«መሬት ላራሹ»፤ ሁለቱ «ህገ መንግስቶች» እና የኢትዮጵያ ገበሬዎች መብት


(Achamyeleh Tamiru) #1

አቻምየለህ ታምሩ

የየካቲት ስድሳ ስድስቱን «አብዮት» ካፈነዱት ችግሮች መካከል ዋነኛው የወቅቱ ተማሪዎች ከጣራው በላይ በመፈክርነት ያጮሁት የነበረው «መሬት ላራሹ» የሚለው የገበሬው መብት ነበር። «የአብዮቱ» ዋና አላማም አርሷደሩን የመሬት ባለቤት ማድረግ ነበር። በርግጥ «ከአብዮቱ» በኋላ በገቢር ሳይሆን በስም ጭሰኛ የሚባል የህብረተሰብ ክፍል ጠፍቷል። ይህ ማለት ግን የየካቲት ስድሳ ስድስት «አብዮት» መሬትን ላራሹ አደረጋት ማለት አይደለም።

የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የመጀመሪያው ህገ መንግስት ለገበሬው የሰጠውን መብት ከዚያ በኋላ የመጡት ወያኔና ደርግ የደረቷቸው «ህገ መንግስቶች» አልሰጡትም። ምናልባትም መሬት ላራሹ ሲባል የሰማ ሁሉ በዚህ ግራ ሊጋባ ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ነገሩ እውነት ነው። «ያ» ትውልድ በዘመኑ ያጠፋቸውን ብዙ ነገሮች በእውቀትና በእውነት እንዳንመረምር ከራሱ ጋር እስከዛሬ ሳይታረቅ እንዳለ በመኖሩ የዛሬዎችን ትውልዶች ጭምሮ ጥሞና እየነሳ በጨለማ ውስጥ እያዳከረን ይገኛል። የሆነው ሆኖ የ«ያ» ትውልድ «የመሬት ላራሹ» አብዮት ዛሬ ላይ የገበሬው መብት ቀነሰ እንጂ አልጨመረውም። ይህንን ሀቅ ለማሳየት የወያኔ ስርዓትና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት የጻፏቸውን ህገ መንግስቶችና በሁለቱም ህገ መንግስቶች ውስጥ ለገበሬው የተሰጠውን መብት በሚመለከት የተጻፉ አንቀጾችን ማወዳደር በቂ ነው።

የወያኔ «ሕገ መንግስት» የንብረት መብትን በሚደነግገው አንቀጽ 40 ቁጥር ሶስት ላይ «የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው።» ይላል። በዚሁ አንቀጽ በተራ ቁጥር ስምንት ላይ ደግሞ «የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መንግስት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረቱን ለመውሰድ ይችላል» ይለናል።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያው ህገ መንግስት ደግሞ መሬት የገበሬው የግል ንብረት እንደሆነ ይደነግግና በአንቀጽ ሰባ ስድስት ላይ « መንግስት ለህዝብ ጥቅም የሚሆን እንደ ምሽግ፣ እንደ መንገድ፣ እንደ ገበያ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ ተማሪ ቤት፣ እንደ ሆስፒታልና እንደ ከተማ፤ ይህንንም የመሰለ ሥራ ሁሉ በሌላ ሰው [በገበሬ] ርስት ላይ ለመስራት የፈለገ እንደሆነ፤ የሚያስፈልግ መሆኑ ለምክር ቤቱ ከቀረበ በኋላ፤ በህግ እንደተወሰነ ለባለርስቱ[ ለገበሬው] የሚገባው ዋጋ ተሰጥቶ ባለስርቱም [ገበሬውም] ቢፈቅድ ሌላ መሰሉን ለውጥ እንዲቀበል ተደርጎ እንዲለቅ ይደረጋል እንጂ ፤ ይህንን ለመሰለ ለህዝብ ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ለትራፊ ጥቅም ተብሎ የሌላ ሰው [የገበሬ] መሬት እንዳይወሰድበት በህግ ተወስኗል።» ይለናል።

ከዚህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያው ህገ መንግስት መረዳት የምንችለው ለህዝብ ጥቅም[ Public use] ካልሆነ በስተቀር ገበሬው ለንግድ ስራ፣ ለግለሰብ ባለሀብትና ለማንኛውም ትርፍ ነክ የኢኮኖሚ ተግባሮች ሲባል ከመሬቱ በምንም መልኩ አይፈናቀልም። በወያኔ ህገ መንግስት ግን ገበሬ ለንግድ ስራ፣ ለግለሰብ ባለሀብትና ለማንኛውም ትርፍ ነክ የኢኮኖሚ ተግባሮች ሲባል በማንኛውም ጊዜ ከመሬቱ እንዲፈናቀል ያደርጋል። በወያኔ ህገ መንግስት በንጉሱ ዘመን የገበሬው የግል ንብረት የነበረው መሬት የመንግስት ሀብት ሆኗል። በተጨማሪም የወያኔ ህገ መንግስት በንጉሱ ዘመን ገበሬው የነበረውን መሬት የመግዛትና የመሸጥ መብት ቀንሶታል።

እንግዲህ! ከዚህ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በመሬት ላራሹ የገበሬው መብት ቢያንስ በሶስት ነገር ቀነሰ እንጂ ፈጽሞ አልጨመረም። በመጀመሪያ በመሬት ላራሹ ገበሬው ለህዝብ ጥቅም ለሚውሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለንግድ ስራ፣ ለግለሰብ ባለሀብትና ለማንኛውም ትርፍ ነክ የኢኮኖሚ ተግባሮች ሲባል በማንኛውም ጊዜ ከመሬቱ ይፈናቀላል። ከመሬት ላራሹ በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ግን ገበሬ ለህዝብ ጥቅም ለሚውሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ብቻ እንጂ ለንግድ ስራ፣ ለግለሰብ ባለሀብትና ለማንኛውም ትርፍ ነክ የኢኮኖሚ ተግባሮች ሲባል በማንኛውም ጊዜ ከመሬቱ እንዳይፈናቀል መብቱ በህገ መንግስት ተረጋግጧል።

ሁለተኛ በመሬት ላራሹ መሬት የገበሬው የግል ሀብት አይደለም። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ግን መሬት የገበሬው የግል ሀብት ነበር። ሶስተኛ በመሬት ላራሹ መሬት ገበሬው መሬት የመግዛትም ሆነ የመሸጥ መብት የለውም። ከመሬት ላራሹ በፊት በንጉሰ ነገስቱ ዘመነ መንግስት ገበሬው መሬት የመግዛትም ሆነ የመሸጥ ያልተገደበ መብት ነበረው። የገበሬውን መብት መጨመር የነበረበት መሬት ላራሹ፤ በወያኔ ዘመነ መንግስት ከመሬት ላራሹ በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው የገበሬ መብት ቢያንስ ሶስቱን ቀንሷል።

መሬት ላራሹ የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬት የግል ባለቤትነት፤ የመግዛትና የመሸጥ ያልተሸራረፈ መብትና ከመሬቱ ለህዝብ ጥቅም ለሚውሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ካልሆነ በስተቀር ለአንዳችም የንግድ ስራ፣ ለግለሰብ ባለሀብትና ለማንኛውም ትርፍ ነክ የኢኮኖሚ ተግባሮች ሲባል በማንኛውም ሁናቴ ከመሬቱ ያለመፈናቀልበት የሙሉ መብት ጠርዝ፤ የግል መሬት ባለቤትነት መብቱ ወደተዳፈነበት፣ መሬት የመግዛትና የመሸጥ ኢኮኖሚያዊ መብቱ ወደታገደበትና ለህዝብ ጥቅም ለሚውሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለንግድ ስራ፣ ለግለሰብ ባለሀብትና ለማንኛውም ትርፍ ነክ የኢኮኖሚ ተግባሮችም ጭምር በማንኛውም ጊዜ ከመሬቱ ወደሚፈላቀልበት የዜሮ መብት ባለቤትነት ደረጃ አወረደው። ስለዚህ መሬት ላራሹ የኢትዮጵያን ገበሬ መብት ቢያንስ ስለሶስት ነገር ቀነሰው እንጂ አልጨመረውም። «ያ» ትውልድ ግን ዛሬም በመሬት ላራሹ የገበሬው መብት ጨምሯል እያለ በባዶው ያደነቁረናል። የ «ያ» ትውልድ የመሬት ላራሹ አብዮት መሬትን ከገበሬው ነጥቆ መሬትን ለካድሬ አደረገ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት መሬት ገበሬው ነበር፤ ዛሬ በዘመነ ወያኔ መሬት ለካድሬ ሆናለች። የ «ያ» ትውልድ የመሬት ላራሹ አብዮት መሬትን የመንግስት ሀብት ስላደረገ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ድሀ ለሀብታም ሲባል የሚፈናቀልባት አገር ሆናለች። ባጠመቃላይ በመሬት ላራሹ የኢትዮጵያ ገበሬ የነበረው መብት ተቀምቷል። እውነታው ይህ ነው። ዶሴው ወጥቶ ሲታይ የሚያሳየን ሀቅ ይህን ነው!

ወረድ ብዬ የወያኔን አገዛዝና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት መንግስትን ህገ መንግስቶች የመሬት አንቀጽ ድንጋጌዎች ለዋቢነት አያይዣለሁ!