የዓርብ ጨዋታ፡- ትውልደ ኦሮሞ ሊቃውንት በጎጃም ጉባኤያት…በጥቂቱ!

kinebet
orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

ቀደም ባለው ጊዜ የመንቀሳቀስ መብታቸውን አሟጠው ይጠቀሙ የነበሩ የሚመስሉ 2 የኅ/ሰብ ክፍሎች አሉ - መነኰሳትና የአብነት ተማሪዎች፡፡ መነኰሳት ከዘመድ፣ ከወገን ተለይተው ራሳቸውን ለዚህ ዓለም ምውታን ያደረጉ ናቸውና ‹‹የማንም ያይደለ፣ የሁሉም ነው›› ተብለው ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ‹‹ዖድዋ ለምድር!›› ተሜም እንዲያ ነው! ይሽከረከራል! አይወስንውም ጋራ ሸንተረር! ብሔሩ - ምግባሩ፣ ቀበሌው - ጉባኤው!

1. የተማሪ ቀበሌው፣ ጉባኤው!

እነሱን አይቼ ነው እንዲህ ማለቴ! ሆነብኛ! የሱስንዮስ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ኦሮሞው አለቃ ጢኖ ሆነብኝ! የቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ዘጋቢው ደብተራ ዘነብ ቋንቋ በአፋን ኦሮሞ ቃናው አጠራጠረኝ! የአጼ ዮሐንስ ባለ ፍትሐ ነገሥት ማን ይሆን ብዬ ባጠያይቅ ጎንደሬው አለቃ መርአዊ ናቸው ለካ! ዕጨጌውም ጎጃሜው ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ኖረዋል! ዮሐንስ አልፈው፣ ምኒልክ ሲተኩ ዕጨጌ የነበሩት ደግሞ የትግራዩ ዕጨጌ ዘመንፈስ ቅዱስ! የሸዋው አባ ወልደ ሰማዕት አጼ ዮሐንስ ከግብፅ በተማረከ ወርቅ አስጀምረዋት፣ አጼ ምኒልክ ባስፈጸሟት የኢየሩሳሌሟ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም እድሞ (መግቢያ በር) ላይ የአጼ ዮሐንስ ሥም ካልተካተተ ብሎ ከምኒልክ ጋር ግብግብ! እንጃ! በመሳፍንትና በመኳንንት ደረጃ የደጃች ባልቻ ሳፎንና የፊ/ሪ ሀብቴ ዲነግዴን ያህል ለኢየሩሳሌም ገዳማት ዛሬ ድረስ የዘለቀ የገቢ ምንጭ የዘረጋ መስፍን መኖሩን እንጃ!

ያገሬን የጎጃም ገናና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዜና ከነጋድራስ አፈወርቅ ገ/ኢሱስ በላይ ቀናኢ ሆኖ የጻፈው ወለጌው አለቃ ተ/ኢየሱስ ነበር! በእነሱ ዘመን የዲማው መምህር የትግራዩ አለቃ ተጠምቆ! ተማሪያቸውና ኋላም የተካቸው የሰቆጣው መምህር ሠረገላ ብርሃን! ተጠምቆም ሠረገላ ብርሃንም አይነ ስውራን - ብርሃናቸው ጎጃም ነበራ! እህሳ! ሰቆጤው ሠረገላ ‹‹አልቦ እምቅድሜሁ፤ ወአልቦ እምድኅሬሁ›› የተባለለት አደል!

የለም! የለም! ጉዱ ካሳ የፈጠራ ገጸ ባህሪ አይደለም! ሕያው የዲማ ሰው ነበር! ተናግረዋል! እነ አለቃ ለማ ኃይሉ፣ መልአከ ብርሃን አድማሱና መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ጉዱ ካሳ ታዋቂ የዲማ ሊቅ እንደነበር ተናግረዋል - ብቻ ስሙ ተገልብጡዋል - ካሳ ጉዱ! ያ! ሰቆጤ ሠረገላ ብርሃንና ካሳ ጉዱ ተወዳድረው ነበር ይሉናል! ጉዱ ካሳ 2ቱን ሙሉ ቤት መወድስ እስክታዘንብ ሠረገላ ማዕበሉ አጣጥፏት እልም! ኧግ እልም ያርገው! ጭራሽ፡-

…ወበክልኤቲ፡ ጌጋይ፤ ቃለ መወድስ፣
አክአብ፡ ጉዱ ካሳ፤ እስከ ማዕዜኑ፡ ተሐነክስ፡፡

ብሎ የመወድሱን ቤት ዘጋባት! ተውማ! ነገሩስ እንዲያ ነበር! ነበር! የተማሪ ቀበሌው፣ ጉባኤው ነበር! ለዚሁ ነበር ጎጃሜው አለቃ አፈወርቅ ‹‹አፈወርቅ ዘአክሱም››፣ ወለጌው የንታ ገብረ ሥላሴ ‹‹ገብረ ሥላሴ ዘኤልያስ››፣ የትግራዩ አለቃ ገብረ መድኅን ‹‹ ገብረ መድኅን ዘሐረር››…ይባሉ የነበር! የትግራዩ አቡነ ናትናኤል ‹‹ቀብሬን አሰላ ላይ›› ብለው አደል እንዴ በቀርቡ የሸኘናቸው! የፍቼ/ሰላሌው አቡነ ጴጥሮስ ጉባኤና ትምህርት ወሎ ነው የተደራጀው! ለዚህ ነው፤ የተማሪ ቀበሌው ጉባኤው ማለታችን! ተሜ ካገርና ከወገን ርቆ፣ በቆራጥ ልቡና መማርን ስለሚሻ ከቀበሌ መራቅ አይከብደውም! ወገኑን ሲናፍቀው እንደ የንታ ገብረ ሥላሴ ‹‹እምዘመደ ሰብእ ይኄይስ፤ ዘመደ እንስሳ…›› እያለ በሰም ይኳሽበታል! ይቅርታ! እንዲያው ስንንጓለል ታላላቆቹን የጎጃም ጉባኤ ፈርጥ የነበሩና ዛሬም የሆኑ ትውልደ ኦሮሞ ሊቃውንት አስቆምናቸው! የንታ ገብሬ ይግቡ…

2. ገብረ ሥላሴ ክንፉ ዘኤልያስ!

ትውልዳቸው ወለጋ ነው፡፡ የተወለዱበትን ዓመተ ምሕረትና የወላጆቻቸውን የተሟላ ሥም ዘግቦ ያቆየልን የለም - ቅኔያቸው ፋታ ስላሳጣ ይሆናል፡፡

ሀ) መምህራኖቻቸው፡- ሰቆጤው ሠረገላ ብርሃን፣ ሸዬ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ሊቀ ጠበብት አይቸህ፣ ቡሬ ገብረ ማርያም ናቸው፡፡

ለ) መምህርነታቸው፡- የቅኔ፣ የመጽሐፈ ሊቃውንት (ሃይማኖተ አበው)፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ነው፡፡

ሐ) የተማሩባቸው ቦታዎች፡- የወገራ ማርያም፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ገነት ኤልያስ፣ ደንበጫ ሚካኤል፡፡

መ) ቅኔያቸው፡- ‹‹አፍራሽና ተከታታይ›› የዋሸራ ሰምና ወርቅ የሚባለው ነው! በንባብም፣ በምስጢርም ጥንቅቅ ያለ ሰምና ወርቅ ሆኖ ታሪክ ማጣቀስ የሚያዘወትር የቅኔ መንገድ!

ሠ) ከተማሪዎቻቸው መካከል፡- አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔና አቡነ ጴጥሮስ ዘጎንደር እጅግ ዝነኞቹ ናቸው፡፡ ለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መጠሪያ የሆነውን ሥም ‹‹ዮፍታሔ›› ብለው ያወጡ እሳቸው አደሉ! እነዚህ 3 የደብረ ኤልያስ የገብረ ሥላሴ ፍሬዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከመምህራቸው ጋር እጅግ ይዋደዱ ነበር! ዮፍታሔ ሲያገባ አንዱ ሽማግሌ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ (ገና አባ መልእክቱ ሳሉ!) ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁን በአዲስ አበባ ተቀብሎ ተማሪ ቤት ያገባ ዮፍታሔ አደል እንዴ! ሁሉም ኤልያሴዎች ናቸው! ሁሉም ብጥር ቅኔ አዋቂዎች ነበሩ! የአንድ ቀበሌ ልጆች ነበሩ! ያ ግዙፍ ቀበሌ መምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ ይባላል! በ1938 ዓ.ም. እስኪሠናበተንና በኤልያስ ደጅ ዕረፍቱን እስኪያደርግ የሚተነፍሰው ቅኔ ነበር! ለከብሩና ከዘመድ በመራቁ የሚጽናናበት ከሚመስለኝ የራሱን ዝነኛ መወድስ የማናቀርብለት!

መወድስ!

እምዘመደ ሰብእ፡ ይኄይሥ፤ ዘመደ እንስሳ፤
ወፍቅረ እንስሳ፡ የዐቢ፤ እምተፋቅሮ ሰብእ፡ ለለጊዜሁ፣
እንዘ ገፋኢሁ፡ ለይስሐቅ፤ እደ አብርሃም፡ አቡሁ፣
በግዕ፤ አኮኑ፤ ለይስሀቅ፡ ቤዛሁ፣
ወከመ ኢይትርፍ፤ አምሳሊሁ፣
ኢየሱስሃ፡ ሰቀሉ፤ አይሑድ፡ አዝማዲሁ፣
ንህነሂ፡ ሶበ ሰማዕነ፤ በመጽሐፈ ዕዳ፡ ዜናሁ፣
ምንት፡ እምእንስሳ፤ ለሰብእ፡ ፍድፋዴሁ፣
እንዘ አድግ፡ የአምር፤ ፍኖተ አሐቲ፡ ምቅማሁ፣
አምጣነ እስራኤል፡ ኢጠየቁ፤ ወኢያእመሩ፡ አምሳሊሁ፡፡

መልእክቱ እንዲህ ነው፡- ከሰው ከመዛመድ፣ከእንስሳ መዛመድ! ከሰው ከሚገኝ ፍቅርም ከእንስሳት የሚገኘው ፍቅር ይበልጣል! አብርሃም በልጁ ላይ እጁን ሲያነሣ፣ በግ ነበር የተቤዠው! ምሳሌያችን በዚህ እንዳይቆም፣ አይሑድ ሰቀሉት ዘመዳቸውን! እረዲያ! ፍርዱን እንዳየን፣ ሰው ከእንስሳቱ መቼ ብልጫ አለው! አሕያ ሲያውቀው መሰማሪያውን፣ እስራኤላውያን መቼ ጠየቁ፣ መቼ ተረዱ የሱን አብነት - አምላካቸውን! ኤዲያ! ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም!

ይላሉ! አይይ! ሰው ባልፈራ የየንታን ቅኔ እንዲያው እንደ ዘፈን አድርጌ በደለቅሁበት ደስ ባለኝ - እንዲወጣልኝ! በቅኔ መደለቅ በኔ አልተጀመረ! ወላዲቴን! አድሙ ዘጫቤ ይባል የነበረ ኦሮሞ የጉብሎችን ዘፈን ወደቅኔ ቀይሮ አስደልቆበታል ብለውን የለ! ጉብሎች፡-

“እናትና አባትሽ፤ አይወዱም እንግዳ፣
ሳሚኝና ልሒድ፤ በሳንቃው ቀዳዳ፡፡”

ሲሉ ቢሰማ፡-

“ሰአምኒ፡ እሁር፤ በስቁረተ ዕፅ፡ አነዳ፣
አቡኪ፤ ወእመ ዚአኪ፤ ኢሠምሩ፡ እንግዳ፡፡”

ብሎ ማርቆስ ላይ አስደለቀ ብለውናል፡፡ ብቻ እኒያ ትሑት ሊቅ የሰላሌው የንታ ጥበቡ ገሜ ባቲ ‹‹አይይ! የባላገር ነገር!›› እንዳይሉን እንጠነቀቃለን!

3. ጥበበ ሥላሴ ገሜ ባቲ!

እንደ እውነቱ የየንታ ጥበቡ ገሜ ታሪክ ይበልጡን ከወሎና ከሸዋ በተለይም ከሰላሌ ጋር ቢሰናሰል የበለጠ ይደምቃል፡፡ የመጀመሪያ የቅኔና የመጽሐፍ ትምህርታቸው ዲማና ማርቆስ ስለነበረ ነው ወዲህ - ወደ ጎጃም የሳብኳቸው፡፡ እሳቸው ገሜ ባቲ ከተባሉ የሞጆ ባላባትና ከመርሐ ቤቴዋ ወይዘሮ ደስታ ጎሹ ሰላሌ/ጎሐጽዮን ሰኔ 10 ቀን 1873 ዓ.ም ተወለዱ ፡፡ ሁለቱንም ወላጆቻውን በልጅነት አጡ፡፡ ሄዱ - ምስካየ ኅዙናን ወደምንላት ቤ/ክ - ጎሐ ጽዮን ማርያም! ተማሩ! ተደቆኑ! ለምን በዲቁና ይቅሩ! ጎጃም ተሻገሩ! ዲማ ገቡ! ቅኔና ብሉይ አጠኑ! ወዲያው ማስተማር ጀመሩ! እየተማሩ ማስተማር መለያቸው ነው! አሁንም አባይን ተሸገሩ - ወደ ወሎ! በላስታና በሰቆጣ ቅኔና ብሉያ እያስተማሩ ጎንለጎን ፍትሐ ነገሠት፣ ሐዲሳት፣ መጽሐፈ መነኮሳት፣ ሃይማኖተ አበው ቀጸሉ…ወሎ ላይ ለዓመታት ቆይተው በ1913 ዓ.ም በ40 ዓመታቸው ሸዋ ተመለሱ! ፍቼ፣ ዝቋላ፣ አዲስ አበባ እየተዘዋወሩ ቅኔውን ዘሩ፣ አበቀሉ፣ አመረቱ! እነዚህ ሲደመሩ 14 ዓመታት ሆኑ! የተቀረው 37 ዓመት በሥሬ መድኃኔዓለም መደበኛ ጉባኤ ዘረጉበት ነው! ስትደምረው 51 ዓመት ይመጣል! ከወሎ ከተመለሱበት የ40 ዓመት ዕድሜያቸው ጋር ብናገናኘው 91 ዓመት ይሆናል! እሱ የጥበቡ ምድራዊ ሕይወት መቋጫ ነው! በሥሬ መድኃኔዓለም፣ የመድኃኔ ዓለም ለታ ሐምሌ 1964 ዓ.ም በክረምቱ ጥበብ ቤቷን አፈረሰች! እሱስ መች የዋዛ! የገፋችውን ክረምት ከነጓዟ አስቀድሞ እንዲህ ተቀኝቶባት ነበር፡-

መወድስ!

ማዕዜ፡ ይገብእ፤ ፍትሐ ግፉዐን፤
በለስ፡ ወወይን፤ እለ በዐመጻ፡ ተቀትሉ፣
ተካየዱሂ፡ ኅቡረ፤ ወተመሓሉ፣
ማያት፤ ነገደ ይሑዳ፤ ዲበ ዕፅ፣ ይስቅሉ፣
ልምላሜ፤ እግዚአ ኵሉ፣
ደመ ልምላሌ፡ ላዕሌነ፤ ለይኩን፤ እንዘ ይብሉ፣
ቅዱሳንሂ፡ ማዕበላት፤ እለ ገዳማተ፡ ዔሉ፣
ምጽላለ፡ ኢኀሠሡ፤ ወማኅደረ፡ ኢሰዐሉ፣
ወደባትሪሁ፡ ለከርም፤ በኀበ ተተክሉ፣
አፍላግ፡ መዘምራን፤ ቃሎሙ፡ ያሌዕሉ፡፡

ሊቃውንት ክረምትን የሚያዩበትን ዐይን ካልተዋስን ባለቅኔውና ሰማዕያኑ የሚገናኙ አይመስለኝም! በክርምት በለስና ወይን ይደርቃሉ፤ ልምላሜ ያጣሉ! ሊቁ እነሱን ነው ተገፉ የሚሉት! በአይሑድ የተመሰሉ ገዳዮች ውሆች ናቸው! አይሑዳውያኑ ማያት (ውሆች) ልምላሜን በእንጨት ሰቀሉት፤ ደሙም በኛ ላይ ይሁን አሉ! እንደ ቅዱሳኑ በበረሃ የሚንከራተቱት ማዕበላትም መጠለያ አልፈለጉም፤ ማደሪያም አልለመኑም፡፡ ክረምት ድንኳኑን ሲተክል በልዑል ድምጽ ዜማ መዘምራን ወንዞች ይዘምራሉ!

እንዲያ ይሉ ነበር ጥቤ! ጥበቡን ከቤ/ክ ቅጽር ውጭ አደረ የሚለው ሰው የለም! ከተማሪው የተለየ ምግብ ሲበላ አልታየም! ኑሮው ሰሌንና በመሥራትና ቁም ጽሑፍ እየጻፈ በመሸጥ ነበር! ሁሉም ሰው ለእሱ እኩል ነው፤ ሁሉንም ‹‹ባላገር›› ይላል! በግእዝ - አማርኛ- ኦሮሚፋ ሳይደናቀፍ ወንጌል ሲዘራ የኖረውና በ1984 ዓ.ም ለፕትርክና እስከ መታጨት የደረሰው የጎሐ ጽዮኑ ተወላጅ አባ ሰለማ ዘባሌ የጥበቡ ፍሬ ነው! ዛሬ መጽሐፈ ቅዳሴን ወደ አፋን ኦሮሞ በመመለሱ ሥራ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የቅኔ፣ የሐዲስና የብሉይ መምህሩ አቡነ ያሬድ በጥበቡ ገሜ የተቀረጸ የሰላሌ ፍሬ ነው! ጥበቡ ካንድም ሁለት ጊዜ ለጵጵስና ታጭቶ ወደ ጉባኤው አደላ፤ ሸሸ! ‹‹የባላገር ነገር! ተውኝማ!›› ብሎ ሸሸ! ለዚህ ነው በቀ.ኃ.ሥ ዘመን የነበረው የሽልማት ድርጅት ለድካማቸው እውቅናና የ10 ሺህ ብር ገጸ በከረከት ያበረከተላቸው! ያን ጊዜ ነው ንጉሡን ‹‹አይይ! የባላገር ነገር!›› አሏቸው እሚባል! ለትንሽ! እንደ ሌሎቹ ሊቃውንት ለድካሙ እውቅና ሳይገኝ አልፎ እንዳይቆጨን አድርገውናልና ቀ.ኃ.ሥን እናመሰግናለን - አኰቴት በዘይደሉ!

4 .ሌሎች ኦሮሞ ሊቃውንት!

  • በጎጃም ካሉ ገዳማትና አድባራት ቀዳማዊቷና ክብርቷ ደብር የኔው ናት - መርጡለ ማርያም! እዚያ ነው አባቴ ቅኔ የተማረው! መምህሩም የሰላሌው የንታ ሀብቴ (ሀብተ ሥላሴ) ናቸው! ዛሬም አሉ! አምና የመርጡለ ማርያም ሰው በነቂስ 80 ሺህ የሚጠጋ ብር አዋጥቶ ባሕር ዳር ድረስ ልኮ አሽሞንሙኖ አሳክሟቸዋል! ከጉባኤው በዕርግና ምክንያት ቢቀሩም ያስተማሯቸው ደባትርና የመርጡል ሕዝብ በክብር ይዟቸዋል! አባቴ በሕይወት ሳለ ሳያያቸው አይመለስም ነበር! በደብሯ በቅብዐትና በተዋሕዶ መካከል ክርክር ተነስቶ በተዋሕዶዎች በላይነት ሲጠናቀቅ የተዋሕዶ ሰልፉን ከመሩት አንዱ እሳቸው ነበሩ!

  • ከመርጡል ዝቅ ስንል፣ አባይ መዳረሻ ላይ ያለች ደብረ መድኃኒት የተሰኘች ደብር አለች! ከ40 ዓመት በላይ በቅኔ መምህርነት የመሯትና አሁንም ልጃቸውን በመንበራቸው አስቀምጠው በክብር የሚኖሩባት የንታ አስካል የአምቦ ሰው ናቸው፡፡

  • አቡነ ሕዝቅኤልን የቅኔና ትርጓሜ ዕውቀት የሰማ ሁሉ ይመሰክረዋል፡፡ ከእርሳቸው ቅኔ መምህራን አንዱ የብቸናው የንታ ፍስሐ ናቸው፡፡ የንታ ፍስሐ የምሥራቅ ሸዋ ኦሮሞ ናቸው፡፡

  • በአሁኑ ሰዓት እየገነነ ስለመጣው ተክሌ አቋቋም የምናወጋ ከሆነ ከደብረ ኤልያሱ ወልደ ሚካኤል ልንጀምር ግድ ነው! እሳቸውም ወዲህ ናቸው! ብቃታቸውን አይተን፣ የባላባት ልጅ አጋብተን መርጡለ ማርያም ላይ ለማስቀረት ሞክረን ነበር! ልጅቷን ይዘው ‹‹ዲበ ሠረገላ ኤልያስ ህየ አነብረክ›› ዘምረው ሄዱ! ዛሬም ይዘምራሉ! ስንቱን እናንሳ…ተዛምዷችን እንዲያ ነው አያ…ጉባኤው መች እንዲህ ቀላል! ዕውቀት በብሔር ድንበር አይታጠረም፤ ተሜም እንዲሁ!