ዘፈን ፥ ትውዝፍት ፥ ማኅሌት

ethiopia
music

(በአማን ነጸረ) #1

ቃላት መልእክትን የመሸከም አቅማቸው ከሚደክማባቸው ጉዳዮች አንዱ ይመስለኛል፡፡ ግእዛችን ዘፈኑንም ፥ ማሕሌቱንም ፥ ትውዝፍቱንም ጀምሎ “ዘፈን/ ማሕሌት” የሚልበት ቦታ ብዙ ነው፡፡ በዘፀዐት ፥ መቃብያን ፥ ቀሌምንጦስ እንዲያ ያሉ ቃላት አሉ፡፡ ቃሉ አንድ ነው ፤ ሆኖም እንደ ጉዳዩ (contexቱ) ለ3 ቡድን ሊጫወት ይችላል፡፡ ይጫወት…

##1.ዘፈን እንደ ዘፈን
አቋሜ ይቅደም! ዘፈን ከማኅበረሰብ ቁልፍ የማንነት መገለጫዎች አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የወፍጮ ላይ የእናቶቻችን እንጉርጉሮዎች ፥ የእረኞች “አሎ ሉሎ” ፥ የሠርግ ቤት “ወሸባዬ” (የመርጡለ ማርያም ዘመዶቼ “ወሰባዬ” ይሉታል)፡፡ አታንሻፍ! ትርጉሙ ሠርጌ ማለት ነው ፤ ግእዙ ለአውሰበ የሚሰጠው ትርጓሜ አገባ ነው ፤ ወሰባዬ = ጋብቻዬ = ወሸባዬ!

ኧኸኸ ወሰባዬ፥
የ…ልጅ ዘመናዬ ፥
ኧኸኸ ወሰባዬ ፥…) ፥

የድል ፥ የአርበኝነት ፥ የእናቶች “እዩት ሎሌው ሲያገሳ” የታቦት ማጀቢያ ፥ የኛዋ ደማቅ ማኅሌተ ገንቦ ፥የብሶት ፥ የሙገሳ ፥ የቅሬታ እንጉርጉሮዎች ባይኖሩ በትውፊት ገባሪነት እየተገማሸረ በግርማ የሚወርደው ማኅበረሰባዊ ሥነ ቃላችን ውሃ በላው! ጌትዬ oral history በገነነበት አገርና አህጉር እየኖርክ ዘፈንን በጅምላ ማነወር cultural suicide መፈጸም ይመስለኛል (ካንተ ባላውቅም!)፡፡

ክርስትናችን በጅማሬዋ ወቅት እንዲህ ያለ ክርክር ነበረባት ይባላል፡፡ ለዚህ ዋና መነሻው የእነ ቅዱስ ጳውሎስ ተደራስያን ምዕመናን የጀርባ ታሪክ አሕዛባዊ መሆንና በዘፈኖቻቸው መካከል “እያንጓለለ…!” አይነት መምለክያነ ጣዕት ዜማዎች ከባህሉ መቀያየጥ ነው፡፡ እኒያ ቅይጦች “ኩን ከማሆሙ!” በሚል መርህ ለአሕዛብ እንደ አሕዛብ ፥ ለዕብራውያን እንደ ዕብራዊ እየሆነ ማንነትን አክብሮ ለሚሰብከው ጳውሎስ እንኳ የሚቻሉ አልነበሩምና ያበጥራቸዋል፡፡ ተጠንቅቆ ያበጥራቸዋል - ትውዝፍትን ከዘፈን እየለየ! ማንነት እንዳይዋዋጥ ነዋ! የኛ አበው በተናግሮም ባይሆን በአርምሞ (ባህላዊ ጨዋታዎችን ባለማውገዝ) ለትውፊቱ መቀጠል የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡

ደርግ እነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በግፍ ሲሰዋ አብሮ የቀሰፈው ጎልማሳው የመካነ ኢየሱስ መሪ ቄስ ጉዲና ቱምሳም “holistic theology” የምትል ባህልን ጀምላ የማትደፈጥጥ ተቋም ለመኮትኮት ይተጋ ነበር፡፡ በቅርቡ ያነበብኩት የሰዮ (የቄለም/ምዕራብ ወለጋ ) ላይ በአንድ የእምነቱ ተከታይ የተሠራ ጥናት የቄስ ጉዲና ቱምሳ መርህ በ"እግዚአብሔር ሰዎች"ና በ"ነቢያት" መዳፈኑን እያነሳሳ “ኧረ በጉዲና!” ይላል፡፡ ጥናቱን በድሉ አሰፋ አያና የተባለ የመካነ ኢየሱስ አማኝ ነው ያጠናው፡፡ በጎግል አስሱትማ!

##2.ትውዝፍት
ጥቅሲቱ ገላ.5 ፥ 20-21 ላይ ናት፡፡ ኃጢአት ስትዘረዝር ግእዙ “ትውዝፍት” እንግሊዝኛው “ravelling” ያለውን “ዘፋኝነት” ብላ ጀመለችው፡፡ ከዚያ ሁዋላማ ምን ቅጡ! ወዲህ ወፈ-ገዝቶች ፥ ወዲያ “የእግዚአብሔር ሰዎች” ፊደሉን አውለበለቡት! አዲስ እረኞች እንቅልፍ ነሡን! የሙዚቃ ባህል የሌለው አገር ዓለም ላይ ያለ ይመስል ወዲህ ያለው ከራሱ ይጣላል ፤ የ"እግዚአብሔር ሰዎች"ም ዘፈን በጅምላ “መንፈስ” ነው ብለው በጅምላ ያነፍሱታል፡፡ ይመቻቸው!

ይቅርታ ጌትዬ! አታስዋሸኝ! ዘፈን ኃጢአት ነው ብዬ አላምንም!

እየውማ! የተወገዘው ድርጊት “ትውዝፍት” ነው በግእዝ፡፡ ትርጓሜው “የምንዝር ጌጥ” - ልቅና መረን የወጣ ተፈታታኝ ሩካቤ-ተኮር ተግባርን ይገልጻል፡፡ ካስፈለገ የ2000ዓ.ም የኢኦተቤክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተመልከት ፡፡ ተቃንቷል ፤ ተተክቷል ፤ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ማለት በፈለገው ተብሏል ! ትውዝፍት=የምንዝር ጌጥ!

ተጨማሪ ኦርቶዶክሳዊ ማጣቀሻ የፈለገ አሁንም ይመልከት ፤ “ባህልና ክርስቲያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ” የተሰኘ መ/ር ካሕሳይ ጽፈውት ማኅበረ ቅዱሳን አሳትሞ በ90 ብር የሚሸጠው ምርጥ መጽሐፍ አለ! ዘፈንን በበጎና በጸያፍ (ትውዝፍት) ከፍሎ ይተነትነዋል፡፡ ደቂቀ ቃየል የወደቁበትን ዝሙት ጠቀስ ስድ ዘፈን (ትውዝፍት) ከባህላዊው እሴት አጎልባች እየለየ መንገድ ይጠቁማል፡፡

ደሴት ላይ የተሰሩ አብያተክርስቲያናትንና ጸበሎችን የጎበኘና የተጠመቀ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በትውዝፍት ተግባር የነበሩ ሰዎች ፍጻሜ በውሃ መዋጥ መሆኑን ይሰማል፡፡ ትውዝፍት ለእምነታችንም ፥ ለባህላችንም ፥ ለኅሊናችንም የሚያስፀይፍ ነው፡፡ እሱን ከነወዛፊው ማውገዝ የተገባ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ዘፈንን ጀምሎ መላ አገሪቱን ቅኔ ማሕሌት ካላደረግሁዋት በሚል የተርእዮ ዘመቻ በሞተ የቅጂ መብት የሚንደፋደፉ ልጆች ላይ በትርጓሜና በውግዘት መጠበብ አይመስጠኝም፡፡

##3. ዘፈን እንደ ማኅሌት
በግእዙ ማኅሌትም ዘፈን ይባላል፡፡ በታሪክ የቅዱስ ያሬድን ዜማ የተቃወሙና የተቹ አሉ፡፡ በድጓ መቅደም ፥ በድርሳነ ዑራኤል ፥ በሱስንዮስ ዙሪያ በተጻፉ መጣጥፎችና በአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጀራ መጽሐፍ እንዲያ ያለ ነገር ተጽፏል፡፡ ቢሆንም የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከዘመነ በእደ ማርያም ጀምሮ በቤተክርስቲያን እንዳያዳግም ተደርጎ በድንጋጌ ስለፀና ትችቱና ተቃውሞው አገልግሎቱን አላቋረጠውም፡፡ በነባሩ ድርሰት ላይ ወረብና ዚቅ እየታከለበት ዘመናትን ተሻግሯል ፤ ገና ይሻገራል፡፡ እሱ ባለምልክት ነዋ! ለተለየው ፥ የተለዩት ፥ በተለየ ዜማ ፥ በተለየ ቦታ ፥ ለእሱ በተለየ ሰዓት ምስጋና ያቀርባሉ፡፡
አንተ እንዲያ ከሆንክ ሕይወቱን አክብረህ ኑረው ፤ አትቀላቀል ፤ ትውዝፍትን አውግዝ ፤ ዘፈንን ግን አደራ! አትጀምለው!

አንዴ ወደ ማኅሌት ፥ ሌላ ጊዜ ወደ ትውዝፍት ከተምታታብህ ጸልይ! ወደ በጎው እንድትጠቃለል ነዋ! እስከዚያው ግን እባክህን! እዚያና እዚህ ከምርገጥ ወደ እድሜዬ ማምሻ ልመለስ ብለህ አትጠፋ! እስኪያስችልህ በምትችለው ቅረብ! ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሚላት ነገር አለች ፤ ይዘቷን እማስታውሳት!

“ብትችል አርሰህና አረስርስህ ዝራ ፥ ጎተራህ ይሞላል ፤ ባትችልም ተስፋ አትቁረጭ ጫጭረህ ዝራ ፥ ጎተራህ ባይሞላም ለእሸት አታጣም፡፡”

እምለውማ ፦

  • የዐቢይ ጾም ብቻ ክርስቲያን ስላሉህ አትንሸራተት!

  • ባህላዊ ማንነትን የሚገልጹ ዜማዎችን ሁሉ ጨፍለቀው “በዘፈን ኃጢአት ነው” ደምሳሽ ኮሮጆ ከትተው ለሚያሰቅቁህ አትሰቀቅ! እንኳን አካባቢያዊ ማነንነትን ለመግለጽ በጋራ መድረክ የሚወጡ ዜማዎች የቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ድርሰትም የራሱን ፈተና አልፎ ነው በደመራ በኩል ዩኒስኮ የጋራ የመንፈስ ቅርስ የተባለው !

  • የዘፈንንና የማሕሌትን ዜማና ዜመኛ ከነማዜሚያ ድንበሩ አክብር ፤ ካብ አትናድ ፤ ካብን የሚንድ እባብ ይነክሰዋል (እንዲል መክብብ)፡፡

  • ከትውዝፍት ፈጽሞ ራቅ!

  • ልለምንህ ፦ የሚሰማኝን በማሰማቴ አታሸ’ማቀኝ! ካልዋሸሁ በቀር የሚሰማኝ እንደዚህ ነው!

  • በጉዳዩ በቅን ልቡና ሐሳብ ቢዋጣ ደስታ እምሞት ነኝ!