ታላቁ የኢትዮጵያ አገልጋይ — ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ

ethiopia
akliluhabtewold

(Achamyeleh Tamiru) #1

ታላቁ አክሊሉ ሀብተወልድ ከዛሬ አንድ መቶ ስድስት ዓመታት በፊት ልክ በዛሬው እለት መጋቢት ፭ ቀን ፲፱፻፬ ዓ.ም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አድአ ወረደ ከአባታቸው ከአለቃ ሀብተወልድ ካብትነህ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፈሉ ተወደሉ። የኢትዮጵያ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ካጠናቀቁ በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ትምሕርት ቤት ለሦስት ዓመታት ያህል ዘመናዊ ትምሕርት ተከታትለው በ፲፱፻፲፯ ዓ.ም ወደ እስክንድርያ በማቅናት እዚያ በሚገኘው የፈረንሳይ «ሊሴ» ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ተላኩ።

እስክንድርያም እስከ ፲፱፻፳፫ ዓ.ም ከተማሩ በኋላ የሊሴ ትምሕርታቸውን የመጀመሪያ ዲግሪያቸው [BA] በማግኘች ካጠናቀቁ በኋላ ለከፍተኛ ትምሕርት ወደ ፓሪስ በማቅናት በታዋቂው የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍልን ተቀላቅለው በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ [LLB]፣ ከዚያም በዚሁ ትምህርት ክፍል ሕግ የዶክትሬት ፕሮግራም [le Programme de doctorat en droit public] ውስጥ ገብተው በፐብሊክ ሎው ዶክትሬታቸውን [Diplôme de doctorat en droit public] ካገኙ በኋላ በኢኮኖሚክስ የዶክተራል ዲፕሎማና በኮመርስ የሰርቲፊኬት ፕሮግራምም ተከታትለዋል።

ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወዲያው ፋሽሽት ኢጣልያ ሀገራችንን በመውረሩ ወጣቱ አክሊሉ ሀብተወልድ ለውድ አገራቸው ነጻነት የአርበኝነት ትግላቸውን በውጭ አገር እዚያው ፈረንሳይና በልዩ ልዩ የአውሮፓ አገሮች ተሰማሩ።

አክሊሉ ጸረ ፋሽስት የአርበኛነት ትግላቸውን የጀመሩት በዓለም መንግሥታት ማኅበር ሸንጎ ፊት ጣልያን ኢትዮጵያን ልትወር በመነሳቷ እና የመንግሥታቱ ማኅበር «የጋራ ደህንነት ዋስትና መርህ» [collective security principle] በመጣሱ አባል አገሮች መሃል ገብተው ጣልያንን እንዲያስታግሱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የፈረንሳይ፣ የብሪታንያ እና የዠኔቭ ዋና ልዑክ የነበሩት የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ዋና ፀሐፊ በመሆን ነበር። አክሊሉ በፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ሥር የኢትዮጵያ ልዑካን ዋና ፀሐፊ ሲሆኑ እድሜያቸው ገና አስራ ዘጠኝ አመት ነበር።

በዚህ መልክ አገር ማገልገል የጀመሩት አክሊሉ ሀብተ ወልድ በነውረኛው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ጓዶቹ ያለክስና ያለፍርድድ በግፍ እስከተገደሉበት እስከ ኅዳር ወር ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ድረስ ያለ አንዳች እረፍት አገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እያሉ በረቀቀ የዲፕሎማሲ ጥበባቸው ኤርትራን ወደ እናት አገራቸው መልሰዋል፤ ጋምቤላ ወደ እናት አገሯ ኢትዮጵያ እንድትለመው ያደረጉ እሳቸው ነበሩ። አፋምቦ የሚባለውን የምስራቅ ኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ሰፊ የግጦሽ መሬት፣ ዛሬ ወያኔ በአስር ሺዎች የሚቆጥሩ ኦሮሞዎችን እያፈናቀለ ወደ ኬንያ የሚያሰድድበትን ምድር ሞያሌ ከእንግሊዟ ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ያደረጉት ታላቁ አክሊሉ ነበሩ። የአፍሪካ መኩሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያቋቋሙት አክሊሉ ናቸው።

ይህንን ሁሉ አገር ያስመለሱት አክሊሉ ግን በኢትዮጵያ ምድር አንድ እንኳ ቦታ በስማቸው የሚጠራ የለም። የሕግ ተቋማትን የገነቡትና የኢትዮጵያን አየር መንገድ ላቋቋሙት ለአክሊሉ ሀብተወልድ አንድ ማስታወሻ እንኳ ሳይኖራቸው ሕግ ጥሰው ወንጀል በመስራት የኢትዮጵያን አየር መንገድ የጠለፉት ለነ ዋለልኝ መኮነንና ለነ ማርታ መብራቱ ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በስማቸው የሚጠራ ካምፓስ ተሰይሞላቸዋል።

ተቋም ገንቢው አክሊሉ የኢትዮጵያን የፍትሕ ስርዓት በማዝመን የፍትሐብሔር ሕግ፣ የወንጀል ሕግ ፣ የንግድ ሕግ፣ የባሕር ሕግ፣ ወዘተ እንዲረቀቁና በተሻሻለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሕገ መንግሥት ቍጥር ፴፬ እና ፹፰ መሠረት የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶች ከመከሩበትትና የሚሻሻለው ተካትቶ ካጸደቁት በኋላ ኢትዮጵያን የሕግ አገር በማድረግ ረገድ ቀዳሚውን ሚና ተጫውተዋል።

ከታች የታተመው ንግግር ታላቁ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በ1958 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ለካቢኔ ሚንስትሮቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያሰሙት ታሪካዊ ንግግር ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ በዚህ ታሪካዊ ንግግራቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያን ከየት አንስተው የት እንዳደረሷት፤ንጉሠ ነገሥቱ ለኢትዮጵያ ስለዘረጉት ተቋማዊ ሥርዓትና ኢትዮጵያን የበለጠ በሥልጣኔ ጎዳና ለማራመድ ስለዘረጉት በአይነቱ ልዩ ስለሆነው አዲስ ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር በሰፊው ይዘረዝራሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ አገራቸውን በእድሜ ዘመናቸው ሙሉ ካገለገሉ በኋላ የ ያን ትውልድ አመጽ ተከትሎ የካትት 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚንስትርነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን በመልቀቅ በአፍሪካ ምድር ቀዳሚው ሰው ናቸው። ወያኔ የአለም መሳቂያ የሆነውንና ምንም ስልጣን ያልነበረው ምንም ያልፈየደውን ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ካባረረች በኋላ በገዛ ፍቃዱ ስልጣን በመልቀቁ ላፍሪካ ምሳሌ የሚሆን አድርጋ ግዑዙን ሰውዬ ስታቀርበው የፈለገች ሁሉ ሰው እንደ ብሔራዊ ውርደት ምልክቶቻን እንደ ኃይለ ማርያምና ደመቀ መኮነን አይነት ሕሊና ቢስና የአገሩን ታሪክ የማያውቅ ደንቆሮ መስሏት ነው።

እንግዲህ! ያ ትውልድ ያንን ዘመን ጨለማ አድርጎ ሲዋሸን የኖረው ዛሬ አብዮት አካሄድን ብለው ካሰፈኑት አገዛዝ ጋር ሊወዳደር የማይችለውን የሕግ የበላይነት የነገሰበት አስተዳደር ነበር። ነውረኛው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የጭካኔ ግብረ አበሮቹ ያለ ፍርድ በጥይት ደብድበው የገደሏቸው እኒህን እድሜ ዘመናቸውን ላገራቸው ብልጽግናና መሻሻል የተጉትን ተራማጅና መተኪያ የማይገኝላቸውን ታላቅ የኢትዮጵያ አገልጋይ ነበር።እኒህ ታላቅ ሰው ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ አንድ መቶ ስድስት አመት ይሆናቸው ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት ታሪክ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት የአክሊሉ ሀብተወልድ ዘመን ተሻጋሪ ንግግሮች መካከል የሚከተሉት ጥቅሶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፤

«… የደረሰው ይድረስ ደካማ ሆኜ መታየት አልፈልግም፤ የሀገሬን ጥቅምና መብት የሚነካ መስሎ ከታየኝ መናገሬን አልተውም።»

«…ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ኢትዮጵያ ያለፉት ታሪኮቿ በትክክል እንዳስረዱት፤ለነፃነቷና ለመንቷ፤በኮሎኒያሊስቶች ጣሊአን ጋር በየጊዜዉ ስተዋጋ፤ያሸነፈችዉ ብቻዋን ነዉ። የተጠቃቺዉም ብቻዋን ስለሆነ፤አገሬ መቸዉንም ለሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነፃነቷን ለመጠበቅ፤ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊዉን ዝግጅት ማድረግ ያለባት፤እሷ ራሷ ብቻ ነች።»

«በዚህ አጋጣሚ ለባልደረቦቼ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተወካዮች፣ በተለይም ለአርጀንቲናው ልዑክ እጅግ በጣም ከባድ ፋይዳ ስላለው ጉዳይ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ዛሬ አገሬ ከግብጽ እና ከላይቤሪያ ጋር ሆና እናንተ ከጣልያን ጋር በማደም የአፍሪቃን ሕዝቦች ለመጨቆን የምትጫወቱትን ሚና በጥንቃቄ እየተመለከትን ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን እዚህ ያለነው ሦስት አፍሪቃውያን አገሮች በአስር እጥፍ በዝተን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተገቢ መቀመጫችንን እንይዛለን። ያን ጊዜ እኛ እንደናንተ ሳይሆን፣ ለዓለም ሰላም ድጋፍ እና ፍትሐዊ ፍርድ ድምጻችንን እንደምናሰማ ጥርጣሬ የለኝም።»

ጠቅላይ ሚንስትር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በ1958 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ለካቢኔ ሚንስትሮቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያሰሙትን ታሪካዊ ንግግር አድምጡና ሕግ እንዳልነበረ፣ በዘውዳዊ ሕገ መንግሥት እንዳልተዳደርን፣ በጨለማ ውስጥ እንደኖርንና የሕዝብ ተመራጭ ፓርላማ እንዳልነበረን ተደርጎ ሲነሳ ስለኖረው የሐጢዓት ክስ እናንተው ፍረዱ!

በልጅ እንዳልካቸው የጠቅላይ ሚንስትርነት ዘመን ተቋቁሞ ለነበረው መርማሪ ኮሚሽን አቅርበውት የነበረውን የሕይወት ዘመን አገልግሎታቸውን ያሰፈሩበትን የጠቅላይ ሚንስትር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ማስራወሻ ያጋራንን ወንድማች Fesseha A Atlaw እያመሰገንሁ የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ፤

የአክሊሉ ማስታወሻ

ጤና ይስጥልኝ!