“ንቁም በበኅላዌነ፤ በያለንበት ጸንተን እንቁም!”


(Admin) #1

በሥነ ፍጥረት ትምህርት ከነጻ ፈቃድ አንጻር ፍጥረታት በሁለት ይከፈላሉ፤ ግእዛን ያላቸውና ግእዛን የሌላቸው ተብለው፡፡ ግእዛን የሌላቸው ፍጥረታት የሚባሉት ነጻ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው፡፡ የሚሠሩትን ሁሉ በደመነፍስ እውቀት ብቻ ይሠሩታል፤ ተግባራቸውን ተፈጥሮ እንደመራቻቸው የሚሠሩት እንጂ፣ አስበውና ተመራምረው የሚያደርጉት አይደለም፡፡ ግእዛን ያላቸው ፍጥረታት ግን የነጻ ፈቃድ ባለቤት ስለሆኑና ተመራማሪ አእምሮ ስላላቸው ሥራቸውን ሁሉ በኅያዊት ነፍስ እውቀት ይሠሩታል፡፡ እንግዲህ ብዙው አንድ፣ ብዙው አንድ እየተባለ ተቆጥሮ ከተፈጠሩት 22 ፍጥረታት ውስጥ ግእዛን ያላቸው ፍጥረታት የሚባሉት ሰውና መላእክት ብቻ ናቸው፡፡

እንደሥነ ፍጥረት መምህራን ትምህርት መላእክት የተፈጠሩት በመጀመሪያው ቀን ሲሆን፣ ሰው ደግሞ የተፈጠረው በመጨረሻው ቀን ነው፡፡ “መጀመሪያ”ና “መጨረሻ” የሚሉት አገላለጾች ደግሞ ለፈጣሪና ለፍጡራን ሲነገሩ እንደቅደም ተከተላቸው ፍጻሜ የሌላቸውና ፍጻሜ ያላቸው ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ “መጀመሪያ”ና “መጨረሻ” የሚሉት ቃላት ለፈጣሪ ሲነገሩ ለ“መጀመሪያው” መጀመሪያ የለውም፤ ለ“መጨረሻው”ም መጨረሻው አይታወቅም፡፡ ስለጊዜ ሲታሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁልጊዜም ዛሬ ብቻ ነው፤ ትናንት በእርሱ ዘንድ የለም፡፡ ሁሉን ከማወቁ የተነሣ ነገ የምንለውም ለእርሱ ዛሬ ነው፡፡ በሥነ ፍጥረት ታሪክ “መጀመሪያ ቀን” ማለትም ፈጣሪ ፍጥረታትን መፍጠር የጀመረበት ቀን ሲሆን፣ ያም እሑድ ነው፤ ለፍጥረት የመጨረሻው ቀን ደግሞ ዓርብ፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረውም መላእክት በተፈጠሩበት ዕለት ስለተከናወነ አንድ ነገር ነው፡፡

መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ተመራማሪ አእምሯቸውን ተጠቅመው ስለተፈጥሯቸው ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ “ከየት መጣን? ማንስ ፈጠረን? እርስ በርስ ተፈጣጠርንን ወይስ ሌላ ፈጣሪ አለን?” ይባባሉ ጀመር፡፡ ከመካከላቸው አንዱ መልአክም (“ሳጥናኤል” ይባል የነበረው) በቁመትም በክብርም ከፍ ያለ ነበርና “እኔ ፈጣሪ ነኝ!” ልበል ብሎ አሰበ፤ አስቦም አልቀረ “እኔ ፈጣሪ ነኝ!” በማለት አሰምቶ ተናገረ፡፡ ይህንን እንዲል ያደረገውም ቀና ብሎ ቢያይ የሚበልጠው የሌለ ስለመሰለው፣ ዝቅ ብሎ ቢመለከትም ሁሉም ከእርሱ በታች ሆነው ስለታዩት ነበር፡፡

በዚህ መልአክ ትዕቢት የተነሣም በመላእክት ከተማ ጽኑ ሁከት ተፈጠረ፡፡ በአንዱ ነገድ ስህተት የተነሣም ሌሎቹ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ታወኩ፡፡ እውነታው እስኪገለጥና የእርሱ ምንነት እስኪታወቅ ድረስም ሳጥናኤል በመላእክት መካከል ክፍፍል መፍጠር ችሎ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ “እውነት ነው፤ ፈጣሪያችን እርሱ ነው” አሉ፤ ሌሎቹ ግን “አይ እርሱ አልፈጠረንም” የሚል የተቃውሞ ቃል አሰሙ፤ አንዳንዶች ደግሞ “ፈጥሮን ይሆንን-አልፈጠረን ይሆንን?” በሚል ሀሳብ ዋለሉ፡፡ መቃወምም ሆነ መደገፍ የነጻ ፈቃድ ውጤቶች ስለሆኑ መላእክት ሀሳባቸውን በድፍረት ገለጹ፡፡ እርግጠኛ የሆነ ማስረጃ እስኪገኝ ድረስም መጠራጠር ተፈጥሯዊ ነው፤ ግእዛን ባላቸው ፍጡራን ዘንድ፡፡

መላእክት እንዲህ በሦስት ጎራ ተከፍለው ሲዋልሉ ሳሉ ነው ዛሬ መታሰቢያው የሚደረግለት ቅዱስ ገብርኤል የተባለው መልአክ ከላይ በርእሱ የተጠቀምነውን ኃይለ ቃል የተናገረው፤ “አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በያለንበት ጸንተን እንቁም፡፡” ብሎ፡፡ የመልአኩን ቃል ምክንያት አድርጎም እግዚአብሔር ለጽኑዐኑ መላእክት ተገለጠላቸው፡፡ እውነተኛው አምላክ ለጽኑዐኑ ሲገለጥም “ፈጣሪ ነኝ” ያለው ያ ክፉ መልአክ ርጉም፣ ውዱቅ ተብሎ ከሥልጣኑ ተሻረ፤ ወደእመቀ እመቃትም ወረደ፡፡

የሳጥናኤልን ቅድመ ውድቀት ክብርና ምን ያህል ለአምላክ የቀረበ እንደነበር ሲገልጹ “ቅሩበ እግዚአብሔር፣ አኀዜ መንጦላዕት ነበር” ይሉታል፤ መምህራኑ፡፡ “ለእግዜር የቀረበ፣ መጋረጃ የሚይዝ” ማለትም ባለሟልነቱን መግለጽ እንጂ በፈጣሪ ዘንድ የሚከፈት የሚዘጋ ኖሮ አይደለም፡፡ ፈጣሪ አለመሆኑ ከተነቃበት በኋላ ሽንፈቱን መቀበል ያቃተው ዲያብሎስ ግን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከቅዱሳን መላእክት ጋር ጦርነት ገጠመ፡፡ በጦርነቱም ብቻውን ሳይሆን ደጋፊዎችም ስለነበሩት ለጊዜውም ቢሆን ድል የተቀዳጀ መስሎት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ክብሩን ተገፎ በኃይሉ የተመካው ያ ሰይጣን የእግዚአብሔር ርዳታ ያለበትን የመላእክትን ኃይል መቋቋም አልተቻለውም፤ ተሸነፈ፡፡ ለእርሱ ግን ወደላይ እየወጣ ይመስለው ነበርና በትዕቢቱ ጸንቶ “እግዚአብሔር ከነሠራዊቱ ዙፋኑን ይዞ ወደላይ ሸሸ” ይል ነበር፡፡ እንዲህ ነው ሽንፈትን አለመቀበል፤ ሲወርዱ እየወጡ ያስመስላልና፡፡

እንደመምህራኑ ትምህርት መላእክት የሚያሸንፉበትን ኃይል ያገኙትና ሰይጣንንም ያሸነፉት በያሉበት ጸንተው ስለቆሙ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ፈጣሪ ነኝ ባይነቱን ካልተቀበሉት መላእክት ወገን የሆነው የቅዱስ ገብርኤል አጽናኝ ቃል አስፈላጊያቸው ነበር፤ “ንቁም በበኅላዌነ፤ በያለንበት ጸንተን እንቁም!” የሚለው፡፡ ይህ ቃል ዛሬም ያስፈልገናል፡፡

እውነቱን ለመናገር ለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስፈልገው ይህ የቅዱስ ገብርኤል ቃል ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶች “የፈጠርናችሁ እኛ ነን፤ ያለእኛ ዋጋ የላችሁም፤ አለቀላችሁ! የሚሻለው የእኛን ፈጣሪነት መቀበል ነው፡፡” ይሉናል፡፡ “ልንገድልም ልናድንም ሥልጣን ያለን እኛ ነን::” ይሉናል፡፡ ከውሸት በቀር መፍጠር ባይችሉም መግደል የ“ባሕሪያቸው” እንደሆነ ግን እያየን ነው፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳንዶች የእነዚህን አካላት “ፈጣሪነት” ለማመንም ላለማመንም ተቸግረው መንታ መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡ “ለፍጡራኑ እንዲህ የሚያደርግ ፈጣሪ ሊኖር አይችልም!” በማለት የተቃወሙት ደግሞ በእስራትና በግርፋት መከራቸውን ያያሉ፤ እውነተኛው ፈጣሪ ራሱን እስኪገልጽላቸው ድረስ በየቀኑ ይገደላሉ፡፡ ለእኩያኑ እድሜ መርዘም ምክንያቶቹ ግን ለ“ፈጣሪነታቸው” የተገዙት “ምእመናን” ናቸው፡፡

ስለዚህም አሁን የሚያስፈልገን ከሁከት የሚያረጋጋ የቅዱስ ገብርኤል ቃል ነው፡፡ ይህንን አጽናኝ ቃልም ከሃይማኖት አባቶች እንጠብቃለን፤ ይህንን ቃል ከምሁራን እንጠብቃለን፤ ይህንን ቃል የብዙኀን ማህል መንገድ ላይ መቆም ከሚያሳስባቸው ሀገር ወዳድ ዜጎች እንጠብቃለን፤ ይህንን ቃል ከእውነተኛ ፖለቲከኞች እንጠብቃለን፤ ይህንን ቃል ከደገኛ አርቲስቶች እንጠብቃለን፤ ይህንን አጽናኝ ቃል ከጋዜጠኞች እንጠብቃለን፡፡ “ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ፤ ፈጣሪያችንን እስክናገኘው ድርስ በያለንበት ጸንተን እንቁም፡፡” ፍትሕ እስኪገኝ ድረስ …፡፡

የቤተ ክርስቲያን መምህራን “ሰማእታት ሰይፍንና ስለትን፣ ደናግል መነኮሳት ፍትወታት እኩያትን ድል ለመንሣት ሲታገሉ ለምን ይኖራሉ?” ለሚለው ጥያቄ “ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት ነዋ!” በሚል ይመልሳሉ፡፡ ይህንንም “መንግሥተ ሰማያት እንጂ ጌታ ራሱ ነው፤ ሌላን አለ? ራሱን ወርሰውት ይኖራሉ፡፡” በማለት ያስተምራሉ፡፡ “መንግሥተ ሰማያት ሕገ ወንጌል፣ ሕገ ወንጌል ተስፋ፣ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ …” እንዲሉ፤ በትርጓሜ ወንጌል፡፡

የወቅቱ የኢትዮጵያውያን ጥያቄስ ደገኛ መሪን ፍለጋ እንጂ ሌላን አለ? ፈጣሪም፣ በሠለስቱ ምእት ቅዳሴ እንደተጠቀሰ፣ “እንደማይሰማ ዝም ይላል፤ እንደማይሰጥ ያዘገያል፡፡” ዴሞክራሲ ማለት “ከሕዝብ፣ ለሕዝብ በሕዝብ የሆነ አስተዳደር ነው” እንዳለ፣ አብርሃም ሊንከን፡፡ እስከዚያው ግን “ንቁም በበኅላዌነ፤ በያለንበት ጸንተን እንቁም!”

በያለንበት ማለት የጀመርነው የመብት ጥያቄ ነው፤ በያለንበት ማለት የፍትሐዊነት ጥያቄ ነው፤ በያለንበት ማለት የሰላም ጥያቄያችን ነው፡፡ በያለንበት እውነተኛ መሪን የመፈለግ፣ ፍትሐዊ መሪን የመፈለግ፣ ክብር ሰጥቶ የሚከበር መሪን የመፈለግ እንጂ፣ ያለንበት ሽብር መፍጠር አይደለም፡፡ በፍጹም እንዲህ አይደለም! የቤታችን ሰዎች ጤና ሲነሱን የውጪ አካላት ተስፋ ሊሆኑን ይችላሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ የሚበጀው ቤትን ማስተካከል ነው፤ ቤቱን ለማስተካከል ደግሞ በያለንበት የድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልገናል፤ ጸንተን፡፡ በመሆኑም ያለፉትን ስህተቶች የምንደመስሰው፣ ከሚመጡትም ስህተቶችም የምንጠበቀው (“ለዘኀለፈ ሥርየት ወለዘይመጽእ ዕቅበት” እንዲሉ) ባለንበት ስንጸና እንጂ በሌለንበት ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ሰዉ ሁሉ በያለበት ጸንቶ ከቆመ ግን የማይቻል ነገር አይኖርም፤ የማይስተካከል ነገር የለም፡፡

ቸር ያሰማን፡፡
ነሐሴ 19/2008 ዓ.ም