መልክእ ዘምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

atseminilik
orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

1.መድፍን

ያለፉ ቅዱሳን በቅድስና ሲጠሩ ከሚደረጉላቸው ነገሮች አንዱ መልክእ መድረስ ነው፡፡ የቀረው በስማቸው ታቦት ቀርጾ፣ መታሰቢያ ቀን ደንግጎ፣ ሥዕል ሥሎ፣ ቤ/ክ በስማቸው አንጾ፣ ‹‹አምላከ ቅዱስ/ቅድስት እከሌ/እከሊት›› እያሉ መማፀን ነው፡፡ ይህ በቅድስና መዓርግ ላሉ የሚደረግ ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን ኑረው ላለፉ ደግሞ መታሰቢያ ይደረጋል፡፡ መታሰቢያው በይዘቱ ነፍስ ይማር ነው፡፡

በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀው ያለፉ ነገሥታት ባሳነፁት ቤ/ክ እንዲያ ዓይነት (ነፍስ ይማር) መታሰቢያ ይደረግላቸዋል፡፡ በቤ/ክ ውስጥ ፎቶአቸው ለመታሰቢያ ይቀመጣል፡፡ ፎቶ ባልነበረበት ጊዜ ‹‹ዘከመ፡ ተማኅፀነ፡ እከሌ/ እከሊት›› እየተባለ በሥዕላት ስር በጎ አድራጊዎች ከዋናው ሥዕል አነስ ተደርገው ይሣላሉ፡፡ ዑራ ኪዳነ ምሕረት (ደሴተ ጣና ውስጥ) ብትሔድ እንዲያ ያለ ሥዕል ሞልቷል፡፡ በደቀቂ እስጢፋኖሱ አባ መዝገበ ሥላሴ ገድል ውስጥም በጎ አድራጊዎች ተሥለው ታገኛለህ፡፡ በጎንደር ቁስቋም የእቴጌ ምንትዋብና ኢያሱ ብርሃን ሰገድ ሥዕሎች እያንዳንዳቸው ከእመቤታችንና ከጌታ ሥዕል ግርጌ ‹‹ዘከመ፡ ተማኅፀነ/ት፡ ኃጥዕ፡ ወአባሲ›› እየተባለ መሣሉን ዜና መዋዕላቸው ይናገራል፡፡ የእነዚህ ሥዕሎች ዓላማ ለአስሣዮች ሥርየት ኃጢአት ማስገኛ፣ ለተወላጆቻቸው መጽናኛ፣ ለሌላው በጎ አድራጊ መናሳሻ እንዲሆን ብቻ ነው፡፡ እና … የአራት ኪሎዋ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሔደህ የአፄ ምኒልክን፣ መርካቶ ራጉኤል የአፄ ኃይለ ሥላሴን፣ ሞጣ ጊዮርጊስ ሔህ የልዕልት ወለተ እስራኤልን፣ ደብረ ብርሃን ሔደህ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብን ፎቶ ቤ/ክ ውስጥ ብታይ እንዲህ ተርጉመው፡፡ mere memorial! አሠሪውን ለማዘከር!! አንዳንድ መልክእም እንደዚያው ነው፡፡

መልክአ ኢትዮጵያ፣ መልክአ አፄ ዮሐንስ (ልጅ #Prestor John እንደ ጠቆመኝ)፣ መልክአ ምኒልክ፣ መልክአ ኃይለ ሥላሴ አለ፡፡ መልኮቹ የሚደረሱት ነገሥታቱ በቁም ሳሉ ከሆነ አትጠራጠር፡፡ ለውዳሴ ያህል ነው! ነገሥታቱን በቅድስና ለመጥራት አይደለም! እህ! ጎጃም ብትሔድ በየተክሊሉ ለጓዶቻቸው መልክእ ደርሰው የሚያበረክቱ ደባትር አታጣም፡፡ ጓደኛዬ ለሠርጉ እንዲያ ተደርጎለታል፡፡ የጅጅጋውን ሚካኤል ለረጅም ዓመት አሳምሮ የመራው ሊቀ ካህናት አባይነህን አንድ ደብተራ መልክእ ደርሶ ሲሰጠው ምስክር ነበርኩ፡፡

እግዚኦ! ይሄን ሁሉ የምወሸክተው በመምህር ወልደ ሥላሴ ጎጃሜ የተደረሰችው መልክአ ሚኒልክ እንዳትነቀፍብኝ ለማድፈንፈን እኮ ነው! መልኳ በቁጥር 44 ናት፡፡ ቀድማ (ከዜና መዋዕሉ ጋር እነድትነበብ) ብትደረስም የታተመችው እ.ኤ.አ.በ1915 ዓ.ም. ሊዝበን (ፖርቱጋል) ውስጥ ነው፡፡ የይዘቷ ማጠንጠኛ አድዋ ነው፡፡ በቀሪዎቹ ይዘቶቿ የንጉሡ ትሩፋትና ምግባራት ማጣፋጫ እየሆኑ አድዋን ያጅባሉ፡፡ ጥቂት ዘለላዎች ከመልክኣቱ (ቁጥሩ በስንተኛ ተራ ቁጥር ላይ እንደሚገኙ ለመግለጽ ነው!)፡-

2.መልክኣት

2.1. ለዝክረ ስምከ

ሰላም፡ ለዝክረ፡ ስምከ፤ መልዕልተ፡ ኵሉ፡ ዘኮነ፡፡
ወበግርማሁ፡ ግሩም፤ እንተ፡ አጥፍዓ፡ ኢጣሊያነ፡፡
ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ምኒልክ፤ ዘኢትዮጵያ፡ መድኅነ፡፡
ቀተልኮ፡ ለአላዊ፤ በምድረ፡ ትግሬ፡ መካነ፡፡
ምስለ፡ ባሺ፡ ብዙቅሂ፡ ዘርዘርኮ፤ ወረሰይኮ፡ በድነ፡፡

2.1.1. ለአፉከ

ሰላም፡ ለአፉከ፤ ለፈጣሪ፡ ዘየአኵቶ፡፡
ኢይትናገር፡ ስላቀ፤ ወኢይነብብ፡ ከንቶ፡፡
ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ምኒልክ፤ ለኢትዮጵያ ማኅቶቶ፡፡
ሐልቀ፡ ማንጆር፤ ወስዕነ፡ ፍኖቶ፡፡
ጀነራል፡ ባራቴሪ፡ ሶበ፡ ገብአ፤ ደንገፀ፡ ዑምበርቶ፡፡

2.1.2. ለአዕዳዊከ

ሰላም፡ ለአዕዳዊከ፤ እንተ፡ አኃዛ፡ ሰይፈ፡፡
ከመ፡ ይምትራ፡ ለባሺ፡ ብዙቅ፤ እምነ፡ ፉዚግራ፡ ዘተርፈ፡፡
ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ምኒልክ፤ እንተ፡ ትኰንን፡ አዕላፈ፡፡
አፍቀረከ፡ አምላክ፤ ወጸሎተከ፡ ተወክፈ፡፡
ተፈጸሙ፡ ጸላእትከ፤ ፩ዱ፡ ኢተርፈ፡፡

3.ማዘከሪያ

ታኅሣሥ 3 ሙት ዓመታቸው ይታሰባል፡፡ መታሲያ ቤት አላቸው፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ጎን ልጃቸው ንግሥተ ንግሥታት ዘውዲቱ በእመቤታችን (በዓታ) ሥም ባሰሩት ቤ/ክ ስር መቃብራቸው አለ፡፡ በስማቸው የአብነት ት/ቤት፣ የአረጋውያን መጦሪያና የዕጓላ ማውታ ማሳደጊያ ተቋም አለ፡፡ ምናልባትም ይህ ተቋም ባገራችን የመጀመሪው ተቋማዊ በጎ አድራጎት ተቋም ነው፡፡ የእነ መቄዶንያ ቅድመ አያት መሆኑ ነው! ተቋሙ አሁንም አለ፡፡ ለመቶ ዓመት ጥቂት ፈሪ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲኗማ መሠረቷ የተጣለበትን መቶ ዓመት ለማክበር ዋዜማ ቆማለች! በአደባባይ ‹‹እግዚኦ፡ አዕርፍ፡ ነፍሰ፡ ንጉሥነ፡ ምኒልክ›› ለማለት!

4.ትካዜና ልመና

ያሳዝናል! ይህ ተቋምም ሆነ አብነት ት/ቤቱ መድረስ ባለባቸው ቦታ ላይ ከመድረስ ይልቅ ቁልቁል ሲሰርግ፣ ስለአብነት ት/ቤቶች አለመጠናከር በሚነገርባት አምስት ኪሎ፣ ያውም ከቅንድቧ ስር ዐይን የሆነ ተቋም ሲደበዝዝ፣ ሲቦዝ፣ ሕንጻው በአጽሙ ሲቆም … ስታይ አፍአዊነታችንን ትታዘባለህ፤ ወይም ከትናንት ለመታረቅ ያለነን አሻፈረኝ ባይነት ለማሰብ ዕድል ታገኛለህ፡፡ ከትግራዩ አቡነ ዮሐንስ (የአባ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ መስራች - ምናልባትም የበዓታው አደረጃጀት ለእሳቸውም መነሳሻ ሳይሆን አይቀርም) እስከ ጎጃሙ አቡነ ጴጥሮስ (ሊቀ ሊቃውንት ትርፌ)፣ ከጎንደሩ አቡነ ድሜጥሮስ እስከ ሸዋዎቹ አቡነ ማቴዎስ፣ ኦሮሞዎቹ እነ አቡነ ያሬድ፣ ከወሎ እነ አቡነ እንድርያስና አቡነ ማትያስ ዘካናዳ፣ … ኧረ ስንቱ አያ! የወጡበትና የኖሩበት ጉባኤ ከመንበረ ፓትርያርኩ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ሆኖ ሲያቃትት ስታይ የሚሰማህን የትካዜ ስሜት ለመቋቋም ቦታውን አለማወቅ ይጠይቃል፡፡

እናም … ያለን በምንችለው ብንረዳ፤ የሌለንም እቦታው ደርሰን በዓታን አንግሠን ችግሩን ብንረዳ … ልመናዬ ነው! የአንድ ክፍለ ዘመን ሕንፃና ተቋም በየቀኑ ዓይንህ ስር እየሞቱ ሲሔዱ ማየት በጣም ያሳዝናልና ከቀብሩ በፊት ለሕመሙ ብንደርስ…አሁም ልመናዬ ነው!