አንዳንድ ነገሮች፡- ስለ ‹‹ዘጠኝ መለኮት›› የዋልድባ ቤተ ጣዕማ ብሒልና ዮሐንስ ተዐቃቢ

orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

‹‹ዘጠኝ መለኮት›› የሚለውን ቃል መጀመሪያ ያነበብኩት በአቡነ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ነበር፡፡ ከእሳቸው ቀጥሎ ከአለቃ ኅሩይ ፈንታ ‹‹ፍኖተ እግዚአብሔር››፣ ከዚያም በመ/ር ገ/ዮሐንስ ገ/ማርያም ‹‹ክርስትና በኢትዮጵያ››፣ (ለብቻው የውዴታና የክብር ሥፍራ በልቤ ካበጀሁለት መ/ር ብርሃኑ አድማስ ካገኘኋቸው) ‹‹ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ››ና ከፕ/ር ሥርግው ‹‹አማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት››፣ ከሃይማኖተ አበው፣ ከመ/ር ይኄይስ ወርቄ ቅኔያት ስብስብና በቅርቡ የመስክ ጉብኝት አድርገው ስለ ጉዳዩና ስለ ባለጉዳዮቹ ከጻፉት (በአንዳንድ አመለካከታቸው አለመስማማቴ ለትሁትና ምሁራዊ አቀራረባቸው ያለኝን አክብሮት ከማይቀንስባቸው) ዶ/ር ክንዴነህ እንደግ መገርም ጽሁፍ ስለ ‹‹ዘጠኝ መለኮት›› ቀራርሜያለሁ፡፡ ጎግልም በመጠኑ ሹክ ብሎኛል፡፡ እነዚህ ሲደማመሩ፡-

 1. ዮሐንስ ተዐቃቢ፡ ሰውየውና ትምህርቱ፣
 2. ባገራችን ዘጠኝ መለኮት ስለሚባለው ትምህርት መነሻዎችና መገኛዎች፣
 3. በርእሱ ዙሪያ የተካሔዱ ክርክሮችና ጉባኤያት፣
 4. በብሒሉ ዙሪያ የቤ/ክ ሊቃውንት አቋም

የሚሉ የመንፈሳዊ ወግ ጎዳናዎችን አስገኙ፡፡ ማጣቀሻዎቻችንን በመጣጥፊቱ ሕፅን እየሸካከፍን በጎዳናዎቹ ጥቂት እንራመድ!

1. ዮሐንስ ተዐቃቢ(John Philoponus)፡ ሰውየውና ትምህርቱ

በእስክንድርያ እንደነበረ ከመነገሩ በቀር ለጊዜው መቼ ተወልዶ መቼ እንደሞተ የነገረን የለም፡፡ ጎግልም በዚህ https://plato.stanford.edu/entries/philoponus/ በኩል አናግረነው የማላውቀውን አትጠይቁኝ ብሏል፡፡ ብቻ በግምት በዚህች ዓለም 80 ዓመት ሳይኖርባት አይቀርም፤ ከ490-570 ዓ.ም.፡፡ ሰውየው ጭንቅላት አለው፡፡ ጠፈረ-ጠፈራቱ፣ አየረ-አየራቱ አይቀሩትም - ሲመራመር፡፡ የተጨረሰ ፈላስፋ፣ ቃላትና ሐሳብ እየፈታ የሚገጥም ደራሲ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ጥንቁቁ / ቀለም ጠንቃቂው/ - Lover of toil / Grammarian / ›› የሚል ትርጓሜ ያለው Philoponus ወይም በእኛ ወደረኛ የግእዝ ትርጓሜ ‹‹ተዐቃቢ›› የሚል ቅጽል የተሰጠው፡፡ መጠንቀቁ ባልከፋ! ችግሩ በቃላት ጨዋታ ከማይወጡበት ምሥጢረ ሥላሴ ገብቶ ሰጥሞ ቀረ! እንዲህ በማለቱ፡-

‹‹… the three hypostáseis of the Trinity are three particular divine substances with distinct properties. Only on this assumption, too, is it reasonable to speak of the consubstantiality of the three Persons, for if there were only one divine substance, what sense would it make to speak of consubstantiality at all?

ሦስቱ አካላተ-ሥላሴ (በየራሳቸው) ሦስት የተለያዩ ባሕርያት ያሉዋቸው መለኮታውያን አካላት ናቸው፡፡ በዚህ ብሒል መነሻነት የሦስቱን አካላት ዕሩይነት (እኩልነት) መናገር ያስኬዳል እንጂ፣ አንድ መለኮታዊ አካል ብቻ ከተባለማ ስለ ዕሩይነት ማተት ምን ስሜት ይሰጣል?››

ይጠይቃል፡፡

‹‹ይሤለሱ፡ በአካላት፡ ወይተወሐዱ፡ በመለኮት - በአካላት ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ አንድ የሆኑ›› ብለህ ስታበቃ ‹‹ዕሩያን ናቸው›› ማለትማ ለንግግርም አያመች፤ በባሕርይ አንድ የሆነ አካል እኩል ነው ቢባል አያስገርምምና - ከቤ/ክ ገብታ የምታፋድስ የዮሐንስ ተዐቃቢ አርስቶትላዊ ሎጂክ ናት፡፡ ‹‹there are three separate divinities, Father, Son, and Spirit - ሦስት የተለያዩ መለኮታት /ሎቱ ስብሐት/ አሉ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ››

የዮሐንስ ተዐቃቢ መፈክር ነበረች፡፡

ውስጥ ውስጡን ስትላወስ ቆይታ እሱ ካለፈ ከ110 ዓመታት በኋላ ኬልቄዶናውያኑ ባካሔዱት የ680 ዓ.ም ጉባኤ-ቁስጥንጥንያ ሰውየውን ለውግዘት ዳርጋዋለች፡፡

2. ባገራችን ዘጠኝ መለኮት ስለሚባለው ትምህርት መነሻዎች፣ መሥራችና መገኛዎች

ሀ. የመጽሐፍና የትርጓሜ መነሻዎች

መቼም በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ኮርቼ አላባራም፡፡ በዓለም የክርስትና ታሪክ ያሉ ጥያቄዎች ሁሉ እዚህ ተሰንደዋል፡፡ ያባቶቻችንን ዐፅም ያለምልም አያ! የዮሐንስ ተዐቃቢን አስተምህሮ አስቀድመው አውቀዋታልና እንዲያ ያለ አስተምህሮ ሲመጣ ‹‹ዮሐንስ ተዐቃቢ በየት ዞሮ መጣ!›› እያሉ ይሞግታሉ፡፡ የአስተምህሮው አራማጆች መጽሐፍ በቅ/ሲኖዶስ በመተጋዱ የእነሱን ሐሳብ እንደወረደ ለማግኘት ባይቻልም ብዚ ጊዜ ‹‹ዘጠኝ መለኮት›› የሚል አስተምህሮ መነሻዎች የሚባሉት፡-

 1. በመልክዐ ሥላሤ መጀመሪያ ላይ ያለው መልክዕ /‹‹ሰላም ለህላዌክሙ››/ 4ኛ ቤት ውስጥ ያለው ‹‹መለኮተ፡ ለለ፩ዱ፡ ዘዚአክሙ፡ ገጻተ - ለእያንዳንዳቸው መለኮት ገንዘባቸው ለሚሆን ገጾቻችሁ›› የሚለው ሐረግ፣

 2. ‹‹መለኮትሰ፡ አካላት፡ ዘውእቱ፡ ገጻት - መለኮትስ አካላት ነው፤ እነዚህም ልዩ የሚሆኑ ገጻት ናቸው›› የሚለው የሃይ.አበው.ዘባ.ዘአንጾኪያም.96፡5 ገጸ ንባብና ሌሎች ይህን የመሰሉ የሃይማኖተ አበው ምንባባት፣

 3. ሦስት አካላት አሉ ካልን ‹‹አካል ያለ ባሕርይ አይኖርምና›› አካላተ ሥላሴ በየራሳቸው ባሕርየ መለኮት አላቸው ብሎ መደምደም፣

 4. በነገረ ሥጋዌ ‹‹ወልድ ቅብዕ፣ በተዋሕዶ ከበረ›› ለማሰኘት ወልድ ከራሱ ብቻ የሆነ (አብና መንፈስ ቅዱስ የማይጋሩት) መለኮታዊ ኃይል ሊኖረው ይገባል የሚል (ምናልባት ‹‹መለኮት አካልን እንጂ ባሕርይን አልተዋሐደም›› ለሚሉ ወገኖች በተሰጠ ምላሽ የተፈጠረ) የከረረ አቋም፣

 5. ‹‹አብ ፀሐይ ነው፣ ወልድ ፀሐይ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ ነው›› የሚለው የቅዳሴ ማርያም 3 ፀሐያትን ጠቃሽ ንባብ በትርጓሜ አንዷን ፀሐይ ብቻ በመውድ ግዘፏ፣ ሙቀቷና ብርሃኗ ከአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ጋር እየተነጻጸረ ከሚሰጠው የምሥጢረ ሥላሴ አመሰጣጠር ጋር ሲገናኝ (ምናልባት ‹‹አሐዱ፡ ውእቱ፡ ፀሐየ፡ ጽድቅ፡ ዘላዕለ፡ ኵሉ›› የሚለውን ማሰሪያ ላላስተዋሉ) የተወሰኑ አባቶቻችን የግርታ ምንጭ መሆኑ፣

 6. እግዚአብሔር የሚለው የገዥነት ሥሙ በነጠላ አኃዝ ብቻ፣ ‹‹ነአምን በአሐዱ እግዚአብሔር አምላክ›› ቢባል የቀና ሆኖ ሳለ ‹‹ነአምን፡ ወናመልክ፡ በአሐዱ፡ እግዚአብሔር ዘእምቅድመ፡ ዓለም፡ ሀሎ፤ ወነአምን፡ ‹በካልዑ›፡ እግዚአብሔር፡ ዘበምልክናሁ፡ ለአብ፡ ይመስሎ፤ ወነአምን፡ ‹በሣልሱ›፡ እግዚአብሔር፡ መንፈሰ፡ ቅዱሰ፡ ዘይመልክ፡ ኵሎ፤›› የሚለውና ‹‹በ1ኛ፣በ2ኛ፣በ3ኛ እግዚአብሔር … ›› ሲል አኃዝ እየቀጸለ የሚሔድ የሐምሌ ሥላሴ ዋዜማ ፀጉር ሰንጣቂ ስሁት ያገኘው እንደሆነ ለጊዜው ሳያደናግርበት አይቀርም…

ሌላም ሌላም የሐሳብ መነሻዎች አይጠፉም፤ ተከራካሪ ሲበረታ መጻሕፍቱን ወደራስ ብሒል እየሳቡ ትርጓሜ መስጠት ያልተመለደ አይደለምና፡፡

ለ. የአስተምሮው መሥራች እየተባሉ የሚነገሩት

በቦታና በግለሰብ ረገድ ለ‹‹መለኮት በአካል ሦስት - [divinity is three in person]›› አስተምህሮ መነሻ የተለያዩ መረጃዎች አሉ፡፡

 1. ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የዚህ ስህተት ምንጭ ደብረ ቢዘን እንደሆነ ይናገራሉ (ኪ.ወ.ክ.ገ.595)፡፡

 2. አለቃ ኅሩይ ፈንታና መ/ር ይኄይስ ወርቄ የአስተምሮው ምንጭ ዮሐንስ ተዐቃቢ ነው ይላሉ፤ በሃይማኖተ አበው ዘኪራኮስ ይኸንኑ የሚጠቁም ፍንጭ አለ፡፡

 3. መፍቀርያነ ቅብዓት የሆኑት ቆጋዎች ያሳተሙት መጽሐፈ ዝክሪ የዚህ ስህተት ባለቤት ‹‹አባርዮስ›› የተባለ ሰው መሆኑን ቢጠቅስም የሰውዬውን ዜግነት አልነገረንም፡፡ ኑፋቄው ‹‹(መለኮተ፡) አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ፡ ቅዱስ፡ በበዚአሆሙ፡ ውእቱ፡ … ከመ፡ ሠለስቱ፡ አካላት፡ ሀሎ፡ ሠለስቱ፡ መለኮት - የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ መለኮት በየራሳቸው ነው፤ … እንደ ሦስቱ አካላት (ሁሉ) ሦስት መለኮት አለ፤›› የሚል እንደሆነ ጽፈዋል - ቅብዓቶች፡፡

 4. በደቂቀ እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ ላይም ከአፄ ዘርዓ ያዕቆብ በኩል እንዲያ ያለ ወቀሳ አለ፡፡ እስጢፋኖሳውያን ለሥላሴ ‹‹ሦስት አምላክ፣ ሦስት መንግሥት፣ ሦስት ግዛት ያላቸውና ለእያንዳንዳቸው በራሳቸው ልብ፣ ቃልና እስትንፋስ እንዳላቸው›› አድርገው ያስተምራሉ ይላቸዋል አፄ ዘርዓ ያዕቆብ (ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ገድለ እስጢፋኖስ፣ ገጽ 101፣ ኅዳግ ቁጥር 148)፡፡ ሆኖም በገድላቱ ውስጥ በዚያ መልኩ የተቀመጠ ምንባብ የለም፡፡ ጉዳዩን ለማጥራት ከአባ ዕዝራ የብራና ገድልና ከፕ/ር ጌታቸው ምስጉን ትርጓሜ አገናኝተን ጥቂት መስመሮች እንጥቀስ፡፡

‹‹አብ፡ ፀሐይ፡ ዘያዋኪ፡ በኑኀ፡ አየራት፡ ወልጐተ፡ ማያት፡ ወአብሕርት፤ ወልድ፡ ፀሐይ፡ ዘያበርህ፡ በስፍሐ፡ ሰማያት፡ ወያዋኪ፡ በልጐተ፡ ቀላያት፣፡ ወአብሕርት፤ወመንፈስ፡ ቅዱስ፡ ፀሐይ፡ ዘያበርህ፡ በስፍሐ፡ ሰማያት፡ ወያዋኪ፡ በልጐተ፡ ቀላያት፡ ወአብሕርት፤ ሥሉስ፡ ገጻት፡ ወአሐዱ፡ መለኮት -

አብ በአየሮቹ ርዝመትና በውሃና በባሕሮች ጥልቀት የሚያንጸባርቅ ፀሐይ ነው፤ ወልድ በሰማዮች ስፋት የሚያበራ፣ በውሐና በባሕሮች ጥልቀት የሚያንፀባርቅ ፀሐይ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ በሰማዮች ስፋት የሚያበራ፣ በውሐና በባሕሮች ጥልቀት የሚያንፀባርቅ ፀሐይ ነው፤ (አምላክ) በገጽ ሦስት ሲሆን በመለኮት አንድ ነው፡፡››

ይሄ የአባ ዕዝራ አቋም በግልጽ ‹‹አንድ መለኮት›› ባይ ነውና በዚህ አቋሙ ከተከሳሾች መደመር አይሆልኝም፡፡ ምናልባት (አንድም) የእስጢፋኖሳውያን አቋም በኋለኞቹ ተከታዮቻቸው ታርሟል፤ ወይም አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በቂ የመሰማት እድል አልሰጣቸውም ብሎ መላ መምታት ይቻል ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የጭብጡ መነሳት የክርክሩን ቀዳሚነት ይጠቁማል፡፡

 1. ሌላኛውና (ሦስት መለኮት ከሚሉት ቤተ ጣዕማዎች በተቃራኒ በቆሙት ቤተ ሚናሶች አማካይነት) በስፋት የተሰራጨው መረጃ ‹‹የመለኮት በአካል ሦስት›› እንቅስቃሴ አባ ጣዕመ ክርስቶስ በተባሉ መነኮስ፣ በዘመነ መሳፍንት (በራስ ማርዬ ቢትወደድነትና በደጃች ኃይለ ማርያም ገብሬ የስሜን ገዥነት ዘመን) የመጣ እንግዳ ትምህርት ነው የሚል ነው - ክንዴነህ እንደግ ከቦታው ደርሰው የሰሙትን እንደጻፉልን፡፡ ቤተ ጣዕማ በአባ ጣዕመ ክርስቶስ እየተመራ ከአብረንታት ገዳም ራሱን ችሎ በ1823 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.በ1830) እንደ ተቋቋመ ይነገራል፡፡

 2. ሥላሴ በአካል የሚጠሩባቸውን አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ፤ በግብር የሚጠሩባቸውን ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራፂ ፤ በባሕርይ ከዊን የሚጠሩባቸውን ልብ፣ ቃል እስትንፋስ ለይቶ አለማወቅ ‹‹ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሠራፂ መለኮት›› ወደሚልና የአካል ግብር እንደማይገናዘብ ወደማያስተውል መደምደሚያ እንዳደረሰ ሊቁ አለቃ ኅሩይ ፈንታ ጽፈዋል ፡፡ ሊቁ እንደሚሉት አብ መለኮት፣ ወልድ መለኮት፣ መንፈስ ቅዱስ መለኮት ቢባል ግን አካል በመለኮት ከዊን ይገናዘባልና አያስነቅፍም፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚሉት ስሞች እንደ ሰው ሰውኛው ሳይሆን አካላት ናቸው ይላሉ - አለቃ ኅሩይና መ/ር ይኄይስ ወርቄ ሃይ.አ.ዘጐርጐርዮስ ም.13፡6፣ ገጽ 40ን እየጠቀሱ፡፡ አክለውም ዮሐንስ ተዓቃቢና በቤተ ጣዕማ ያሉ አበው ይህን ምሥጢር ባለማስተዋል እንደሳቱ ይናገራሉ፡፡

 3. የደብረ ዓባዮችና የአክሱሞች የእርስ በርስ የርስት፣ የክብርና የመዓርግ ፉክክር የወለደው ነው የሚሉም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ፕ/ር ሥርግው ሀብለ ሥላሴና ገ/ዮሐንስ ገ/ማርያም፡፡

 4. በ1760ዎቹ በጸጋዎችና በቅብዓቶች ጥምር አሳዳጆች ሰለባ በነበሩት በ‹‹ካራ››ው ያቦ ባርያ ሳይመሠረት አይቀርም የሚለውም ሌላኛው (የብርሃን ሰገድ ኢያሱንና የምንትዋብን ዜና መዋዕል ያጣቀሰ) የክንዴነህ መላ ምት ነው፡፡ ክንዴነህ ‹‹ካራ›› እና ‹‹ሦስት መለኮት›› አንድ ነው ብለው ወደ መደምደሙ ስለሚያደሉ ይህኛው አቋማቸው ላይ ተዐቅቦ ይኖረኛል፡፡

ሐ. ቤተ ጣዕማ እንደ ሦስት መለኮት (‹‹ዘጠኝ መለኮት›› አስተምህሮ) መገኛ

በዋልድባ ሰቋር፣ ዳልሻና አብረንታት የተባሉ ገዳማት አሉ፡፡ ከእነዚህም በአብረንታት ሁለት ቤቶች አሉ፡፡ ቤተ ጣዕማና ቤተ ሚናስ፡፡ ቤተ ሚናስ በአሁኑ ጊዜ የተዋሕዶውን ‹‹አንድ መለኮት›› ወገን የሚደግፍ ነው፡፡ ከነገሥታቱ ቴዎድሮስና ዮሐንስ በተዋሕዶ መከታነት መነሣስት አስቀድሞ ገዳሙ በጸጋ ብሒል መገኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የቦሩ ሜዳ የጸጐች ወገን ተከራካሪዎች ተወካይ ከነበሩት አንዱ የዋልድባው እንግዳ (ዋልድቤ እንግዳ) መሆናቸውን ስለጉዳዩ የሚያወሱ የቤ/ክ ታሪክ መጻሕፍት ሁሉ አንስተውታል፡፡ በዚህ የተነሣ ጣዕማዎች ቤተ ሚናስን አሁን ድረስ እንደ ጸጋ የመመልከት አዝማሚያ አላቸው፡፡ ቤተ ሚናሶች በበኩላቸው ቤተ ጣዕማዎችን ቀደም ሲል ‹‹ካራ››፣ አሁን ደግሞ ‹‹ዘጠኝ መለኮት›› ይሉዋቸዋል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ እኛንም፣ ጣዕማዎችንና ቢዘኖችንም ደምረው ‹‹ካሮች›› እያሉ የሚነካኩንና ከ3-5 ዘርፍ የሚከፋፍሉን በዚህ የቤተ ሚናስ የቆየ የስድብ ሌጋሲ መሆኑ ነው፡፡

ጣዕማዎች የራሳቸውን አስተምህሮ ‹‹መለኮት በአካል ሦስት›› ( አባባሉ መለኮትን አኃዝ ሰጥቶ 3 መለኮ/ታ/ት ብሎ በመጥራት ስሜት ነው) ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ‹‹ዘጠኝ መለኮት›› የሚል ሥም ያወጡላቸው አስተምህሮውን የተቃወሙ ሊቃውንት ናቸው፡፡ የአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የኩነት ስሞች የሚባሉትን ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ እንደ ተገናዛቢ (አብ በልብነቱ ለራሱ ልብ /ማወቂያ/ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስም ልባቸው /ማወቂያቸው/ ነው፤ ወልድ ለራሱ ቃል /ማገሪያ/ ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስም ቃላቸው / ንግግራቸው/ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ለራሱ እስትንፋስ /ሕይወት/ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስም ሕይወት ነው ብሎ) ከመረዳት ይልቅ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ እንዳላቸው በመግለጽ (አብ ብቻውን የራሱ ልብ፣ ቃልና እስትንፋስ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ በየራሳቸው ልብ፣ ቃልና እስትንፋስ እንዳላቸው በመግለጻቸው እንዲያ ከሆነማ ‹‹3ቱ ኩነታት በ3ቱ አካላት ሲባዙ= 9 መለኮት ይመጣል /ሎቱ ስብሐት/›› ብለዋቸዋል ርቱዓን ሊቃውንት፡፡ )

3. በርእሱ ዙሪያ የተካሔዱ ክርክሮችና ጉባኤያት

ክርክሩ ከጣዕማዎች በዐት አልፎ ሽሬ በመድረሱ ደብረ ዓባዮች ከጣዕማዎች ጋር በ‹‹ሦስት መለኮት›› ባይነት፣ አክሱሞች በ‹‹አንድ መለኮት›› ባይነት እየቆሙ ሲቆራቆሱ ኖረዋል፡፡ በ20ኛው ክ.ዘ. መዳረሻ ደሴ ላይ (እ.ኤ.አ1914 ዓ.ም) በተካሔደ ጉባኤም ታዋቂው መ/ር አካለ ወልድ ወደ ደ/ዓባዮች አጋድለዋል የሚል ወቀሳ በወቅቱ የትግራይና የወሎ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ (በአፄ ዮሐንስ ከመጡት 4 ጳጳሳት አንዱ) የተሰነዘረ ቢሆንም ሊቁ አካልዬ ለአቡነ ማቴዎስ የላኩት ደብዳቤ ይህን ክስ አጠንክሮ እንደሚያስተባብል የገ/ዮሐንስ ገ/ማርያምና የቴዎድሮስ አብርሃ ጽሁፎች ይጠቁማሉ፡፡

ሊቀ ጳጳሱ (ግብጻዊው) አቡነ ማቴዎስ ከአክሱሞች ወገን ቆመው ‹‹ሦስት መለኮት›› ባዮችን ጣዕማዎችን ያወገዙ ሲሆን አፄ ምኒልክ (እ.ኤ.አ.በ1907 ዓ.ም.) አስተምህሮው ለገነነባቸው ገዳማትና አካባቢዎች እንዲደርስ በጻፉት ደብዳቤ ይህን ‹‹የሦስት መለኮት›› አስተምህሮ የሚያስተምር ቢገኝ በዓለማዊውም በመንፈሳዊውም እንደሚቀጣ አስጠንቅቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማስጠንቀቂያና ውግዘቱ አስተምህሮውን በቤተ ጣዕማ ተወስኖ እንዲቀርና ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንዳይስፋፋ ከማድረግ በቀር ከሥሩ ነቅሎ የጣለው አይመስልም፡፡ ሊቁ ፕ/ር ሥርገው እንደሚሉት ይህንኑ ክርክር ለመቋጨት በ1950 ዓ.ም. እነ አለቃ ለማ ኃይሉን ጨምሮ 9 ሊቃውንት የተካተቱበት ጉባኤ ተሠይሞ የአስተምህሮውን ታሪክ ነቅፎና ኢ-ርቱዕነቱን በማስረጃ አስደግፎ ቢያቀርብም የሊቃውንቱ ቃለ ጉባኤ በቅ/ሲኖዶስ ደረጃ ፀድቆ ይፋዊ የቤ/ክ ዶግማ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡

ከዚያ ወዲህ አቡነ ጎርጎርዮስ የአስተምህሮውን መኖር ብቻ ዳስሰው አልፈውታል፡፡ በእሳቸው ጽሁፍ የተቆጩ የሚመስሉት ጣዕማዎች ጊዜ ጠብቀው (ቤተ ሚናሶች ጣዕማዎችን እንደ ‹‹ባለጊዜ›› ያዩዋቸዋል፤ የወልቃይት የስኳር ፕሮጀክትን በዋናነት የተቃወሙት ቤተ ሚናሶች ሲሆኑ ቤተ ጣዕማዎች ዳተኞችና እንዲያውም ተባባሪዎች ነበሩ ይባላል፤ ቤተ ጣዕማዎች ከ1983 ዓ.ም. ለውጥ ወዲህ ባሉት የአቡነ ጳውሎስ የፕትርክና ዘመናት ብቻ 9 መነኮሳት ለመዓርገ ጵጵስና ስላበቁ ከአንገታቸው ቀና ብለው፣… ‹‹ምሥጢረ ሥላሴ በአበው ሊቃውንት›› በሚል ርዕስ አባ ገብረ እግዚአብሔር አብርሃ በተባሉ መነኮስ አማካይነት አሳትመው ነበር፡፡ ከላይ እንደ ተጠቆመው ቋሚ ሲኖዶስ በ16/09/2005 ዓ.ም. (በዘመነ አቡነ ማትያስ) በተጻፈ ደብዳቤ መጽሐፉን አግዶታል፡፡

(በነገራችን ላይ፡- እንደ አንዳንድ አክራሪ ቤተ ጣዕማዎች አገላለጽ ከሆነ የነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በመኪና አደጋ ማለፍ በእነሱ አስተምህሮ ላይ ያልተገባ ንግግር በመናገራቸው የደረሰ የእግዚአብሔር ቁጣ ነው ተብሎ በማኅበረ መነኮሳቱ ይታመናል - ዶ/ር ክንዴነህ እንደግ ከገዳሙ ሰው ቃለ ምልልስ አድርገው እንደጻፉልን፡፡ አቡነ ጳውሎስ ሲያልፉም የቤተ ሚናሶች ኀዘን ‹‹ወሰዳቸው›› ተብሏል፡፡ እንዲህ ዓይነት አባባሎች በዓለማዊው /እከሌ በእከሌ ተመርዞ ሞተ እየተባለ/ በመንፈሳዊውም እንዲህ እንዳሁኑ ይደጋገማሉ፡፡ በበኩሌ አስደስተውኝም አያውቁ!)

4. በአስተምህሮው ዙሪያ የሊቃውንት አቋም

‹‹መለኮት በአካል ሦስት›› የሚለውን አስተምህሮ ሁሉም ማለትም የተዋሕዶውም ወገን (የሚገርመው ጣዕማዎችም ‹ከእኛ በላይ ጥንቁቅ ተዋሕዶ ላሳር› ባዮች ሆነው በቤተ ሚናስ የወጣውን የዋልድባ ገዳም ታሪክም በፕሮቴስታንት ድጋፍ የወጣ ሲሉ ቢከስሱም)፣ ጸጐችና ቅብዓቶችም ከቤተ ጣዕማ የወጣውን አስተምህሮ በፍጹም አይቀበሉትም፡፡ ይተቹታል፡፡ ከሁላቸውም ጉዳዩን ደኅና አድርገው የተቹት ደግሞ ሊቁ አለቃ ኅሩይ ናቸው፡፡ እሳቸው ‹‹ፍኖተ እግዚአብሔር›› በተሰኘ አስደማሚና ከመ/ብ አድማሱ ‹‹መድሎተ አሚን›› ጋር በምሥጢር የሚተባበር መጽሐፋቸው ገጽ 54 ላይ

‹‹መለኮት እንደ አካላት ከሦስት ይከፈላል የሚል ሰው ይህን ነገር ከራሱ አንቅቶ በልብ ወለድ ቃል ተናግሮታል እንጂ መጻሕፍት ከተናገሩት … አምጥቶ ለማስረዳት አይችልም፡፡ የሥላሴን ባሕርይ እንደ ሰው ባሕርይና አካል አድርጎ ‹አካል የሌለው ባሕርይ፣ ባሕርይም የሌለው አካል የለምና፣ ባሕርይ አካልን ተከትሎ ከሦስት ይከፈላል› ይላል፡፡ … ሥላሴ አካላቸው የተለየ ሲሆን ባሕርያቸው ተከፍሎ የሌለበት አንድ ለመሆኑ ማስረጃው የሦስቱ ልብ አንድ አብ ሆኖ አንድ ዕውቀትን ያውቃሉ፡፡ የሦስቱ ቃል አንድ ወልድ ሆኖ አንድ ነገርን ይናገራሉ፡፡ የሦስቱ እስትንፋስ አንድ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ አንድ የሕይወትን ሥራ ይሠራሉ፡፡ … ‹ይሤለሱ፡ በአካላት፡ ወይትወሐዱ፡ በመለኮት› … ፡፡ ባሕርየ መለኮት በአካል ከሦስት የማትከፈል መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ ከዚህ ወጥቶ ግን ‹መለኮት እንደ አካል ከሦስት ይከፈላል ማለት አብን ልብ፣ ወልድን ቃል፣ መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ› ማለትን ትቶ ‹ለሦስቱ በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው› ብሎ፣ ሦስት አማልክት የዮሐንስ ተዐቃቢን ሃይማኖት መመስከር ነው፤››

ይላሉ፡፡

ሃይማኖተ አበው ዘኪራኮስ ምዕራፍ 91፡11፣ ገጽ 399 ላይ የዮሐንስ ተዐቃቢን እምነት በቅዱሳን አበው ሲነቀፍ እናገኘዋለን፡፡ እንጥቀስ፡-

‹‹ … በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ ብለን የምናምን የእኛ ግን ሃይማኖታችን እንዲህ አይደለም፤ አንድ አምላክን እንሰብካለን እንጂ አንድ ባሕርይ፣ አንድ መለኮት፣ አንድ ኃይል ብለን፤ በዚህም አንድነት ለእያንዳንዱ አካላት ይከፈላል አንልም፤ ‹ሦስት አማልክት ሦስት ባሕርያት› ከሚሉት መናፍቃን ጋር አንድ በሚሆን በድንቁርናው የሚመካ ተዐቃቢ የሚባል ዮሐንስ እንደተናገረ ይህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አነጋገር አይደለም፤…››

እያሉ የዮሐንስ ኑፋቄ ከምሁራዊ ትምህርትና በአመክንዮ መራቀቅ መምጣቱን ይጠቋቁሙናል፡፡

በጎግል በኩል ከሰሜን-ምሥራቅ አፍሪካ የእንግሊዝኛ የጥናት መጽሔት ያነበብኳት የዶ/ር ክንዴነህ እንደግ ምጥን ጽሁፍ በታሪክና በወቅታዊ ሁኔታ ትንተናዋ ብትጣፍጠኝም በአስተምህሮ ትንተና ረገድ አላጠገበችኝም፡፡ ምሁሩ (በእኔ ትሁት እይታ) ሃይማኖተ አበውን፣ የአለቃ ኅሩይ ፈንታናን የመልአከ ብርሃን አድማሱን የምሥጢረ ሥላሴ ትንታኔዎች በጥሞና ሳይሔዱባቸው በተዋሕዶው ወገን የሥጋዌ ትረካ ላይ ያነሳሷቸውና ተዐቅቦ ያደረግሁባቸው 3 ነጥቦች አሉ፡፡ አምላክ ቢፈቅድ የሆነልኝ ቀን የአቅሜን አንብቤ የምመለስባቸው ነኝ፡፡ ላሁን በባለቅኔው ሐሳብ መጣጥፊቱ ትቋጭ! የመ/ር ይኄይስ ወርቄን ሰባልዮስንና ዮሐንስ ተዐቃቤን ሞጋች ቅኔ ከነትርጓሜዋ ከራሳቸው አንደበት በዕዘነ ልቡና እንስማት! የሙግቷ ማጠንጠኛ ኩነታትን ከፀሐይ ባሕርያት ጋር ያነጻጽራል፡፡

ሥላሴ

ባህል፡ ዘተዐቃቢ፤
ወባህለ፡ ሰባልዮስ፡ አስሐትያ፤
ለዘበአካላት፡ ኢክህሉ፤ ሥላሴ፤ አዕሩገ፡ ሠለስቱ፡ ኩነት፣
አልቦሙ፤ እምነ፡ ፀሐይ፤ ወእሳት፡ ፍልጠት፣
አጽፈ፡ ያዕቆብ፡ ወዔሳው፤ ምንታዌ፤ ወሰንዱነ፡ አርባብ፡ ትርብዕት፣
እስመ፡ ኢሀለዎሙ፤ እምትካት፣
እንበለ፡ አሐቲ፡ ልብሶሙ፤ ጽምረተ፡ ትሥልስት፣
ዘትሄሉ፡ በመዝገብ፤ ቅድመት፡፡

ትርጓሜው፡-

የዮሐንስ ተዐቃቢ ባህል ቅዝቃዜንና የሰባልዮስ ባህል ትምህርት ብርድን በአካላት ለማይችሉ ሦስት ኩነት (አኳኋን) ሽማግሎች ሥላሴ ከፀሐይና ከእሳት መለየት የለባቸውም፤ በሣጥን ቅድምና ከምትኖር አንዲት ልብስ ሦስትነት መገናዘብ በቀር የኤሳውና የያዕቆብ አጽፍ (መጐናጸፊያ) መንታነት ( ምንታዌ)ና የኪሩቤል ቀሚስ አራትነት (ርባዔ) ከጥንት ጀምሮ የላቸውምና፡፡

ምሥጢሩ፡-

ዮሐንስ ተዐቃቢ ሦስት አካላት በየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው ብሏል፡፡ (ይህ አባባል) የሥላሴ ልባቸውም፣ ቃላቸውም፣ እስትንፋሳቸውም አካላዊ ነውና ዘጠኝ አካላት አሉ ያሰኛል፡፡ ሰባልዮስም አንድ ገጽ ብሏል፤ (ሥላሴ) በአካል፣ በሥምና በግብር (ሦስት) ማለት ይቀራል፡፡ ስለዚህ ይህን ለማስረዳት ማለትም የዮሐንስ ተዐቃቢን ‹‹ሦስት መለኮት››ና የሰባልዮስን ‹‹አንድ ገጽ›› አስተምህሮ ለመሸሽ (የሥላሴ) የባሕርይ ኩነታት ሥሞች (ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ) በቅድምና የምትኖር ፀሐይን የሚሹ 3 አረጋውያን ተመስለው ቀርበዋል፡፡ ለፀሐይ 3 አካላዊ ኩነታት አሏትና፡፡

(አባቶች እንዳስተማሩን) የፀሐይን አካላዊ ኩነት ለሥላሴ ባሕርያዊ ኩነታት ሰጥተን (በምሳሌ ዘየሐፅፅ) እንናገራለን፡፡ ይኸውም ለፀሐይ በመንበሯ ያለ ክበበ አካል ( ፀሐይ /ግዘፈ-ፀሐይ/)፣ ብርሃንና ዋዕይ (ሙቀት) አላት፡፡ ብርሃኑ ወደ ብሌናችን ገብቶ በነጸብራቁ ማየታችንን ስንገልጽ ስለ ፀሐይ ብርሃን እንጂ ስለሙቀቱና ስለ ክበበ ፀሐይ (ግዘፈ-ፀሐይ) እያወጋን ወይም በሌላ አነጋገር ጠቅላላውን የፀሐይ አካላዊ ባሕርይ እየጠቀስን አይደለም፡፡ ፀሐይ (ግዘፈ-ፀሐይ) የተባለ አብ ነው፤ ብርሃን የተባለ ወልድ፣ ዋዕይ (ሙቀት) የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ብርሃን ስናይ ስለ ሙቀትና ፀሐይ ማውጋት ግድ እንዳይደለ ሁሉ ቃል (ወልድ) በተለየ አካሉ ከባሕርያችን ተዋሐደ ሲባል ‹‹የ3ቱ አካላት ባሕርየ መለኮት አንድ ነውና፣ ባሕርይ ተዋሕዶ አካል አይቀርምና 3ቱም በአካልና በባሕርይ ከሥጋ ማርያም ተዋሐዱ ያሰኝብሃል›› የሚለው አፀፋዊ ክርክር ‹‹ዓይን በብርሃን አየ›› ማለትን ‹‹በሙቀትና በግዘፈ ፀሐይ ጭምር አየ ካላልክ ብርሃን እንደታየ አይቆጠርም›› ብሎ እንደ መተርጎም ይቈጠራል፡፡ ብርሃነ-ፀሐይ ከፀሐይ አካል ተወልዶ፣ ፀሐያዊ ባሕርዩን ሳይለቅ ከብሌናችን ተዋሕዶ በብርሃኑ እንድንመላለስ ካደረገን ወዲያ የዓይንን እይታ ለማረጋገጥ የፀሐይ ከሰማይ መውረድና የሙቀት መሰማት ግድ ሲሆን አላየንም፡፡

‹‹ኅቡረ፡ ኅላዌ፡ ምስለ፡ አብ፡ በመለኮቱ፣ ኅቡረ፡ ኅላዌ፡ ምስሌነ፡ በትስብእቱ፤ ውእቱመ፡ አሐደ - እንደ አምላክነቱ ከአብ ጋራ በባሕርይ አንድ የሚሆን፣ እንደ ሰውነቱም ከእኛ ጋር በባሕርይ አንድ የሚሆን፤ እርሱ አንድ ነው፤››

የሚለው ከተረፈ ቄርሎስ የተወሰ ቃል ለርእሳችን መልካም ማሳረጊያ ነው፡፡

በአሚነ ሥላሴ ያጽናን !