋል፡፡ ቴዎድሮስ ጎጃምን፣ የጁን በጉልበቱ እንደሚጠቀልልም ተናግረዋል፡፡ እና ከተናገሩት አንዳንዱ አልደረስም ለማለት አቅም አለኝ? የዳግማዌ ቴዎድሮስን ታሪክ ያየ ይፍረድ!
ዛሬም በአንጻረ ራዕዩ፣ ‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ ቴዎድሮስን የፀነሰችበት ማኅፀኗ እንደ ለመለመ ለዘለዓለም ይኑር›› ማለትን አናቋርጥም!