የዓርብ ጨዋታ፡- የክረምት ጓዝና ቅኔያት…ከ‹‹ለፌ፡ወለፌ›› ሐተታዎች ጋር!


(በአማን ነጸረ) #1

ክረምት ቤቱን ሊሠራ ነው፡፡የ3 ወር መኖሪያውን በጭቃ ሊሠራ ነው፡፡‹ዝግጅቱ ተጠናቋል› ነው እሚባል፡፡ያዩ ናቸው የነገሩን፡፡ሕዝብ ተሰባስቦ ለጌታው ክረምት ቤት ግንባታ ጭቃ ሲረግጥ ያስተዋሉ እንዲህ ሲሉ ጠቆሙን፡-

ቤተ-ፍጡራን፡ክረምት፤ከመ-ተወጥነ፡ተአምረ፣
ኵሉ፡ሕዝብ፤እስመ-ይረግጽ፡ጽቡረ፡፡

ለክረምት የቤት ግንባታ ቅ/ያሬድ ዕርገትንና ገሪማን ተሰናብቶ መጥቶ ሲያዜም ተሰማ፡፡‹‹የዝናብ ኮቴ ተሰማ … ደምጸ:እገሪሁ:ለዝናም›› ማለቱን ተረዳን፡፡መስከረም 26 ደርሶ ‹‹ኀለፈ፡ክረምት፤ቆመ፡በረከት›› እስኪባል ድረስ የቅ/ያሬድ ዝማሬ በክረምት ዙሪያ ይሽከረከራል፡፡ኳኳታ፣ጉርምርምታ፣ዜማና በረከት የማይለየው ክረምት የሚሉት ጉድ ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ፡-‹‹ከርመ=ከረመ፡፡ክረምት=መክረም፡፡ደመናውን፣ጉሙን፣ዝናሙን፣ጭጋጉን፣ጭቃውን፣እርሻውን፣ጉልጓሎውን፣የጎመን ቁልሉን (‹‹…ሰኔ፡አቆለቆለ፤በግማሽ፡እንጀራ፡ጎመን ተቆለለ›› እንዲል ጎጄ!)፣ማዕበሉን፣ውሃ ሙላቱን፣ረሀቡን፣ቁሩን…ንንን…ኑን…አልፎ የምድርን ልምላሜ ተስፋ በማድረግ ከሰኔ 25_መስከረም 25 ድረስ ከርሞ መገኘት–ክረምት!›› ይሏል!

ባላገር ‹‹እንዴት ከረምክ፤እንዴት ከረማችሁ›› የሚለውን ቃል ለሌላ ወቅት አይጠቀምበትም፤ለክረምት ብቻ ነው፤ሰላምታው ለሌላ ወቅት ሲውል የቋንቋ ጸያፍ አድርጎ ያሽሟጥጠዋል፡፡ክረምት ጓዙ ብዙ ነው፡፡ክረምት ዓለም ነው፡፡ሰማይና ምድር ዓለማቸውን የሚቀጩበት፡፡ክረምት ቢጨፈግግም በውስጡ ወፍራም ተስፋ አለ፡፡ክረምት ቢያስደገድግም፣ቢያስገመግምም ይገባዋል፤ጌታ ነው፡፡

##1. ክረምት ጌታ ነው!

በላይ፣በሰማያት፣መንበሩን በኢዮር አድርጓል፡፡የቤቱ ጠፈር/ኮርኒስ ‹‹ሀኖስ›› የተባለ የውሃ ጂፕሰም ነው፡፡መጓጓዣው በግርማ የሚርመሰመስ የሰማየ-ሰማይ ደመና፡፡እናወድሰዋለን!ይሄን ሁሉ የምንለው አንድዬን ነው፡፡እሱን ለመፎከካር የሚቃጣው ጌታ አለ–ክረምት!እኔ አላልኩም! ክረምትን ‹‹እግዚእ…ጌታ!›› የሚሉት ‹‹ያለመከሰስ መብት ያላቸው›› ባለቅኔዎች ናቸው፡፡

…ለእግዚአ-ዝናም፡ክረምት፤ዘዲበ-ኢዮር፡መንበሩ፣
እስመ-እንዘ-ማይ፡ጠፈረ-ቤቱ፤ደመና፡መንኰራኩሩ፣…

ያሉት (ከመድኃኔዓለም ጋር አወዳድረው) እነሱ ናቸው፡፡ይሉታል፡፡‹‹እግዚአ-ውላጤ ክረምት…የለውጡ ጌታ!›› ይሉታል!ይሉታል! ምድርን ሽፍን…ፍን አድርጎ በማዕበል፣በልምላሜ፣በደመና ሲከድናት እያዩ!

##2. ደረሰ ክረምት … እቃቃ እናጫውት!

ጥቂት እንኳሽ!ክረምት አይደል!ድጥ ነው፤ጭቃ ነው!ልጅነታችንን እንዘክረው!ሰማይና ምድርን እቃ-እቃ…እናጫውታቸው!ባልና ሚስት ይሁኑ፡፡ሰማይ ባል፣ምድር ሚስት!ደመና ብርድ ልብስ!ጨለመ፡፡ተኙ፡፡አትዩአቸው፡፡ያፍራሉ፡፡ ቆይ-ቆይ!እህ!(እንዴ!ሆ!)እረ!ሰማይ ጠብ አደረገ!ልጆቹ ተበላሽተዋል!ጉድ!ጉድ!ጉድ!ምድር አረገዘች!እረ ይዛለች መሰል!አምሮባታል!በዚህ እድሜዋ!እረረረ!ህም!ቁመቷ ሽቅብ ባይነሳ እንጂ እድሜዋ መች የዋዛ!እዋ!ዘር ቋጥራለች ለካ!ማኅፀኗ ለምልሟል!አይይ!ለዚያ ለሰማይ ራሷን ጣለች!በበጋ ስትንቀለቀል በክረምት ሰማይ ተደፋባት!ኑማ በዘአምላኪየ ቅኔ እንማት፡-

ምድረ-ውርዝውና፡ተአውቀት፤ከመ-ኢኰነት፡ለርእሳ፣
ሰማይ፤አምጣነ-ተከድነ፤ወኰነ፡መልበሳ፣
ዘርዐ-ልምላሜ፡ፍጥረት፤አመ-ተአቁረ፡በከርሣ፡፡

ይሄን ሁሉ ያደረገ ደመና ነው፡፡ከላይ ከልሎ ምድርና ሰማይን አኳሻቸው(‹‹አገናኛቸው›› እንዳልል፣እንዴት?የት?በምን ሁኔታ ‹‹ተገናኙ››?ምን አይነት ‹‹ግንኙነት›› ነው ያገናኛቸው?የመሳሰሉ ጥያቄዎች ፈርቼ ነው !)! ውይ!ይሄ ደመና ግንባሩን አጥቁሮ አስወሸከተኝ!ምነ እንደ ጉም ብን አድርጎ ቢያጠፋው!

##3. ጉም!

ጉም የደመና ቅርብ ዘመድ ነው፡፡ሥራው ማመላለስ!ያመላልሳል፡፡የሰማዩ ባለሥልጣን ተላላኪ ነው፡፡ትነቷን (evaporation) ሁሉ ከየውቅያኖስ እየጨለፈ መልሶ ከሰማይ ያወርዳታል–ውሃ ቅዳ፣ውሃ መልስ!አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲያ ሲያደርግ ዐይቶት በዜማ፡-

…በተነ-ጊሜ፡ረቂቅ፤ዘየዐቁሮ፡ለማይ፣
ያዐርጎ፤እምቀላይ፣
ወያወርዶ፤እምኑኀ-ሰማይ፡፡

ብሎ በአራራይ የለሆሳስ ዜማ አማው፡፡ዜማው የታይታ ሳይሆን የግርምት ነው!አባ ጊዮርጊስ የበቃ መምህር እንጂ የክረምት ነጭ ጉም አይደል በየተራራው ተከምሮ ልታይ-ልታይ የሚል!ጉም የሚሉት ቀሊለ-እግር አናቱን ነጭ አድርጎ (ቢከፍቱት ተልባ!) ከሩቅ ሲታይ የካሕን ጥምጥም በመምስሉ ተማሪ ተቀኘበት፤ከአናቱ ባዘቶ መስሎ ወጣቱን ክረምት ሽማግሌ አስመስለ ብሎ ተሜ ተቀኘበት፡-

ደብረ-ከርም፡ይመስል፤ካሕነ-ብዙኅ፡ዕድሜ፣
እስመ-ዲበ-ርእሱ፡ይጠውም፤ፀዐዳ፤ሐሚለተ-ርእስ፡ጊሜ፡፡

##4. መምሬ ቢተውና ማዕበሉ!

የካሕን ወግ ከተነሳ የመምሬ ቢተውን ጉዳይ ሳናወሳ ማለፍ አያኗኑርም፡፡ቄስ ቢተው ያገራችን ቄስ ነበሩ፡፡ዝክርና ተዝካር አለ ከተባሉ 7 ወንዝ ያቋርጣሉ ተብለው ይታማሉ፡፡አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፡፡ቄስ ቢተው የክረምት ዝክር ሰሙ፡፡ገሰገሱ፡፡ወንዙ ሞልቷል፡፡የፈለገ ይሙላ!ድግስ እኮ ነው!ልብሳቸውን አወላልቀው፣ጋቢያቸውን አውርደው ሁሉንም አልባስ ደግልለው በአናታቻው ይዘው በቁም ዋና ወንዙን መሻገር ጀመሩ፡፡ወይኔ!ማዕበል መጣባቸው!አላጋቸው!ተላግተው-ተላግተው ነፍሳቸውን አተረፉ፡፡ባሕሩን ተሻገሩ፡፡አልባሶቻቸው ግን በማዕበል ተወሰዱ፡፡ባሻገር ሆኖ ማዕበል ሲያንገላታቸው ያየ ባላገር ሩጦ ሄዶ ባደፈ ጋቢ እርቃናቸውን ሸፈነላቸው፡፡ተሜ ይሄን ሰማ፡፡ኳሸ! ‹‹ዕምነት ካለ በባሕር መራመድ እንደሚቻል ከክርስቶስ የተረዳው መምሬ ቢተው መክፈልቱን መታመኛ አድርጎ ባሕሩን ተራመደበት›› ሲል ኳሸ፡-

መምሬ-ቢተው፡ዴገነ፤እንተ-ክርስቶስ፡አሰረ፣
በተአምኖ፡መክፈልት፤አምጣነ-ገሠጸ፡ባሕረ፡፡

##5. የቅኔ ተማሪ!

ፀደይ፣በጋ፣በልግ፣ክረምት የዓመቱ አዝማናት መቁጠሪያ ናቸው፤12ቱን ወራት ለ4 ተካፍለው ይፈራረቃሉ፡፡በቅኔ ቤትም አዝማናት (ሴሚስተርስ/ወሰነ-ትምህርቶች) አሉ፡፡ፅጌ፣ስብከት፣ዓቢይ ጾም፣ክረምት ይባላሉ፡፡ለቅኔ መቁጠሪያ የተመቹ ወቅቶች ናቸው፡፡ከእነዚህ ውስጥ ክረምት ይለያል፡፡ገበሬ እጁ ያጥራል፡፡ቁራሽ ለመስጠት እጁ ያጥራል–ለራሱም በጎመን ነው የሚወተረተር፡፡ተሜ ይሕን የማያውቅ ድኩመ-ኅሊና አይደለም፡፡በዘመነ-ፋሲካ ባጭር ታጥቆ የጾም-ከፍስክ ሳይለይ ስንቁን ያጠራቅማል፡፡‹‹ኮፊዳ ውስጥ የገባ እህል ጾም አያሰገድፍም›› ብሂሉ ነው፡፡የለመነውን ፍርፋሪ እያሰጣ፣እየወቀጠ ጉሽጉሽት አበጅቶ ኮቸሮውን (ይከዝናል) ያኖራል፡፡ ክረምት ሲገባ እሷን አንዳችም ማጣፈጫ ባልተጨመረባት ብረት ድስት በተሞቀች ውሃ ላይ ጭብጥ ሙሉ ዘግኖ ብን ያደርግባታል፡፡አይቸኩልም፡፡ከድኖ ያቆያታል፡፡ሚጢጢዋ የተወቀጠች ኮቸሮ ሽቅብ ተነፍታ ብረት ድስቱን ታስጨንቃለች፡፡ያን ጊዜ ይሰየምባታል፡፡የክረምትን ቁር እሷን ጋሻ አድርጎ ሲያበቃ በደበሎው ተጠቅልሎ ክረምቱን ከነጎድጓዱ ጋር ‹‹አንጎደጎደ፡ዘንም፤ሠረገላ-ራማ፡ወኢዮር…›› እያለ ያሳልፈዋል፤ይቀኝበታል፡፡እንዲህ የሚያደርግ ልባም ተማሪ ነው፡፡ሰነፉማ ወይ በጊዜ ወደ ወላጆቹ ሂዶ ከነሱ ተጋግዞ አላሳለፈ፣ወይ ኮቸሮ ከዝኖ በቅጡ አልተማረ፣ረሀብ ሲሞሸልቀው ከረምቱን በመስለምለም (ሃይበርኔት-hibernate-አድርጎ ብንለውስ!) እንዳይሻገሩ ሆኖ ይሻገረዋል፡፡

…ረሀብሂ፡ገጸ-ወጨፎ፤በገባ-ጊዜ፡ካንጀቴ፣
ንዑ፡ክዳናትየ፤እናቴ፡ወአባቴ፣…

እያለ፣እየተንጠራወዘ!ይዞት ይሂድ አያ!ይሄ ድኩም!እንደ ወይን፣እንደ በለስ፣እንደ አሽክት፣እንደ ዶግ፣እንደ ችፍርግ፣የክረምት ልምላሜ ሳይታደል ጠውልጎ እንደምንም ለደብረ ታቦር ይደርሳል!

##6. ዕፀዋት!

ወይን፣በለስ፣ችፍርግ(በግእዝ አቃኒ)፣ዶግ(በግእዝ ራምኖን)፣አሽክት(ሁስጱ)፣አከያ(ጳውቄና?)…የመሳሰሉ ዕፀዋት በክረምት ይደርቃሉ፤አይለመልሙም፡፡የባለቅኔዎች ትኩረት እነሱ ናቸው፡፡በክረምት አብዝቶ ስለልምላሜ መቀኘት ‹‹ክሊሼ›› ነው–የክረምት ልምላሜ አያስደንቅማ፤የሚያስደንቀው ድርቀቱ፡፡በክረምት የሚለመልሙና የማይለመልሙ ዕፀዋት ብጥር ተደርገው ይታወቃሉ፡፡ሕይወት የሚዘራውንና የማይዘራውን መለየት መች ከበዳቸው አበው!‹‹ዕፀው(ዕፀዋት) ሕይወት አላቸው›› የሚለው ትምህርት በ4ኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስ ብቻ የሚገኝ እንዳይመስለን!በጉባኤ ቤትም ይታወቃል!ባሕርያቸው ከ4ቱ ባሕርያተ-ሥጋ ተነጻጽሮ ስለነሱ በትውፊታችን የሚባለውን አክሲማሮስ በገጽ149 እማይነግረን!ንሳማ ግለጠው አትሮንሱን፡-

‹‹…አዝርዕት፣አትክልት፣ዕፀዋትስ ደመ-ነፍስ አላቸውን፤ቢሉ አዎን አላቸው፡፡ሁሉም በየግብሩ የማይዋለድ የማይራባ የለም፤አዝርዕቱም አትክልቱም ዕፀዋቱም በተዘሩ በተተከሉ ጊዜ በእግራቸው አርባ፣ሃምሳ ይወልዳሉ፡፡በራሳቸው መቶ፣ሁለት መቶ ያፈራሉ፡፡በነፋስነታቸው ይናወጣሉ፡፡በእሳትነታቸው እንጨት ለእንጨት ባሳበቋቸው ጊዜ እሳት ይወጣቸዋል፡፡በውሃነታቸው በብረት ቢወጓቸው ደም፣ውሃ፣ወተት፣ይፈስሳቸዋል፡፡በመሬትነታቸው ያድጋሉ፣ይገዝፋሉ/ይወፍራሉ፣ያብባሉ፣ያፈራሉ፡፡በምሳር ተቆርጠው በወደቁም ጊዜ ይደርቃሉ(ይሞታሉ)፣ይፈርሳሉ፣ይበሰብሳሉ፣አፈር-ትቢያ ይሆናሉ፡፡››

እህሳ!በገጠር የቤ/ክ አፀድ በዕፀዋት መከበቡ ሕይወትን የመቀጠል ተምሳሌት የሆነው የዕፀዋት ልምላሜ በዐፅመ-ምውታን ላይ፣በመቃብራቸው ስለሚተከል አደል!ሟች መቃብር ላይ ለምለም ተክል ስታይ የሕያውነት መንፈስህ ያብባል!የተከልከው ወይን ከሆነና በክረምት ካልለመለመ አደራህን!ተስፋ አትቁረጥ፤ልማዱ ነው፡፡ወይን ከዕፀዋት ተለይቶ በክረምት ለምጥ የመታው መስሎ ቅጠሉ ይረግፋል፡፡ለዚህ ነው፡-

እስራኤል፡ዕፀው፤አውጽእዎ፤እማኅበሮሙ፡ልምላሜ፣
ለእንተ-ደወየ፡ወይን፤በለምጸ-ከናፍር፡ጊሜ፡፡

የሚባል፡፡በዚህች ቅኔ እያንጎራጎርክ ፀደይን ጠብቅ!ጥረትህ አይጓደል! ጥረትህ እግረ መንገድ ለተፈጥሮም ይተርፋላ!እረግ!‹‹አካባቢ ጥበቃ…›› እያሉ መጮህ ለባለቅኔዎችም እኮ ብርቅ አይደለም!ወላዲቴን!ብርቅ አይደለም!ይኸው፡- ዕፀዋትና ዝናማት ያላቸውን ተዘምዶ የሚያጠቃቅስ ጉባኤ ቃና፡፡ምስጢሩ በአንድ ዐ/ነገር ሲጠቃለል ‹‹ወዳጄ!የሰማይ ጉድለት፣ምድርን በዕፀዋት ስትከድናት ይሞላል›› የሚል ነው፤ዕፀዋት ካሉ፣ዝናማት አሉ!የዝናም መውረድ-መቆም በዕፀዋት ነው!

ጽድቅ፡ውእቱ፤አውርዶ፤ወአቅሞ-ዝናም፡በዕፅ፣
በተኪለ-ዕፀው፡ይመልእ፤አኰኑ፤ዘዝናመ-ሰማይ፡ሕፀፅ፡፡

ዝናሙን በሚሻበት ቦታ ያዝንምልን፤ውሆችን እስከ ወሰናቸው ይምላልን፤የተዘራውን ያስምርልን፤ክረምቱን የበረከት (በኤልኒኖ የማይሸነፍ!) ያድርግልን!አሜን!!!

ምንጭ -

  • የተለመዱት 2ኛ እና 3ኛ የግእዝ ቅኔያት መድብሎች

  • የምወዳቸው ኳሾቹ ጓደኞቼ

  • የግል ትዝታዎቼና ቅኔያት

ክረምት በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ቀለማት ስላለው ሥፍራና አከፋፈል ቁምነገር ለማግኘት እልፍ እንበል፤ ወዲህ http://eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1507-2014-07-02-17-04-52