ያልተዘመረላቸው ጀግና — ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን


(Achamyeleh Tamiru) #1

ኢትዮጵያ መቼም የጀግኖቿን ውለታ ቅርጥፍ አድርጋ የምትበላ አገር ሆናለች። ከአርበኞቻችን ቀን ጋር በተያያዘ ዛሬ ከዚህ በፊት አስተዋውቄያቸው የነበሩን አንድ ያልተዘመረላቸው ጀግና ደግሜ ላስተዋውቃችሁ ወደድሁ። እኒህ ያልተዘመረላቸው ጀግና ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን ይባላሉ።

ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን ተከዜ አጠገብ እንዳባጉና የተባለውን ጣሊያኖች መሽገው የተቀመጡበትን ቦታ ከብበው እንዲጠብቁ በሰሜን ጦር አዛዡ በደጃዝማች አያሌው ብሩ የተላኩ የጦር አለቃ ነበሩ። ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን ታህሳብ 5 ፥ 1928 አመተ ምህረት ሌሊቱን ተከዜን ተሻግረው አፋፉን ከወጡ በኋላ፥ ተሸሽገው የሚቆዩበት ጫካ ፍለጋ ወደፊት ሲሄዱ እንዳባጉና አጠገብ እንደደረሱ ስለነጋባቸው ትንሽ ቆጥቋጦ አግኝተው እዚያው መስፈር ግድ ሆነባቸው።

ያ የሰፈሩበት ቦታ ትንሽ ቆጥቋጦ እንጂ ጫካ የሌለበት በመሆኑ እንዳባጉና እንደደረሱ በጠላት ዘንድ ባይታወቅም ሳይታዩ ሊውሉና ሊያድሩ ግን አይችሉም ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ጦራቸው ጠላት ባለበት እንኳ ሳይደርስ በጣሊያን አውሮፕላን እንዳያልቅ በመስጋት በበነጋታው ንጋት ላይ እንዳባጉናን ለመምታት ወሰኑ።

ከዚያ በኋያ ያለውን የጦርነቱን ዝርዝርና ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን የፈጸሙትን ጀብዱ ሀዲስ አለማየሁ «ትዝታ» በሚል የጻፉትን መጽሀፍ ከሶስት አመታት በፊት ሳነብ ከገጽ 58 እንከ ገጽ 59 እንደወረደ የከተብሁትን እንደዚህ አቅቤዋለሁ።

የእንዳባጉና ጦርነት ታህሳስ 6፥ 1928 አመተ ምህረት ነበር የተደረገው። በሰው ቁጥር፥ እንዳባጉና መሽጎ ከተዋጋው የጣሊያን ጦር፥ የፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን ይበዛ እንደነበር በጦርነቱ ተካፋዮች የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ። በመሳሪያ በኩል ግን በሁለቱ ወገኖች መሀከል የነበረው ልዩነት የሰማይና የምድርን ያህል የተራራቀ ነበር! የኢትዮጵያውያን መሳሪያ አበዛኛው ያው አሮጌ ጠመንጃ ነበር። በዚያ አንጻር የጣሊያኖች ጦር ምሽጉን አጠንክሮ ሰርቶ ይዋጋ የነበረ ከመሆኑ ሌላ፥ መድፎች፥ ብዙ ከባድና ቀላል መትረየሶች፥ እንዲሁም የጅ ቦንብ በብዛትና ታንኮች ነበሩት። ያም ሆኖ በመጨረሻ ድሉ ለኢትዮጵያውያን ሆነ።

በጦር ሜዳ እንኳንስ የጠላትን ሙታትንና ቁስለኞች፥ የራሳችንንም፥ ቆጥሮ የመያዝ ልምድ ስለሌለን፥ በእንዳባጉና ጦርነት ከኛም፥ ከጠላትም ምን ያክል ሞተው ምን ያክል እንደቆሰሉ፥ በኛ በኩል እርግጡን የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፤ መቼም እኔ አላውቅም። ማርሻል ባዶግሊዮ ግን፥ «የኢትዮጵያ ጦርነት» (La guerra di Ethiopia) በተሰኘው መጽሀፉ፥ ከጣሊያን ጦር ወገን የሞቱና የቆሰሉ 392 ወታደሮችና 9 መኮንኖች በድምር 401 መሆናቸውን ጽፏል።

ታዲያ እንዳባጉና ጦር ሜዳ ላይ ከሞቱት ተርፈው የእንዳ ስላሴን መንገድ ይዘው ሲሸሹ እስከ ብዙ ኪሎ ሜትር ድረስ ወድቀው ይታዮ የነበሩ የጣሊያንና የመለዮ ለባሽ «አሽከሬ» ሬሳዎች ቁጥር ተይዞ ሲገመት፥ ማርሻል ባዶግሊዮ የሰጠውን የሙታንና የቁስለኞች ቁጥር የሚያስተባብል ሆኖ ይገኛል፤ ከጣሊያንም ከኢትዮጵያም ወገን የሞቱትና የቆሰሉት ትክክለኛ ቁጥራቸው ባይታወቅም ብዙ ነበሩ። ከጣሊያኖች የተማረከው መሳሪያም እጅግ ብዙ ነበር። ከባዱና ቀላሉ መትረየስ፥ ጠመንጃው፥ የመትረየሱና የጠመንጃው ጥይት በሳጥን በሳጥን እንዳለ፥ ሁሉም ብዙ ነበር። ሊሬው ከወታደሩ ተርፎ በባላገሩ እጅ በብዛት ይገኝ ስለነበር እኛ ስንደርስ፥ ባንድ ብር እስከ ሺህ ሊሬ ይለወጥ ነበር። የተሰባበሩም፥ ያልተሰባበሩም ታንኮችና ብረት ለበስ ካሚዎኖች በጦሩ ሜዳና በእንዳ ስላሴ መንገድ ቆመውም ተገልብጠውም በብዛት ይታዩ ነበር።

ማርሻል ባዶግሊዮ ስለጦርነቱ በመጽሀፉ ሲተች፥ «የእንዳባጉና ጦርነት ከጠቅላላው ጦርነት አንጻር ሲታይ፥ ከቁም ነገር የሚቆጠር አይደለም» ብሏል። እርግጥ ከጠቅላላው ጦርነት አንጻር ሲታይ፥ የእየንዳባጉና ጦርነት ትንሽ ነው። ነገር ግን ብቻውን ሲታይ፥ ብቻውን መታየትም ይገባዋልና፥ ታሪካዊ ነው። የእንዳባጉና ጦርነት የተደረገበት ቦታ፥ የተደረገበት ቀን፥ በጦርነቱ ድል ያደረጉት ኢትዮጵያውያንና ድል የሆኑት ጣሊያኖች፥ የራሳቸው የሆነ መልክና ጠባይ ያሏቸው ናቸው። ስለዚህ ኢጣሊያ በመጨረሻው በጠቅላላው ጦርነት ድል አድራጊ ሆና ኢትዮጵያን መያዝዋ፥ የእንዳባጉናን መልክና ጠባይ አይለውጠውም። ኢጣሊያ በመጨረሻ ኢትዮጵያን ድል አድርጋ መያዟ፥ እንዳባጉና ያለቁትን ጀግኖች ከሞቱበት በግዝፈ—ሥጋ አያስነሳቸውም፤ አካላተ ጎደሎዎች የሆኑትን ባለሙሉ አካላት አያደርጋቸውም። ይህ የተደረገ አድርጎት ስለሆነ የተደረገው እንደገና እንዳልተደረገ ሊሆን አይችልም! እርግጥ በሌሎች ቦታዎችና በሌሎች ቀኖች ኢጣሊያ ድል አድርጋ ኢትዮጵያን ይዛለች።

ነገር ግን ያ ሁሉ ጀግናው ፊታውራሪ ሽፈራውና ጀግኖች ተከታዮቻቸው የኢጣሊያን ምሽግ አፍርሰው፥ የመድፍና የመትረየስ አጥር ጥሰው፥ ታንክ ሰባብረው፥ የሚበዙትን ጣሊያኖች ገድለው፥ የተረፉትን መሳሪያቸውን እያስጣሉ አባርረው የእንዳባጉናን ድል የተቀዳጁ መሆናቸውን በምንም መንገድ ሊለውጠው አይችልም! ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ድል አድርጋ መያዝዋ፥ የፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁንን ጀግንነት ሊቀማው አይችልም! ሽፈራው ድል ባደረገበት ቦታ፥ እንዳባጉና ላይ ቢወድቅም፥ ምድርን ከነታሪኳ የሚያጠፋ መአት እስካልመጣ ድረስ፥ ጀግንነቱና ስሙ ከእንዳባጉና ተራራ ጋር ለሁልጊዜ ይኖራሉ።