የዓርብ ጨዋታ፡- ዕጣ ፈንታ!

religion
philosophy
በአማንነጸረ
fate
luck

(በአማን ነጸረ) #1

በሃይማኖትም በሳይንስም ስለሰው ነጻ ፈቃድና ዕጣ ፈንታ ክርክር አለ፡፡ክርክሩ የኖረ ነው፤ደግሞም ዓለም አቀፋዊ፡፡ ፈረንጆቹ ዕጣ ፈንታን ለሃይማኖዊ ሐተታው pre-destination ፣ ለዓለማዊ ሐተታው pre-determination ሲሉ ዐየሁ (መሰል)፡፡ከወላጅ ተላላፊ ሕማም ስለመውረስ ስናወጋ፣ ባሕርየ-ሰብእ በዘር ውርስ እንደሚወሰን ስንተንተን፣ ስለ ዲ.ኤን.ኤ ምርመራ ስንሰማ፣ የአቡሎ ብሔር አባል ከድንቡሎ ብሔር በተለየ ያለውን የኑሮ ዘይቤ ስናብራራ የግለሰቡ ባሕርይና ማንነት ከቡድኑ በመነሳት አስቀድሞ ተወሰነ - pre-determination- ነው አሉ እሚባል፤(አሉ-ተባለ-ይባላል…በዘብኝሳ!)

በአስተዳደግና አስተሳሰብም ‹‹እናቷን ዐይተህ ልጅቷን አግባ፤›› ይተረታል፡፡ ወይም ‹‹ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትክን እንግርሀለሁ፡፡››፡፡ ወይም እንደሰሞኑ የሀገራችን አመዛኝ ሁኔታ ‹‹ብሔርክን ንገረኝና ባገሪቱ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ያለህን አመለካከት ልገምት፤›› አይነት ግለሰቡን ከብሔሩ ተነስተህ ቀድመህ መበየን (ይሄስ ሕመም ነው፤እግዜር ይማረን!)፡፡ በዓለማዊው የዕጣ ፈንታ አወሳሰን ትንታኔ አስቀድሞ ወሳኙ ፈጣሪ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ዘረ መል (ጂን)፣ አየር ጸባይ፣ ሥነ ልቡና፣ አስተዳደግ … የመሳሰሉ የማንነት ቀራጽያን ይጠቀሳሉ፤ በእነሱው ይቆማል፡፡ያቁማቸው አያ! አቁመናቸው ወደ የፈጣሪያችን ስም ወዳለበት እንራመድ! ወደ pre-destination ተራመድን፡፡

##1. እሱ ካለው…በቅኔና በባህል!
አጼ ኃይለ ሥላሴ ግእዝ ይሰማሉ፤ ይጠቅሳሉ፡፡በቃላቸው ይዘው ከሚጠቅሷቸው የግእዝ ሐረጎች ውስጥ የሚከተሉት ለአጼ ተክለ ጊዮርጊስ ከተደረገ ሥላሴ ቅኔ የተቀነጨቡ ሐረጋት ይገኙበታል፡፡

…እስመ-እመ-ይቤ፡ ለይኩን፤ ፈጣሪ፤ መላእክተ - ሰማይ፡ወምድር፣
ይትቀነዩ፡ ለከ፤ አርአያ - ገብር፣
ወለእመ-ይቤ፡ ኢይኩን፤ እግዚአብሔር፣
ይኤምጹ፤ አዕዳው፡ ወእግር፡፡

ይላሉ ሐረጎቹ፡፡

ትርጉሙ፡- ‹‹ፈጣሪ ‹ይሁን› ካለ የሰማይ መላእክት፣ የምድር መኳንንት እንደ ባሪያ ይገዙልሀል፤ እሱ ‹አይሆንም› ካለ ግን የገዛ እጆችህና እግሮችህም ያምጹብሀል፤›› ማለት ነው፡፡ በዕጣ ፈንታ ሳያምኑ አይቀርም! ማን ያውቃል?! ወይ ያደጉበት ባህል ተጭኗቸው ይሆናል፡፡ባህላችን እንደዚህ ማለት ይቀናዋል፤ ‹‹እሱ ካለው…! ከላይ ከታዘዘ…! ፍርጃ’ኮ ነው …! አይጣል…! የ40 ቀን እድል…! ለመከራ የጣፈው፣ቢነግድ አይተርፈው!›› ማለት ይቀናዋል፡፡ ገጣሚዎቻችንም ከዚህ ለዘመናት እንደ ባሕር የረጋ ሥነ ልቡና ጥበብ ይቀዳሉ መሰለኝ - ከበዕውቀቱ ግጥሞች እንዳየሁት!

##2. ዕጣ ፈንታ በበዕውቀቱ ስዩም ግጥሞች ውስጥ!
በግጥሞቹም፣ በእንቅልፍና ዕድሜ ልቦለዱም ውስጥ ስለነጻ ፈቃድና ስለዕጣ ፈንታ ደጋግሞ ሲናገር አየዋለሁ - በዕውቀቱ ስዩም፡፡ንግግሩ ከዓለማዊው ይልቅ ሃይማኖታዊውን ዕጣ ፈንታ የሚያጣቅስ ሆኖ ይስሰማኛል፡፡ ይሄን ኳሽ ከሥራው ጥቂት እንቆንጥርለትማ…
####ሀ. ዳዊትና ጎልያድ!

እግዜርና ዳዊት፤ አብረው ተቧደኑ፣
ብቻውን ታጠቀ፤ ጎልያድ ምስኪኑ፣
አንዳንዱ ተገዶ፤ ለሽንፈት ሲፈጠር፣
በጥቅሻ ይወድቃል፤ እንኳንስ በጠጠር፡፡

ይለናል በዕውቄ፡፡

በዚህ ግጥም ውስጥ የዳዊት ልባምነት (ወኔ)፣ ጥንካሬው (ዳዊት የዱር እንስሳትን በክርን የሚደቁስ ቀጭን ወንድ ነበር እኮ! እህ!)፣ የወንጭፉ ኃይል፣ የጎልያድ ጠላትን ዝቅ አድርጎ ገምቶ፣ ደረትን ገልብጦ፣ ግንባርን አፍጥጦ ራስን ለጠላት ማጋለጥ ለሽንፈቱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ተዘንግቷል፡፡ ወንድማችን ‹‹ጎልያድ ሲፈጥረው ለሽንፈት ነው፤›› ብሎ ደምድሟል፡፡ ለተሸናፊው ራርቶ ሳይሆን አይቀርም! ለተሸናፊ ማዘን ያለ ነው፤ በዕውቄ ግን ገዳይንም ‹‹ፍርጃ ነው!›› ሲል ነጻ ለማውጣት ይፋለማል፤ ለቃየልም ይቆምለታል፡፡

####ለ. አቤልና ቃየል!

በሰላም ሰፍሮ ሳል፤ ‹‹ምድር›› ባላት ዛፉ፣
ባዳኙ ሲመታ፤ አቤል ጫጩት ወፉ፣
ቃየን ጠጠር ነበር፤ ለባለወንጭፉ፡፡

ሲል የአቤል ገዳይ ቃየል ሳይሆን ሌላ ባለ ወንጭፍ (ምናልባት እግዚአብሔር!) እንደሆነና በግድያው ቃየል የገዳይ መሳሪያ ከመሆን ያለፈ ነጻ ፈቃድ እንዳልነበረው ይነግረናል፡፡ ስገምት ልጅ በዕውቀት፡-

ክልኤቱ፡አኃው፤ አመ-ውስተ-ቀላይ፡ወረዱ፣
አሐዱ፡ተመይጠ፤ ወኢተመይጠ፡ዐሐዱ፡፡

ተብሎ እንደ ሰፈራችን ፖ/ጣቢያ የዕለት ሁኔታ ማስመዝገቢያ በቅኔ የቀረበውን አቤቱታ በመርማሪነት እንዲያጣራ ቢመደብ፡- ቃየል አቤልን የገደለው፣ ጥሎበት ነው! አያድርስ ነው እናንተው! ምን ይባላል!፣ አቤልም የሞተው በዚህ ጥፋ ብሎት ነው - ዕጣ ፈንታ! የሚል ይመስለኛል፡፡ግምቴ በዕውቄ ለ‹‹መልክአ ሕይት›› ካለው አመለካከት ትነሣለች፡፡

####ሐ. መልክአ ሕይወት!

አዳኝ በንስሐ፤ ሰይፉ አልዶለዶመም፣
ታዳኝ በጸሎቱ፤ ካራጆቹ አልዳነም፣
ተኳሹ ቢዋልል፤ አልመታ ቢል ተኩሱ፣
ካፈሙዝ ይጠጋል፤ ዒላማው ራሱ፡፡

ብሎ የተቀኘ ሰው በቃየል ላይ ለመፍረድ የሚነሣ አይመስለኝም፡፡ ‹‹ገዳይ ሲያረፋፍድ፣ ሟች ይገሠግሳል›› የሚለውን ብሂል ይጠቅሳል እንጂ፡፡ ሌሊት በምናቤ እንዲያው ከበዕውቀቱ ጋር ባወጋ ‹የነነዌ ሕዝብ ከታዘዘ መዓት ሲድን እያየህ፣ ቀሳውስት ነጋ ጠባ ‹ከታዘዘ መቅሰፍት ይሰውረን› ሲሉ እየሰማህ› እንዲህ አትበልማ እምለው ነኝ!› ብዬ ነበር፡፡ ‹ባክህ ጓዴ! አንዴ ከታዘዘ፣ መቅሰፍቱ ወደኛ ባይመጣም እኛ ወደ መቅሰፍቱ መሄዳችን አይቀርም፤› ከማለት አይመለስም ብዬ ነገር ማብላላቱን ተውኩትና ወደ ቅዳሴዬ ገሰገስኩ፡፡

##3. ዕጣ ፈንታ በመጽሐፈ ቅዳሴ!
ቀኑ አብዷል! መቅደስም ብገባ ውቦች የመጽሐፈ ቅዳሴ ምንባባት ስለ ዕጣ ፈንታ በሚናገሩ አናቅጽ ተጊጠው አገኘሁዋቸው፡፡ ብቻ በደረቅ ንባቡ ‹‹ዕጣ ፈንታ ነው!›› ይሉና በትርጓሜ ያቃኑታል፡፡ ፍጠኑማ! የመጽሐፈ ቅዳሴን ንባብና ትርጓሜ ለማየት አትሮንስ እንዘርጋ!

###ሀ. ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት!
‹‹ውእቱሰ፡ እምቅድመ - ይግበር፡ ፈጸመ … እሱስ ሳይደረግ አስቀድሞ አወቀ … አዳምን ሳይፈጥረው ገነትን አዘጋጀ፤ የወደደውን ያገባበት ዘንድ … ሲኦልን አዘጋጀ፤ የጠላውን ያገባበት ዘንድ፤›› ይላል ደረቁ ንባብ፡፡ በደረቅ ንባብ እንዳንዳረቅ የማለዘብ ሥራ የሠሩልን መተርጉማን ‹‹እንዳትሳሳቱ!›› ይላሉ፤ ‹ጌታ ሰውን የሚወድና የሚጠላው በሕጉና በሥርዓቱ መጽናት አለመጽናቱን መሠረት አድርጎ እንጂ አስቀድሞ ለፀብና ለፍቅር የመደበው የለም፤ እዛው በመንደራችሁ! የ40 ቀን እድል ብሎ ቋንቋ በእርሱ ዘንድ አይነገርም› ይላሉ፡፡ የተረፈውን ከአትናቴዎስ ቅዳሴ ትርጓሜ እንስማ…

###ለ. ቅዳሴ አትናቴዎስ!
የአትናቴዎስ ቅዳሴ ‹‹አቤቱ ሕፃንን ካባቱ አብራክ ከፍለህ በናቱ ማኅፀን የምታሳድረው አንተ ነህ፡፡ …ልጅነትን የምታድለው አንተ ነህ፡፡ … በሆነ ሁኖ በ40 ቀን ታድለዋለህ፡፡ …ባለጸጋ፣ ድኃ ለመሆንም ቢሆን፤ ለመጽደቅም ቢሆን፣ ለመኮነንም ቢሆን …›› እያለ በጥሬ ንባቡ ያዋልለናል፡፡ መተርጉም ይጠራ! ተጠርቷል፤ ደርሷል! ይቀጥል፡- ‹‹ጽንስ ሲጸነስ፡ የወንዱና የሼቷ ዘት ተዋሕዶ ሲያበቃ ሲዋልል ይሰነብታል፤ ይረጋል፤ ሕዋሳት መብቀል ይጀምራሉ፤ የጽንሱ የሰውነት ሕዋሳት በ40 ቀን ተሠርተው (በቅለው) ይፈጸማሉ፡፡ስለዚህ የደረቅ ንባቡ ምስጢር እሚነግረን ‹በዚህ በ40 ቀን ውስጥ በተገኙ የሰውነት ሕዋሳት በጎነት ከሠራህ በጎ ይገጥምሀል፤ ክፋት ከሠራህ ክፉ ያገኝሀል፤ እንጂ የ40 ቀን እድል ብሎ ጣጣ የለም፤ ዕጣ ፈንታህ በእጅህ ነው፤ ነጻ ፈቃድ አለህ፤ ምረጥ! ባይሆን ደጉን ምረጥና ቡራኬውን ውሰድ!›› አዎ! ምረጥ ሳትደናገጥ፤ እሱ የሚናገር አስቀድሞ አዋቂነቱን! ማወቁንስ ኤጲፋንዮስ ያሳውቀን!

###ሐ. ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ!
ፈጣሪ የፍጡሩ መጨረሻ ምን እንደሆነ ያውቃል፤ ‹‹የአምሮ፡ ለጻድቅ፡ እንበለ - ይግበር ጽድቀ …ሥራውን ሣይሠራ ጻድቁን ከኃጥዕ ለይቶ ያውቀዋል፡፡›› ለዚህ ነው ኤርምያስን ‹‹ቀደስኩከ፡ እምከርሠ፡ እምከ፤›› ያለው፣‹‹ያዕቆብን ወደድኩ፣ኤሳውን ጠላሁ፤›› ሲል የተናገረው - ገና በማኅፀን ሳሉ፡፡ አዋቂ ነው! ዘመን አይገድበው፣ ግድግዳ አይከልለው! ‹‹አልቦ ዘይትኃብዖ፣ ወአልቦ ዘይሤዎሮ…›› ነው ነገሩ፡፡ቢሆንም…

##4. አስቀድሞ ማወቅ ሌላ፤ አስቀድሞ መወሰን ሌላ!
ሥላሴ አዳምን ሲፈጥሩ ገነትንና ሲዖልን ቀድመው አዘጋጅተዋል፤ ሰውየው ለፌ ወለፌ ማለቱ እንደማይቀር ስለሚያውቁ! ከፍጡራን ሁል የላቀ የምድር ፍጥረታት ገዥ አድርገው ሾሙት፤ ኋላ ለሥልጣን ጎምዥቶ ሲወድቅ ቢንፈራገጥ ሰበብ እንዳይኖረው! እስኪት (የመራቢያ አካል) አበቀሉለት፤ ኋላ በራሱ ጥፋት ሞቱን ሲጠራ ያለ ዘር እንዳይቀር! እንዲያ ስላደረጉ ግን ዕጣ ፈንታውን አስቀድመው ወስነዋል አንልም፡፡ሁሉም የሆነው በውል ነው፡፡ አለ አይደል … ቀነ ገደብ የሌለው የሊዝ ውል ነገር! (ያው ለምሳሌ እንጂ እንዲህ አይነት የሊዝ ውል የለም!) ውሉ ቀነ ገደብ አልተቀመጠበትም፡፡ብቻ የማፍረሻ (termination clause) እና የመቀጮ አንቀጽ (penalty clause) አለው፡፡ አዳም በዚህ ውል ተስማምቶ ነው ገነትን የተረከበ፡፡ ራሱ እንዳመነው ውሉን አላከበረም፡፡ውሉ ተቋረጠ፤ ተባረረ፤ መቀጮው ተግባራዊ ሆነ፡፡ (ህጹጽ ምሳሌ ነው ምሳሌውስ!)
ቢሆንም እስኪ ፍረዱ፡- አስቀድሞ የተዋዋይን መብትና ግዴታ፣ ግዴታውን ባይወጣ ሊመጣ የሚችለውን ከውል የሚመነጭ ተጠያቂነትና መቀጮ በግልጽ ያስቀመጠ ውል ሰጪ መልሶ ‹‹የውል ተቀባይን ግዴታም መሸከም ነበረበት፤›› ተባለ፤ ተወነጀለ፤ ‹‹ጌታ አስቀድሞ ወሰነ›› ማለት ይኸው ነው - ውንጀላ፡፡ ኧረ ጡር አንናገር! ባይሆን ለአዳም የተሰጠውን የችሮታ ጊዜ (grace period) ማየት አይቀልም! የላይኛው አካል እኮ ‹‹ያልኩት ካልሆነ…›› የሚል እማደል! ወላዲቴን እንዲያ የሚል ጨካኝ እማደል! መላው የነነዌ ሕዝብ ይመስክር፤ ከታዘዘ መቅሰፍት ድኖ የለም እንዴ! ሞት ከመጣበት ወዲያ ተጩዋጩኾ የ15 ዓመት የዕድሜ ቦነስ ያገኘው ሕዝቅያስም ዝም አይልም፤ (በነፍስ) ሕያው የሚሆን ምስክር ነዋ!
ጓዶች፡- የ40 ቀን እድል ብሎ ከማለቃቀስ ወይም ከስንት አንድ ጊዜ በተከሠተ አጋጣሚ ባለ አንድ እጁ አጼ ዮሐንስ፡-

ጊዜያትሂ፡አዕላፈ፤ እመ፡መከሩ፡አዕላፍ፣
አንተ፡ዘኃለይኮ፤ ወዘወሰንኮ፡ኢይተርፍ፡፡

እንዲል እያሉ ብሂል ቅኔ እየጠቀሱ እጅና እግር አጣጥፎ መቀመጥ አይበጀንም፡፡‹ዕጣ ፈንታችን ነው!› ከማለት እንደ ነነዌና እንደ ነቢዩ ሕዝቅያስ እጥፍ ዘርጋ ማለት ነው ሸጋ፤ እሱ አስቀድሞ አወቀ ማለት ወሰነ ማለት አይደለምና፡፡ በዕጣ ፈንታ ብሂል ከመታሠር እኛ እንስራ፣እሱ ይባርክ! እኛ እንፋቀር፣እሱ ይገኝ! እኛ እንጩኽ፣እሱ ይስማ! ፎርሙላው፡-

የኛ እምነትና ጥረት + የአምላክ አጋዥነት = ፍቅር - ጸጋ - በረከት ዕጣ ፈንታ!