የዓርብ ጨዋታ፡- ጾም፡ መግረሪተ ፍትወተ ሥጋ

orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

1. መዳልወ ባሕርያት (የባሕርያት ሚዛን)

‹‹ሶበ፡ ፈጠሮ፡ እግዚአብሔር፡ ለአቡነ፡ አዳም፡ ወለእምነ፡ ሔዋን፡ ወአኅደጎሙ፡ ውስተ፡ ገነት፡ ኢሀሎ፡ ውስቴቶሙ፡ ፍትወተ፡ አውስቦ፡ እስመ፡ እግዚአብሔር፡ ፈጠረ፡ ሥጋሆሙ፡ ዕሩየ፡ በ፬፡ ጠባይዓት፡ … ወኢትክል፡ አሐቲ፡ ትማእ፡ ካልእታ፡ እስመ፡ ኃይል፡ ውስቴቶሙ፡ ዕሩይ፡ ወለአሐቲ፡ እምኔሆሙ፡ ተዓቅብ፡ ርእሳ፡ ወበእንተዝ፡ ኢሀሎ፡ ውስተ፡ አዳም፡ ወሔዋን፡ ፍትወተ፡ አውስቦ፡ ወፍትወተ፡ አውስቦ፡ ኢትከውን፡ ዘእንበለ፡ በኃይለ፡ ላህብ፡ እንተ፡ ይእቲ፡ ነጾራር

እግዚአብሔር አባትችን አዳምንና እናታችን ሔዋንን ፈጥሮ በገነት ባኖራቸው ጊዜ በውስጣቸው የሩካቤ ፍላጎት አልነበረም፤ እግዚአብሔር 4ቱን ባሕርያት አስተካክሎ ሥጋቸውን ፈጥሯልና፤ ከእነሱም አንዷ ሌላዋን አታሸንፋትም፤ በውስጣቸው የተመዛዘነ ኃይል አለና፤ ከእነሳቸውም አንዷ ራሷን ትጠብቃለች፤ ስለዚህ በአዳምና ሔዋን ውስጥ የሩካቤ ፍላጎት አልነበረም፤ የሩካቤ ፍላጎትም የህሊና ፃዕር ከምትሆን የሙቀት ኃይል በቀር አትከሠትም፡፡››

የላይኛው ንባብ ሐሳብ፡- እግዚአብሔር ሰውን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ - ከመሬት፣ ውሃ፣ ነፋስና እሳት - ፈጥሮታል፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት ሳሉ የመራቢያ አካል ቢኖራቸውን እነዚህ የተፈጠሩባቸው ባሕርያት እያንዳንዳቸው አንዱ የሌላውን ሚዛን ይጠብቅ ነበር፡፡ ባሕርያቱ በእኩልነት፣ ሚዛን ጠብቀው ስለሚኖሩ አንዱ ሌላውን ሳይገፋ ተገናዝበው ይኖሩ ነበር፡፡ ይህም አዳምና ሔዋን ምክረ ሰይጣንን ሰምተው እስኪስቱ ድረስ ነበር፡፡

2. ስህተት የሥጋን ሚዛን አዛባ

‹‹ወሶበ፡ ተአዘዙ፡ አዳም፡ ወሔዋን፡ ለሰይጣን፡ ወሰምዑ፡ እምፍትወቱ፡ ወገደፈቶሙ፡ ኃይለ፡ እግዚአብሔር፡ ወረሰየ፡ ላህብ፡ ይማኦ፡ ለቈሪር፡ ወይቡስ፡ ለርጡብ፡ ኮነ፡ ውስቴቶሙ፡ ፍትወተ፡ አውስቦ፡ በይእቲ፡ ሰዓት፡ ወፍትወተ፡ አውስቦሰ፡ ኮነት፡ ውስቴቶሙ፡ እምጊዜ፡ ተዐድዎት

አዳምና ሔዋን ለሰይጣን በታዘዙ፣ ፍላጎቱንም በሰሙ ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል ተለየቻቸው፤ ሙቀት ቅዝቃዜን፣ ድርቀት ርጥበተን የሚያሸንፈው ሆነ፤ ያን ጊዜ የሩካቤ ፍላጎታቸው ታወከ፤ ከመተላለፋቸው ጊዜ ጀምሮ የሩካቤ ፍላጎት ተከሠተች፡፡››

የንባቡ ሐሳብ፡- ከስህተት በኋላ የውሃ የቅዝቃዜ ባሕርይ በእሳታዊ የሙቀት ባሕርይ፣ ነፋሳዊ የነፋሻነት ባሕርይ በመሬታዊ የድርቀት ባሕርይ፣ እርስ በርስ፣ አንዱ ባንዱ ይሸነፍ ጀመር፡፡ በአራቱ ባሕርያት መካከል ሚዛን ጠፋ፡፡ እርስ በርስ መታገል ሆነ፡፡ ባሕርያዊ ሁከት ተፈጠረ፡፡ ሥጋ የራሱን ሚዛን ስቶ በነፍስ የማገናዘብ ባሕርይ ላይ ጫና አሳደረ፡፡ ነፍስን እስከ መዋጥ ድረስ ሥጋዊ ፍትወት ገነነች፡፡ ሥጋን መግራት አስፈለገ፡፡ መግረሪተ ፍትወተ ሥጋ - ሥጋዊ ፍላጎትን የምታሸንፍ - መድኃኒት ተፈለገች፡፡

3. ስለዚህ ጾም ታዘዘች

‹‹ወበእንተዝ፡ አዘዞሙ፡ ከመ፡ ይጹሙ፡ በእንቲአሃ፡ እምጊዜያት፡ … ዛቲ፡ ፍትወት፡ ኮነት፡ ውስቴትነ፡ እምጊዜ፡ ተዐድዎት፡ ወይእቲ፡ ታረኵሰነ፡ ለእመ፡ ወጽአት፡ እምኔነ፡ ወይደሉ፡ ላዕሌነ፡ ንጹም፡ እምኔሃ፡ በከመ፡ መጠነ፡ ክሂሎትነ፡ እስመ፡ ይእቲ፡ ውስቴትነ፡ ጠባይዓዊት፡ … ንጹም፡ እመብልዕ፡ ከመ፡ ይድክም፡ ሥጋነ፡ እምፍትወተ፡ አውስቦ - ስለዚህ በታዘዘው ጊዜ ከእርሷ ይጾሙ ዘንድ አዘዘ፤

ይህቺውም ከመተላለፋችን ጊዜ ጀምሮ የተከሠተች ፍትወት ከቁጥጥራችን ውጪ ከሆነች ታረክሰናለችና እንደተቻለን መጠን ከእርሷ ልንታቀብ ይገባል፤ በውስጣችን ያለች ተፈጥሮአዊት ናትና፤ … ሥጋችን ሩካቤን ከመፈለግ ይደክም ዘንድ ከመመገብ ይልቅ እንጹም፡፡››

ከላይ ያሉት ምንባባት ጸሀፊ ሳዊሮስ ዘእስሙናይን ነው፡፡ የኛው ቅዱስ ያሬድም ‹‹ጾም፡ ትፌውስ፡ ቁስለ፡ ነፍስ፡ ወታጸምም፡ ለኵሎ፡ ፍትወታተ፡ ዘሥጋ - ጾም የነፍስን ቁስል ትፈውሳለች፤ የሥጋ ፍላጎቶችን ሁሉም ታስታግሣለች፤›› ይላል፡፡ እንዲያ ሲባልም ‹‹ብዙ ተባዙ›› ያለውን ቃል መሠረት አድርጎ በንጹህ መኝታ የሚፈጸመውን ቃል ኪዳናዊ ሩካቤ ሥጋ ለመንቀፍ አይደለም፡፡ ሩካቤ ከታለመለት ዘርን ማስቀጠያነትና ድካመ ሥጋን በሕግ ስር ሆኖ በአግባቡ በተጋቢዎች መካከል ከመወሰን ባለፈ ገደብ ተላልፎ እንደ መደበኛ የደስታ ምንጭ እንዳይሆን፣ ነፍሳችን ለሥጋ ፍላጎት እስረኛ እንዳትሆን፣ ሥጋችን ልቅ ሹፌር እንዳይሆን ጾም ሥጋን የምትቆጣጠር መንፈሳዊት ትራፊክ መሆኗን ለመግለጽ እንጂ፡፡

ጾማችንን ሥጋውያን ፍላጎቶች በመንፈሳውያን ትሩፋቶች የሚሸነፉበት ያድርግልን!