የቡሔ(የደብረ ታቦር) በዓል ትርጓሜና አከባበር


(Admin) #1

ቡሔ ተብሎ በሐመሩ’ሐ’ ኀምስ ፊደል ሲፃፍ ደስታ፣ፍስሃ ማለት ይሆናል። ይኸውም “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” መዝ 88፡12 ተብሎ የተነገረው የትንቢትን ቃል መሰረት ያደረገ ነው። በታቦር የተገለጠው መለኮታዊ ብርሃን እሥስ አርሞንኤም ተራራ ታይቷልና ነው። ለዚህም ነው ሌሊቱ እንደ መዓልት ስላበራ እረኞች ወደ ቤታቸው ያልገቡት።

አንድም ‘ሐ’ የሰላምታና የቡራኬ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ፍስሃ፣ ሰላም” የሚል ነው። ይኸውም እረኞች በሚያት ብርሃን በደስታ ተሞልተው ስለቀሩ ወላጆቻቸው የሚበሉትን ይዘው ሄደው “በሓ” ብለዋቸዋል። “እንዴት ዋልክ ፣ ጤና ይስጥህ፣ ደስታ ሰላም ለእናንተ ይሁን፣ ጠላትህን ያውድቅ ፣ቢሰኛህን ያርክ” ማለት ነው። አንድም ቡሔ ወላጆች ልጆቻቸውን (እረኞችን) ብርሃናዊውን ክስተት “ምንድነው?” ብለው ቢጠይቋቸው “ብሔ” ብለዋል። ይኸውም በእብራይስጥ ቋንቋ “አምላክ” ማለት ነው።

ሐዋርያት ብርሃነ መለኮቱ ስለተገለጠላቸው እረኞችም በብርሃኑ ሲቸዋወቱ በማምሸታቸው የደብረ ታቦር በዓል የደቀመዛሙርትና የእረኞች በዓል ይባላል። በሃገራችንም ልጆች (እረኞች) ከየዘመዶቻቸው፣ ከወላጆቻቸው የተሰጣቸውን ሙልሙል ዳቦ ወይም ህብስት በህብረት በመመገብና ከበዓሉ ቀድመው(ገምደው) ያዘጋጁትን ጅራፍ በማጮህ የችቦ ማብራት በዓሉን ያከብሩታል። ይኸውም ቢሆን ሃይማኖታዊ ትርጓሜ ያለው እንጂ በዘልማድ የሚደረግ አይደለም።

ሙልሙል ዳቦ(ህብስቱን) በታቦር ዙሪያ ስለነበሩ እረኞች ወላጆች ምግባቸውን ይዘው መሄዳቸውን ያመለክታል። አንድም ህብስቱ ምሳሌነቱ ለክርስቶስ ነው። “አነ ውእቱ ህብስተ ህይወት ዘወረደ እምሰማያት፤ እኔ ከሰማይ የወረድኩ የህይወት እንጀራ ነኝ” እንዳለ ዮሃ 6፡32

የጅራፍ ጩኸትና ማስደንገጡ ሶስቱ አዕማደ ሐዋርያት(ጴጥሮስ፣ያዕቆብና ዮሃንስ) በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያመለክታል። የጅራፉም ድምፅ በየተራራውና በአፋፍ ላይ እንዲጮህ ይደረጋል እንጂ እንደዘመኑ በየመንደሩ ሰው ለማወክ በርችት ከትውፊታችን ውጪ በሆነ መልኩ በማከናወን የሚገለፅ አለመሆኑን ልብ ይሏል።

ሌላው በዚህ በዓል የሚከናወነው በዜማ የታጀበ ጭፈራ ነው “ሆያ ሆዬ” እየተባለ ይጨፈራል። ይህ ቃል “ጌታይ ሆይ እመቤቴ ሆይ” እያሉ አባወራውንና እማወራዋን የሚያከብሩበትንና የሚያቆላምጡበት የፍቅር አጠራር ነው እንጂ ጥርጉም የለሽ ቃል አይደለም።ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓሉን የሚያወሱ የግጥሞች ስብሰባም በአንድነት ይነገርበታል።