የዓርብ ጨዋታ፡- የግእዝ ዘፈን፣ ፉከራና ሙገሳዎች

music
geez

(በአማን ነጸረ) #1

የቅ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ግእዝ መምህር ‹‹ግእዝ የእግዚአብሔር ቋንቋ ነው፤ ግን የእግዚአብሔር ቋንቋ ግእዝ ‹ብቻ› አይደለም፤›› ብለው የቋንቋዎችን እኩልነት አጽንተውልን ነበር፡፡ ብቻ ልቤ እሺ አይለኝም፡፡ ካልዋሸሁ በቀር ‹‹አባታችን ሆይ…›› ስልና ‹‹አቡነ ዘበሰማያት …›› ስል እኩል ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ አሁን ድረስ ግእዝ የቤተ እግዚአብሔር የብቻ ቋንቋ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡ የግእዝ ጽሁፍ ሳይ መንፈሴ ከዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት ትለወጣለች፡፡ ግና ይሄ ስሜት ከነባራዊ የታሪክ ሀቅ አብዝቶ ቢገናኝም ሁልጊዜ ይገጥማል ማለት እንዳልሆነ አንዳንድ ገጠመኞች ይሞግታሉ፡፡ ገጠመኞቹ ‹‹ግእዝ ቋንቋ ነው፤›› ማለትን እንዳንዘነጋ ያስታውሱናል፡፡ ግእዝ ቋንቋ ነው፤ ፍልስፍና፣ ኵሸት፣ ታሪክ፣ ቅኔ፣ ውዳሴ፣ ነቀፋ፣…ተጽፎበታል - ዘፈንና ሽለላ ሳይቀር፡፡

##1. ወደ ግእዝ የተመለሱ ትርጓሜ ዘፈኖች
በአፄ ልብነ ድንግል ዘመን ነው፡፡ ከሽምብራ ቆሬ ጦርነት አስቀድሞ ቀጭን አቦክር የተባለው የአዳል ዘማች የአፄ ልብነ ድንግል ሠራዊትን ድል ነሳ፡፡ ለክብሩም ቆነጃጅት ዘፈኑለት፡፡ ዘፈኑን የግእዝ ታሪክ ጸሀፊው ሰማ፡፡ ተርጉሞ እንደሚከተለው አስቀመጠው፡፡

ወልድ፡ መዋኢ፡ ተንሥአ፡ ቃውመ፡ ለሕዝቡ፣
ወልድ፡ ኃያል፡ ሰለበ፡ ምህርካ-ኃያላን፡ ዘፄወውዋ፡ ለሀገሩ፣
ወልድ፡ መስተቃትል፡ ፈደየ፡ ምክዕቢተ፡ እምቀታልያነ-ሕዝቡ፡፡

…ተዛማጅ ትርጉም…

አሸናፊው ወጣት፥ ቆመ ተሰለፈ
ያገሩን ማራኪ፥ ምርኮ አጨናገፈ፣
የወገኑን ገዳይ፥ ደጋግሞ ሰየፈ፡፡

ከአፋን ኦሮሞ ወደ ግእዝ የተመለሰው ውዳሴ-ኢያሱ ሌላኛው ዋቢያችን ነው፡፡ ዘፋኞቹ ጠለታ፣ ሆሮ እና ጅማ የተባሉ የኦሮሞ ጎሳዎች ናቸው፡፡ እነሱ፡- ‹‹መጽኡ፡ ጠለታ፡ ሆሮ፡ ወጅማ፡ እንዘ፡ ይዘፍኑ፡ ወይቤልዎ፡ ለንጉሥ፡-

እግዚኦ፡ ሰማዕነ፡ ድምጸከ፡ ወፈራህነ፣
ርኢነ፡ ግብረከ፡ ወአንከርነ፣
ይእዜኒ፡ መጻእነ፡ ከመ፡ ንስግድ፡ ለከ፣
ባሕቱ፡ ቦአ፡ ኵናተ፡ ኑፋቄ፡ ውስተ፡ ልብነ፡ በጐነድዮትከ፡፡

…ተዛማጅ ትርጉም…

ድምጽህን ሰማን፥ ፈራን፣
ሥራህን አየን፥ አደነቅን፣
እጅ ልንነሳህ፥ መጣን፣
ግና …፥ ብትዘገይ ጊዜ፣
በልባችን ገባ፥ የስጋት አባዜ፡፡

እያሉ ቀደም ሲል ከአባቱ በኮበለለበት ወራት ያስጠጉትን ኢያሱ በአረጋዊው ስምዖን ብሒል ያወድሱታል፡፡ እሱም ውለታውን አልረሳም፡፡ ‹‹ኢትበርብሩ፡ ቤተ፡ ጅማ፡ እስመ፡ ገብየር፡ ውእቱ - የባለሟሌን የጅማን ቤት (ሀገረ ጅማ) አትዝረፉ›› ሲል ከሠራዊቱ ብርበራ ታድጓቸዋል፡፡

##2. የግእዝ ፉከራዎች
ፉከራ የኖረ ባህላችን ነው፡፡ ‹‹የእገሌ ልጅ!›› ብሎ በአባት መፎከር ትውፊታችን ነው፡፡ በአፄ ሚናስ (አድማስ ሰገድ) ታሪክ ‹‹ተንሥአ፡ ንጉስ፡ እምስካቡ፡ እንዘ፡ ይጥህር፡ ከመ፡ አንበሳ፡ ወያዘምር፡ በስመ፡ አቡሁ - ንጉሥ (ሚናስ) ከመኝታው እንደ አንበሳ ተነሣ፤ በአባቱ ስም ፎከረ፤›› የሚል ገጸ ንባብ አለ፡፡ በአጼ ሠርፀ ድንግል (መለክ ሰገድ) ታሪክ ደግሞ ተከታዩ ፉከራ ቀርቧል፡፡ ፎካሪው በስሙ ነው የሚፎክር፡፡ ፎካሪው ከንጉሡ ጋር የነበረው አለመግባባት በዕርቅ ሲቋጭ - ወእምዝ፡ አዝመረ፡ ወይቤ - ከዚያ እንዲህ እያለ ፎከረ፡-

አነ፡ ሐመልማል፡ ወልደ፡ ሮማነ፡ ወርቅ፡ አንገሥኩ፡ እግዚእየ፣
መለክ፡ ሰገድ፡ ወልደ፡ አጋእዝትየ፣
ወናግ፡ ሰገድ፣ አጽናፍ፡ ሰገድ፣ ወአድማስ፡ ሰገድ፣
እምቅድመ፡ ዝኒ፡ ዘአበስኩ፡ ኃደጉ፡ ሊተ፡ አበሳየ፣
ስሕተተ፡ ዛቲሰ፡ ዕለት፡ አኮ፡ በምክርየ፣
አላ፡ እመከራ፡ ሰይጣን፡ ኮነ፡ በእደ፡ ወዓልያንየ፣
እምድኅረ፡ ዝንቱሰ፡ እመኒ፡ ሐየውኩ፡ ምስለ፡ እግዚእየ፣
ወእመኒ፡ ሞትኩ፡ ምስለ፡ እግዚእየ፡፡

…ተዛማጅ ትርጉም…

እኔ ሐመልማል፥ የሮማን ወርቅ ትውልድ፣
ጌታዬን አነገሥኩ፥ ጌታ መለክ ሰገድ፣
ስህተቴን ፍቆልኝ፥ ቀዳሚ በደሌን፣
አስቤ አብሰልስዬ፥ ያላደረግሁትን፣
በክፉ መካሪ፣ ሰይጣን ያሳተኝን፣
ከእንግዲህስ ወዲያ፥ ብሞትም ብኖርም፣
ከጌታዬ ጋራ፥ ያድርገኝ ዘላለም፡፡

የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች በመጠነኛ ለውጥ በየጊዜው ይባላሉ፡፡ በብዙዎቹ ነገሥታት ዜና መዋዕሎች ባለሟሎች ታማኝነታቸውን ሲገልጹ፡-

ሞትኒ፡ ወሕይወትኒ፣
እከሌ፡ ምስሌከ፡ ይክፍለኒ፡፡

ይላሉ፡፡ ይህቺ ስንኚ ወደ አማርኛ ሳትገለበጥ አትቀርም፡፡ በአማርኛም፡-

አከልዬ እከሊት ፥ እንሁን አብረን አብረን፣
ሞት እንኳ ቢመጣ ፥ አብረን ተነባብረን፡፡

የምትለዋ የልጃገረዶች የጫካ እንጉርጉሮ ከግእዙ ስንኝ ስምም ናት፡፡ ከጫካው ሳንወጣ በአጼ ኢያሱ ላይ የተነሳውን ስመ ሞክሼ ሽፍታ (ኢያሱ) ፉከራ እንስማ፡፡ ሽፍታው ኢያሱ ከንጉሡ ኢያሱ ተገዳድሮ፡-

አንተሂ፡ ኢያሱ፡ ወአነሂ፡ ኢያሱ፣
ንትራከብ፡ ለወግረ፡ ድባ፡ መልእልተ፡ ርእሱ፡፡

…ትርጉም…

አንተም ኢያሱ፥ እኔም ኢያሱ፣
በድባ ኮረብታ፥ ላግኝህ በራሱ፡፡

ብሎ ነበር፡፡ አልሆነለትም፡፡ አፍና ተግባር አልገጠመም፡፡ ተሸነፈ፡፡ አልጀገነም፡፡

##3. የጀግና ሙገሳ
ብላቴን ጌታ ወልደ ልዑል የሚባል የዳግማይ ኢያሱ (ቋረኛ) ኃይለኛ ጦረኛ ነበር፡፡ ‹‹ኢተአምረኒኑ - አታውቀኝም እንዴ›› ማለት የሚቀናው መገርም፣ ጀግና፡፡ እሱን ሰውየ የንጉሡ ታሪክ ጸሀፊ እንዲህ ያሞግሰዋል፡-

ይነድድ፡ ልቡ፡ ከመ፡ እሳት፣
ወጽኑዕ፡ ከመ፡ ቀስተ፡ ብርት፣
ወይውኅጦ፡ ለአረር፡ ከመ፡ ፍትፍት፣
ወከመ፡ ወይን፡ ይሰትዮ፡ ለበሊሃ፡ ኵናት፣
ወይሬእዮ፡ ለኵሉ፡ መከራ፡ ከመ፡ ወኢምንት፣
አምጣነ፡ አልቦ፡ ውስተ፡ ልቡናሁ፡ ፍርሃት፣
በእንተ፡ ፍቅረ፡ ወልዱ፡ ኢያሱ፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡፡

…ትርጉም…

ልቡ እንደ ነዲድ፥ የሚቀጣጠል፣
እንደ ፍላጻ፥ የሚወረወር፣
ልክ እንደ ፍትፍት፥ የሚውጥ አረር፣
እንደ ጥሩ ወይን፥ ጦር የሚጨልጥ፣
ለጽኑዕ ችግር፥ እጁን የማይሰጥ፣
በልቡ መዝገብ፥ ፍርሃት ያልጻፈ፣
በኢያሱ ፍቅር፥ የተነደፈ…፡፡

እና ምን ለማለት ነው? ግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ የተለያየ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች ተጽፈውበታል፡፡ የአብዛኞቹም መገኛ (ጠባቂ) የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ናት፡፡ ያ ማለት ግን ለእነዚህ ሁሉ ጽሁፎች ይዘት የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ኃላፊነት ትወስዳለች ማለት አይደለም፡፡