ህየንተ ዓርብ ፡- ዝምድና!

kinebet
orthodox

(በአማን ነጸረ) #1

ቃሉ ፊደላዊ ትርጓሜ አይፈልግም፡፡ ብቻ አይነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ አይነቱም ይቅር፡፡ አይነተኛውን እናውጋ፡፡ አይነተኛ ዘመድ በትውፊትና በቤተ ክርስቲያን አቆጣጠር እስከ ሰባት ቤት ይቆጠራል፡፡ ማለቴ ይቆጠር ነበር! ኋላ በ1992 ዓ.ም የፌደራል የቤተሰብ ሕግ ሲሻሻል ዝምድና እስከ አክስት ተባለ፡፡ጮኸች! ቤተ ክርስቲያን ‹‹እረ እስከ 7 ቤት አድርጉት›› ብላ ጮኸች! ‹‹አይ! ተናግረናል፤ተናግረናል! ከፈለግሽ የራስሽን ምዕመናን እስከ 7 ቤት እየቆጠርሽ በተክሊል መዳር ትችያለሽ፤ እኛ ግን ዝምድና እስከ አክስት ብለናል፤›› ተባለች፡፡ ሕጉ ፀደቀ፡፡ ከኦሮሚያ በቀር ብዙኃኑ ክልሎች ዝምድና እስከ አክስት አሉ፡፡ የአክስት ልጅ ሚስት/ባል ትሆናለች! ሯ!ዘመድና ዘመድ ደግሰን ልንድር!

##1. ባልና ሚስት ለማለያየት የደገስን ጊዜ!

የአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ የወጣ ሰሞን ነው! የጎጃሙ አጎቴ ልጅ በስህተት ያገባትን ዘመድ (7 ትውልድ ሳይሞላ በ6ኛው ላይ በስህተት የተጋቡ!) ‹አልፈታም፤ ሕጉ ፈቅዷል አሉ› ብሎ ተገለገለ፡፡ ተገለገለ፡፡ ቢባል ቢሠራ…ወይ ፍንክች! ኋላ ቤተ ዘመዱ ሚስቲቱ ላይ ዘመቻ ከፈተ፤ ሆን ብሎ ማበሳጨት - በራሷ ጊዜ እንድትሄድ - መነትረክ! እረ’ዲያ! እነሱ’ቴ! ይብስ ተጣበቁ! ቤተ ዘመድ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ደገሰ፡፡ ባልና ሚስት ተጠሩ፡፡ ‹‹ሰርፕራ…ይዝ! ልናለያያችሁ ነው!›› ነገር ነው ነገሩ፡፡ ሰው ለማለያየት ሲደገስ ለተአምር ዐየን፡፡ ወንድዬው ተፎገላ፤ ሴቲቱ ተንፈቀፈቀች፡፡ ቤተ ዘመድ ‹‹ወይ ተለያዩ ፣ ወይ ረግመን ከእድር፣ ከማኅበር፣ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ጭምር እናስወጣችኋለን፤›› አለ፡፡ ወንድየው ‹‹እንኳንስ ከእድር ለምን ከጎጃም አታስወጡንም (ዘመዶቼ ቁመታቸውን በአባይ ምንጭ እየለኩ ጎጃምን ከግብፅ ጋር ነው የሚያነጻጽሩት - ሪፐብሊክ ነው ለነሱ ጎጃም - ከጎጃም መውጣትም ካገር መውጣት ነው ትርጓሜው!)፤ አልፈታትም!›› ደረቀ፡፡ ያን ጊዜ ነው አባቱ የተነሣው፡፡ ወላጅ አባቱ ተነሣ፡፡ የነብር አነሳስ ተነሣ፡፡ ጠመንጃውን ስቦ፣ ሸቅሽቆ፣ ፎክሮ ተነሣ! ‹‹እንዲች ነችና የሰውየው ልጅ! ምን በወጣኝ በወለድኩ የምዋረድ?! ታዋርደኝ አንተ?! ስማ፡- ከእንግዲህ ከዚች ልጅ ጋር ባንድ መደብ ለመተኛት ካሰብክ ከቤተ ክርስቲያን ጓሮ አስቀድመህ 3 መቃብር ቆፍር፤ 2ቱ ለአንተና ለሚሽትህ ፣ አንዱ ለኔ! አዎ! 2ታችሁንም አንጥፌያችሁ ሳበቃ እከተላችኋለሁ! ቃሌ ነው፤ ፈጣሪዬ አይለመነኝ፤ የተባልከውን ካላደረግህ የተናገርኩትን አደርገዋለሁ፤›› ሲል ሰውነቱ በእልህና በሲቃ እየተንዘፈዘፈ ተናገረ፡፡ ፀጥ! ወመጽአ ዓቢይ ድንጋጼ! ከድንጉጻን መካከል ካሕኑ አባቴ በቀኝ እጁ መስቀሉን ወድሮ፣ በግራ እጁ ረጅም ጺሙን እየላገ ተንገታግቶ ተነሣ! አዳም ልጆቹ አቤልና ቃየል መንትያዎቻቸውን እንዳያገቡ ከደነገገው ሕገ ልቡና እስከ ፍትሐ ነገሥት እያጣቀሰ በዘመዳሞች መካከል ጋብቻ ነውር እንደሆነ ሲናገር ቆይቶ በአጎቴ ዛቻ ላይ ውግዘት ጨመረበት፡፡ በዚሁ በዘመዳሞች መካከል 7 ትውልድ ሳይሞላ መጋባት ስለበዛ የቤተሰብ ማኅበር ይመስረት ተባለ፡፡ ግዙፉ ዓመታዊ የ7 ትውልድ ዘር ማንዘራችን መገናኛ ማኅበር ተመሠረተ፡፡ ጋብቻ አፍርሰን፣ ማኅበር መሠረትን፡፡ ዘመዳሞቹ ባልና ሚስቶች ተሸነፉ፡፡ መሸነፋቸውን በወንድዬው እንባ አረጋገጥን፡፡ የልጁ ከሚስቱ የመለየት እንባ አባቱን ከገባበት ውርደት ሰፈፍ ሲያደርገው ታዘብን፡፡ አጎቴ በመሀይም አንደበቱ ‹‹ዘመድ ከቀደመ ውርደት አይመጣም፤ ውርደት ከቀደመ ግን ዘመድ አይገኝም፤ ቢገኝም አይረዳም›› ብሎ የተረተው የዚያ ጊዜ አይደል?! ተረቱ ትገርመኛለች፤ ደግሞም ታስታውሰኛለች! ቅኔ…

##2. አልቦ ዘመድ (ከእናት በቀር!)

‹‹አልቦ ዘመድ›› የታወቀ መወድስ ነው፤ የመጽሐፍ ርእስም ነው - የአመጸኛው አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ድንቅ መጽሐፍ፡፡ ትራሴ ላይ ላጣቸው ከማልፈልግ፣ ቁም ነገራቸው በገጻቸው ማነስ ከማይለካ 5 መጻሕፍት አንዱ - አልቦ ዘመድ! (የተቀሩት የዶ/ር እጓለ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ የአቡነ ጎርጎርዮስ መጻሕፍት፣ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደርና የበእውቀቱ ስዩም ኗሪ አልባ ጎጆዎች ናቸው፡፡)ቢሆንም ዛሬ ‹‹አልቦ ዘመድ›› ላይ ቅሬታ ማቅረብ ሽቶኛል፡፡ ቅኔውን አስቀድሜ ሚጢጢ ቅሬታዬን አስከትላለሁ፡፡

መወድስ!

አልቦ፡ ዘመድ፤ ጊዜ - ተዋርዶ፤
ወይከውን፡ ባዕደ፤ ጊዜ - ተዋርዶ፡ ዘመድ፣
እመሰ፡ ይትሌአል፤ በንብረተ - ሥጋ፡ ማዕድ፣
ጥቀ፡ ዘመዱ፤ ወጥቀ፡ ነገድ፣
ባዕደ፡ ይዛመድ፣
እምኀበ - አልቦ፡ ነገድ፤ ወእምኀበ - አልቦ፡ ትውልድ፡፡
ሶበሂ፡ ተሰአልዎ፤ ለሐዋርያ፡ አይሑድ፣
ኀደገ፡ ፈጣሪሁ፤ ወቆመ፡ ምስለ - ባዕድ፣
ዘመድሰ፡ ዮሐንስ፤ ወልደ - ነጎድጓድ፣
ኢተፈልጠ፡ ምስለ - እሙ፤ እስከነ - መቃብረ፡ ይወርድ፡፡

መልእክቱ፡- ሰው ዝቅ ባለ (በተዋረደ) ጊዜ ዘመድ የለውም፤ እንዲያውም ዘመድም ባዕድ ይሆናል፡፡ ንብረት ሲደረጅ ግን ዘመድና ነገድ ቀርቶ ከነገድና ከዘመድ የማይወለድ ባዕድም ይዛመዳል፡፡ ሐዋርያው (ጴጥሮስን) አይሑድ (በቁርጡ ሰዓት) በጠየቁት ጊዜ ፈጣሪውን ትቶ ከባዕዳን ጋር (የምትሉትን ሰው አላውቀውም) ብሎ ቆመ፡፡ ዘመድ ማለትስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ እሱ (ፈጣሪው) መቃብረ እስከወርድ ከእናቱ (ከእመቤታችን) አልተለየም ማለት ነው - መልእክቱ፡፡

ሚጢጢ ቅሬታዬ ባለቅኔው ዮሐንስን ለማቅረብ ሲል ታላቂቷን የሰውና እግዚአብሔር አዛማጅ ድልድይ ዘነጋት - እመቤታችንን እንደ ዘመድ ማየት ተሳነው፡፡ መስቀሉ ስር ቆማ እያያት ከዮሐንስ አዳብሎ አለፋት፡፡ ‹‹ባለቅኔና ሠርግ ጥሪ የሩቁን ሲያይ የቅርቡን ይዘነጋል፤›› ብለን ካላለፍነው በቀር ተሳስቷል፡፡ እኔ እሱን ብሆን ‹‹አልቦ፡ ዘመድ፡ ዘእንበለ - እም፤›› ነበር እምል! ከወገን ሁሉ ‹‹አልቦ ዘመድ›› የማትሰኝ እሷ ናታ!

##3. ወገንተኛነት!

በተወሰኑ ሐሳቦቻቸው ያለኝን ልዩነት ጠብቄ የማከብራቸው ሰዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ፕ//ር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው፡፡ ባገር ውስጥ የታተሙ ሥራዎቻቸውን፣ በኢንተርኔት የሚለቀቁ ጽሑፎቻቸውን በማልስማማበት ላይ ተዐቅቦ እያደረግሁ እከታተላቸዋለሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙኃን የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ መዛግብት አፍቃሪዎች ይከታተሉዋቸዋል፡፡ ለዚህ ይመስለኛል፣ በሚሊኒየሙ ቤተ ክህነቱ ባሳተመው መጽሐፍ ለሠሩት የጥንታዊ መዛግብት ካታሎግ ስማቸው በክብርና በውዳሴ የተጠራው፡፡ የአባ እስጢፋኖስን ገድል ከእሳቸው በኋላ ያሳተመው የጉንዳጉንዲ ገዳምም በገድሉ መግቢያ ስማቸውን በበጎ ያነሣዋል፡፡ አሁን ደግሞ በዚሁ ሥራቸው የበጎ ሰው ሽልማት አሸነፉ መባልን ሰማሁ፡፡ ደስ ብሎኛል፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ አባትን ማክበር ለራስ ነው፡፡ ወገናዊ አክብሮቴን ስለ ወገንተኛነት ከጻፉት በመጥቀስ ልግለጽ፡፡ ከአንዳፍታ ላውጋችሁ መጽሐፋቸው ጥቂት መስመሮች እንደ ወረደ…

‹‹ወደ ወገኔ አልሳብም፤ ለወገኔ አላደላም የሚል የዋሾ ጎረቤት ነው፡፡ ይኸ በግልጽ የሚታየው ወገናችን በማናደርገው ኅብረተሰብ ማህል ወገን የምናደርገው ግለሰብ ብቅ ሲል ነው፡፡ አበሻ ይገኝበታል ብለን በማንጠረጥርበት ቦታ እግር ቢጥለንና ድንገት አንድ አበሻ ቢያጋጥመን ልናነጋግረው እንሞክራለን፡፡ አሜሪካ አገር በየአውሮፕላኑ ጣቢያ የማገኛቸው ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ መሆኔን ሲያውቁ ከሚጠበቅባቸው በላይ እርዳታ ሳያቀርቡልኝ አያልፉም፤ ይሄ ወገንተኛነት ነው፡፡››

‹‹ወገንተኛነት በመሠረቱ ስሕተት የለበትም፡፡ ወገንተኛነት ሁለት አይነት ናቸው - ቅዱስና ርኩስ፡፡ ቤተሰብ የሚመሠረተው፣ ማኅበር የሚቋቋመው፣ ሀገር፣ መንግሥት የሚገነባው በቅዱስ ወገንተኛነት ላይ ነው፡፡ ቤተሰብ፣ ማኅበር፣ ሀገር የሚቋቋሙት ግለሰቦችን በእኩልነት በማገናኘት ነው፡፡ አንድ ሰው የቤተሰብ፣ የማኅበር፣ የሀገር አባል ከሆነና አባላቱን ሁሉ ወገኖቹ መሆናቸውን ከተቀበለ በኋላ በቤተሰብ ውስጥ፣ በማኅበር ውስጥ፣ በሀገር ውስጥ ወገን ከለየ ሥራው ርኵስ ወገንተኛነት ነው፡፡ እሱም ከሓዲ ነው፤ ከዳተኛ ነው፤ ማተበ ቢስ ነው፡፡ አንድ ሰው የቤተሰብ፣ የማኅበር፣ የሀገር አባል ከሆነና አባላቱን ሁሉ ወገኖቹ መሆናቸውን ከተቀበለ በኋላ የቤተሰብ፣ የማኅበር፣ የሀገር ጉዳይ በሚተችበት ጊዜ የቤተሰቡን፣ የማኅበሩን፣ የሀገሩን ጥቅም ማየቱን ትቶ ማዳላት ካሳየ እርኩስ እርጉም ወገንተኛ ነው፡፡…››

እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ ፕ/ር እንደሚሉት አንድ ሰው በግል ሕይወቱ ለቤተሰቡ ያለውን ሁሉ አሟጦ መጠቀሙ ወገንተኛነት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከግል ሕይወቱ (ከቤተሰቡ) ባለፈ የማኅበር ባለሥልጣን ሲሆን የቤተሰብ ሕይወቱ ከማኅበር ሥልጣኑ ያንሳል፣ ከማኅበር ወደ ሀገር ሲሻገር ደግሞ ትልቁ ወገንተኛነት ይመጣል፡፡ ስለዚህ በሀገር ወንበር ላይ ስትሆን ለቤተሰብ፣ ለብሔር፣ ለማኅበር እያልክ ወገን ከለየህ እሱ ርኩስ ወገንተኛነት ይሆናል፡፡ ከቤተሰብ ወጥተህ በቀበሌ ወንበር ስትቀመጥ የቀበሌውን ነዋሪና ቤተሰብህን እኩል ማየት አለብህ፡፡ ከቀበሌ ወደ ወረዳ ስትሻገር የቀበሌህን ነዋሪ ከሌሎች ቀበሌዎች እኩል ማየት አለብህ፡፡ ከወረዳ ወደ ዞን፣ ከዞን ወደ ክልል፣ ከክልል ወደ ሀገር፤ ከሀገር ወደ አህጉር መንበርህ ከፍ ባለ ቁጥር ወገንተኛነትህን እየገታህና እያመጣጠንክ ካልሄድክ ወገንተኛነትህ ርኩስ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡

ባለቅኔዎች እንኳ ፕሮፌሰርን የሚሰሙዋቸው አይመስለኝም፡፡ እነሱ፡- አስቀድመው ‹‹ከሌለህ የለህም›› በሚለው በጥላሁን ገሰሰና ኤፍሬም ታምሩ ዜማ ሳይወሰዱ አልቀሩም፡፡ ‹‹የዘመድ ነገር በሩቅ›› ይላሉ ባለቅኔዎቹ!

##4.ዘመድ በሩቁ!

###ሀ. ከሌለህ የለህም!
ጉባኤ ቃና!

አልቦ፡ ዘመድ፤ ሶበ - የኀልቅ፡ ንዋይ፣
እስመ - ኢይሬኢ፡ ዐይን፤ ሶበ - የዓርብ ፡ ፀሐይ፡፡

እንዲህ ያሉት ሰይፉ ደሴ የተባሉ ግፉዕ ባለቅኔ ናቸው፡፡ ኑሮ የገፋቸው ሊቅ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ደጋግመው የብሶት ቅኔያት ይዘርፋሉ፡፡ ይህቺም ጉባኤ ቃና እንዲያ ናት፡፡

ጀንበር ስትጠልቅ፤ ዐይን ይደፈናል፣
ገንዘብ ሲጠፋም፤ ዘመድ ይርቃል፡፡

እንደማለት ነው ትርጓሜዋ (ትርጓሜዋ ግእዙን መሸከሙን ግን እንጃ!)፡፡ ምናልባት፡-

ዘመዶቼ ጠሉኝ፤ እኔም ጠላኋቸው፣
ያጣ የማያገኝ፤ እየመሰላቸው፡፡

የሚለው የድሮ የግድግዳ ጥቅስ ለጉባኤ ቃናዋ ሳይቀርብ አይቀርም፡፡ የንታ ገብረ ሥላሴ ደግሞ ‹‹ልፉ ቢላችሁ እኮ ነው! ወዲያላችሁ! ከዘመድስ መራቅ ነው የሚሻል!›› ይላሉ

###ለ. ዘመድ በሩቁ!
መወድስ!

ተራኅቆ - ዘመድ፡ ይኄይስ፤ እምተቃርቦቱ፤
ለዝኒ፡ ንባብ፤ ከመ - ንለቡ፡ ምስጢሮ፣
በዋሕድ፡ ከርሥ፤ አመ - ጊዜ - ፅንሱ፡ አንጸሮ፣
ያዕቆብ፡ ለኤሳው፤
አእመረ፡ ከመ - ጸላኢሁ፤ ወአዕቀጸ፡ እግሮ፣
ወዘክልኤሆሙ፤ ተጻርሮ፣
እመጽሐፈ - ዛራ፡ ወፋሬስ፤ ንህነ፡ ንዜከሮ፡፡
ፈቀደሰ፡ ተራክቦቶ፤ ከርሠ - ወላዲቱ፤ ሰቊሮ፣
ዮሐንስ፡ ለእግዚኡ፤ ውስተ - ከርሠ - እሙ፡ ሶበ - አእመሮ፣
ርኅቀተ - መካን፡ ወከርሥ፤ ኀበ - ለዝንቱ፡ አሥመሮ፣
ወንጌል፡ ተራኅቆ፤ አምጣነ - ትሰብክ፡ ተፋቅሮ፡፡

ያሉት ከወለጋ ዘመዶቻቸው ርቀው በጎጃም ኖረው እዚያው የተቀበሩት የንታ ገ/ሥላሴ ናቸው፡፡ የቅኔው ምስጢር እንዲህ ነው፡- ያዕቆብና ኤሳው በአንድ ማኅፀን ነበሩ፣ ዛራና ፋሬስም እንዲሁ መንትዮች ነበሩ፡፡ ሆኖም ሽኩቻ የጀመሩት ገና በማኅፀን ሳሉ ነበር፡፡ ከማኅፀን ቀድሞ ለመውጣት (ቅድሚያ ለታላቅ ሳይባባሉ፣ ቀድሞው የመጣውን ለመለየት ፈትል ሲታሠር፣ ከኋላ ያለው ጎትቶት ቀድሞ እየመጣ) ተሻኮቱ፡፡ በአንጻሩ በኤልሳቤጥ ማኅፀን የነበረው ዮሐንስ በእመቤታችን ማኅፀን ለነበረው ጌታ ካለበት ሆኖ ሰገደ፡፡ ይሕን ስናስተውል ‹‹መራራቅ ወንጌል ናት፤ ፍቅርን ትሰብካለችና፡፡ አዎ! ዘመድ ከመቅረብ መራቅ ይሻላል - ተራኅቆ ዘመድ ይኄይስ እምተቃርቦቱ - እንላለን›› ይላሉ፡፡
እሳቸው ባሉት ላይ እማሆይ ይጨምሩበት! የኔ እማሆይ - የይልማና ዴንሳዋ - የጽላሎዋ! እማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ኪዳናት ያሳርጉት! እግረ መንገድ ‹‹ሴት ብታውቅ፣ በወንድ ያልቅ›› የሚለውን ብሂል እንገዳደረው! እህሳ እማሆይ…!

###ሐ. ከሩቅ ዘመድ፣ የቅርብ ጎረቤት!
ቅኔው ሰምና ወርቅ ነው፡፡ በሰሙ ‹‹ከሩቅ ዘመድ፣ ቅርብ ጎረቤት ይሻላል፤›› ይላል፡፡ በወርቁ ደግሞ እመቤታችን ጥንተ አብሶ የለባትም ይለናል፡፡ ከዚህ በፊት በጥንተ አብሶ ዙሪያ ተጠቅሜው ስለነበር ሙለውን ዋዜማ ቅኔ ከነትርጓሜው ከሊቀ ኅሩያን በላይ ተውሼ ላቅርበው፡-

ዋዜማ!

ሳዶቅ፡ ወብእሲቱ፤
አመ - ወለዱ፡ ሕጻነ፤ እስመ - አልቦሙ: ውሉድ፣
ለሕጻን፤ ሐቀፋ፤ ሱራፊ፡ በእድ፣
ወኢሐቀፋ፡ ዳዊት፤ ዘመደ - ሥጋሃ፡ ዋሕድ፣
አኮኑ፡ ይኄይስ፤ ቅሩብ፡ ባእድ፣
እምርኁቅ፤ ዘሥጋ፡ ዘመድ፡፡

ትርጓሜውን እንለፈው፡፡ ምስጢሩ ግን፡- “በቤት ውስጥ ሌሎች ልጆች ወይም ረዳት የሌላቸው ወላጆች ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ እናትዮዋ ሥራ ስትይዝ ባዕድ ቢሆንም የጎረቤት ሰው ሕጻንዋን ሊታቀፋት ይችላል፡፡ እንደዚሁም ሳዶቅ የተባለው ኢያቄም (ሳዶቅ የኢያቄም ሌላ ስም ነው) እና ሐና ልጅ የሆነችው ቅድስት ማርያም ሱራፊ የተባለው መልአክ ታቀፋት፤ማለት ቅድስት ማርያም እንደ መልአክ ንጽሕት ናት፡፡ ዳዊት ግን አልታቀፋትም፤ ሲባል ቅድስት ማርያም ከዳዊት ዘር ብትወለድም የዳዊት በደል የለባትም እንደሆነ ሊቅዋ አመስጥረዋል”

ከላይ ያለው ወርቁ ነው፡፡ ለዚህ ርእስ ተገቢነት ያለው ግን፡-

…አኮኑ፡ ይኄይስ፤ ቅሩብ፡ ባእድ፣
እምርኁቅ፤ ዘሥጋ፡ ዘመድ፡፡

የሚለው ነው፡፡ ለማንኛውም ልመርቅ፡-

መጪውን ዘመን ዘመድ ያድርግልን (2008ስ ውይ!ውይ!ዘመድ አልሆነንም!)፤ ዘመኑን መሰማሚያና መስማሚያ ያድርግልን፤ ‹‹ይሄን ብናገር እከሌ ምን ይለኛል፤›› ከሚል መሳቀቅ በአንጻራዊነት የተላቀቀና በቅን ልቡና፣ በኃላፊነት ስሜት፣ በተፋቅሮ መነጋገሪያ ጊዜ ይሁንልን! አሜን!!!