የቆዳ ቀለምንና ዘርን ምን አገናኛቸው?


(Achamyeleh Tamiru) #1

አቻምየለህ ታምሩ

ከስር የለጠፍሁት አርቲክል ዶክተር ጸጋዬ አራርሳ የደረተው ነው። ዶክተር ጸጋዬ በዳግማዊ ምኒልክ ላይ ያለውን ጥላቻ በቃላት መግለጽ የተቸገረ ይመስላል። በዚህ አርቲክሉ ምኒልክ «ካውካሶይድ ነኝ እንጂ ኔግሮ አይደለሁም» ስላለ ጥቁር አይደለም ይለናል። ስለዚህም «ምኒልክ ጥቁር ሰው» የሚለው ዘፈን፤ «ምኒልክ ነጭን ድል የመታ የጥቁር ህዝብ ንጉስ»፤ ወዘተ መባል የለበትም ይለናል።

ዶክተር ጸጋዬ በጥላቻ ባጎነጡ የቃላት ክምሮቹም የአድዋን ድል ክብር ለማጉደፍ ያልመዘዘር አታካራ፤ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
ሆኖም ግን ዶክተሩ ይህንን ሁሉ ሲደርት አንድ ነገር ባለማስተዋሉ የጥላቻ አቅሙን አሟጦ የጻፈው ይህ ረጅም አርቲክል በአንድ ማፍረሻ ብቻ በዜሮ ተባዛ። ነገሩ እንዲህ ነው።

ዶክተር ጸጋዬ ዘርና ቀለምን መለየት አልቻለም። ካውካሶይድ ዘር ነው፤ ጥቁር ማለት ደግሞ ቀለም ነው። ካውካሶይድ የተባለ ዘር ነጭ ወይንም ጥቁር የቆዳ ቀለም ሊኖረው ይችላል። ለምሳሴ Hamites ካውካሶይድ ናቸው፤ ነገር ግን የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር ነው። በዚህም የተነሳ ሄማይቶች ጥቁር ካውካሶይድ ይባላሉ።

ዶክተር ጸጋዬ ግን ዳግማዊ ምኒልክን ያዋረደ መስሎት ዘርና ቀለም መለየት ተስኖት ካውካሶይድን ነጭ፤ ኔግሮይድን ጥቁር ብሎ ተረጎመው። ሆኖም ኔግሮይድም ሆነ ካውካሶይድ የዘር እንጅ የቀለም ልዩነቶች አይደሉም። ምኒልክ ካውካሶይድ ነኝ ቢሉም እንኳ «ነጭ ነኝ» አሉ አያሰኝም። ካውካሶይድ ጥቁር ሊሆን ይችላል፤ ኔግሮይድም ነጭ ሊሆን ይችላል። ይህንን ያላገናዘበው ዶክተር ጸጋዬ ዳግማዊ ምኒልክ «ካውካሶይድ ነኝ እንጂ ኔግሮ አይደለሁም» አለ ይልና «ነጭ እንጂ ጥቁር አይደለሁም» ብሏል በማለት የራሱን ድምዳሜ ይሰጣል። ይህ ትልቅ የግንዛቤ ስህተት ነው። የዶክተር ጸጋዬ ስህተት የሚጀምረው ኔግሮ[ይድ] የሚለውን ጥቁር ብሎ መፍታቱ ነው። ኔግሮ[ይድ] ዘር እንጂ ቀለም አይደለም። ካውካሶይድም እንደዚያው። ስለዚህ «ምኒልክ ካውካሶይድ ነኝ እንጂ ኔግሮ አይደለሁም» አለ ያለውን «ነጭ እንጂ ጥቁር አይደለሁም» ብሎ የፈታው ካለማወቅ የመጠ ስህተት ነው ማለት ነው።

እዚህ ላይ አንድ ሌላ ነገር ልጨምር። አንድ የቆዳ ቀለም ያለው ከጥቁር ወደ ነጭ ወይንም ከነጭ ወደ ጥቁር ለመለወጥ ሁለት ትውልድ ብቻ ይበቃዋል። ይህንን ያላጤኑ አንዳንድ ደነቋቁርት የኛዎቹ ንጉሰ ነገስቶች «የሰለሞን ዘር ነን» ስላሉ ብቻ ዝያቸውን «የነጭ ዘር» አድርገው ይተረጉሙታል። ይህ ግን አላዋቂነት ነው። የሰለሞን ዘር ከአንድ ትውልድ በኋላ ጥቁር ሊሆን ይችላል።
አቻምየለህ ታምሩ

ለምሳሌ ቀዳማዊ ምኒልክን እንውሰድ። የቀዳማዊ ምኒልክ አባት እስራዔላዊው ንጉስ ሰለሞን ሲሆን እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ንግስተ ሳባ እንደሆነች ይነገራል። የሰለሞንና የሳባ ልጅ ቀለሙ ባራክ ኦባማን የሚመስለው ነው። ባራክ ኦባማ «የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝደንት» ነው። በዚህ መሰረት ቀዳማዊ ምኒልክም የመጀመሪያው የሰለሞን ዘር ኢትዮጵያዊ ንጉስ ነው ማለት ነው። የሰለሞን የልጅ ልጅ የሆኑት የቀዳማዊ ምኒልክ ልጆች ደግሞ ቀለማቸው እንደ ባራክ ኦባማ ልጆች ጥቁር ይሆናል ማለት ነው። ይህ ማለት የነጩ የሰለሞን የልጅ ልጆች ጥቁር ሆኑ ማለት ነው። የሰለሞን የልጅ ልጆች ጥቁር ስለሆነ የሰለሞን ዘርነታቸውን አይለውጠውም። ለዚያም ነው ነጭ የቆዳ ቀለም ያለው ወደ ጥቁር ለመለወጥ ወይንም ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ወደ ነጭ ለመለወጥ ሁለት ያህል ትውልድ ብቻ ይበቃዋል ያልሁት።

ስለዚህ የኛዎቹ ንጉሰ ነገስቶች «የሰለሞን ዘር ነን» ቢሉ የነጭ ዘር ነን ማለታቸው አይደለም፤ የሰለሞን ዘር የሆኑት የጥቁሮቹ የነ ቀዳማዊ ምኒልክ ዘር ነን ማለታቸው እንጂ!