የዓርብ ጨዋታ፡- ጠበቅ ያሉ ሃይማኖታዊ ክርክሮች በቅኔያት

kinebet
orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

መስከረም 21 ቀን ብዙኃን ማርያም ናት - ብዙኃን ሊቃውንት በኒቅያ ለአውግዞተ አርዮስ የተሰባሰቡባት፡፡ እሷን መነሻ አድርገን ያገራችን ሊቃውንት በየብሂላቸው ያቀረቧቸውን ቅኔያት በጥቂቱ እንይ፡፡ ሃይማኖት ስስ ነው፡፡ ስለዚህ ከቅኔ ጋር ስምም ነው፡፡ ይወዳላ! ቅኔ ስስ ስሜት ይወዳል፡፡ ቀደም ሲል የነበሩ የሃይማኖት ክርክሮች ይካሄዱ የነበሩት ምሥጢረ ሥጋዌን (በጌታ ጽንሰት አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰው አምላክ የሆነበትን ክስተት) ማዕከል ባደረጉ መልኩ ነበር፡፡ በሱ ለመከራከር ደግሞ ሰው ተሠርቶ ያልቃል ባይባልም በሰው ሰውኛው ‹‹የተጨረሱ›› ሊቃውንት ያስፈልጋሉ፡፡ ኩሸቱንም፣ ምስጢሩንም የሚያውቁ፤ የንግግር መላውንም እንዲሁ! ቢቻል ደግሞ ዐይናሞች - 4 ዐይናዎች!

##1. ምስጢረ ቅብዐት በ4 ዐይና ጎሹ

አራት ዐይና ጎሹ ሞጣ/ ጎጃም ይኖሩ የነበሩ፣ መደባቸውን ብሉይ አድርገው ሁሉንም የመጻሕፍት ትርጓሜ የሚነግሩ በእውቀታቸው አራት ዐይና፣ በኑሯቸው ግን ዐይነ ስውር የነበሩ ሊቅ ናቸው፡፡ ‹‹አራት ዐይና…›› የሚለው የሊቃውንት ቅጽል ሲሰማ ወደ ብዙ ሰው አእምሮ ሳይመጡ አይቀሩም፡፡ እሳቸው በእምነት በኩል የቅብዐት ብሒል አራማጅ ነበሩ፡፡ ተከታይዋ ቅኔ ለዚሁ አቋማቸው ማስረገጫ የተደረገች ዝነኛ ሥላሴ ናት፡፡ እንያት፡-

ሥላሴ!

ኢያጥፍዐ፡ ንዴተ ሥጋ፤
ተዋሕዶተ ቃል፡ ምስለ ሥጋነ፤
እመ ሐተትነ፡ በልብ፤ ይእዜ፤ እንበለ ማሕየዊ፡ ቅብዐት፣
ወኢይኩን፤ በዐውደ ሮምያ፤ በይነ ዝ፡ ሑከት፣
ይክልኑ፡ በእግር፤ ተሐውሶ፤ ኀበ ፍኖተ ላዕል፡ ወታሕት?
ነፍስ፡ ዘአልቦ፤ ሥጋ፡ ምውት፣
ወጽልመተኑ፡ ያሴስል፤ እምዓይን፡ ማኅቶት?
ዘላዕሌሁ፤ ኢሀለወ፡ ዘይት፡፡

ትርጉሙ፡- ‹‹ዛሬ በልባችን ብንመረምር ሕይወትን ከሚሰጥ (ማሕየዊ) ቅብዐት (መንፈስ ቅዱስ) በቀር የቃል (ወልደ አብ) ከሥጋችን (ወልደ ማርያም) መዋሐድ የትስብዕትን (የሥጋን) ንዴት (ዝቅተኛነት) አላጠፋም፡፡ በዚህ ነገር በሮም አደባባይ ሁከት አይደረግ፡፡ (በውኑ) ነፍስ የሌለው ሥጋ ላይና ታች መንከላወስ ይችላልን? በውስጡ ዘይት የሌለው መቅረዝስ (ፋኖስ) ጨለማን ሊያጠፋ ይችላልን?›› እያለ በተጠየቅ የሚሞግት ነው፡፡ ዘይት የሚሉት መንፈስ ቅዱስን ነው - ቅብዐት!

ምስጢሩ፡- ‹‹ሥጋን የሚያንቀሳቅሰው ነፍስ/ እስትንፋስ ነው፡፡ መቅረዝ የሚበራው ዘይት ሲያገኝ ነው፡፡ በዚህ አምሳል እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን የነሣው ሥጋ የአብና ወልድ ሕይወት/ እስትንፋስ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በቅብዐት ካላከበረው የሥጋ ንዴት(ዝቅተኛነት) በ(መለኰትና በሥጋ) ተዋሕዶ ብቻ ሊጠፋ አይችልም፡፡›› የሚል ነው፡፡ ቅብዐቶች ‹‹ተዋሕዶ ሁለትነትን አጥፍቶ፣ አንድነትን ቢያፀናም ትስብዕትን የአብ የባሕርይ ልጅ ለማሰኘት አልበቃም፤ ሥጋ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ሲከብር ነው የአብ የባሕርይ ልጅ የተሰኘ›› ይላሉ፡፡ ጎሽዬ ይህቺን ሥላሴ አስጽፈው ለዲሞች ላኳት፡፡ ሰዎቹ መቼ የዋዛ! ሆ! እዛም ቤት እሳት አለ! እሳቶቹ ሥላሴዋን ቅኔ በሥላሴ አጣፏት! ‹‹ኧግ! ወልድን በድንና ጨለማ ታደርገው አንተው?›› ሳይሉ አልቀሩም ተከታዩ ሊቅ፡፡

##2. ተዋሕዶው ቄስ ገበዝ ኑርልኝ ዘዲማ ለ4 ዐይና ጎሹ የሰጡት መልስ

ሥላሴ!

ኢየኀሥሥ፡ ለአብርሆ፤
ቅብዐ ዘይት፡ ፀሐይ፤ ዘላዕለ ኵሉ፤
ወዘየዓቢ፡ ፀሐይ፤ ከማሁ፤ ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ፡ ክብረነ፣
ኢየኃሥሥ፤ አምጣነ ፀሐይ፤ ዘያበርህ፡ ለነ፣
ወኢይትሐወክ፡ ብዙኅ፤ በዝንቱ፤ አርዮሳዌ፡ ዘኮነ፣
ከመ ቃል፡ ብርሃን፤ ኀበ ኢአምነ፣
ዐይንኑ፡ የኀሥሥ፤ ካልአ፡ ዐይነ፣
ወብርሃን፤ ካልአ፡ ብርሃነ፡፡

ትርጉሙ፡- ከኹሉ በላይ የሚሆን ፀሐይ (ብርሃኑን) ለማብራት ዘይት አይፈልግም፡፡ ታላቁ ፀሐይ (ኢሱስ ክርስቶስ) እንዲሁ ለኛ የሚያበራልን (በራሱ ለራሱ) ፀሐይ ነውና ክብራችን የሚሆን የመንፈስ ቅዱስን ቅብዐትነት አይሻም፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ቃል (ወልድ) ብርሃን እንደ ሆነ የማያምን አርዮሳዊ (ተጠራጣሪ) ሰው ብዙ እንዳይታወክ! (በውኑ) ዐይን ለማየት ሌላ ዐይን ይሻልን? ብርሃንስ ብርሃንነቱን ለመግለጽ ሌላ ብርሃን ይፈልጋልን?

ምስጢሩ፡- ከላይ እንዳየነው 4 ዐይና ጎሽዬ ‹‹መቅረዝ ያለ ዘይት አይበራም›› ብለው ነበር፡፡ ቄሰ ገበዝ ግን እርሳቸው መቅረዝ ያሉት ጌታ (ወልድ) በራሱ ብርሃንና ፀሐይ (‹‹አብ ፀሐይ፣ ወልድ ፀሐይ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ›› የምትለዋን ቅዳሴ ማርያም ንባብ እናስታውስ) ስለሆነ ለብርሃንነቱ እንደ እኛ የመንፈስ ቅዱስን ዘይት (ቅብዐት) አይሻም፤ ትስብዕት የከበረው በተዋሕዶ ነው ማለታቸው ነው፡፡ (ትስብዕት) በተዋሕዶ ከበረ! አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ - በተዋሕዶ!

ጎጃም ይብቃን! ሸዋ እንግባ! ኽዱ፤ እንኽድ! ‹‹…ማደሬ ነው፤ … ኧረ ማደሬ ነው፤ … ማደሬ ነው! … እኔስ ማደሬ ነው! ከበላሁ ከበላሁ ከጠጣሁ ሁሉም አገሬ ነው፤›› የሚለውን ያገራችን ጨዋታ ክፈትማ ሹፌር! ሸጋ! … በቃ! እህ! ደርሰናል’ኮ አንተው! ንሳማ ለሹፌሩ ደ/ሊባኖስ ላይ ወራጅ አለ በለው! ደርሰናል! ወርደናል! በሉ አረፍ እንበል! ባረፍንበት ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የሚወዷትን የጸጋ ብሒል ዋነኛ አስረጅ ሚበዝኁ እንስማት!

##3. የጸጋዎች ቅኔ

የቅኔው ማንጸሪያ ታሪክ ይቅደም! በዘፍጥረት 19 እንደ ተጻፈ ሎጥ ከመአተ ሰዶም አመለጠ፡፡ ሚስቱ ግን የጨው ሐውልት ሆነች፡፡ ሎጥ ፈት ሆነ፤ ሚስት አልነበረውም፡፡ 2 ሴቶች ልጆች ነበሩት፡፡ እነሱም ባል አልነበራቸው፡፡ ዘር ከማስቀጠልና ዝምድናን ከማፍረስ መምረጥ ግድ ሆነ! ሴቶቹ ዘር ማስቀጠልን አስቀደሙ! አጠጡት! አባታቸውን ወይን አስጎነጩት! አስተኙት፤ ሎጥ በየተራ አብሯቸው ለጥ አለ! ተኝተው ሲነሡ አረገዙ፤ አሞንና ሞዐብን ወለዱ! (((‹‹ተኝተው ምን ሲያረጉ ነበር?›› ትሉና ዋ! ትቀሰፋላችሁ!))) ሎጥ በአንድ ጊዜ አባትም አያትም ሆነ! ሴት ልጆቹም በአንድ ጊዜ ለልጆቻው እናትም እኅትም ሆኑ! ባለቅኔው ይህቺን ታሪክ ወደ ጌታና እመቤታችን አመጡዋት! እንደ እሳቸው አባባል ጌታ በለበሰው ሥጋ የተነሣ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ተብሎ ለመጠራት ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው የጸጋ ልደት (3ኛ ልደት) ያስፈልገዋል! እመቤታችን በሰውነቷ ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘችውን የጸጋ ልደት ጌታም ማግኘት አለበት! ስለዚህ እሷ እንደ ሎጥ ልጆች ለልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ወላጅ እናት፣ (በጸጋ ከመንፈስ ቅዱስ በመወለድ እንዲሁ) እህት ናት ይላሉ፡፡ እሷም እሱም ለባሴ ሥጋ ስለሆኑ ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደዋልና ያንድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች - እኅትና ወንድሞች - ናቸው እያሉን ነው! አይ! እንግዲህ…ምስጢሩ በቀላል ባይገባም ቅኔው ይምጣ፡-

ሚበዝኁ!

በዘርዐ አቡሆን፡ ኮና፤ እኅተ ውሉዶን፡ አኃት፤ አመ ወርኀ ሕፀፅ፡ ወንትጋ፣
ለከሰ፡ አምላክ፤ ክርስቶስ፡ ቀዳሜ ጸጋ፣
ወለተ ሐና፡ ጠባብ፤ በመንፈስ ቅዱስ፡ እኅትከ፤ እንዘ እምከ፡ በሥጋ፡፡

ተዛማጅ ትርጉም፡- (ሰው) በጎደለበትና ባነሰበት ወራት እኅትማማቾቹ ከአባታቸው ዘር ተቀብለው የልጆቻቸው እኅቶች ሆኑ፡፡ የጸጋ ባለቤት ክርስቶስ ሆይ! ላንተም ብልኋ የሐና ልጅ በሥጋ እናትህ ስትሆን ከመንፈስ ቅዱስ (ጸጋ) በመወለድ ግን እኅትህ ናት!

…በሣልስ፡ ልደት፤ ምስለ አቡሁ፣
ሀለወነ፤ ተዘምዶ፡ ምስሌሁ፡፡

የምትል የሥላሴ ትሁን የዋዜማ ቁራጭ ሐረግ ብሒሉን ደኅና አድረጋ ሳትገልጸው አትቀርም፡፡ ብቻ የቅኔው ምስጢር፡ ከላይ እንደተገለጸው ነው፤ ከሎጥና ከሴት ልጆቹ ታሪክ ይዛመዳል! የክርስቶስን የባሕርይ ልጅነት፣ ክህነት፣ ነቢይነትና ንግሥና ከአባትና እናት የዘርና የደም ተከፍሎን ከሚሻ ልደት፣ የሚክን ጳጳስ ወይም ሊቀ ካህናትን ከሚሻ የፍጡራን ክህነት፣ አንጋሽን ከሚፈልግ ዓለማዊ ንግሥና ጋር የሚያዛምድ እጅግ ህጹጽና ውጉዝ ማንጸሪያ ነው ተብሎ ይተቻል፡፡ እርግጥ ለዚህ ቅኔ ቀጥታ በቅኔ መልስ የሰጠ ባለቅኔ አልተገኘም፡፡ ብቻ እነ አለቃ ለማ ኃይሉ፣ መልአከ ብርሃን አድማሱና አቡነ ጎርጎርዮስ ብሒሉ ቦሩ ሜዳ ላይ እንዴት እንደ ተረታ በሥዕላዊ መልኩ ስላስቀመጡልን መልሱ ዝርው ቢሆንም ከነሱ እንዋስ! ተዋሕዶዎች 2 ልደት የሚል ብሒላቸውን በአኃዝ ከሃይማኖተ አበው ጠቅሰው ካስረዱ በኋላ የጸጋዎቹ ተከራካሪ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ ካቀረቡት በመነሳት ይቀጥሉ አቡነ ጎርጎርዮስ፡-

‹‹ከዚህ በኋላ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ ‹ተጠየቅ› አሉና ‹እናትና ልጁን ልደት እንጂ ያገናኛቸዋል› ሲሉ ጠየቁ፡፡ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ እንዲህ ብለው መጠየቃቸው ‹እመቤታን አዳም (ሲፈጠር በንፍሐተ መንፈስ ቅዱስ ባገኘው ልጅነት) ወስዶት የነበረውን የጸጋ ልደት እንደ ሌላው ሰው ሁሉ (በጸጋ) ተወልዳለች ፤ ልጅዋንም እንደ እሷ የጸጋ ልደት ተወለደ› ባይ ናቸውና ይህ (የጸጋ) ልደት ያገናኛቸዋል ለማለት ነበር፡፡ (የተዋሕዶው ተከራካሪና በሃይማኖታቸው የተነሣ በጸጋዎች ከሸዋ ተባርረው ትግራይ በስደት የነበሩት) መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ግን ካፋቸው ጠለፍ አድርገው፣ ሁሉ ወደሚያውቀው ወደ ግዙፉ ልደተ ሥጋ ለውጠው ‹አባዬ! አባዬ! ያራዳ መምህር! የርሷ ልደት በዘር በሩካቤ፣ የርሱ እንበለ ዘርዕ! ምን አገናኛቸው?› ብለው መለሱ በዚህ ጊዜ በአደባባይ ያለው ሰው ሁሉ ሳቀ፡፡››

ቀደም ሲል እንዲህ ነበር! አሁን እንኳ የሃይማኖት ክርክር በባስና በታክሲ ሰልፍ ልታልቅ የምትችል ቀለል ያለች ‹‹የታማልዳለች - አታማልድም›› የዐ/ነገር ልውውጥ የሚገታት ናት! ይህቺ አካሄድ በ1950ዎቹ በቤተ ክህነት አሳሳቢ ሆና ነበር! ንጉሡ ‹‹ሃይማኖት የግል፣ ሀገር የጋራ›› በማለታቸው ሊቃውንቱ ለአዲስ የአሳብ ግብግብ መዘጋጀት ነበረባቸው! ችግር የሆነው እነሱ የለመዱት በቅኔ መጎሻሸም አለዚያም ቀጠሮና ቦታ እየተያዘ የመኻል ዳኛ ተመርጦ በምስጢረ መጻሕፍት መጋፈጥ ነበር፡፡ በቀ.ኃ.ሥ ፈቃድ በተከፈተው የሚሲዮን ሬዲዮ የሚተላለፈው ስብከት አዲስ ግንባር ሆነባቸው! በውስጥ ካሉትም የተወሰኑት ምንታዌ ውስጥ ወደቁ፤ ተሐድሶ የምትባል የሹራብ ትርተራ የመሰለች ነገር መተርተር ተጀመረ - ሹራቧን ተርትሬ እንደገና በልኬ ካልሰፋሁ ትርተራዬ የማይቆም ነው የሚል እቡይ ትርተራ! የነበረው አማራጭ ለአቅመ ሬዲዮ ያልደረሰችውን ቤ/ክ ለማጽናናት ያችኑ የጥንቷን ቅኔ እየቀጠፉ የውስጡን ቀሳጢ ተርታሪ መሸንቆጥ ነበር! ሸንቁጥ - በአዲስ ግንባር!

##4. ቅኔያትና አዲሱ ግንባር (ተሐድሶ)!

በኦርቶዶክሳዊው ትውፊት ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው›› ማለት ‹‹ከእመቤታችን የነሣው ሥጋ በተዋሕዶ ከብሮ፣ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ፣ አምላክ፣ ወልደ አምላክ ተሰኝቷል›› ማለት ነው፡፡ ብሒሉ የንስጥሮስን ‹‹ማርያም ወላዲተ ሰብእ (ክብር ይግባውና መለኰትነት የሌለው ኢየሱስ - Christotokos- Christ-Bearer, Jesus as just man)›› የሚል ብሒል ነቅፎ ‹‹ወላዲተ አምላክ - Theotokos- God-Bearer, Jesus as God and man.›› ለማሰኘት የሚጠቀስ ነበር፡፡ ባጭሩ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው = የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ!›› አይሑድም የከሰሱት ‹‹ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል›› ብለው ነበር፡፡

በ1950ዎቹ ‹ውላጤ፣ እንበለ ተውላጠ መካን - ቤተ መቅደሱን እንደያዝን ራሳችንን እንለውጣለን› የሚሉ ተስፈንጣሪዎች (ራሳቸውን ተሐድሶ የሚሉ) ‹‹የምን ወላዲተ አምላክ?! መጽሐፉ <የኢየሱስ እናት> ብቻ ነው የሚል፤ የምንጠራትም እንዲያ ነው፤›› ብለው ተገለገሉ፡፡ ‹‹ኧረ በፈጠራችሁ?! እሷን ስታርቁ፣ ከንስጥሮስን 2 ባሕርይ ኑፋቄ ተላጠቃችሁ?›› ቢባሉም ወይ ፍንክች! ያን ጊዜ መልአከ ብርሃን አድማሱ ብእራቸውን ከአፎቱ መዘዙና ያችን ሾተል ወዘወዟት - ኰኵሐ ሃይማኖት - ከመ ሰይፈ መልአክ! ከሐረር መካነ ሥላሴ ደሞ ሊቀ ጠበብት ማእምር አለማየሁ የተባሉ የቅኔ ሊቅ ተከታዩን መወድስ አስወነጨፉ - ወዮልሽ!

መወድስ!

አሌ፡ ለክሙ፤ ደቂቀ ውላጤ፤
ለእሳተ ንስጥሮስ፡ ካህድ፤ እለ ድልዋን፡ በሐሰት፣
እስመ ውስጥክሙ፡ ኮነ፤ ምሉዐ ዐመፃ፡ ክህደት፣
ወእንዘ ሀሎ፡ ውስተ ቤትነ፤
ቄርሎስ፤ እንተ ይሴሰዮ፤ ሃይማኖት፡ ኅብስት፣
ትሴሰዩ፡ በዐመፃ፤ መበልዐ ንስጥሮስ፡ ካህደ፤ እንተ ኢይከውን፡ ለሕይወት፣
ቅድመሂ፡ እምከርሠ እም፤ ተፈጥሮክሙ፡ ምንት?
እስመ ገቢረ ጽድቅ፡ ምረርክሙ፤ ወመዐርክሙ፡ ኃጢአት፣
ባሕቱ፡ ንስእል፤ ነገደ ሌዊ፡ ካህናት፣
ከመ ንኩን፡ ድልዋነ፤ ለሰሚዐ ወንጌል፡ ፍቅረ እግዝእት፡፡

ትርጉም፡- እናንት! ለከሀዲ ንስጥሮስ እሳት በሐሰት (ተሠርታችሁ) የተዘጋጃችሁ የተለዋዋጭ ልጆች! ወዮላችሁ! ውስጣችሁ ዐመፃና ክህደትን ተመልቷልና! በቤታችን ቄርሎስ የሚመገበው ኅብስት ሃይማኖታችን ሳለ፣ በእምቢተኛነት ለሕይወት የማይሆን የንስጥሮስን የክህደት መብል ትመገባላችሁና! ከቶ ከእናታችሁ ሆድ ተፈጥሮአችሁ ምንድን ነው? በጎ መሥራት ምሬታችሁ፣ ኃጢአትን ማድረግ መአራችሁ ነውና፡፡ (ለማንኛውም) እኛ (በተምሳሌት) ከነገድ ሌዊ የምንሆን ካህናት ግን የጌታ ፍቅርት የምትሆንን ወንጌል ለመስማት የተዘጋጀን እንሆን ዘንድ እንለምናለን፡፡

አሉና የአጸፋ ዘመቻውን አስጀመሩ፤ ዘመቻው የተቋጨ አልመሰለኝም፤ ይቀጥላል…