የዓርብ ጨዋታ፡- ፈትኖ መቀበል - ጳጳስም ቢሆን!

orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ’ንን የግብጽ ጳጳሳት እንዳሻቸው ሲነዷት እና ሲንዷት እንደኖሩ የሚገልጹ ተረኮች ቁጥራቸው ከሚያነጫንጩኝ ዘመናውያን ተረኮች ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ግብጻውያን የጫኑብን፣ ግብጻውያን የተጫወቱብን፣ …›› እያሉ የአዛኝ ቅቤ ለማንጎት ራስ-አንጋሽ የአውራጅና ጫኝ ወይም የተጨዋች አጫዋች (ጆከር ቢጤ) አስተሳሰብና አረዳድ ሳይጠይቅ አይቀርም እስከማለት ድርስ እነጫነጫለሁ፡፡ የምነጫነጭ ተከታዮቹን ጳጳስ ፈታኝ አያቶቼን እያሰብኩ ነው፡፡ ከፈተናዎቹ ለማሳያ ያህል፡-

1. ጳጳስን ፈትኖ መቀበል ሐሳዊ ጳጳስን እስከ መግደል

ሳዊሮስ ዘእስሙናይን ድርሳን ዐሥር ላይ በሙስሊሞች ጫና ሥር ለወደቀችው ለግብጽ ቤ/ክ የሚተክዝበት ታሪክ አለ፡፡ ‹ዐረብኛ ሠልጥኖ የቅብጥ ቋንቋ በመዳከሙ፣ ቋንቋ ሲደበላለቅ አባቶች ተሳነፉ፤ ነገረ መለከቱም ተፋለሰ› እያለ ይቆረቆራል፡፡

‹‹እስመ፡ ልሳነ፡ ዐረብ፡ ሞዖሙ፡ ወኢተርፈ፡ እምኔሆሙ፡ ዘየአምር፡ ዘይትነበብ፡ በውስተ፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፡ በልሳነ፡ ቅብጢ፡ ወኮኑ፡ ይሰምዑ፡ ወኢይሌብዉ - የዓረብኛ ቋንቋ አሸንፏቸዋልና በቅብጢ ቋንቋ በቤተ ክርስቲያን የሚነበበውን ምንባብ የሚያውቅ እንኳ ከእነሳቸው ውስጥ አልተገኘም፤ የሚሰሙ ግን የማያስተውሉ ሆኑ፤››

እያለ ይተክዛል፡፡

የእኛዎቹ ይህችን ይይዙና እኒህ ‹‹ይሰምዑ፡ ወኢይሌብዉ›› የተባሉ ጳጳሳት ኢትዮጵያንም የማትሰማ የማትለማ አደረጓት እያሉ ይጽፋሉ፡፡ ‹‹ብሔራዊ ስሜት ያንገበግባቸዋል!›› እንደው ያለቦታው! ግብጽ እንዲያ በታማችበት ዘመን የኢትዮጵያ ክርስትና ድርሳነ ቄርሎስን ተርጉሞ፣ በቋንቋው ዝማሬ ቀምሮ፣ ለእምነቱ የመን ድረስ ዘምቶና መካ መዲናን ገርምሞ፣ ግብፅ ላይ መፈንቅለ ፓትርያርክ ተፈጽሞ የተላከለትን አርዮሳዊ ጳጳስ አክሱም ላይ ፈትኖ እስከ መረሸን የሚያደርስ ርቱዕ ዶግማና ቀኖና መትከሉን ለማረጋገጥ የነ ፕ/ር ሥርገውን የ"Ancient and Medieval Ethiopia" ተራራ መውጣት ይጠይቃል፡፡ እና ከተራራው ሳይወጡ፣ እንዲያው እግረ ደብር ሳይደርሱ ‹‹እሽክም! ይሰምዑ፡ ወኢይሌብዉ!››ን አለቦታው መጥቀስ አሄሄሄ …! ‹‹ወይገብእ፡ ጻማሁ፡ ዲበ፡ ድማሁ!›› ያስጠቅሳል! አባቶች አባት የሚቀበሉት እንዲህም አልነበር፤ ሰምተው፣ አስተውለው፣ ፈትነው እንጂ!

2. ‹‹ሳንፈትን አንባረክም!››

አቡነ ሲኖዳ በአፄ ዮሐንስ ጻድቁና በአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የነበሩ ግብጻዊ ጳጳስ ናቸው፡፡ ጽኑ አቋም የላቸውም በሚል ባገራችን የእርስ በርስ ተከራካሪ የክርስትና ዘውጎች አይመሰገኑም፡፡ በዚህ የተነሣ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ እሳቸው እንዲወርዱላቸው ከግብጽ ፓትርያርክ ተጻጽፈው በምትካቸው ከእሳቸው ዘመነ መንግሥት እስከ አፄ ዳዊት በመንበሩ የቆዩትን አቡነ ማርቆስ 4ኛን አስመጡ፡፡ የአቡነ ማርቆስ የሹመት ደብዳቤ በንጉሡ ፊት ተነበበ፡፡ ‹‹ሤምናሁ፡ ለአባ፡ ማርቆስ፡ ወሠዐርናሁ፡ ለአባ፡ ሲኖዳ - አባ ማርቆስን ሾምነው፤ አባ ሲኖዳን ሻርነው›› ይላል የፓትርያርኩ ደብዳቤ፡፡ ሆኖም ጳጳሱ እንደ መጡ መንበሩ አልተለቀቀላቸውም፡፡ ምክንያቱም ይህ እንደሚባለው መላው ማኅበረ ክርስቲያን ‹‹ይሰምዑ፡ ወኢይሌብዉ›› የሆነበት አይደለም፤ አልነበረም፡፡ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ምዕመናኑ ከየገዳማት አድባራቱ ተሰባሰቡ፡፡ ሊቃውንትና መምህራን ቀረቡ፡፡ ጳጳሱ ወደ ዐውደ ምሕረት ወጡ፡፡ ለቡራኬ አይደለም፡፡ ያልተፈነ አይባርክማ! አባቶቻችን ‹‹ይሰምዑ፡ ወኢይሌበዉ›› ሳይሆን ‹‹ሳንፈትን አንባረክም!›› ባዮች ነበሩ፡፡ ስለዚህ እንደ ደምቡ ጳጳሱ እንዲፈተኑ ንጉሡ ለሊቃውንቱና ለመምህራኑ ትእዛዝ ሰጡ፡፡

‹‹ወአዘዞሙ፡ ንጉሥ፡ ለኵሎሙ፡ ሊቃውንት፡ ወመምህራን፡ ከመ፡ ይሰአልዎ፡ ለአባ፡ ማርቆስ፡ ነገረ፡ ሃይማኖት፡ ርትዕት፡ እኂዞሙ፡ እምነገረ፡ ቅድስት፡ ሥላሴ፡ ወነገረ፡ ተዋሕዶ፡ እስከ፡ ነገረ፡ ቅብዓት፡ ወሥርዓተ፡ ቁርባን፡ ወኵሎ፡ ቀኖና፡ ቤተ ክርስቲያን፡ ዘሐዋርያት፡ ወሊቃውንት፡፡ ወእሙንቱ፡ ተስእልዎ፡ ለአባ፡ ማርቆስ፡ … ወኀብረ፡ ቃሉ፡ ለአባ፡ ማርቆስ፡ ምስለ፡ ቃለ፡ አሐቲ፡ ቅድስት፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን፡ እንተ፡ ላዕለ፡ ኵሉ፡ ጉባኤ፡ ዘሐዋርያት፡ በኩሉ፡ ሥርዓት፡ ወበኩሉ፡ ሃይማኖት፡ እንተ፡ ቆመት፡ ማእከለ፡ ጉባኤ፡ በስምዓ፡ ቅዱሳት፡ መጻሕፍት፡፡ ወእምድኀረዝ፡ አንበሮ፡ ላዕለ፡ መንበር፡ ወአልበሶ፡ ልብሰ፡ ክህነት፡፡ ወሤሞ፡ በሥርዓተ፡ ሕገ፡ ጵጵስና፡፡፡ ወተለውዎ፡ ኩሎሙ፡ ከተማ፡ ወአብእዎ፡ ውስተ፡ ቤቱ፡

ለጳጳስ - ንጉሡም መላውን ሊቀውንትና መምህራን አባ ማርቆስን ስለ ቀናች ሃይማኖት ጉዳይ ከነገረ ሥላሴ እስከ ነገረ ተዋሕዶና ቅብዓት ስለ ሥርዓተ ቁርባንና ስለመላው የሐዋርያትና የሊቃውንት ቀኖና እንዲጠይቁት ትእዛዝ ሰጠ፡፡ እነሱም ጠየቁት፡፡ … የአባ ማርቆስ ቃል በሃይማኖትና በሥርዓት ሁሉ አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊት፣ ከሁሉ በላይ ከምትሆን፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ከቆመችው ቤተ ክርስቲያን (ዶግማ / ሃይማኖት/ እና ቀኖና /ሥርዓት/) ጋር አንድ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ (ንጉሡ) በመንበሩ አስቀመጠው፤ (የመዓርገ-) ክህነት ልብሱን አለበሰው፡፡ በጵጵስና የሹመት ሥነ ሥርዓት ሕግ (መሠረት) ሾመው፡፡ የከተማው ነዋሪዎች ጳጳሱን አጅበው እቤቱ አገቡት፡፡››

ተፈትኗላ!

3. ጳጳስ ፈትኖ ማባረር፣ ለጥያቄ ማቅረብ፣ መግለብ፣ ሥም አለመጥራት!

እንዲያ ነዋ! ከተማው የሚከተለው ሊቃውንቱ ከፈተኑት ወዲያ ነው! ተኩነስንሶ የመጣ ሁሉ አይታጅብም፡፡ ቢታጀብም እስከ ጊዜው ነው፡፡ አባ ተክለ ሥላሴ እንደሚለው ‹‹ርዝቅ›› የተባለው አጭበርባሪ ዓረብ እንዳደረገው ተሾልኮ ከመጣም መርምረው ያጠድፉታል! ከአፄ ዳዊት እስከ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደ ኖሩት አቡነ በርተሎሜዎስ በኑፋቄ የሚጠረጠር ካለም ብሔራውያን ሊቃውንት ገትረው ይመረምሩታል! ወይም አባ ኤዊስጣቴዎስ ግብጻዊውን አባ ያዕቆብና የግብፁን ፓትርያርክ አባ ብንያሚንን እንዳደረገው፣ ተፈታኙ በፈታኙ ቢወድቅም ፈተናውን አርሞ ውጤት የሚሰጥ ከጠፋ፣ ነገሩ ከአቅም በላይ ከሆነ፣ በዓት ለይተው፣ ድንበር ተሻግረው አስተምህሮአቸውን ለማሻገር ድንበር እስከመሻገር የሚያደርስ ጽናት ነበራቸው! አባቶቻችን ‹‹ካልፈተንን አንባረክም፤ ካልፈተንን አንካንም!›› ያሉበት ጊዜ ነበረ! የግብጽ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ የግዝረት ትውፊትን በተቃወሙ ጊዜ ፈተናው ቀሚስ እስከ መግለብ ይደርስ እንደ ነበር የፕ/ር ታደሰ ታምራት ጥናትና የኢያሱ ብርሃን ሰገድ ዜና መዋዕል መጠቆሙን ከዚህ በፊት ሳናወጋው አንቀርም! ዋልድባዎች አንድ ወቅት አባ ክርስቶዶሉ የተባሉትን ጳጳስ ሥም በቅዳሴ ለመጥራት የጳጳሱን እምነት ቀጥታ ከራሳቸው ከጳጳሱ ጠይቀው ማረጋገጥ ነበረባቸው፡፡ ስለተሾመ ብቻ ሥሙ አይጠራም! ሳይፈተን አይጠራም! ትውፊቱ ዛሬም ባገራችን ጳጳስ ወይም ፓትርያርክ ለመዓርገ ሢመት ሲበቃ ይተገበራል!

ፈታኝ ሊቃውንትንና የተፈተኑ ጳጳሳትን አያሳጣን!