ካሣ ለተዋሕዶ! (አማኝ አብዮተኛ)

ethiopia
atsetewodros
orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

ካሣ አማኝ አብዮተኛ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የካሣ አብዮት መንፈሳዊ ገጽታም ነበረው፡፡ በዘመነ መሣፍንት ክርስትናችን በሦስት ውሳጣውያን ዘውጎች ትታመስ ነበር፡፡ በንግሥናው መንበር ጠንካራ ንጉሥ አለመኖር ከካቶሊካውያን ሌጋሲ ጋር ተዳምሮ የጳጳሳቱን ተሰሚነት ገደል አገባው፡፡ የየክፍለ ሀገሩ ቤተ ክህነት አመራር የየመሣፍንቱ ቶፋ ሆነና የየራሱን ብሒል ክፍለ ሀገራዊ ገጽታ አላብሶ ገናናዋን ሀገር ያለማዕከል አስቀራት፡፡ በተለይም የተዋሕዶው ወገን ሁነኛ መሣፍንታዊና ቤተ ክህነታዊ ውክልና ለማግኘት ይቸገር ጀመር፡፡ ለጸጋ ብሒል የተገዙት እጨጌዎች በበቅሎ እየተንጎራደዱ ጳጳሳቱን ከነተዋሕዶ ብሒላቸው ያጠድፏቸው ጀመር - ከማዕከለ መንግሥት - ከጎንደር፡፡ እጨጌ ወልደ ዮናና እጨጌ ማኅፀንቱ እንዲያ አድርገዋል፡፡ በዚህ መካከል ከፈረንሳይ መንግሥት ከለላ የተሰጣቸው የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ይሠርጉ ጀመር፡፡ ግብፅ ድንበር ለድንበር ታገሣ ጀመር፡፡ ይህ ሀገራዊ ድኩምነትና ሃይማኖታዊ መበጣጠስ በብዙኃኑ የተዋሕዶ ተከታይ ኢትዮጵያዊና በተራው ካህን ዘንድ ቁጭትን ሳይቀሰቅስ አይቀርም፡፡ ካሣ በዚህ ቁጭት ነድዶ ከቋራ የተወረወረ ነዲድ ፍላጻ ነበር፡፡ ነደደ፡፡ መሣፍንቱን አነደደ፡፡ አከሰመ፡፡ ለንግሥናው ተቃረበ፡፡ ከዚያ በፊት ግን አንድ የቤት ሥራ ነበር፡፡ ምስኪናን ምዕመናንና ካህናት የጮሁለት አጀንዳ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ አንድነት፡፡ እሱ ደግሞ እንዲሁ በኃይል ብቻ የሚሆን አልነበረም፡፡ ጉባኤና የጳጳስ ግዝት ያስፈልገዋል፡፡ ከጉባኤ በፊት ሊቃውት መጠራት አለባቸው፡፡ የሰከነ ምክክርና ከቂም በቀል የፀዳ ልብም እንዲሁ፡፡

1. ጉባኤው፡ የአምባጫራ ጉባኤ

ብቻቸውን ሕያው ተቋም የሆኑልን ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ከዶንልድ ክሩሚ ጋር ያኖሩልን መዝገብ (Abuna Salama: Metropolitan of Ethiopia, 1841-1867 A new Ge’ez Biography) እንዲህ ይላል፤

ወእምድኅረዝ፡ ተመይጠ፡ ደጅ፡ አዝማች፡ ካሳ፡ እምኀበ፡ ጎጃም፡ ምስለ፡ ብዙኅ፡ ምህርካ፡፡ … ወገብረ፡ ትዕይንተ፡ በወይና፡ ደጋ፡ ዘትሰመይ አምባጫራ፡፡ ወህየ፡ ነቢሮ፡ ጸውዖ ለጳጳስነ፡ ሰላማ፡ እምኀበጎንደር፡ ኀቤሁ፡፡ … ወነበሩ፡ ኅቡረ፡ ሰሙነ፡ መዋዕለ፡ እንዘ፡ ይዛውዑ፡ ነገረ፡ ሃይማኖት፡ ኦርቶዶክሳዊት

ከዚህም በኋላ ደጅ አዝማች ካሳ ከብዙ ምርኮ ጋር ከጎጃም ተመለሰ፡፡ … አምባ ጫራ በምትሰኝ (ቦታም) ከተማ (ሰፈራ) አደረገ፡፡ እዚያ ሁኖ ጳጳሳችን ሰላማን ከጎንደር ጠራው፡፡ … የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትም ጉዳይ እየተጨዋወቱ ለሳምንት ተቀመጡ፡፡

ከዚህ በኋላ ሊቃውንት ከየክፍለ ሀገሩ ተጠሩ፡፡ ‹‹እኩሌቶቹ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት የአብ የባሕርይ ልጅ ነው ይሉ ነበር፡፡ እኩሌቶችም ኢየሱስ ክርስቶስ በስጦታ (በጸጋ) ተቀባ፤ መጽሐፍ ሰወ በሆነበት ግብር ተቀባ ይላልና፤ በዚህም ቅብዓት በጸጋ የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ የሚሉ ነበሩ፤ ይህንንም ጸጋ ሦስተኛ ልደት ይሉታል - ዘመንፈቆሙ፡ ይቤሉ፡ ኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ በቅብዓተ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ ወልደ፡ ባሕርየ፡ አብ፡ ውእቱ፡፡ ወመንፈቆሙ፡ ይቤሉ፡ ኢየሱስ፡ ክርሰቶስ፡ በዘአምኀ፡ ተቀብዓ፡ እንዘ፡ ይብል፡ መጽሐፍ፡ በዘተሰብአ፡ ተቀብዐ፡፡ ወበዝቅብዓት፡ ኮነ፡ ወልደ፡ እግዚአብሔር፡ በጸጋ፡፡ ወለዝ፡ ቅብዓት፡ ይብልዎ፡ ሣልሳይ፡ ልደት፡፡››

ልዩነቱ ከላይ የተገለጸው ብቻ አልነበረም፡፡

  1. በኩነታዊ የሥላሴ የባሕርይ መገናዘብ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ጌታን ማንኛውም ቅዱስ እንደሚራዳ ይራዳው ነበር፣
  2. ጌታ ካረገም በኋላ በለበሰው ሥጋ የበታች ነውና እንደ ሌሎች ቅዱሳን ለአብ ምስጋና ያቀርባል፣
  3. ሕፃናት በማኅፀን ሳሉ ያውቃሉ፣
  4. ‹‹ወላዲተ አምላክ ኃጥአንን ለመቤዠት ሞተች - ወላዲተ፡ አምላክ፡ ሞተት፡ ለቤዛ፡ ኃጥን››፤ ሐዋርያትና ጻድቃን ግን ከኃጢአት ፍጹማን ስላልሆኑ ሞቱ የሚሉ ኢመጽሐፋውያን አባባሎችና
  5. ከሞተ በኋላ ምውትን የማቁረብ ሥርዓት ነበር፡፡

በዚህ ላይ ቅብዓትና ጸጋ ሲጨመሩ ከካሣ ፊት የተደቀኑት ሃይማኖታዊ አጀንዳዎት 7 ደረሱ፡፡ ስለ 5ቱ ፍጻሜ ባይነገረንም አቀራረቡ መወገዛቸውን ያመለክታል፡፡ በተለይም ሕፃናት በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ ያውቃሉ - ‹‹የአምሩ፡ ሕፃናት፡ በከርሠ፡ እሞሙ›› የሚለው አቋም በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመንም ሙስሊሞችን ባሳተፈ መልኩ አከራክሯል፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም እንዲያ ዓይነት አቋም አላቸው፡፡ የአቋሙ ችግር ‹‹ነፍስ ከእናትና አባት የምትከፈል ሳትሆን አስቀድማ ያለችና ያለሥጋም ሕልውና ያላት ፍጥረት ናት›› ከማለት የመነጨ ነው፡፡ እመቤታችን ለቤዛ ኃጥአን ሞተች የሚለው ፖሮቴስታንቱን መዓልም ጴጥሮስን ለመቃወም ሲባል ገደብ በተላለፈ ቀናዒነት የተስፋፋ ብሂል መሆን አለበት፡፡ ሰጊድን በሚመለከትም ለእመቤታችን የሚደረገውን የጸጋ ስግደት ከአምልኮው ጋር የሚያምታቱ ‹‹ዘምስለ ወልዳዎች›› ከቅብዓትና ከጸጋ ወገኖች መካከል አይታጡም፡፡ በ2009 ዓ.ም. በቅብዓቶች የወጣው ‹‹መጽሐፈ ሚስጢር›› (ገጽ 124) መዓልምን መቃወሙና እመቤታችንን ማክበሩ መልካም ሆኖ ሳለ ለእመቤታችን ከአብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ የተጠጋ ምስጋና ስግደት ለመስጠት መዳዳቱ ይከብዳል፡፡ በዚሁ አንጻር ጌታ ዛሬም በለበሰው ሥጋ ለአብ ምስጋና ያቀርባል የሚለው አባባል ከመዓልም ጴጥሮስ ትሩፋቶች የመሆን እድል አያጣም፡፡ የተዘረዘሩት ኢ-ኦርቶዶክሳውያን ብሒሎች ቅድመ-ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ለመኖራቸው የነኢዘንበርግ የጉዞ ማስታወሻ (Journal of the Rev.Mesers, Isenberg and Krapf, 1843) ያረጋግጣል፡፡

ወደ እጩው ነጋሢ - ወደ ካሣ - የአምባ ጫራ ጉባኤ እንመለስ፡፡ ካሳ ሊቃውንቱን ይጠይቃል ፤

‹‹መኑ፡ ውእቱ፡ ሐዋርያሃ፡ ለኢትዮጵያ፤ ወመኑ፡ ውእቱ፡ ዘአምጽአ፡ ክርስትና፡ ለብሔረ፡ አግአዚ

የኢትዮጵያ ሐዋርያዋ፣ ክርስትናን ለሀገረ አግአዚ ያመጣስ ማን ነበር?

[ አግአዚና አግአዝያውያን መባል በመዛግብቶቻችን ለትግራይ-ኤርትራ የሚነገርበት ጊዜ አለ፤ ለመላ ኢትዮጵያም የሚነገርበት ጊዜ አለና ካሳ ሀገሩን ‹‹ብሔረ አግአዚ›› ይላታል፡፡ ]

ሊቃውንቱ ጵጵስናው ከእስክንድርያዋ የማርቆስ መንበር የሆነው ከሳቴ ብርሃን ሰላማ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከሣ እንደገና ይጠይቃል፤

‹‹ቦኑ፡ እምሊቃነ፡ ጳጳሳት፡ ዘእስክንድርያ፡ ዘሰበከ፡ ልደተ፡ ጸጋ፡ ሣልሳዌ፡፡ ወሚመ፡ ልደተ፡ ባሕርያዌ፡ በቅብዓተ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ -

ከቶ ከእስክንድርያ ጳጳሳት ሦስተኛ የጸጋ ልደትን ወይም በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት የባሕርይ ልደትን የሰበከ አለን?››

ሊቃውንቱ ይመልሳሉ፤

‹‹እንዲህስ በእስክንድርያ የለም፤ አባቶቻችን እዚሁ አስተማሩን እንጂ - ዝሰ፡ አልቦ፡ በእስክንድርያ፡ ዳዕሙ፡ አበዊነ፡ በዝየ፡ መሐሩነ፡፡››

ከዚህ በኋላ ካሣ ብዙ አላወራም፡፡ አጭር አዋጅ ታወጀ፡፡

‹‹ኢትፃዑ፡ እምሃይማኖተ፡ እሉ፡ አበዊነ፡ ጳጳሳት - ከዚህ የአባቶቻችን ጳጳሳት ሃይማኖት አትውጡ!››

ትእዛዝ ነው! በትእዛዙ ላይ እንደገና ዐዋጅ የሚከተለው የሰላማ ግዝት ተጨመረ!

2. የአቡነ ሰላማ ሣልሳይ ቃለ ሃይማኖትና ግዝት

የደብረ ታቦር ዕለት (ነሐሴ 13 ቀን 1846 ዓ.ም.) ተከታዩ የአቡነ ሰላማ ንግግር በአምባ ጫራ ጉባኤ ተላለፈ፡፡

‹‹ቃል፡ ሥጋ፡ ኮነ፤ ወሥጋኒ፡ ኮነ፡ አምላከ፡ በተዋሕዶ፡፡ ወበዝተዋሕዶ፡ ቃል፡ ምስለ፡ ሥጋ፡ ወሥጋ፡ ምስለ፡ ቃል፡ ፩ አካል፡ ፩ ባሕርይ፡ [ውእቱ]፡፡ ወበሰብእናሁ፡ የአምር፡ ከመ፡ አብ፡ ወመንፈስ፡ ቅዱስ፡ ወበተዋሕዶ፡ ወልደ፡ ባሕርየ፡ አብ፡ ውእቱ፡፡ ወበሰብእናሁ፡ አምላክ፡ ውእቱ፡፡

ቃል ሥጋ ሆነ፤ ሥጋም በተዋሕዶ አምላክ ሆነ፡፡ በቃል ከሥጋ ጋር፣ በሥጋ ከቃል ጋር በሆነ ተዋሕዶ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ነው፡፡ በሰውነቱ እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ ያውቃል፤ በተዋሕዶ የአብ የባሕርይ ልጅ ነው፡፡ በሰውነቱ አምላክ ነው፡፡››

ከዚህ ቃለ ሃይማኖት በኋላ ማንም ከተናገሩት እንዳይወጣ ጳጳሱ ከነግኅ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ሲገዝቱ ዋሉ፡፡ በዘጠኝ ሰዓት ዳግመኛ የንጉሡ ዐዋጅ ተሰማ፡፡ በግዝት ላይ ዐዋጅ ተጨመረ፡፡ ዐዋጁ ካሣ ነውና ‹ከፍ ብሎ አንገትን፣ ዝቅ ብሎ ባትን› እስከማሳጣት የሚደርስ ነው፡፡ አቡነ ሰላማ በኑፋቄ ያወገዙትን ካሣ በወንጀል ይጠይቀዋል ማለት ነው፡፡ የተዋሕዶ ማዕከላዊ ሉዓሌ (ልዕልና) በዘመነ መሳፍንት ማግስት፣ ቅድመ ንግሥና ቴዎድሮስ፣ አምባ ጫራ ላይ ዳግም ተተከለ፡፡ ከሣ ዘውድ የደፋው ቀድሞ ተዋሕዶን አንግሦ ነው፡፡ ካሣ ዘውድ የደፋው በሰሎሞናውያን ነገሥታት ጸያፍ ልማድ ሆኖ የኖረውን ዕቁባት ማበጀት ከልቶ በሥርዓተ ተክሊል ነው፡፡ ካሣ ዘውድ የደፋው ለተዋሕዶ ተቋማዊ ቁመና ሰጥቶ ሲያበቃ ነው፡፡ በውጥኑ ዘልቋል አልዘለቀም፣ ከሳላማ ጋር የነበረው ፍቅር ዘለቀ አልዘለቀም፣ ዐላማውን ለማስፈጸም የሔደበት ጎዳና የቀና ነበር ወይስ ጐፃጕፅ የበዛበት፣ በሥርዓተ ቁርባን መወሰኑን ከተዋበች ወዲህ ገፋበት ወይስ ቁርባኑን አፈረሰ … ለሰለጠነ የመወያያና የቡና መጠጫ ወጎች አርዕስት መሆን ይችላሉ፡፡

በበኩሌ፡- ቦሩ ላይ እንዳትናወጽ ሆና በካሳ ምርጫ የተሰቀለችውን የተዋሕዶ ባንዲራ ከሀገራዊ ህልሙ ጋር አምባ ጫራ ላይ ሸምኖ ለትውልድ አስተላልፏት አሳልፏት ላለፈው ካሣ ያለኝ ፍቅር ደም የሚያሞቅ፣ ባቆረዘዙ ዓይኖች የሚታሰብ፣ ፍትሐ ነገሥት ገልጦ ግብሩን ለመዳኘት የሚከለክል ጥጥር፣ ውጥር ያለ ሲቃ የተሞላበት መንፈስ ነው፡፡ ካሣ ላይ እንደሰው፣ እንደ ንጉሥ፣ እንደ ሀገር መሪ ለሚሰነዘሩ ምክንያታውያን ትችቶች ጆሮ አልነፍግም፡፡ ራሱም በፍጻሜ ዘመኑ ይወስዳቸው የነበሩ እርምጃዎች ያፀፀቱት እንደነበር ሳይናገር የቀረ አይመስለኝምና ለመማማሪያና ለተግሳጽ ቢነገሩ አይከፋኝም፡፡ የሚከፋኝ አጥንት ለመስበር የሚሮጡ መስለው በሚታዩኝ ክቡራን ጸሀፍት ነው፡፡

3. መጽልማነ ቴዎድሮስ

ዐፅሜ አዲስ ገብ ካቶሊክ ናቸው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የቦሩ ውጉዛን የነአለቃ ክፍለ ጊዮርጊስና የቀለም ልጅና የአለቃ ተክለ ጽዮን የጸጋ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ ሁለቱ ጸሀፍት በኢትዮጵያ ታሪክና የግእዝ-አማርኛ የቋንቋ እድገት አስተዋጽኦ ያላቸው ድርሻ ከተቋም የሚተካከል ነው፡፡ ክፋቱ፣ ለየሚያምኑበት እምነት የሃይማኖት ብሒልንና ታሪክን ጠምዘው ይሠዋሉ፡፡ መይሣው ካሣ አምባ ጫራ ላይ በነበረው ፀረ-ጸጋ (ኋላም) ወካቶሊክ አቋም የተነሣ፣ ሸዋ ሲዘምት እነ አለቃ አሥራት ከጸጋ ብሒል ደጋፊው ከንጉሠ ሣህለ ሥላሴ በወሰዱት ተልእኮ አቡነ ሰላማ ላይ ያደረሱትን መሳደድ ለመበቀል በአቡነ ሳላ ተገፋፍቶ በወሰደው መጠን የተላለፈ እርምጃ መነሻነት፣ የእጨጌነትን ሥልጣን ከቤተ ተክለ ሃይማኖት ገፍፏል በሚል ቂም፣ ሊቀ ካሃናትነቱን ከእጨጌው ወስዶ ለአቡኑ ሰጠ በሚል ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ሽኩቻ የተነሣ፣ … በብዕራቸው ይጨክኑበታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ አፄ ቴዎድሮስን ‹‹ዳግማዊ ግራኝ›› እስከ ማለት አቡነ ሰላማን ‹‹ኢሰላማ›› እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ የአቡነ ሰላማን ሰብእና ለመግደል የሚሔዱበት ርቀት ካቶሊካውያኑ እነ አባ አንጦንዮስ በኢ/ ካቶሊካዊት ቤ/ክ ላይ የጻፉትን ያስንቃል፡፡ የነአለቃ አሥራትን አሳዳጅነት ‹‹ትግሬ መርቶት መጣ ያን ረጅም አቡን›› እያሉ ባንቆለጳጰሱበት ብዕር በእሳቸው የብሒል ወገን ላይ ጦሩ ሲዞር ግን ለማውገዝ መናሳሳታቸው ያስተዛዝባል፡፡ ያም አልበቃ ብሎ ከሊቃውንት ጉባኤ እይታ ውጪ በቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ በታተመተው ተአምረ ማርያም ላይ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴን ከፍ ለማድረግ ካሣ ‹‹ካሣ›› ሆኖ ቀርቧል፡፡ ያሳዝናል!!! ደግነቱ፣ ለተግባር ዳተኛነት አያጣውም የምንለው ቅደሱ ሲኖዶሳችን ማዕከላዊነትን ባልጠበቁ ኅትመቶች ላይ ተግሳጽ አሳርፏልና በዳግም ኅትመት መጽልማነ-ቴዎድሮስ የሆኑ ስርዋጾች ይወጣሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

4. ትንሣኤ ቴዎድሮስ

1960ዎቹ ለአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ የትንሣኤ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሦስት ልደቶችንና ቅብዐዓቶችን የገሠጸው ቴዎድሮስ ከነጸጋዬ ገብረ መድኅን ብዕር - በጥበብ አምባ - ዳግም ተወለደ፡፡ በተወሰኑ የ1960ዎቹ ትውድ አባላት ለተምሳሌትነት ተጠራ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም እንኳ ከካሣ ተጣግቶ፡-

‹‹ካሣ፤ በመቶ ዓመቱ ቢያገሳ፣
ስንቱን … ስንቱን ቀሰቀሰውሳ፡፡››

ተባለለት፡፡ ቴዎድሮስ ተነሣ፡፡ ከቤተ ክህነት ወገንም ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው ተገኘ፡፡ በታሪክ የተዋሕዶ አምባ መሆኑን መዛግብቱ ከመሰከሩለት የላስታ መስመር የመጡት ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ ‹‹በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ›› መጽሐፋቸው የካሳን ታሪክ ቄደር የማጥመቅ ያህል ከድቀቱ አነሡት፡፡ የካሣ የአምባ ጫራ ውለታ ተዘከረ፡፡ ካሣ ‹‹የቤተ ክርስቲያናንን ይዞታ ነጠቀ›› ሲባል የምንሰማው ፕሮፖጋንዳ ‹‹የቶፋ አሳዳሪ ባላባቶች›› ንብረት እንጂ የምስኪናን ካህናት እንዳልነበር ዘግይቶ ገባን፡፡ ሞቱንም ‹‹በኢግዙራን እጅ ላለመውደቅ›› እንደሚደረግ የብሉይ ዘመን ቤተ እስራኤላውያን፣ የነሶምሶን ዓይነት የክብር ሞት አድርገን ቆጠርንና ዳግም ስሙን በጸሎታ እናነሣው ጀመር፡፡ በአንዳንድ ባለቅኔዎችም እንደ መድኃኔ ዓለም በገዛ ፈቃዱ ሞተ እየተባለ ይነገር ጀመር፡-

‹‹…መድኃኔዓለም፡ ቴዎድሮስ፤
በፈቃደ፡ ርእሱ፡ዘሞተ፤ ወተመጠወ፡ ኵነኔ፣
ለእለ፡ ተዘርው፤ በብዙህ፡ ኩርጓኔ፣
አባግዐ-በቀል፡ ወቂም፤ መሳፍንተ-ኀሊፍ፡ ምጣኔ፣…››

በእርግጥ፣ መንገዱ አባጣና ጎርባጣ ቢሆንም፣ የተረከባት ኢትዮጵያ ጓዘ ብዙ ሆና ሸክሙ ከብዶት በግራና ቀኝ ገጭቶ ያለፋቸው ነፍሳት ቁጥር ቀላል ባይሆንም፣ ልዩ ልዩና ከአመክንዮ የወጣ መነሻ ባላቸው ጸሀፍት ቢዘመትብትም፣ ታሪኩና ዘሩ ትርጓሜው ቢበዛም፣ … ሁለት ነገር እርግጥ ነው - እንደ እኔ!

  1. ቴዎድሮስ፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተነሥቶ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኖሮ፣ በኢትዮጵያዊነት ኩራት ብቻውን ለብቻው በብቻው የተሸኘ ሰው!
  2. ቴዎድሮስ ተዋሕዶ ነበር!

እናም፡- በእኔ አጥቢያ ቤ/ክ፡- ‹‹ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለነፍሰ ንጉሥነ ቴዎድሮስ›› ማለት ከጀመርን ሰነበትን!

ማስታወሻ፡-

  1. አፄ ቴዎድሮስ በደብረ ታቦር ጉባኤ ማካሄዳቸውን አንዳንድ መዛግብትና መልአከ ታቦር ተሾመ ጽፈዋል፡፡ እንደ አምባ ጫራ ጉባኤ የአስተዋጽኦአቸውን ያህል በእኔ ትውልድ የሚገባቸውን እውቅና ባለማግኘታቸው የምጸጸትባቸው የቤተ ክህነቱ ቤተ መጻሕፍት አደራጂ ገብረ ዮሐንስ ገብረ ማርያም የደብረ ታቦሩ ጉባኤ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ-መንግሥት መሆኑን አይናገሩም፡፡ በራሱ ጉግሣ የምስፍና ዘመን እንደሆነ ነው የሚናገሩ፡፡ የእኔም ልብ ወደ እሳቸው ያደላል፡፡
  2. የቦሩ ሜዳ ጉባኤ ብዙ ያልተነገረለት የአምባ ጫራ ጉባኤ ማሳረጊያ ነበር! አምባ ጫራ ከጎንደር ደቡብ-ምሥራቅ 30 ኪ.ሜ. ላይ የምትገኝ ፕላቶአማ ሥፍራ ናት፡፡
  3. ሃይማኖት ውስጥ ኃይል መግባት የለበትም በሚለው አቋም አስማማለሁ፡፡ በታሪክ ግን እንዲያ አለመሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ለጸጋ የወገኑ ነገሥታት ደጋግመው የላስታና የዋግ ተዋሕዶዎችን (በእነሱ አነጋገር ‹‹ካራዎችን››) ማሳደዳቸውን ዜና መዋዕሎቻቸው አይሸሽጉም፡፡ ቅብዓቶች የበላይነት ባገኙበት ጊዜ ተዋሕዶዎችንና ጸጋዎችን በድንጋይ ውግራት እስከ ማጥፋት መድረሳቸውን የራሳቸው ‹‹መጽሐፈ ሚስጢር›› አይሸሽግም፡፡ ለተዋሕዶ ቀናዕያን የነበሩት ነገሥታት አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሐንስም ከተዋሕዶ ባልወገኑት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡ አፄ ሱስንዮስ ደግሞ ቅብዓትን ከተዋሕዶ ሳይለዩ በሁሉም ላይ እስከተቻላቸው ዘምተዋል፡፡ ስለዚህ በኃይል አጠቃቀም ረገድ፡- ሁሉንም ታሪክ ደምሮ የራስ ሀገራዊ ታሪክ አድርጎ ከመቀበል በቀር ማን የማንን የታሪክ አናት ለመግመስ የውግረት ድንጋይ ማንሣት ይችላል?

መልሱን ለየራሳችን ይዘን ሦስቱም ዘውጎች በሚያኑበት ጸሎት እንዝጋ፡- ‹‹ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ ይዕቀባ እመዓተ ወልዳ!››