ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ በ‹‹ያ!ትውልድ›› መካከል … ‹‹ሞትህ ደጅ አደረ››!


(በአማን ነጸረ) #1

በአማን ነጸረ

የአቡነ ቴዎፍሎስ ዝክረ-ሥምዕ በቤተ ክህነቱም በአዲሱ ትውልድም ዘንድ እየተዘነጋ ሄደ፡፡ እኛ ስንዘነጋው ታሪካቸው በቆናጽላን (ተሐድሶዎች) እንዳልሆነ-እንዳልሆነ ተተረከ፡፡ የአቡነ ቴዎፍሎስን በመሥዋዕትነት የከበረ ታሪክ የቤ/ክ ታሪክ አድርጎ ለማየት ፍላጎት ጠፋ፤ ሰቆቃቸው የሚዲያ ሽፋን ተነፈገ፡፡ እንዲያ ተሰማኝ! ይሕን ሁሉ ችለን ሕመማችንን እንዳናስታምም ወዲህ ከቤተ ክህነት፣ ወዲያ ከአብዮታውያን ወገን ያሉ ትሩፋን አበው ጭራሽ አጽመ-ቴዎፍሎስን በግፍ በወደቀበት እንበለ-ርኅራኄ አነወሩ፡፡ ሲሻቸው ለቀ.ኃ.ሥ ተቆርቋሪ መስለው፣ ሲሻቸው የሲሶ ግዛትን ተረክ ከለላ በማድረግ ከ2 ወገን በሚወረወር የብዕር ፍላጻ መቃብሩን እየፈለሱ በወደቀበት አለሳርፍ አሉት፡፡ መንበሩን በግፍ ከለቀቀ 40 ዓመት የደፈነው ግፉዕ እረፍት አጣ፡፡ አላስተኛ አሉት፡፡ ዘለግ ያለችውና መቼቷ ከ1953-1971 ዓ.ም የሆነው የዚህች ክታብ ‹ምክንያተ-ጽሕፈት› ይኸው ነው–ሕማሙ፡፡ የሚከተሉት አርእስት ለነዚህ ዐፅመ-ቴዎፍሎስን እንቅልፍ ለሚነሱ ልብ ሰባሪ ከሳሾች ‹‹እናንት የዛሬ ሕያዋን! ስለ ጉልበታችሁ አምላክ፤ ሟች ሞቱን ይሙትበት፤ ዐፅሙን ሰላም አትንሱ! ›› ለማለት ያህል ከማስረጃ ጋር ተከረተሱ፡-

 1. የሲሶ ግዛት ተረክ …‹‹ሲሶ ግዛት›› ወይስ ‹‹የቶፋ ሥርዓት››?!
 2. አብዮታዊ ኢ-አማኒነትና የአቡነ ቴዎፍሎስ ምዕዳን!
 3. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ… ቅድመ-ሞት፣ ጊዜ-ሞት፣ ድኅረ-ሞት…ሞትህ ደጅ አደረ!
 4. ዝክረ-ቴዎፍሎስ በአፈ-ጳጳሳት ወሊቃውንት!

የሚሉ አርእስትን መራኅያን አድርጌ በተቻለኝ መጠን ስሜቴን ገትቼ (እንዲያው መግታቱ ከሆነልኝ) የመዛግብቱን ሀቅ ለማሳየት እሞክራለሁ፤ ለዚህም የአምላከ ግፉዐን ረድኤትና ጥበቃ እንደማይለየኝ አምናለሁ፡፡

1. የሲሶ ግዛት ተረክ … ሲሶ ግዛት ወይስ የቶፋ ሥርዓት?!

በትርጓሜ-ቃላት እንጀምር፡፡

 1. ‹‹ያ! ትውልድ›› የምለው በተለምዶ ‹‹ተራማጅ/የተማሪው ንቅናቄ/የ1960ዎቹ ትውልድ›› እየተባለ የሚጠራውን ድኅረ-ፋሽስት ወረራ ተፈጥሮ ለአዲስ ኅብረተሰባዊ ግንኙነትና የሥርዓት ለውጥ የታገለ ቀለም-ቀመስ ትውልድ ነው፡፡ አደረጃጀቱ ብሔር-ተኮር ወይም ኅብረ-ብሔራዊ ሊሆን ይችላል፡፡
 2. ‹‹ሲሶ ግዛት›› ማለት የኢኦተቤክ (አንድ-ሦስተኛ ወይም 33%) የሀገር ሀብት (መሬት) ተጋሪነት ለማለት ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው፡፡ ቀሪዎቹ ባለሲሶዎች ‹‹ነጋሽ›› (መንግሥት) እና ‹‹አንጋሽ›› (ሕዝብ) ናቸው!
 3. ‹‹ተረክ›› የምትለዋ ቃል የኢህአፓው ጃርሶ ሞት ባይኖር ኪሩቤል መለያ ቃል ናት፡፡ ጃርሶ ይቺን ቃል ‹‹ተረትና ታሪክ አንድ ላይ ተሠርተው ሲቀርቡ›› የሚሰጡትን ትርጓሜ ለመግለጽ እንደሚጠቀምባት ተናግሮ ነበር (ሩሕ መጽሔት፣ የካቲት 1993)፡፡ በሲሶ ግዛት ዙሪያ የሚጻፉ መዛግብት እንዲያ አይነት ማለትም ተረትና ታሪክ የቀላቀሉ ሆነው ስለሚሰሙኝ ቃሉን ከጃርሶ ተዋስኩት፡፡
 4. ‹ቶፋ›› የሚለው ቃል በጽሑፉ ውስጥ በተደጋጋሚ በዝርዝር ይብራራል፡፡ ባጭሩ ‹‹በቤ/ክ ሥም በዘር በወረደ የእልቅና ወይም ሌላ የክሕነት ተግባር የሰሞን መሬት ለያዘ/ለያዘች ባላባት ለአገልግሎት ተገዝቶ ቅዳሴና ውዳሴው እንዳይታጎል እየሸፈነ በምላሹ ቀለብ የሚቆረጥለት ገባር ቄስ/ደብተራ/ዲያቆን›› ማለት ነው፡፡

አሁን ወደተረኩ እንሂድ…

1.1. የያ ትውልድ የሲሶ ግዛት ተረኮች!

1.1.1. የሲሶ ግዛት ተለዋጭ ሥሙ ‹‹የሰሞን መሬት›› ነው፡፡ ‹‹ሰሞን›› ትርጓሜው በየሳምንቱ (በየ8 ቀኑ) የሚዞር የካሕናት የፈረቃ አገልግሎት ማለት ነው፡፡ በግእዝ ‹‹ዕብሬት›› እንለዋለን፡፡ ‹‹የሰሞን መሬት›› ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ነበር! በመዝገብ ትርጓሜው ‹‹የሰሞን መሬት፡- የእልቅና፣ የግብዝና፣ የቅስና፣ የዲቁና፣ የደብተርነትና ሌላም ይህነን የመሳሰለ ከቤተ መቅደስ የገባ የቤተ ክርስቲያን ርስት ነው፡፡ … አለቃው … በሹመቱ ጊዜ … መትከያ የሆነ ማደሪያ ይቀበላል፡፡ በያውራጃው አንዳንድ ቦታ ‹አቅንቶ› ርስቱ ሆኖ የሚኖር ደግሞ መንግሥት ፈቅዶለት ለተከለው ታቦት ‹እልቅናውን ርስት ያስደረገ› አለ›› ተብሎ ተተርጉሟል(ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ፣ ዝክረ ነገር፡ገ.120)፡፡ ከዚህ ትርጓሜ 2 ቁም ነገሮች እንወስዳለን፡፡

 1. የሰሞን መሬት እንደ መርህ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ነው፡፡
 2. ነገር ግን መንግሥት የፈቀደለት አለቃ አለቅነቱን በሰሞን መሬት ላይ ርስት ማስደረግ ይችላል፡፡ ‹አለቅነት ርስት ሆነ› ማለት ባለቤትነቱ ለሥም
  ያህል (bare possession–ሌጣ ይዞታ) የቤተ ክርስቲያን እየተባለ የመሬቱ ፍሬ ተጠቃሚዎች ግን ከአለቃው ሞት በኋላ እልቅናው በዘር የሚተላለፍላቸው የአለቃው ተወላጆች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የያ ትውልድ ፀሐፍት የሚስቱት ዓቢይ ነጥብ ይሕ ነው፡፡ ተራማጆቹ ይሕን ሀቅ ይራመዱታል!

1.1.2. ያ! ትውልድ ጽንሰቱን ከ1953 ዓ.ም የታሕሳስ ግርግር ጋር ያያይዛል፡፡ ተራማጁ ኃይል በአደባባይ የነጄ/ል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ደጋፊ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር የነበሩት ቀዳማይ ፓትርያርክ ወእጨጌ አቡነ ባስልዮስ ደግሞ ከተራማጆች በተቃራኒ ቆመው መፈንቅሉን በማውገዝ ለክሽፈቱ አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አቡነ ባስልዮስ በመፈንቅለ መንግሥቱ አድራጊዎች ላይ ያስተላለፉት ውግዘት አስመራ ታትሞ ሻለቃ ቸርነት በተባሉ መኰንን አማካይነት በየክፍል ሀገሩ በአውሮፕላን ተበትኗል(ብርሃኑ አስረስ፣ ማን ይናገር የነበረ፡ገ.223)፡፡ ይሕ አባታችን ድርጊት የመፈንቅሉ ደጋፊ በነበረው ተራማጅ ምሁር ዘንድ ቤተ ክርስቲያኗ እንደ ተቋም ‹‹የፊውዳሉና ከፊል ካፒታሊስቱ አሮጌ ሥርዓት ተቀጽላ›› ተደርጋ የጎሪጥ እንድትታይ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ በዚህ የተነሳ ማዕከላዊውን የቤተ ክሕነት ተቋም፣ መሪዎቹን ጳጳሳትና ፓትርያርኮችን ዒላማ ያደረጉ ፕሮፖጋንዳዎች ይካሄዳሉ፡፡ አንዳንዶች ጠቅላላ ሃይማኖቱ ላይ ሲዘምቱ የተወሰኑት ደግሞ ካሕናቱን በተዋረድ ጭቁን የሆኑና ያልሆኑ በማለት በመደብ ከፋፍልው ለማየት ሞከሩ፡፡ ቅስቀሳው በአብዮቱ የመሬት ላራሹ አዋጅ ዋዜማ በተለይ ተጡዋጡዋፈ፡፡

1.1.3. ኮ/ል ፍስሐ ደስታ እንደነገሩን ደርግ የነበረው አቋም ከሀገራችን መሬት ‹‹30 ከመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተያዘ ነው›› ወደሚል ያጋደለ ነው (አብዮቱና ትዝታዬ፡ገ.236)፡፡ ኢሕአፓ በበኩሉ ከሀገሪቱ መሬት ውስጥ ‹‹ከመቶው ሥሳ አምስት /65%/ እጁ የእርሻ መሬት በንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ይገኛል›› ካለ በኋላ ከቀሪው 35 በመቶ ውስጥ ደግሞ ‹‹ከሃያ እስከ ሠላሳ በመቶው /20-30%/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እጅ ይገኛል›› ብሎ ነበር (ዲሞክራሲያ፣ ቅጽ 1፣ ቁጥር 12፡ገ.2)፡፡ የአንዳንድ የኦሮሞ ተራማጅ ልሂቃንን ያልተስማማሁባቸው አንዳንድ አመለካከቶች ከዚህ በፊት ያቅሜን ለብቻው ስለዳሰስኩ አልመለስባቸውም፡፡ ህወሓትን በሚመለከት በትግራይ የነበሩ ገዳማት ሰፋፊ እርሻ ይዘው እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ‹‹ሕምሾ›› (20%) የምርት ውጤት ከአራሾች ይወስዳሉ ተብሎ ይታመን እንደነበር በአረጋዊ በርሀ በኩል ተነግሮናል (Aregawi Berhe,A Political History of the Tigrays People’s Liberation Front:p.285-287)፡፡ ሥርወ-ድርጅቱን ከያ ትውልድ የሚመዘው ኢህአዴግ እንዲሁ የኛዋ ‹‹የክርስትና ሃይማኖት የአገሪቱን ሲሶ መሬት ስትቆጣጠር›› እንደነበር ይገልጻል (የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ፣ 2006 ዓ.ም፡ገ.63)፡፡ ብዙኃኑ ተራማጅ ድርጅቶች ይህን የሲሶ መሬትና ሌላ ሌላም ትረካ በደምሳሳው እንደ መፈክር ከማንሳት በቀር ዝርዝር መረጃ አይሰጡንም፡፡

1.1.4. ያም ሆኖ ዶክመንቱ እንደሚያሳየው ከነዚህ የያ ትውልድ አባላት (ተራማጅ ድርጅቶች) ውስጥ ግነትና ኵሸት ባያጣውም የወቅቱን ነባራዊ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ተጠቃሚ በመለየትና በመረዳት ረገድ ኢሕአፓ የተሻለ ዘርዘር ያለ ግንዛቤ የነበረው ይመስላል፡፡ ምናልባት በውስጡ እነ ፀገየወይን ገብረመድኅን (ደብተራው) እና የእስጢፋኖስ ካሕን ከነበሩ ወላጅ የተገኘው ኃይሉ ዮሐንስ (ገሞራው) የመሳሰሉ መደባቸው ለማዕከላዊ ቤተ ክህነት አስተዳደር ቅርብ ከሆነ ቤተሰብና አኗኗር የሚመዘዝ አባላት ስለነበሩበት ይሆናል፡፡ የኢሕአፓን ዝርዝር ትንታኔ ከድርጅቱ ዝነኛ ልሳን ዲሞክራሲያ እንጨልፍ፡፡

1.1.5. ኢሕአፓዊቷ ዲሞክራሲያ በጥያቄ ነው የምትጀምረው፤ ‹‹ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሬት ሲባል ምን ማለት ነው? ድኃ ቀሳውስትና ዝቅተኛ ካሕናት የያዙት መሬት ማለት ነውን? በርግጥ በቤተ ክርስቲያን መሬት የሚጠቀምበት ማነው? አብዛኛው በቤተ ክርስቲያን ሥም የሚጠራው መሬት በተዘዋዋሪ መንገድ የንጉሣውያን ቤተሰብ ሀብት ነው፡፡ ስማቸው እንዳይጠፋ፣ ብዙ መሬት መያዛቸው እንዳይታወቅባቸው፣ ንጉሣውያን ቤተሰብ በልዩ ልዩ አድባራት ሥም በመጠቀም፣ ደባትሩ፣ ቀሳውስቱ፣ ዲያቆናቱ… ወዘተ ጥቅሙ ሳይደርሳቸው ርስቱንና ግብሩን በነሱ ሥም በማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያን ከለላ ሆነው ሠፊውን ሕዝብ ከማታለል ከመበዝበዛቸውም ሌላ በምዕመናኑ ላይ ተሣልቀዋል፡፡ በምሳሌ ለማሳየት፣ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ብቻ ንጉሣውያን ቤተሰብና ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ዝምድና መጥቀሱ ይበቃል›› ትላለች የኢሕአፓ ልሳን በቅጽ 1፣ ቁጥር 12፣ ጥቅምት 5 ቀን 1967 ዓ.ም እትሟ፡፡ በመቀጠልም አልጋ ወራሹ(ልዑል አስፋወሰን) በሐረር ጠቅላይ ግዛት ባሉት አደሬ ጢቆ ሥላሴና ሐረር መድኃኔዓለም ሥም የያዙትን ከ50-70 ጋሻ የሚለካ መሬት፣ ልዕልት ተናኘወርቅ በነዚሁ አድባራት፣ በጊዮርጊስና ተ/ሃይማኖት ሥም በደብተርነት፣ ግብዝና፣ መንበር እየተባለ በውርስ የያዟቸውን 13 ጋሻ መሬቶች፣ እንዲሁም ልዑል ሣሕለሥላሴና ልዕልት አይዳ በግብዝና ሥም የያዟቸውን በብዙ ጋሻ የሚቆጠሩ መሬቶች ትዘረዝራለች፡፡

1.1.6. እንዲህ እንዲያ ሲባል የመሬት ላራሹ አዋጅ አዲስ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ለማዋለድ ሀገሪቱን ‹ማርያም! ማርያም! › ሊያሰኛት ይጀምራል፡፡ በዚህ ጊዜ የያ! ትውልድ አባላት በቤተ ክርስቲያን ሥም በተያዘው መሬት እጣ ፈንታ ላይ አስተያየቶቻቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ የኢሕአፓዎችን አስተያየት እንይ፤ ‹‹አብዛኛው ሕዝብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ባልሆነባቸው ቦታዎች ቤተ ክርስቲያንና ገዳማቷ የያዟቸውን የእርሻ መሬቶች ያለምንም ካሳ ወርሶ መሬት ለሌላቸውና ላነሳቸው ገበሬዎች በነጻ መስጠት፣ …አብዛኛው ሕዝብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ በሆነባቸው ደጋ ክፍለ ግዛቶች /ጎጃም፣ በጌምድር፣ ትግራይ፣ ሸዋ…ወዘተ./ ቤተ ክርስቲያንዋና ገዳማቷ የሚይዙት የእርሻ መሬት ልክ በሕግ ይወሰናል፡፡ /ንጉሣውያን ቤተሰብ በቤተ ክህነት ሥም የሚጠቀሙትን አይጨምርም፡፡ / ከዚህ ልክ በላይ የሆነው ትርፍ መሬት በሁለት ክፍል ተመድቦ፣ አንደኛው ክፍል ያለ ምንም ካሣ ተወርሶ ደሞዝ ወይንም በቂ መሬት ለሌላቸው ቄስ ገበሬዎች በነጻ ይሰጣል፡፡ ሁለተኛውን ክፍል መንግሥት ከቤተ ክርስቲያንና ገዳማቷ ወስዶ መሬት ለሌላቸውና ላነሳቸው ገበሬዎች በነጻ ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት…በሕግ ከሚወሰነው ሳያልፉ መሬት ለመያዝ ያላቸውን መብት መንግሥት ያከብርላቸዋል፡፡ ቅጽረ ግቢያቸውንና ንብረታቸውንም ይጠብቅላቸዋል›› (ዝኒ ከማሁ፡ገ.5 እና ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ፣ ቅጽ 1፡ገ.292)፡፡

1.1.7. የመላ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) በመሬት ላራሹ አዋጅ ዋዜማ በቤተ ክርስቲያን ሥም ስለተያዙ ይዞታዎች ያለውን አቋም ‹‹በቤተ ክርስቲያን ሥም የተያዘው መሬት ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በቅድሚያ ተከፋፍሎ፣ የተረፈው ለሌላው አርሶ አደር እንዲደለደል፣ በአርሶ አደሩ ላይ የተጫነውም በቤተ ክርስቲያን ሥም የሚሰበሰብ ልዩ ልዩ ግብር(?) እንዲሰረዝ፣ ቤተ ክርስቲያን ከምዕመናን በምታገኘው እርዳታና ምጽዋት ብቻ እንድትተዳደር›› በማለት በወቅቱ የድርጅቱ ልሳን ከነበሩ ባንዱ ‹‹የሕዝብ ድምጽ›› ጋዜጣ የመጋቢት 23 ቀን 1966 ዓ.ም እትም አስታውቆ ነበር፡፡

1.1.8. በደርግ በኩል የመሬት አዋጅ ከረቂቁ እስከ ማጽደቁ በተጓዘው ሂደት በቤተ ክርስቲያን ሥም ስላሉ ይዞታዎች ብልጠትና ጥልቀት የተሞላባቸው ዝግጅቶች ሳይካሄዱ አልቀሩም፡፡ የመሬት አዋጁን ረቂቅ ለደርግ ያቀረቡት የአዋጁ መሐንዲሶች እነ አቶ ዘገየ አስፋው ‹‹በቤተ ክሕነት ይዞታ ስር የሚገኘው መሬትና በጭሰኝነት የሚተዳደረውም የገበሬ ብዛት በቀላሉ የማይገመት ስለሆነ ቤተ ክህነትም የያዘችው መሬት መወረስ ይኖርበታል፡፡ በዚህ የተነሳ ቤተ ክህነት ችግር እንዳይገጥማት መንግሥት በየዓመቱ የተወሰነ ገንዘብ በበጀት መልክ ሊመድብላት ይችላል›› አሉ፡፡ በዚህ ማብራሪያ ላይ ኮ/ል አጥናፉ ‹‹ቤተ ክህነት የምትተዳደረው ከመሬት በምታገኘው ጥቅም ሲሆን መሬት በመወረሱ ምክንያት ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች እንደሚዘጉና በዚህም የተነሳ ከምዕመናን ጋር ቅሬታ እንደምንገባ›› ተረድታችሁ ማሻሻያ አድርጉ የሚል ድምጽ አሰሙ፡፡ ከመድረኩ የተሰጣቸው ምላሽ ‹‹ቤተ ክህነትን በሚመለከት መንግሥት በቂ በጀት ከመመደቡም በላይ ከምዕመናን ከሚሰበሰበው ዕርዳታና ከተለያዩ ገቢዎች መተዳደር ስለምትችል በዚህ በኩል ችግር አይገጥመንም›› የሚል ነበር (ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ እኛና አብዮቱ፡ ገ.181-182)፡፡

1.1.9. በወቅቱ ከቤተ ክህነት ለሚወረሰው መሬት በቂ ማካካሻ ተብሎ የተመደበው ገንዘብ ለ17 ዓመታት ያለምንም ማሻሻያ የዘለቀ የ4 ሚሊዮን ብር ተቆራጭ ሲሆን በዚህ ረቂቅ የቤተ ክህነቱን አስተያየት ለመስማት የተደረገ ጥረት ስለመኖሩ የተመዘገበ ታሪክ አላነበብኩም፡፡ በዚህ የተነሣ ውይይቶቹ በቤተ ክርስቲያን ሥም መሳፍንትና መኳንንት የያዟቸውን ንብረቶች ሁሉ ጠቅልሎ የቤተ ክርስቲያን የማስመሰል መንፈስ ይነበብባቸዋል፡፡ ያም ሆነ ይሕ ከየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚፀና የሚገልጸው ሚያዚያ 21 ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው ‹‹የገጠርን መሬት የሕዝብ ሀብት ለማድረግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 31/1967›› በስፋት የሚተረከውን ‹‹የሲሶ መሬት ድርሻ›› በሥም ሳይጠቅስ በአንቀጽ 3(2) ‹‹ማንኛውም ሰው ወይም የንግድ ማኅበር ወይም ሌላ ድርጅት የገጠር መሬትን በግል ባለሀብትነት መያዝ አይችልም›› ሲል ደነገገ፡፡ ይሕ ድንጋጌ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክሕነት›› የሚለውን ቃል ቀጥታ ስዶ አልተጠቀመም፡፡ ነገር ግን ‹‹ድርጅት›› የሚለውን ቃል በአንቀጽ 2(6) ሲተረጉም በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 398 የተመለከተውን እንደሚያጠቃልል ይገልጻል፡፡ ይሕ የፍትሐ ብሔር ድንጋጌ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና መዋቅሮቿ የሕግ ሰውነት የሚደነግግ ነውና የመሬት አዋጁ በለሰስታ የሰሞን መሬት ስሪትን መናዱን እንረዳላን፡፡

1.1.10. የሰሞን መሬት ፋይል በዚሁ ተዘጋ፡፡ ታሪክ ሆነ፡፡ አሁን የሚያከራክረን የታሪኩ አተራረክ ነው፡፡ የተወሰኑ የያ ትውልድ አባላት ዛሬ ድረስ የ1967 ዓ.ም አዋጅ ከቤተ ክርስቲያን ሲሶ ሥልጣንና ሲሶ የመሬት ድርሻ የገፈፈ አንጸባራቂ ድል አድርገው አጋንነው ያቀርባሉ፡፡ ገፋ ሲልም በወቅቱ በነበሩት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ እና የቤተ ክሕነት ኃላፊዎች ላይ ለተወሰዱ ኢ-ሰብአዊና ሰቆቃዊ ግድያዎች መሸፋፈኛ ለማድረግ ሲሉ በሙታን አጽም ላይ ክስ ይደረድራሉ፡፡ ኢሕአፓ ከላይ በተጠቀሰችው ልሳኑ አቡነ ቴዎፍሎስ ከ120-180 ጋሻ የሚደርስ መሬት ነበራቸው ሲል በማጋነን ይከስሳል፡፡ ገድሎ ሥም ማውጣት የሚያዘወትረው ደርግ አባል የነበሩት ኮ/ል ፍስሐ ደስታ ያላንዳች ርኅራኄ፣ ያላንዳች ማጣቀሻ፣ ያላንዳች ይሉኝታ ቤተ ክርስቲያንና አቡነ ቴዎፍሎስን ወረፉበት ብዕር ‹‹…ምንም እንኳ መንግሥት የ4 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ድጎማ ቢሰጣትም ቤተ ክሕነት የመሬት ውርሱን በፀጋ ልተቀበለችውም፡፡ በቀድሞው ሥርዓት ቀብታ የምታነግሥ ሲሶ መንግሥት ስለነበረች ሶሻሊዝም ሲታወጅ ተሰሚነቱዋንና የነበራትን ቦታ እንደምታጣ ከወዲሁ መገንዘቧ አልቀረም፡፡ ፓትርያርኩ አቡነ ቴዎፍሎስም የራሳቸውን ወዳጆች በመሾምና በመመደብ በደርግ ላይ ውስጥ ውስጡን የመቃወምና የማጥላላት ዘመቻ ጀመሩ›› ይላሉ (ኮ/ል ፍስሐ ደስታ፡ ገ.199)፡፡ ለነዚህ ተረኮች ዛሬ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ተከሳሽ አበው የሉም፤ አልፈዋል፡፡ ቢሆንም ‹‹እመ ነባቢሁ ተቀብረ፤ አምጣነ ንባቡ ኢይትቀበር…ተናጋሪው ቢቀበር ንግግሩ አይቀበርም›› ብለን በወቅቱ የነበሩ የቤተ ክሕነት መዛግብት ስለ ሲሶ ግዛት ባዶ የቃላት ጋጋታነት ካኖሩልን በመጠኑ እንጠቅሳለን፡፡

1.2. ‹‹የቶፋ ሥርዓት››! … በተራማጆች ጆሮ የተነፈገው የታሪክ ጩኸት!

1.2.1. በአቡነ ባስልዮስ 9ኛ የበዓለ-ሲመት አከባበር ወቅት ማለትም በ1960 ዓ.ም መንበረ ፓትርያርኩ ባወጣው ርእሰ አንቀጽ ‹በ13ኛው ክ/ዘ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና የአጼ ይኩኖ አምላክ ቃል ኪዳን ወለደው› የሚባለው ሲሶ ግዛት ወደ ‹‹ተረክነት›› ስለመውረዱ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡ ‹‹ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተሰጠው ሲሶ መንግሥት ግን አሁን አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በመሰረቱ ግምቱ (የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ) የምታገኘው ጠቅላላ የዓመት ገቢ (ብር) 1,821,142.24 ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም ከዓሥራት 1,259,872.93 ሲሆን ከትምህርት ታክስ (በፊደል አስቆጣሪነት ሚናዋ) ደግሞ 561,269.31 (ብር) ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ የቤተ ክርስቲያናችን ገቢ ከአንድ ሚሊዮን ተኩል ብዙ የማይበልጥ ሲሆን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሶ መንግሥት አላት ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ገቢ 3 ሚሊዮን ብቻ ነው ማት ይሆናል፡፡ የመንግሥቱ ገቢ ይሕ ብቻ አለመሆኑ በማንም ዘንድ በግልጥ ስለሚታወቅ በአሁኑ ጊዜ ‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሶ መንግሥት አላት› የሚባለው ወሬ እውነት አይደለም›› ሲል የቀዳማይ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ጽ/ቤት አቋሙን ይገልጻል፡፡

1.2.2. አስከትሎም የያ ትውልድ አባላት ከጽንሰታቸው እስከ ዕርግናቸው ዐይናችንን ግንባር ያድርገው ብለው የሚገድፉትን የ‹‹ቶፋ›› ሥርዓት ያብራራል፡፡ ከፈረሱ አፍ እንስማ፤ ‹‹ቀድሞ የተሰጠው ሲሶ ሀብት የት ሄደና ነው ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገቢ ይሕ ብቻ የሆነው? የተባለ እንደሆነ ርግጥ ይሕ ሲሶ ሀብት በማንኛውም ንጉሥ አዋጅ አልተሻረም፡፡ …ይሁን እንጂ ይህ የቀዳሽ ወይም የቤተ ክርስቲያን ተብሎ የተሰጠው ሀብት በቀን ብዛት ወደ አንጋሹ [ነጋሹ ቢባል ይሻል ነበር] እየተደረበ ሄዷል፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆነው ቀዳሹ ቤተ ክርስቲያን እያገለገለና እየቀደሰ በልዩ ልዩ ትክል ማለት በእልቅና፣ በግብዝና፣ በመሪጌትነት፣ በሰዓታት፣ በቅዳሴ ይሕን በመሳሰለው አገልግሎት ተተክሎ እንዲጠቀምበት በደመወዝ መልክ ከተሰጠው በኋላ እስከ ዕድሜው ያገለግልና ሲሞት ያንን ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ርስት ለልጆቹ ያወርሳል፡፡ ልጆቹ ደግሞ በሞያና በክህነት አባታቸውን መስለው ስለማይወጡ ለቤተ ክርስቲያኑ ግብር ‹ቶፋ› የሚባል ደጀ ጠኚ ይገዙና እነሱ መሬቱን ይዘው ወደ ሌላ ሥራቸው ይሄዳሉ፡፡ ለቶፋውም እንኳ በቂ ደመወዝ ይሰጡትም፡፡ ምናልባት ደጎች የሆኑ እንደሆነ በዓመት ከ10 ብር እስከ 15 ብር ቢሰጡት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ነው ሲሶ ለቀዳሽ ተብሎ የተሰጠው ሲሶ መንግሥት ወደ አንጋሹ [ነጋሹ] ተደርቦ ሊሄድ የቻለው›› ይላል የአቡነ ባስልዮስ 9ኛ በዓለ-ሲመት መታሰቢያ መጽሔት ከገጽ 16-18 ባሳፈረው ሐተታ፡፡ ‹‹ቶፋ›› የተባለው አለቅነትን ከዘር ወርሶ በቤ/ክ ሥም የመሬት ይዞታን ለተቆናጠጠ ተወላጅ ተቀጥሮ የሚሠራ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ደብተራ ነው፡፡ ለምሳሌ በበቾ አካባቢ ‹‹ቶፍነት›› ለሚሠራ ዲያቆን በዓመት ከብ 10-14 ሲከፈል ለቄስ ደግሞ ከብር 18-20 ይከፈል ነበር፡፡ ክፍያው ስሙ ‹‹ግዢ›› ነው፡፡ ዲያቆን ወይም ቄስ ‹‹ገዝቶ አስቀደሰ›› ነው የሚባል(ዝክረ ነገር፡ ገ.136)፡፡

1.2.3. አብዮቱ መፋጀት ሲጀምር ለአቡነ ቴዎፍሎስ 3ኛ ዓመት በዓለ-ሲመት በወጣው ‹‹አዲስ ሕይወት፣ ቁጥር 4›› መጽሔት ተመሳሳይ ሐሳብ ይንጸባረቃል፡፡ መጽሔቱ የሲሶ መንግሥት ተረክን ከላይ በሰፈረው አኳኋን ካብራራ በኋላ ሐተታውን በምሬት ሲደመድም ‹‹…የሲሶ መንግሥት ቃል ኪዳን ጥንታዊውን የታሪክ መዝገብ ይዞ የሚገኝ እንጂ ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ካለው የመንግሥት ገቢ ላይ ሲሶውን አግኝታለች ወይም ታገኛለች ማለት አለመሆኑና ቤተ ክርስቲያን ባሁኑ ጊዜ እንኳንስ የመንግሥቱን ሲሶ ገቢ ይቅርና ከመቶ አንዱን እንኳ የማታገኝ መሆኗ ባጭር የተሰጠው ሐተታ በቀላሉ ሊያስረዳ ይችላል›› ይላል (አዲስ ሕይወት፣ ቁጥር 4፣ ግንቦት 1 ቀን 1966፡ ገ.29)፡፡

1.2.4. እነ ኮ/ል ፍስሐ ደስታ በመሬት ላራሹ የተገኘውን ድል ያሳንስብናል ብለው ሳይሆን አይቀርም ይሕን ቤተ ክሕነታዊ ድምጽ መስማት
አይፈልጉም፡፡ ኮለኔሉ በትዝታቸው ገጽ 145 ስለ አክሱም አካባቢ የመሬት ስሪት ሲያብራሩ ‹‹የአክሱም ጽዮን ገዳም በርካታ ጉልት ስለነበራት በደርግ የመሬት አዋጅ እስኪታወጅ ድረስ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ መነኮሳት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመስጠት ብቻ የገዳሚቱን ርስተ ጉልት እያሳረሱ ይተዳደሩ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረት ከአይጥ ለሚጠብቁ ድመቶችና በየዓመቱ የንግሥ በዓል በወግ ልብስ ተሸልመው ለሚወጡ በቅሎዎች ሳይቀር በስማቸው ከተያዘው የጉልት መሬት ቀለብ ይሠፈርላቸዋል›› ይላሉ፡፡ የተከበሩ ኮሎኔል ለዚህ አባባለቸው አስረጅ አልጠቀሱልንም፤ ‹እማኝ ነኝና እመኑኝ› ነው የሚሉ፡፡ ግና ቃላቸውን እንደወረደ እንዳንቀበል ቤተ ክሕነታዊ ምንጮቻችን ይገዳደሩናል፡፡

1.2.5. ኮ/ል ስለ አክሱም ጽዮን አካባቢ የመሬት ስሪት የጻፉትን ታሪክ በሌላው ትግራዋይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊ ገ/ዮሐንስ ገብረ ማርያም(M.T) ‹‹ክርስትና በኢትዮጵያ›› መጽሐፍ በቀላሉ ማፍረስ ይቻላል፡፡ ገ/ዮሐንስ የአክሱም አካባቢ የመሬት ሥሪት ቅርጹን የቀየረው በአጼ ዮሐንስ 4ኛ ዘመን መሆኑን ይተርካሉ፡፡ ንጉሡ ሕዝቡ መሬቱን ለእሳቸው እንዲሰጥ አስገደዱት፡፡ ሕዝቡ በምሬት ወደ ምዕራብ ትግራይ ሸሸ፡፡ ንጉሡ ሕዝቡን ‹‹ወደ ቦታህ ተመለስ፤ ምሬሃለሁ›› ካሉት በኋላ የመሬቱን ዋጋ ጨርቅ እየሰጡ የትም እንዳይሄድ በወታደር አስጠበቁት፡፡ መሬቱን ግን ለመጤ ደባትር፣ ለካሕናት፣ ለወይዛዝርት፣ ለመኳንንት አደሉት፡፡ ይሕ ድርጊት ይላሉ የዐጼ ዮሐንስን ዓለምአቀፋዊ ገናና ታሪክ ሳይስቱ ድክመታቸውን የሚጠቅሱት ገ/ዮሐንስ፣ ‹‹ይሕ ድርጊት የአጼ ዮሐንስ ደካማ ጎናቸው ነው፡፡ …ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ የከበደ ቀንበር በአክሱም አካባቢ ነዋሪ ተጫነበት፡፡ በሌሎች አድባራት ትክለኛ ሲሞት ትክለኛ ይተካ ነበር(?)፡፡ ‹የአክሱም የአጼ ዮሐንስ ትክለኛ ግን በትክለኛነት የተረከበውን መሬት ለልጅ ልጁ አወረሰ›፡፡ ደብተራው፣ መኰንኑና ሴት ወይዘሮዋ ከየትም የተጠራቀሙ ቢሆኑም ተተከሉ፡፡ ገበሬው ደግሞ ከአያት ከቅድመ አያቶቹ ጀምሮ በነበረበት ቦታ ለአስከፊ ባርነት ተዳረገ፡፡ የተገላቢጦሽም መጻተኛ ተባለ፡፡ በዚህም እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ኖረ›› ይላሉ (ገ/ዮሐንስ ገ/ማርያም፣ ክርስትና በኢትዮጵያ፣ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 19፡ ገ.165)፡፡ ስለዚህ አክሱም የነበረው ስሪት ኮ/ል እንደሚሉት የካሕናት ሲሶ ድርሻ ሳይሆን ያው በተቀረው አገር እንደነበረው ‹‹ቶፋ›› የሚባለው መሳፍንታዊ ሥርዓት ነው፡፡

1.2.6. የተከበሩ ኮ/ል ትኩረት ሰጥተው በጊዜው አላስተዋሉትም እንጂ በደርግ ቡራኬ አቡነ ቴዎፍሎስ ወርደው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ መንበሩ ሲመጡ ካሕናቱ ያስደመጡት ድምጽ በመሰረታዊነት በቀደሙት ፓትርያርኮች ከተሰማው የተለየ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ለበዓለ ሲመቱ የታተመው መጽሔት በገጽ 36 እንዲህ ይላል፤ ‹‹…መሳፍንቱና መኳንንቱ እልቅናውንና ግብዝናውን ርስት አድርገው ስለሚይዙት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቀላዶችና ጋሻ መሬቶች በተዘዋዋሪ መንገድ ተመልሰው ወደ ልዑላኑ እጅ ይገባሉ፡፡ ወይዛዝሮቶቹ፣ ባህሉና ሥርዓቱ የማይፈቅድላቸው የቤተ ክርስቲያንን የሹመት መዓርግ በተጽእኖ እየያዙ ምሁራን ካሕናትን በትንሽ አበል እየገዙና ‹ቶፋ› የሚል የዝቅተኝነት መጠሪያ ሥም እየሰጡ ሲያስገብሩት ኖረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ስሙ የቤተ ክርስቲያን፣ ጥቅሙ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ሆኖ ቆይቷል›› ብሎ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል?! ኮ/ል አላይተው፣ አልሰምተው! አሁን ድረስ በሕይወት ያሉት ታላላቅ ብፁዐን አበው እነ አቡነ ገሪማ (ዶ/ር) እና አቡነ ቀውስጦስ የሲሶ ግዛትን ተረክነት መናገር አላቆሙም፤ አድማጩ ቢያንስም፡፡ ስለ ቶፋ ሥርዓትና ስለ ባለግብር ድመቶች ካሕናትን የሚወነጅል ምውት ወቀሳ የተሰነዘረው ተቃውሞ (ማስተባበያ) በደረቅ ንባብ ካልተሰማ በ1968 ዓ.ም ካሕናት ካቀረቡት ግጥም እንቀንጭብ፡-

…የዱሮ መሳፍንት፤ ለጉዳቸው፣
ምርቱን እየበሉ፤ እራሳቸው፣
ሰሞን መሬት፤ ማለታቸው፡፡
እነኝህ ሞኞች፤ ያልተማሩ፣
መሬት በደወል፤ የሚጠሩ፣
ቀዳሹ እያለ፤ ካሕኑ፣
መሬት በድመት፤ ወሰኑ፡፡

ብለው ነበር፤ የኛ ባለ ‹‹ሲሶ ግዛት›› ተራኪዎች ግን ወይ ፍንክች! በመጽሐፋቸውም፣ በንድፈ ሐሳብ የሥልጠና ሰነዶቻቸውም ወይ ፍንክች! ሲሶ! ሲሶ! ሲሶ! ኧረ የሥላሴ ያለህ! ልባቸው መጠንከሩ! 50 ዓመት ሙሉ–ሳያምኑ!

2. አብዮታዊ ኢ-አማኒነትና የአቡነ ቴዎፍሎስ ምዕዳን!

በ1978 ዓ.ም የታተመው ‹‹ማርክሲስስት ሌኒንስት መዝገበ ቃላት›› ሃይማኖትን ሲተረጉመው ‹‹…ቀኖና ላይ የተመሠረተ ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት…በማስፈራራት ሰዎች በጭፍን እንዲያምኑ በማድረግ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የሚጥር የሳይንሳዊ ዕውቀት ፍጹም ተጻራሪ የሆነ አመለካከት ነው፡፡ …ሃይማኖት ገዥ መደቦች የሚጠቅማቸውን ሥርዓት ለማቆየትና ለማጠናከር ዋነኛ የርዕዮተ ዓለም መሣሪያም በመሆን ሰፊውን ሕዝብ አደንዝዘውና አደንቁረው ለመግዛት እንዲቻላቸው ያገለግላል፡፡ …ጭቆናና ብዝበዛ ከነሱም ጋር በዝባዥ መደቦች ሲጠፉ ሃይማኖቱም አብሮ ይከስማል፡፡ ይሕ እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ በኮሚኒስት ኅብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ …ይሑንና የሃይማኖት መጥፋት ወይም መደምሰስ ቅጽበታዊ ሂደት አይደለም፡፡ …ሰፊውን ሕዝብ በኢ-አማኒነት መንፈስ የማነጹ ተግባር ሰፊ የሳይንስን ዕውቀት፣ የማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም ትምህርትንና ፕሮፖጋንዳን ባልተቋረጠ ሁኔታ አጠናክሮ ማካሄድን ይጠይቃል›› ብሎ ነበር፡፡ ብዙኃኑ የያ ትውልድ አባላት ከዚህ ትርጉም የተስማማ አቋምን በጊዜያቸው አንጸባርቀዋል፡፡ ጥቂት እንጥቀስ፡፡

2.1. መጀመሪያ አካባቢ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተባባሪ ደርግ ሶሻሊዝምን እንደ ርዕዮተ ዓለም መመሪያ በገሀድ ስላልተቀበለ ከላይ ከተጠቀሰው የማሌ (ማርክሲስት ሊኒንስት) የሃይማኖት ትርጓሜ ጋር የተዋወቀ አይመስልም፡፡ ይሕም ሰኔ 1966 ዓ.ም በተደረገ ጉባኤ እያንዳንዱ የደርጉ አባል እንደየእምነቱ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርዐን በመያዝ ‹‹እኔ…የጦር ኃይሎች አስተባባሪ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ትቅደም ብሎ በተነሳበት ዓላማ መሠረት የኢትዮጵያን ሕዝብ…የግል ጥቅሜንና ሕይወቴን መሥዋዕት በማድረግ በፍጹም ታማኝነት አገለግላለሁ፡፡ …በሕያው እግዚአብሔር/አላህ ሥም ምያለሁ›› ሲል በሀልዎተ-ፈጣሪ ማመኑን ይጠቁመናል (አብዮቱና ትዝታዬ፡ገ.81)፡፡ ደርጎች ሰኔ 26 ቀን 1966 ዓ.ም ጃንሆይ ፊት ቀርበው ለንጉሡ ያላቸውን ታማኝነት ሲገልጹ በሃይማኖተኛነት ቃና ‹‹ለግርማዊነትዎ ረጅም እድሜ እየለመንን ኢትዮጵያ ትቅደም ብለን ለተነሣንበት ዓላማችን የኃያሉ እግዚአብሔር ድጋፍ እንዳይለየን እንጸልያለን›› ብለው ለዚሁም የጃንሆይን ይሑንታ አግኝተው ነበር(ዝኒ ከማሁ፡ገ.82)፡፡ በዚህ የተነሣ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለው መፈክር ወደ ቤተ ክህነቱም ገብቶ ከፓትርያርኩ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ የደብዳቤና የመግለጫ ማሳረጊያ ሆኖ ነበር፡፡ ‹‹የኃያሉ እግዚአብሔር ድጋፍ አይለየን›› ተማጽኖ የነመንጌ ሥላቅና ወጥመድ መሆኑን ማን ልብ አለው!

2.2. ደርግ እየቆየ በማርክሲዝምና ሌኒንዝም በይፋ ተጠመቀ፡፡ ይሕን የተረዳው ተቃዋሚው የመሳፍንት ባለነፍጥ ፓርቲ ኢዲህ(የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረት) ጠንካራ ኦርቶዶክሳዊ መሠረት ባለው የሰሜኑ ሕዝብ ዘንድ ደርግን በፀረ-ኦርቶዶክስነት እየከሰሰ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ከፈተበት፡፡ የደርግ አመራሮች ይሕን ለመቀልበስ ወደ ሰሜን ሄደው በምዕመኑ መካከል ቆመው እስከማስቀደስ በደረሰ የማሳመን ዘመቻ ተጠመዱ፡፡ ‹‹…ደርግ ሃይማኖት የለሽና ሃይማኖትን ለማጥፋት የመጣ ኃይል ሳይሆን በተቃራኒው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ነጻነቷን አግኝታ እንድትጠናከርና እንድትስፋፋ ለመርዳት ከጎኗ የቆመ መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ ለማሳመን ተሞከረ፡፡ …ለአንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚውሉ ንዋየ-ቅድሳት በመንግሥት ሥም በመስጠታቸው ምዕመናኑ አደነቁ›› ይላሉ ሻምበል ፍቅር ሥላሴ ወግደረስ (እኛና አብዮቱ፡ገ.207)፡፡ በኤርትራ ለነበረው ግጭት እንዲሁ ‹‹ጄ/ል አማን በሻዕቢያ ውስጥ ያሉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የኤርትራን አቶኖሚ በመቀበል ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሌሎቹን ይወጋሉ የሚል እምነት ስለነበራቸውም በሽማግሌዎች በኩል ግንኙነት እንዲደረግ ፈቀዱ››፤ ሆኖም የኢትዮጵያን መንግሥት ከሻዕቢያ ጋር ያግባባሉ ተብለው የተላኩት ክርስቲያን ሽማግሌዎች በተቃራኒው ሻዕቢያንና ጀብሃን አስታርቀው የጄነራሉን ክርስትናን ተስፋ ያደረገ የሰላም እቅድ ውሃ ቸለሱበት(ኮ/ል ፍስሐ ደስታ፡ገ.117)፡፡

2.3. የደርግን ርዕዮተ ዓለማዊ የሃይማኖት እይታ ፍቅረሥላሴ አርዓያ የተባሉ የፖለቲካ ምሁር ባጭሩ ሲገልጹት ‹‹ደርግ መጀመሪያ ሲነሣ ፀረ ሃይማኖት ሆኖ ነበር የተነሣው፡፡ …ቆይቶ ወደ አለመቃወም ነበር የመጣው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በሃይማኖቱ አስተምህሮና መዋቅር መጣ›› ይላሉ በሐመር መጽሔት የ1998 ዓ.ም ኅዳር/ታሕሣሥ እትም ባሰፈሩት መጣጥፍ፡፡ በዚህ የምሁሩ አመለካከት ላይ ደርግ ፀረ ሃይማኖት የነበረው ከመጀመሪያ ሲነሳ ሳይሆን ታሕሳስ 11 ቀን 1967 ዓ.ም በግልጽ ሶሻሊዝምን እንደ ርዕዮተ ዓለም ከተቀበለ በኋላ ነው ብዬ ከማመን በቀር በሌላው እስማማለሁ፡፡ በሃይማኖቱ አስተምህሮና መዋቅር ለመጠቀም መሞከርን በሚመለከት በሥራ አስኪያጅ ቀጥተኛ ምደባ፣ በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ፣ መሪጌቶችን ለቀበሌ ሊቀ መንበርነት በመመልመል፣ በየሸንጎው ጳጳሳትንና ፓትርያርኮችን በማስገባት፣ የተሐድሶ ጉባኤ የተባለውን ኢ-መዋቅራዊ ተቋም በማጠናከር ደርግ እጁን በሰፊው ወደቤተ ክሕነት ሰድዶ ነበር፡፡ የሚገርመው የመደብ ጀርባው ከያ! ትውልድ የሚመዘዘው ኢህአዴግም ‹‹ሕዝባችን ጠንካራ የሃይማኖት እምነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አስተሳሰቡና ባህሉ በተቋማቱ ተጽዕኖ ስር ማደሩ በፍጹም የማይቀር ጉዳይ ሆኗል፡፡ እናም እምነቶቹ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ እንደምታ ባለው መልኩ እንዲቀረጹ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው›› ሲል የደርግን ሌጋሲ በለሆሳስ የማስቀጠል ዝንባሌ ያሳያል(የተሐድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ሕዳሴ፣ 2006፡ገ.102)፡፡ መቀመጫውን በዋናነት አሜሪካ ያደረገው የያ ትውልድ ተረፍ የሆነ ልዩ ልዩ ተቃዋሚ ኃይል ዛሬ ድረስ ለሰልፉ በካሕን መታጀብን እንደ ትግል ስልት አድርጎታል፡፡ በጥቅሉ ያ ትውልድ እንደ ንጉሣዊው ሥርዓት በግላጭ አይሁን እንጂ ተቋማትን እንደተቋም ሳይሆን እንደመሳሪያ የመጠቀም (instrumentalist) አዝማሚያ ያንጸባርቃል፡፡ በዚሁ አንጻር በየዘመኑ የሚነሱ የቤ/ክ መራኅያን በአጸፋ መንግሥትን መሳሪያ በማድረግ ተቋማዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መጣጣራቸውንም መግለጽ ይገባል፡፡ ‹ማን የበለጠ ሌላውን መሳሪያ አድርጎ ጥቅሙን አስከበረ?› የሚለው እንዳለ ሆኖ አንዱ ባንዱ የራስን ግብ ከፍጻሜ ለማድረስ መሳሪያ የማድረግ ውሳጣዊ መገፋፋት በ2ቱም ወገን ነባራዊ ክስተት ሆኖ ይታየኛል–አሁን ድረስ!

2.4. ወደ ኢ-አማንያን ሶሻሊስቶች እንመለስ፡፡ ኢ-አማኒነት የደርግ የብቻው መለያ አይደለም፡፡ ኢሕአፓን ጨምሮ ብዙኃኑ የማሌ ድርጅት አባላት ተራማጅነታቸውን የሚያሳዩ አስቀድሞ ኢ-አማኒ በመሆን ይመስላል፡፡ ከሞላ ጎደል የሁሉም የ1960ዎቹ የብሔር-አቀፍና ኅብረ-ብሔራውያን ድርጅቶች መሪዎች የማርክሲስት ሌኒኒስት አስተሳሰብ የሰረጻቸው ኢ-አማኒዎች ነበሩ ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ ለምሳሌ፡- በኢሕአፓ የአንጃ መሪ ተብሎ የተሳደደው ብርሃነመስቀል ረዳ በመርሐ ቤቴ (ሰሜን ሸዋ) ስለነበረው የአመጽ ቆይታ ለደርግ መርማሪዎች በ1971 ዓ.ም በሰጠው ቃል ገጽ 45 ‹‹እኛ ረቡዕና ዓርብ ባንጾም ወይም ቤተ ክርስቲያን ባንሄድም የሌሎችን ሃይማኖት እንደማንሰድብና እስላም ወይም ክርስቲያን እኛ ጋ ቢቀላቀል ሃይማኖቱን እንደምናከብርለትና የኛን እምነት እንዲቀበል እንደማናስገድደው በሰፊው እንገልጽ ነበር›› ይላል፡፡ እዚህ ላይ ብርሃነመስቀል ‹‹የኛ እምነት›› የሚለው ሶሻሊዝም መሆኑ ነው፡፡

2.5. ለኢሕአፓ ለድል ያለመብቃት ምክንያቶች አንዱ ርዕዮተ ዓለሙን ከሚታገልበት አካባቢ ሕዝብ ባህልና ሃይማኖት ጋር ያለማጣጣም ችግር እንደነበር በራሱ መስተጋድላን ተብራርቷል፡፡

‹‹…ለድል ያላበቃን፤ ነበረን ዐላማ፣
ሕይወት የሰጠነው፤ ምንም ሳናቅማማ፡፡ …››

እያለ ያንጎራጉር የነበረው ተጋዳይ አስማማው ኃይሉ ኢሕአፓ ለስኬት ካልበቃበት ምክንያት ውስጥ፤ ‹‹ወጣቱ ለትግል ከነበረው ጉጉት አንጻር ከአገራችን ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ጋር ሊጋጭና ሊስማማ የሚችልበትን መመዘኛ ከወዲሁ አላጤነም፡፡ …አገሪቱ በባዕድ በተወረረች ቁጥር ርስትህን የሚቀማና ሃይማኖትህን የሚያረክስ ጠላት መጥቶብሃልና ለዘመቻ ተዘጋጅ ሲባል በሬዎችን ሳይከውን ጋሻና ጦሩን አንግቦ በሚነሣ ሕዝብ መካከል የማርክሲስዝም ሌኒንዝምን ርዕዮት አንግቦ የሶሻሊስት ሥርዓት ለመመስረት መነሣት ከታሪክ፣ ከባህልና ሃይማኖት ጋር መጋጨታችንን ልብ አላልንም››
ሲል ግለ-ሂስ ያወርዳል(አስማማው ኃይሉ፣ ኢህአሠ፣ ቅጽ ሁለት፡ገ.306)፡፡ ሌላኛው የኢሕአፓ አባል ዶክተር ዮናስ አድማሱ ለያ ትውልድ ሕልምና ራዕይ ክብራቸውን ሳያጓድሉ በሰጡት ትችት-አዘል አስተያየት ‹‹የኔ የምለው ትውልድ በትንሹም ቢሆን ጥራዝ ነጠቅ የመሆን አዝማሚያ ነበረው፡፡ የንድፈ ሐሳቡም ይሁን የሚያቅዳቸው እቅዶች መሠረት በብዙው ድምፁን ያሰማለትና ደሙን ያፈሰሰለት ሕዝብ እውነታ ከመሆን ይልቅ በሌላ ጊዜና ቦታ የተካበቱ ሐሳቦችን አምጥቶ ባለውና ሙሉ ለሙሉ አወቅን ልንለው በማንችለው ሁኔታ ላይ ለመጫን የሞከረው ረቂቅ እውቀት ነበር›› ብለው ነበር(ጦቢያ መጽሔት፣ 7ኛ ዓመት፣ ቁጥር 3፣ 1992 ዓ.ም፡ገ.16)፡፡

2.6. በዚህ ጊዜ ግን በተራማጆች ጫጫታ የተዋጠ አንድ የፓትርያርክ ድምጽ ‹‹ተው! ከሀገራዊ ባህልና ሃይማኖት ያልተገናዘበ የፖለቲካ ብሂል አያዛልቅም›› ይል ነበር፡፡ ማንም አልሰማው፡፡ ታሪክ መዝግቦ ያቆየውን የግንቦት 17 ቀን 1967 ዓ.ም ድምጽ አሁን እንስማው፡፡

‹‹…ምዕመናን ሆይ! …ኅብረተሰቡ ውስጥ በደል የሚደርሰው የኅብረተሰቡ ሥነ ሥርዓት የቤተሰብን ሥነ ሥርዓት አልመስል ሲል ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ከሌላ የመጣ ሳይሆን በመጠኗ በፍላጎቷ የተሠራ ሥርዓት ለማውጣት ሁላችንም እንትጋ፡፡ ጥረቱም በበለጠ ፍሬ እንዲያፈራ በያለንበት ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንጸልይ፡፡ እያንዳንዱ ለአቅመ-ውክልና የደረሰ ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ሥርዓት እስካልተናገረ ድረስ የሚቋቋመው የአስተዳደር ሥርዓት በምንም ዓይነት ኢትዮጵያዊ ስለማይባል ዘላቂ አስተዳደርን ለማቋቋም ያለው ዘመቻ መላ ኢትዮጵያን እንጂ እንደሌሎች ዘመቻዎች ‹ለወታደሮች ብቻ የሚተው አይደለም›፡፡ ጸጥታና እርጋታ በሌለበት ጊዜ በጽሞና ለማሰብ ስለማይችል ሁለተኛም ካሁን በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሕን አይነቱን ሥርዓተ-መንግሥት የማቋቋም ልምድ ስለሌለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የማወቅ፣ የማስተዋል፣ የማማረጥ፣ የማሰብ ሱባዔ ያስፈልገዋል፤ ሆኖም ለአሁኑ የአስተዳደር ዘመን በዚህ ምክንያት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማዘጋጀት የማስተማር ግዳጃችንን በያለንበት እንፈጽም፤ ጸሎታችንንም አናቋርጥ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጃትን ለመሥራት እንትጋ፤ ኩራታችንም እኛ በሠራነው፣ እኛ ባስገኘነው ይሁን፤ የኛነታችን መገለጫ የሆነውን ባህላችንን እንጠብቅ››

(አዲስ ሕይወት፣ ቁጥር 5፣ ግንቦት 1/19967 ዓ.ም)::

2.7. በአቡነ ቴዎፍሎስ ቃለ-ምዕዳን ውስጥ ‹‹ዘላቂ አስተዳደርን ለማቋቋም ያለው ዘመቻ መላ ኢትዮጵያን እንጂ እንደሌሎች ዘመቻዎች ለወታደሮች ብቻ የሚተው አይደለም›› የምትለዋ ሐረግ የቴዎፍሎስን ሕልውና ማክተሚያ ያቃረበች፣ ሐብለ-ሰማዕትነትን በአንገታቸው ላይ የጠመጠመች፣ በተቀናቃኞቻቸው ወጥመድ ሰተት ብለው እንዲገቡ ያደረገች ናት፡፡ ከዚህ በኋላ ክሱ በገፍ መቅረብ ይጀምራል፡፡ ፓትርያርክ የማውረዱ ሴራ ኮ/ል አጥናፉ ተጠሪ በሆኑለት ‹‹የተሐድሶ ጉባኤ›› በተባለ መፍቀሬ-ደርግ ኮሚቴ ይጎነጎናል፡፡ ከሰሳና ወቀሳ ይዥጎደጎዳል፡፡ የሰቆቃወ-ቴዎፍሎስ ምጽአት ይቃረባል፡፡ ተከታዩ ርእሳችን እሱ ነው፡፡

3. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ… ቅድመ-ሞት፣ ጊዜ-ሞት፣ ድኅረ-ሞት…ሞትህ ደጅ አደረ!

ከሞመቱ በፊት ስብዕናውን ለመግደል ተሞከረ፡፡ ሲሞት የፓትርርክነት ወግና ሥርዓቱ ቀርቶ ሞቱን ለሙት በሚገባ ክብር ሳያደርጉለት ቀሩ፡፡ ድኅረ-ሞት ታሪኩን ለማስተሀቀር ተሽቀዳደሙ፡፡ ሞቱን፣ እረፍቱን ከለከሉት፤ ሞቱን ደጅ አሳደሩበት፡፡ ሰቆቃውን አበዙበት፡፡ ስለሰቆቃው መዛግብት ካኖሩልን ልናወጋ ጀምረናል፡፡

3.1. ቅድመ-ሞት…የተሐድሶ ጉባኤ (የኮ/ል አጥናፉ የቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ)!

3.1.1. የ1966 ዓ.ም አብዮት እየጋመ፣ እየፋመ፣ እየተቀጣጠለ የንጉሡን ዙፋን በይፋ ለመገልበጥ 25 ቀናት ሲቀሩት ነሐሴ 11 ቀን 1966 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለኮ/ል አጥናፉ የሆነ ‹‹ጠቅላይ ቤተ ክሕነት እስከ አሁን በምትሠራበት ደንብና ሥርዓት ሥራዋን ስትቀጥል…ከጎን ሆኖ የሚሠራ›› በሚል ሽፋን ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥኝ ጊዜያዊ ጉባኤ›› ተቋቋመ(ድምጸ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ ሐምሌና ነሐሴ 1983 ዓ.ም፡ገ.7)፡፡ ይሕ ጉባኤ በቤተ ክህነት አካባቢ ‹‹የተሐድሶ ጉባኤ›› በሚል ሲታወቅ የጉባኤው አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ደግሞ ‹‹የኮ/ል አጥናፉ የቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ›› ይሉታል፡፡ በወቅቱ ሸዋ ክፍለ ሀገርን ወክለው የደርግ ሸንጎ(መማክርት ጉባኤ) አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው እንዴት የኮ/ል አጥናፉ ኮሚቴ አባል እንደሆኑና የኮሚቴውን አባላት ዝርዝር ሲገልጹ ‹‹…ኮ/ል አጥናፉ አባተ ጠርቶኝ ‹ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ወጥታ ራሷን የምትችለበትን መንገድ የሚፈልግ ኮሚቴ ልናቋቋም ነውና በአባልነት እንዲያገለግሉ እፈልጋለሁ› አለኝ፡፡ ንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ ገብረማርያም፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ቄስ ዳኛቸው ካሳሁን፣ ዶክተር ክንፈርግብ ዘለቀ፣ አቶ ፍቅረድንግል በየነ፣ አቶ መርስዔኀዘን አበበ፣ አቶ አእምሮ ወንድማገኘሁ፣ አቶ(በኋላ ሊቀ ማዕምራን) አበባው ይግዛው የኮሚቴው አባላት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ኮሚቴው ሊቀ መንበር ሲመርጥ…ዶ/ር ክነፈርግብ ዘለቀ ተመረጠ›› ይላሉ(ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፡ገ.202)፡፡ የኮሚቴው አባላት 9 ሰዎች ነበሩ ማለት ነው፡፡

3.1.2. ኮሚቴው እየቆየ ሲሄድ የቤተ ክህነቱ ተራዳኢ ሳይሆን አድራጊና ፈጣሪ ወደመሆን ይሸጋገራል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱን፣ የቅዱስ ፓትርያርኩንና የጠቅላይ ቤተ ክሕነቱን ሥልጣንና ኃላፊነት መንጠቅ መቀናቀን ይጀምራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለ6 ወራት መሻኮቱ ከቀጠለ በኋላ የወቅቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጥር 13 ቀን 1968 ዓ.ም ‹‹የጊዜያዊው ጉባኤ ሥልጣን ከቤተ ክሕነቱ በላይ አይደለም፤ ለጥናት ያህል የሚያካሂደውን ሥራ ደርግ ባዘዘው መሠረት እንተባበራለን፡፡ ከዚህ ውጭ የጊዜያዊ አጥኝ ጉባዔን ትእዛዝ በቤተ ክሕነት አስተዳደር ውስጥ በቀጥታ ተቀብሎ በሥራ ላይ ማዋል ከተሰጠው መመሪያ ጽሑፍ ውጭ በመሆኑ ኃላፊነት ያስከትላል›› ሲሉ ደብዳቤ ጻፉ(ከላይ የተጠቀሰው ድምጸ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ ገ.7)፡፡ የቅዱስ ፓትርያርኩን ደብዳቤ እንደ ትልቅ ንቀት የቆጠረው ጉባኤ ከጥር 16 ቀን ጀምሮ በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በኩል የሚወጡ ደብዳቤዎችን አገደ፤ በይፋ ፀረ-ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ዘመቻዎች በጽሑፍና በሰልፍ ማቀጣጠሉን ተያያዘው ይላል ድምጸ ተዋሕዶ ጋዜጣ፡፡

3.1.3. በወቅቱ የደርግ እስረኛ የነበሩት የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማርያም ወርቅነህ (የአሁኑ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ) በበኩላቸው ስለ ተሐድሶ ጉባኤው ሲተርኩ ‹‹ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ የሚሠራ መስሎ ደርግ ቤተ ክርስቲያንን ከሥር ነቅሎ ለመጣል ከሲኖዶሱ ጉባኤ ውጭ ወይም ለርሱ ተቃራኒ የሚሆን ‹ተሐድሶ ጉባኤ› የሚል ጉባኤ ተቋቋመ፤ …የዚህ ጉባኤ የበላይ መሪና ጠባቂ ኮ/ል አጥናፉ አባተ…ሆነ፣ …የተሐድሶ ጉባኤ ሊቀ መንበር የሆነው ዶክተር ክነፈርግብ ዘለቀ…ነበር…፡፡ እነዚህ የኮሚቴ አባላት…ሲኖዶሱን ሳያማክሩ የሚለወጠውን መለወጥ፣ የሚሻረውን መሻር ጀመሩ፡፡ ልክ እንደ ቤተ መንግሥቱ በቤተ ክህነቱም ሥር ነቀል ለውጥ ለማድረግ ሞከሩ፣ ከለውጥ ሐዋርያት ስብከትና ማታለል የተነሣ ሕዝቡም ካሕናቱም እምነቱን በደርግ ላይ ስለጣለ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የተሻለ ለውጥ የሚያመጣ መስሎት በደስታ ተቀበለው፣ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ግን መብታቸው ስለተነካባቸው በየዕለቱ ግጭት ማንሳታቸው አልቀረም ነበር፡፡ …ከዚህ ከተሐድሶ ጉባኤ ሌላ ደርግ በቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ይሾም ጀመር››(አባ መልከጼዴቅ በአባ ኪዳነ ማርያም ጌታሁን ‹‹የሐሰት ምክርነት›› መጽሐፍ እንደተጠቀሱት፡ገ.109)፡፡ አቡነ መልከጼዴቅ የአቡነ ቴዎፍሎስን ተቃውሞ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ከማስጠበቅ አንጻር ሳይሆን ከግላዊ ክብር ጋር ብቻ ለማያያዝ መሞከራቸው ያሳዝናል፤ ቢሆንም በተደጋጋሚ ይሕን ተግባር ስለሚከውኑት አያስገርምም፡፡

3.1.4. በጊዜው የጉባኤው አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው የተሐድሶ ኮሚቴው እንዴት ፀረ-ቴዎፍሎስ አንጃ እንዳበቀለና የፓትርያርኩን አቋም ስላሰፈሩልን በአቡነ መልከጼዴቅ ከደረሰብን ኀዘን እንጽናናለን፡፡ ፕሮፌሰር ኮሚቴው በዶ/ር ክነፈርግብ መሪነት ጥናቱን ሲቀጥል ስላጋጠመው መሰናክል እንዲህ ይላሉ፤ ቃላቸው እንደወረደ ይኸው፡-

‹‹ኮሚቴው በእሱ [በዶ/ር ክነፈርግብ] ሊቀ መንበርነት ጥናቱን ሲጀምር፡በአቶ አበባው ይግዛው መሪነት በማኅላችን ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከሥልጣን እንዲነሡ አጥብቆ የሚጥር አንጃ ተፈጠረብን፡፡ አንድ ቀን ስብሰባችንን እንደጀመርን ሊቀ መንበሩ ‹የዛሬው አጀንዳችን ፓትርያርኩ ጳጳሳት ሊሾሙ ስለወሰኑ ውሳኔያቸውን እንዲያነሡ የምንጽፍላቸውን ደብዳቤ ለማርቀቅ ነው› አለ፡፡ ‹ያልታዘዝነውን አንሥራ› በማለት ተቃወምኩ፡፡ … በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ‹ያልታዘዝነውን አንሥራ› በማለቴ አዲስ የጦር ግምባር ተከፈተብኝ፡፡ እኔ የተከራከርኩት የነዚህ መነኮሳት መሾም አለመሾም ገድዶኝ ወይም አቡነ ቴዎፍሎስ ተደፈሩ በማለት ሳይሆን የኢትዮጵያ ቤተ ክርሰቲያን ፓትርያርክ ለማዘዝ እንኳን እኛ ደርግም ቢሆን (ንጉሡም ቢሆኑ) ሥልጣን ሊኖረው አይገባም፤ ክብሯ ክብራችንን ይነካል በማለት ነበር፡፡ አለቃ አያሌው ታምሩና እኔ በድምጽ ብልጫ ተሸነፍን፡፡ ሌላው ቢቀር ደብዳቤው ለስላሳ እንዲሆን ተሸቀዳድሜ እኔ ላርቅቀው አልኩ፤ አረቀቅሁት፡፡ ለስላሳ ቢሆንም (እንዴትስ ብቃት ያለው ለስላሳ ሊሆን ይችላል! ) ቅዱስ ፓትርያርኩ ሐሳባቸውን አላስለወጣቸውም፡፡ ‹በእኔ ፓትርያርክነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አትደፈረም› በማለት በጀግንነት መነኮሳቱን አጰጰሷቸው (ከሦስቱ ተሹዋሚዎች ውስጥ አንዱ ዶክተር አባ ጳውሎስ ነበሩ፡፡ ) ከዚያ በኋላ የሆነውን የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፤ ቅዱስ ፓትርያርኩም አዲስ የተሾሙት ጳጳሳትም ታሰሩ፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ አባቶቻቸው እንደነአቡነ ጴጥሮስ በጀግንነት በሰማዕትነት ሕይወታቸው አለፈች››

(ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፡ገ.202)::

3.2. ለአመክንዮ ምክንያት ለኃጢኣት…(ሰበበ-) ሞቱ ለቴዎፍሎስ!

3.2.1. የተሐድሶ ጉባኤውና የደርግ ጥምረት ፓትርያርኩን ለማውረድ በሚዲያ እየታገዘ 5 ድኩማን ምክንያቶቹን “ሲጠበቅ የቆየው ፍርድ” በማለት መዘርዘር ጀመረ፡፡ እንዲህ እያለ፡-

 1. ለፓትርያርክነት የበቁት የንጉሡ ወዳጅ ስለነበሩ በጥቂት መራጮች ድምጽ ብቻ ነውና ከስልጣን ይውረዱ፡፡
 2. ከሕገ ቤ/ክ ውጭ በካፒታሊስት መንፈስ በመነሳት ሕንጻ እያሰሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት አካብተዋል፡፡
 3. 20 የተለያዩ የሂሳብ ቁጥሮች በግል ስማቸው ከመክፈታቸውም በላይ በግል አሽከሮቻቸውና ወዳጆቻቸው ስም ብዙ የሂሳብ ቁጥሮች ከፍተው ባሁኑ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብር 4,029,350 ያንቀሳቀሳሉ፡፡
 4. በግል ፈቃዳቸውና ሥልጣናቸው 3 ጳጳሳትን ሾመዋል፡፡
 5. ከታሪክ ሲሸሹ የወደቁ፣ የወንጌልን ሥራ ትተው ወደ ጎን ገሸሽ ያደረጉ፣ የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበራትን ያፈረሱ፣ ቤ/ክ የቅርስ ደኃ ስትሆን ዝም ብለው የሚመለከቱ፣ ከቤ/ክ ሥርዓት ውጭ ሥጋ-አምላክን በማቀበል ሕገ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ያፈረሱ ናቸው አለ፡፡

3.2.2. ፓትርያርኩ አልፈጸሙዋቸውም እንጅ ፈጸሙዋቸው ቢባል እንኳ ከላይ የተዘረዘሩት ክሶች በአብዛኛው መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው በመሆናቸው በደርግ ዓደባባይ የሚታዩበት የሕግ ምክንያት አልነበረም፡፡ ከ10 አመት በላይ የእንደራሴነት አገልግሎት ልምድ ያላቸውንና ከ144 መራጭ የ123ቱን ድምጽ ያገኙትን አባት በንጉሡ ስለተወደዱ ብቻ እንዲህ ያለ ሰንካላ ምክንያት ሰጥቶ ማውረድ ታላቅ ኃፍረት ነው፡፡ እርግጥ ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም የተወሰኑ የእርሻ ቦታዎች ነበሯቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከደሞዝና ከእርሻ ያገኙት ገቢ የጀመሩትን የጎፋ ገብርኤል ሕንጻ እና የደብረ ኤልያስ እድሳት እንኳ ለማጠናቀቅ ስላላስቻላቸው ከዚህ ዓለም ሲያልፉ ያልተከፈለ ብድር ውስጥ ነበሩ፡፡ በጽ/ቤታቸው የተገኙ አካውንቶች በእሳቸውም ሆነ በማንም ዘመዳቸው ሥም ሳይሆኑ በመንፈሳውያን ተቋማት ሥም የተመዘገቡና በነሱ ኃላፊዎች ፊርማ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ቡኮች ነበሩ፡፡ ጳጳሳትን ስለመሾምም ደርግ ‹‹ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተለያይተዋል›› ብሎ ስላወጀ ይሕን መብት መጠቀማቸው ነበር ለደርግ ሳያሳውቁ 3ቱን መነኮሳት ማጰጰሳቸው፡፡

3.2.3. ሌሎቹ አስገራሚና ዛሬም ድረስ በተሐድሶዎች ፓትርያርኩ ተሐድሶ ተደርገው እንዲታዩ በር የከፈቱ ምውታን ክሶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-

 1. ከቤተ መቅደስ ውጭ ሥጋ ወደሙ እንዲሰጥ አድርገዋል፤
 2. በድንኳን እንዲቀደስ ፈቅደዋል፤
 3. ቅዳሴ በ2 ቀዳስያን እንዲካሄድ አድርገዋል፤
 4. በባሕታውያንና ተዘዋዋሪ ሰባኪዮች ላይ እቀባ ጥለዋል፤
 5. የበዓላትና አጽዋማት አዋጅ በቀኖና እንዲታይ አመራር ሰጥተዋል

የመሳሰሉ ጉዳዮች የፓትርያርኩን ሰቆቃዊ ግድያ ለምጽአተ-ተሐድሶ የተከፈለ መሥዋዕትነት ለማስመሰል የሚሽሞነሞኑ ክሶች ናቸው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ከ5 ባነሱ ልዑካን በድንኳን ውስጥ ተቀድሶ ሥርዓተ ቁርባን እንዲፈጸም የፈቀዱት በወቅቱ የጃማይካና ካሪቢያን ጥቁሮች ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያላቸው ውዴታ ወደ አምልኮ በመሸጋገሩ የተነሣ ይሕንን ለማስተው በተከታታይ አቡነ ሳሙኤል ቀዳማዊ እና አቡነ ይስሐቅ በሐዋርያነት ሲላኩ የካሕናትና የቤተ መቅደስ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ነበር፡፡ የበዓላትና የአጽዋማትን ቀኖና በሚመለከት መሠረታዊውን ሕገ ጾምና በዓላትን የማክበር ጉዳይ ሳይነካ ሲኖዶሱ ስለ ሥርዓተ-ጾምና በዓል አከባበር የመደንገግ ሥልጣን በፍትሐ ነገሥቱ ተሰጥቶታል፡፡ ይሕ ደግሞ በኋለኞቹ ብፁዐን አበው በነአቡነ ጎርጎርዮስ (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቶያን ታሪክ) ተወስቷል፤ ቤተ ክህነቱም በተደጋጋሚ በይፋ ጽፎበታል (የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ከል/ክ እስከ 2000 ዓ.ም፡ገ.37-38 እና 51-53)፡፡ ‹‹ሊቃውንትና ምዕመናን ከተወያዩበት በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ይወስናል›› ከማለት ውጭ አቡነ ቴዎፍሎስ ከዚህ የተለየ ያደረጉት ወይም ሥልጣን አለኝ ባለው ያወጁት ምንም አይነት ቀኖና አልነበረም፡፡ የለም! ግርግሩ ቂማቸውን ለመወጣት የተመቻቸው የዛን ጊዜዎቹ ሐሳውያን መነኮሳትና የዛሬዎቹ ቀሳጥያን ተሐድሶዎች ግን አጀንዳውን እንዳይሆን አድርገው ጠልፈው የፓትርያርኩን ሥም ባልዋሉበት አዋሉት፡፡ ይሄው እኛም እስካሁን ዝም ብለናል፡፡ ከአባቶች መካከል ግን የተናገሩ አሉ፡፡ ለአብነት ታላቁ አባት ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ምግባራቸው የቀና፣ ሃይማኖታቸው የፀና ስለነበሩ በዘመናቸው ለቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ጠቃሚ ሥራ ሠርተዋል›› ሲሉ የአቡነ ቴዎፍሎስን ርቱዐ-ሃይማኖት መሆን መስከረዋል በ1989 ዓ.ም በታተመው ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት መጽሔት፡፡

3.2.4. ተሐድሶዎችን ካነሳን በተደጋጋሚ የ1966ቱን የተሐድሶ ጉባኤ ልክ ዛሬ እነሱ የሚያራምዱትን መፍቀሬ-ፕሮቴስታንት ስመ ተሐድሶ ዘመቻ ለማከናወን የተቋቋመ በማድረግ ለማወናበድ ስለሚሞክሩ በጉዳዩ ላይ ትንሽ ልናገር፡፡ ይሕ ‹‹የተሐድሶ ጉባኤ/ጊዜያዊ ጉባኤ›› ይባል የነበረ ኮሚቴ ከአስተዳደራዊ ተሐድሶና በጊዜው ጭቁን የተባሉ ካሕናትን ሽፋን አድርጎ ርእሰ መንበር ለመለወጥ ከመንቀሳቀስ በቀር ሃይማኖታዊ ተሐድሶ ዐላማውና ግቡ አልነበረም፡፡ ይሕንንም በተሐድሶ ጉባዔው ሊቀ መንበር ዶ/ር ክነፈርግብ አስተባባሪነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ወርደው ከታሰሩ በኋላ እሳቸው በሕይወት እያሉ ፓትርያርክ ሆነው በተሰየሙት አቡነ ተክለሃይማኖት በዓለ ሲመት ከወጣው መጽሔት መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ መጽሔት ርእሰ አንቀጽ ‹‹የዛሬው ሹመት እንዳለፈው ጊዜ ለዝናና ለመታወቂያ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን በአመራር ተሐድሶ ላይ ስለሆነች የተጀመረውን የተሐድሶ ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ ለሕዝበ ክርሰቲያኑ ቃል ኪዳን የሚገቡበትና ቤተ ክርሰቲያንም አሁን ካለችበት የተመሰቃቀለ የአስተዳደር ሁኔታ ለማውጣት በሚያደርጉት ትግል እንዲረዳቸው ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚጠይቁበት ዕለት ነው›› ተብሎ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ 4 ዐላማዎች ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱ ‹‹በየጊዜው በሚለዋወጠው አዲስ ዓለም ፊት የማይለወጠውን ቃለ እግዚአብሔር በአዲስ ቋንቋ አቀራረብ ለመስበክ መቻል›› የሚል እንደነበረበት በዚሁ መጽሔት ገጽ 27 ተመልክቷል፡፡ የተሐድሶ ኮሚቴው አባል የነበሩት ፍቅረድንግል በየነ በጻፉት መጣጥፍ እንዲሁ ‹‹የጨበጥነው ዲሞክራሲያዊ መንፈሳዊ መብት ከእጃችን በምንም ምክንያት ሊወጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ የአስተዳደሩ ተሐድሶ ወደፊት ይቀጥላል›› በማለት ስለ አስተዳደር ተሐድሶ አወሱ እንጂ የቤተ ክርሰቲያኗ ዶግማና ቀኖና ይከለስ/ይታደስ ያለ ኮሚቴ አልነበረም፤ በፍጹም አልነበረም! ! ! የጉባኤው አባላት በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ባራመዱት አቋም ብንወቅሳቸውም በነገረ ሃይማኖት ረገድ አናማቸውም፡፡ ዕውቀት ክፋትን አታሸንፍ እንጂ ለመማሩስ ዘመናዊውን ከመንፈሳዊው ያስተባበሩ ነበሩ፤ ማዕተባቸውንም ጭርሱን እንደቀሳጢ ተሐድሶ አልበጠሱም፡፡

3.2.5. ስለዚህ ዛሬ ተሐድሶዎች ከአቡነ ቴዎፍሎስ ታሪክ ጋር ለመጣበቅ የሚያደርጉት ሙከራም ሆነ አንዳንድ ልበ-ደንዳና ወገኖቻችን በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የሚያቀርቡት የተሐድሶነት ሐሜታ ውሃ የማይቋጥር ምውት ክስ ነው፡፡ ጎጃም ላይ የነቢዩ ኤልያስን ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የሚያስውበው፣ አዲስ አበባ በመልአኩ ቅ/ገብርኤልና በነቢዩ ኤልያስ ሥም ቤተ ክርስቲያን የተከለው፣ የመዝሙረ ዳዊት አንድምታ በእጁ ጽፎ ያሳተመው፣ የኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ያዘጋጀው፣ ለሞቱ ግብጻውያኑ እነ አቡነ ሺኖዳ በአደባባይ የተብሰከሰኩለት፣ በሐረር-ዝዋይ-አዲስ አበባ-መቐለ፣ ወዘተርፈ የካሕናት ማሰልጠኛዎች መቋቋም አንገቱ ላይ ገመድ እስከተጠመጠመበት ቅጽበት የተራወጠው፣ በፕትርክና ጊዜው የተገኙ ጥሪቶች ለቀዳስያንና ሰዓታት ቋሚዎች መደገፊያ እንዲውሉ በቁሙ የተናዘዘው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የራሷ መንበረ-ፕትርክና እንዲኖራት ከአዲስ አበባ-ካይሮ ያለድካም በባሕርና በአየር ተመላለሰው፣ ወህኒ ሳለ መስቀሌንና ሥዕሌን አትንኩብኝ ሲል አሳሪዎቹን የተማጸነው፣ ዓቢይ ጾምን በጥልቅና ጥብቅ ቀኖና ሆኖ ያሳልፍ የነበረው ፓትርያርክ የሕይወት ታሪኩ ተቆርቋሪ ባለቤት አጥቶ በማንም ሥርዓት ዘርጣጭ ቁንጽል ተሐድሶ ሲቆነጸል ማየት እንዴት አያም?ወደ ውስጠ-ውስጥ የሚሰረስር ሕማም
ይሰማኛል፡፡ ከእነሱ ቀሳጢነት በላይ የኛ ቸልተኝነት ያመኛል፤ በጣም ያመኛል! ሰቆቃወ-ሰቆቃ ይሆንብኛል!

3.3. ቅትለተ-ሰብእና (character assassination)…ነፍሱ ሳትወጣ…!

3.3.1… አቡነ ቴዎፍሎስ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ.ም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከመንበራቸው ወረዱ፤ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ታሰሩ፡፡ በታሰሩ በ12ኛው ቀን የካቲት 21 ቀን 1968 ዓ.ም ከተሐድሶ ጉባኤ አባላት አንዱ የነበሩት መልአከ ሰላም ቀሲስ ዳኛቸው (በወቅቱ የመካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ አስተዳዳሪ) ለኅበረተሰባዊት ኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት የደስታ መግለጫ ደብዳቤ ጻፉ፤ በቤተ ክህነት መዝገብ ቤት የተሰነደው ደብዳቤ እንደሚከተለው ይነበባል፡-

‹‹ቀደምት አበው በጸሎትና በትሩፋት ያቆዩትን የምግባረ ሠናይ ውል አጥፍተው፣ ደገኛውን የቅድስና ክብር አበላሽተው፣ በየዋህነትና በቅን ኅሊና የሚከተላቸውን፣ በመንፈሳዊነት እንዲመሩት የሚጠበቅባቸውን መንጋ ከተመሳቀለ ጎዳና ላይ በትነው እንዲባዝን ያደረጉት፣ በሥጋ ምቾት ተውጠው የግፉዓን ካሕናትን፣ የንጹሐን ምዕመናንን ዋይታና እንባ ከምንም ሳይቆጥሩ በማናለብኝ የኖሩትን የአባ ቴዎፍሎስን ከ[መንበረ] ሥልጣን መነሳት የተቀበልነው ተገቢ ውሳኔ መሆኑን ከልብ አምነንበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ የታሪክ ገጽ ሰፊ የአገልግሎት ድርሻ ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ላይ [የተጠመጠመ] የተንኮል አሽክላ ስለወደቀላት የታሪክ ባለውለታነቷ እንዳልተዘነጋ መተማመኛ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ለጭቁኑ ሰፊ ሕዝብ ፍጹም የሆነ ነጻነትንና የልማት ቁልፍ ለማስጨበጥ የሚያደርገው ትግል መስመሩን ይዞ ከግቡ እንዲደርስ ቤተ ክርስቲያን በጾምና በጸሎት ያላትን ተባባሪነት በዚህ አጋጣሚ እናረጋግጣለን፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ተሐድሶ ጊዜያዊ ጉባዔም በተሰጠው አደራና ኃላፊነት የጀመረውን መንፈሳዊ ተግባር በጥንቃቄ እንደሚከታተል ልባዊ ዕምነታችን መሆኑን በደብሩ ካሕናትና በምዕመናን ሥም እንገልጻለን፡፡ ››፡፡

ይቺ ደብዳቤ ደርግና የተሐድሶ ጉባኤ የነበራቸውን ጥምረት ታሳያለች፡፡

3.3.2. አቡነ ቴዎፍሎስን ታስረው ገና በሕይወት እያሉ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተመርጠው በግዳጅ (እሳቸው በመንበሩ ለመሰየም ፈቃደኛ አልነበሩም) ተተኪ ፓትርያርክ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ የሲመታቸው ቀን እሳቸውን ለማወደስ ሳይሆን አቡነ ቴዎፍሎስን ለመክሰስ ብዙ የጋዜጣና የመጽሔት ቃላት ባከኑ፡፡ እንደየሥርዓተ-መንግሥቱ የሚያፋችለው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ትናንት ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሲሾሙ(ግንቦት 18 ቀን 1963 ዓ.ም) ‹‹…የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ማፋጠንና ዘመናዊ አድርጎ ማቅረብ ዋናው አብነት ነው፡፡ ለዚህም የጊዜውን አስተሳሰብ፣ የዘመኑን ዕውቀት፣ ያገሩን ኑሮ ሁኔታ…የያዙ የቤተ ክርስቲያን መሪና ካሕናት ያስፈልጋሉ፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መመረጥ የሚያጽናናው ለዚህ ነው›› እንዳላለ ዘመን ሲለወጥ ቃሉን ለወጠ፡፡ የቀደመ ቃሉን በ5ኛው ዓመት ፈጽሞ አጠፈው፡፡ ‹‹…ስለ 20ኛው ክፍለ ዘመን ሰፊ አስተያየት ያለው፣ በዓለም አቀፍ ጉባኤ ቢያቀርቡት በአለባበሱ የሚያኮራ፣ በአነጋገሩ የሚረታ፣ በዘመኑ ትምህርት የበቃ እየተባለ ከፊውዳሉ ሥርዓት ጋር እንደባልና ሚስት ተቃቅፈው፣ በልክ እንደተሠራ ጫማ ተስማምተው፣ እንደብቅልና ጌሾ ተዋሐወደው…›› እያለ በጸያፍ ቋንቋ መዝለፍ ጀመረ፡፡ ቅትለተ-ሰብእናሁ ለቴዎፍሎስ ቀጠለ!

3.3.3. በዚህ መካከል ጠባቂዎቻቸው የአፍሪካን ዋንጫ በመመልከት ላይ ሳሉ ‹‹ውጣ! ውጣ! ›› የሚል ድምጽ የገፋፋቸው አቡነ ቴዎፍሎስ ከእስር ቤት (ጃን ሜዳ ክብር ዘበኛ ቅጥር ግቢ ውስጥ) ወጥተው ያጋጠማቸውን ታክሲ አስቁመው ወደ ጎፋ ገብርኤል ያመራሉ (አሐዱ ሳቡሬ ለኢሳቱ ሲሳይ አጌና በዚህ በኩል እንዳጫወቱት)፡፡ ደርግ በሔሊኮፍተር የታገዘ አሰሳ ይጀምራል፡፡ አሰሳውን በሚመለከት ሻለቃ ጌታቸው የሮም የተባሉ የአሰሳው ተሳታፊ ‹‹የለውጡ ረመጥ፡የታሪክ ማስታወሻ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ስለተረኩልን ሥዕላዊ መልኩን
(የአሰሳውን) ይገልጽልን ዘንድ ሳልነካካ ላቅርበው፡፡

‹‹እኔና የሥራ ጓደኛዬ ቢሮ ተቀምጠን ስለ ሥራ ጉዳይ በመወያየት ላይ እንዳለን ከጠዋቱ አራት ሰዓት ሌ/ኰ ዳንኤል አስፋው ስልክ ደውሎ የሥራ ጓደኛዬን አነጋገረው፡፡ ዳንኤልም ሲናገር ‹አብዮታችን ካጋጠመን ሁኔታዎች ውስጥ እንደዛሬ ሆነን አናውቅም፣ ያ የማይረባ ቄስ ከታሰረበት ጠፍቷል፡፡ ወዴት እንደሄደ አናውቅምና እናንተም በፍለጋውው ተባበሩን› አለ፡፡ የሥራ ጓደኛዬም የጠፋው ማን እንደሆነ ስላልገባው ዳንኤልን ጠየቀው፡፡ ‹ፓትርያርኩ ነዋ! › አለ፡፡ ቀጥሎም ‹አገሩ ጎጃም ስለሆነ ወደዚያው ሊሄድ ይችላል፡፡ በሔሊኮፕተር ወይም በትንሽ አውሮፕላን ካገር ሊወጣ ይችላል ብለን ስለምንገምት የጥበቃ ቦታዎችን ሁሉ አጠናክሩ› አለ፡፡ …የፓትርያርኩ መጥፋት የምንደግፈው ስለነበረ በጎጃም አቅጣጫ የሚደረገው ፍለጋ በሬዲዮ እንዲተላለፍ አላደረግንም፤ ነገር ግን ፍቼ፣ ገብረ ጉራቻ፣ ጎሐ ጽዮን በተባሉት ከተሞች እየደረስን በዕለት ሁኔታ በመመዝገብ አባሎች ፍለጋውን እንዲቀጥሉ ካደረግን በኋላ በዚያው አካባቢ ስንዝናና ዋልን፡፡ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ከዳንኤል ጋር ለመነጋገር ሬዲዮ ከፍተን ጥሪ ስናደርግ በደስታ ተውጦ ‹ያ ቀጣፊ ቄስ አረፋ አስደፍቀን ያዝነው፤ እዚሁ በአዲስ አበባ ጎፋ ሰፈር እራሱ በሠራው ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሸጉጦ ባሳደገው በራሱ አሽከር ጥቆማ ተያዘ፤ ስለተባበራችሁን አመሰግናለሁ› አለና ሬዲዮኑን ዘጋው፡፡ በፓትርያርኩ መያዝ እኛ ብቻ አይደለንም የተበሳጨነው፡፡ አያሌ ወታደራዊና የሲቪል አባሎችን ሁሉ አሳዝኗል፡፡ …ስለ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ጉዳይ ለሻለቃ ዮሐንስ [የደርግ ምርመራ ሹም የነበረና ኋላ ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም በነበረው የደርግ ክፍፍል ሌ/ኰ ዳንኤልን ገድሎ ራሱን ያጠፋው ነው ሻለቃ ዮሐንስ ማለት] ስናደርግ የዋልነውን ፍለጋ አስረድቼው ነበር፡፡ እሱም በጣም ተናደደ፡፡ ከኔም ሆነ ከዳንኤል የተሻለ ጉዳዩን ያውቀዋል፡፡ ዮሐንስም እንዲህ አለ፣ ‹ያዋረዱት ራሳቸውን ሳይሆን ሁላችንንም ነው፤ እንደደረስንበት ከሆነ መውጣት ይችሉ ነበር፡፡ አሁን የዳንኤል መጫወቻ ሆኑ፡፡ በባዶ እግራቸው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፤ ጸጉራቸው ተላጭቷል፤ ቁምጣ አስለብሷቸዋል፤ እጃቸውንና እግራቸውን አጣምሮ አስሯቸዋል፤ ወደፊትም ሊገላቸው ይችላል› አለና ስሜቱን ገለጠልኝ››

(ሻለቃ ጌታቸው የሮም፣ የለውጡ ረመጥ የታሪክ ማስታወሻ፡ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም፡ገ.60-62)::

3.4. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ…ጊዜ-ሞቱ … ሞትህ ደጅ አደረ!

3.4.1. አቡነ ቴዎፍሎስ በሌ/ኰ ዳንኤል ተይዘው ወደ እስር ቤት ሲገቡ የነበራቸውን ሁኔታና የእስረኛውን ትካዜ አቶ አበራ ጀምበሬ ተርከውልናል፡፡ ትረካቸውን ልዋስ፡-

‹‹በታላቁ ቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ንጹሕ አየር ለማግኘት፣ በፀሐይ አካላቸውን ለማሞቅ፣ የተሳሰሩ እግሮቻቸውን ለማፍታታት በዙፋን አዳራሽ አጠገብ በሚገኝ በሽቦ በታጠረ ጠባብ ክፍል ውስጥ ይንከላወሳሉ፡፡ ቀኑ መጋቢት 3 ቀን 1968 ዓ.ም ከእኩለ ቀን በኋላ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታላቁ መንፈሳዊ አባት ሁለት እጆቻቸው በአንድ ላይ በሰንሰለት ታስረው እየተገፈተሩ ያለመጫሚያ በባዶ እግራቸው ሲመጡ የተመለከቱት እነዚያ እስረኞች ባሉበት ክው ብለው ቀሩ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር አንዱ እስረኛ ልቡ ተነክቶ ‹አዲዮስ! የኢትዮጵያውያን ሰብአዊነትና መንፈሳዊነት! › ያለው፡፡ ‹…የኢትዮጵያ ሕዝብ ግብረ ገብነትና መንፈሳዊነት በእነዚህ ጋጠ ወጦች አይለካም› አለ ሌላው–በድርጊቱ መብገኑን ሁኔታው እየነገረበት፡፡ …ያደፈ ሽሮአማ ቀሚስ እንደለበሱ ከቀኝም፣ ከግራም፣ ከኋላም ሳንጃ የተሰካበት ጠብመንጃ ተደግኖባቸው ወደዚያች የፖለቲካ እስረኞች መቀየጃ ቅጥር ሲገቡ መንፈሳዊው አባት ‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው› በማለት የሚጸልዩ እንጂ የተበሳጩና የተሸበሩ አይመስሉም ነበር፡፡ እስረኛው ከድንጋጤው ገና ሳይላቀቅ፣ ምን እንደሚልና እንደሚናገር አሰላስሎ ሳይጨርስ፣ ከቆመበት ሳይላወስ ነበር ከአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ አስገብተው የቆለፉባቸውና እግራቸውን በእግረ ሙቅ፣ እጃቸውን በሰንሰለት ጠፍረው ካልጋ ጋር ያሠሯቸው፡፡ ‹ይሕን አዚመኛ ቄስ ተጠንቅቃችሁ ጠብቁ› በማለት ለወታደሮች ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቶ የዘቡ አዛዥ ከአጥሩ ወጥቶ ሄደ››

(የአቶ አበራ ጀምበሬ ‹‹የእስር ቤቱ አበሳ›› በዜና ጳጳሳት መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፡ገ.58-59)::

3.4.2. ፓትርያርኩ በዚህ መልኩ በጾምና በቀኖና ተወስነው ለ3 ዓመታት በእስራት ከቆዩ በኋላ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም ከሌሎች 33 ታሳሪዎች ጋር በሞት መልእክተኞች ተጠሩ፡፡ ተሰለፉ፡፡ በተራቸው ገቡ፡፡ ወደ ጨለማው ቤት ውስጥ ገቡ፡፡ የተለያዩ ኮሪደሮች ባሉት የጨለማ ቤት ውስጥ ጥግ ላይ ያለው ሰው ‹ና› አላቸው፡፡ ወደሱ አተኩረው ሲራመዱ በጨለማው ኮሪደር ለግድያ ካሸመቁ ሰልጣኝ ኮማንዶዎች አንዱ ሳያስቡት በሲባጎ አነቃቸው፡፡ ኮማንዶው ሲባጎውን በሁለት እጆቹ ጠምጥሞ አጥብቆ በአንገታቸው ላይ ካጠለቀ በኋላ ገመዱን በመሸረብና በማሳጠር በስተመጨረሻ ፓትርያርኩን በገመዱ እንደታነቁ የእንግላሊት ጀርባው ላይ አውጥቶ በአንገታቸው የገባውን ገመድ በእጁ እየጠቀለለ በማሳጠርና በማጥበቅ ትንፋሻውን ቋጨ፡፡ አስከሬናቸውን ጎትቶ ከሌሎች እስረኞች ጋር ሸራ አለበሰው፡፡ ማታ ሦስት ሰዓት ኖራ ተነስንሶባቸው ከ33ቱ እስረኞች ጋር በጅምላ በአንድ ጉድጓድ ተቀበሩ፡፡ ከፓትርያርኩ ጋር አብረው ከተቀበሩት ሰዎች አንዱ የመኢሶኑ የአመራር አባል ኃይሌ ፊዳ ነበር፡፡ አብዮተኛው ባለብሩህ ጭንቅላት ወጣትና ባለራዕይው አረጋዊ ፓትርያርክ በአንድ ጉድጓድ ተጣሉ፡፡ (ርዕዮተ ዓለሙ ዛሬ ባያማልለንም! ) እሱ ከአውሮፓ ለአዲስ ሥርዓት ለውጥ መጥቶ እሳቸው ከነበሩበት መንበር በግፍ ተገፍተው ባንድ ጉድጓድ ተቀበሩ፡፡ ታዋቂው ገጣሚና መፍቀሬ-መኢሶን የሚባለው ዮሐንስ አድማሱ
‹‹ዕንባሽ›› በሚለው ግጥሙ፡-

ዘመን ቢያርቃችሁ፣
ሥፍራ ቢለያችሁ፣
ዕንብ አገናኛችሁ፡፡

ያለው በዚያ ዘመን ልጆቿ ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግሥት እየተነዱ በገዳዮቻቸው ለተፈጁባት ኢትዮጵያና ለግፉዓን ልጆቿ ሙሾ ሆኖ ይስሰማኛል!

3.4.3. አቡነ ቴዎፍሎስ 2ኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ሀገር ውስጥ በራሳችን አባቶች በመሾም ግን የመጀመሪያ ናቸው፡፡ የጀመሩት ነገር የመብዛቱን ያህል ሰቆቃቸውም በብዙ መልኩ የመጀመሪያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በራሳቸው ወንድሞች ተላልፈው ተሰጥተው በገዛ ወንድሞቻቸው ታንቀው የተገደሉ ቀዳሚ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ለቀረበባቸው ክስ የማስተባበል እድል ተነፍጓቸው፣ ማዕረጋቸውን የሚገልጹ አልባሳትና ንዋያተ-ቅድሳት ሁሉ እንደምርኮ ተቆጥረው ተገፈው በግፍዕ የወደቁ እሳቸው ናቸው፡፡ ሲሞቱ ለቅሶአቸውን መድረስ አልተቻለም፤ ሞታቸውም በገሀድ አልታወቀ፡፡ በጊዜው ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ፓትርያርኩ አስከሬን ማሳረፊያ ቦታ አልነበራትም፡፡ ሥማቸው እንደ ማንኛውም አማኝ ያሕል በጸሎ-ፍትሐት እንዲጠራ ልተፈቀደም፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ወጣትነታቸውን፣ ጉልምስናቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ነጻነቷን ወደ መንበረ-ፕትርክና አሳድጋ እንድትራመድ የደከሙት ቴዎፍሎስ እንዲያ ተሸኙ፤ ዘለላ ዕንባ፤ አንድ መስመር ዳዊት ሳይደገምለቻው ተሸኙ፡፡ ሊቁ ይሕን ሰቆቃ ለመወጣት ማርገጃ ቢከለከል በጋቢው ተጀቡኖ አንብቶ ከዕንባው ሰምና ወርቅ ቋጠረ፡፡ የቋጠረውን የሰቆቃ ሥላሴ ቅኔ ከ13 ዓመታት በኋላ ዐፅመ-ቴዎፍሎስ ሚያዚያ 23 ቀን 1984 ዓ.ም በቁፋሮ ወጥቶ በቅ/ማርያም ቤ/ክ ዐርፎ፣ ሐምሌ 3 ቀን ጸሎተ ፍትሐት ተደርሶለት በማግሥቱ ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም ወደማረፊያው ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ ሳጥኑ በጳጳሳት ትከሻ ተይዞ ሲፈልስ ከዕንባው ጋር ቅኔው አፈሰሰው፡፡ ‹‹ቴዎፍሎስ! ምሕረት በጠፋበት ዘመን ተገኘህና ሞትህ ደጅ አደረ! ›› ብሎ ቅኔውን ከዕንባው ጋር ዘራው፡፡ እንስማው፡-

ምሕረት፤ ኀበ-አልቦ፤
ወኀበ-ፈድፈደ፤ እከዮሙ፤
ለሰብአ-ዛቲ፡ሀገር፤ ዘወለዶሙ፡ይሑዳ፣
ኀደረ፤ በአፍአ፤ ሞትከ፡እንግዳ፣
ቴዎፍሎስ፡ሊቅ፤ ለባሴ-መስቀል፡ፀዐዳ፡፡
አመሰ፡አልጸቀ፤ ዓመተ-ፍዳ፣
ለትሑት፡ሥጋከ፤ ነቢየ-ጋዳ፣
አክበርዎ፤ ለምሕረት፤ ውሉዳ፡፡

ሊቁ ይሕን ይበል እንጂ የቴዎፍሎስ ዐፅም ዛሬም እረፍት አላገኝም፡፡ በአንድ በኩል ጃማይካውያን በሌላ በኩል እነ አቡነ መልከጼዴቅና ኮ/ል ፍስሐ ደስታ ያላንዳች ርኅራኄ ራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ያሉትን አባት እንደ ኢሕአፓና መኢሶን አጸፋ የሚሰጥላቸው የመደብ ጀርባ እንደሌላቸው በማየት ያልተገባ-ያልተገባ ቃለ-ግፍዕ ይጽፉባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ቀስቃሽ ምክንያት ይኼው ዐፅም ወቃሽ ሐተታ በመብዛቱ ነው፡፡ ራሱን አስችለን እንየው፡፡

3.5. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ…ድኅረ-ሞት!

ይሕን ቅሬታ-መራሽ ርእስ በምወደው ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን፡‹‹እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ›› የተሰኘ ግጥም ቀንጭቤ ልጀምር፡፡ ቅሬታዬ በአቡነ መልከጼዴቅና በኮ/ል ፍስሐ ደስታ ላይ ያነጣጥርና ጃማይካውያንን በእግረ መንገድ ብቻ ዳስሶ ያልፋል፡፡ ባለቅኔው ይቅደም፡-

…ዝም አልኳቸው፤ ዝም ይበሉኝ፣
ትቻቸዋለሁ፤ ይተውኝ፣
አልነካቸውም፤ አይንኩኝ፣
…ብለህ እንዴት ትመኛለህ፤ እንደማይተውህ ስታውቀው?
የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፤ የወጋ መች እንቅልፍ አለው፡፡

3.5.1. የአቡነ መልከጼዴቅ ቃላተ-ግፍዕ በአጽመ ቴዎፍሎስ ላይ!

3.5.1.1. በጉባኤ ቤቱም፣ በበባሕር ማዶ ቲዎሎጂውም ቀድመው ከተማሩት ወገኖች ሆነው ሳለ፣ አያሌ ትውልድ ያነጹ መጻሕፍትን መጻፋቸው ሳይካድ፣ ወጣቶች በተለይ ሴቶች በቤተ ክርሰቲያን ያላቸው የአገልግሎት ተሳትፎ ከፍ እንዲል መድከማቸው እየታመነ፣ በልዩ ልዩ የመገናኛ ስልት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ በብዙ ደክመው፤ በስተመጨረሻ ግን በዕርግናቸው ወራት የደከሙበትን ሁሉ የኋሊት እያስኬዱ ሆነው የሚታዩኝ አረጋዊ አባት አሉ፡፡ አቡነ መልከጼዴቅ! የአቡነ መልከ ጼዴቅ የቅርብ ዓመታት ሪከርዶች በአንድ ቃል ይጠቃለላሉ! -እልህ-! የራሳቸውን ስደት በቴዎፍሎስ ሰማዕትነት አንጻር ሲያዩት ኅሊናቸውን ሳይጋፋቸው አልቀረምና በእልህ ፓትርያርኩ ቀ.ኃ.ሥ ሲወርዱ መቃወም ነበረባቸው እያሉ አጽማቸውን ይወርፋሉ፡፡ እንዲህ እያሉ

‹‹የፓትርያርክነት ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ እርሳቸው እንዲመረጡ ትእዛዝ ሲሰጡ፣ አስተያየት ሲያቀርቡላቸው የነበሩትን ንጉሠ ነገሥት በመክዳት ከዙፋናቸው ሲወርዱ፣ በአረመኔዎች ብዙ እንግልት ሲደርስባቸው ዝም ብለው በማየታቸው…በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የአባትነት ስማቸው ጠፋ››

(የቋሚ ምስክርነት፡ገ.56)::

ይሕ ‹ዐፅም ወቃሽ፣ መቃብር ፈላሽ› አነጋገር በወቅቱ ሀገሪቱና ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ የነበሩበትን ሁኔታ ከነባሩ ትውፊት ጋር በማጣጣም ረገድ ዓቢይ ጉድለት አለበት፡፡ ጉድለቱን ለማሳየት ልውተርተር!

3.5.1.2. እውነት ነው፤ የሀገራችን ኦርቶዶክሳውያን ነገሥታት የሥልጣናቸው ሕጋዊነት (Legitimacy) የሚመነጨው ከሕዝብ ነጻ ፈቃድ ሳይሆን እንደማንኛውም ንጉሣዊ አአስተዳደር ከሐረገ-ትውልድ ቆጠራና በእደ-ጳጳሳት ከሚከናወን ቅብዐ-መንግሥት ነው፡፡ ንጉሡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት እንደሚፀና፣ ሕዝቡን በርኅራኄና በትዕግሥት እንደሚያስተዳድር፣ ሕግ አክብሮ እንደሚራመድ፣ መንፈሳዊና ሥጋዊ ትምህርት እንዲስፋፋ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በጳጳሱ ፊት የመሃላ ቃል ይገባል፡፡ ጳጳሱ/ፓትርያርኩ በበኩሉ ‹‹ለግርማዊነትዎ አገልጋይ መሆኔን ስገልጽ በፊትዎ የታመንሁና እውነተኛ ነኝ፡፡ ሃይማኖትና እውነትም ይመሰክሩልኛል፡፡ …በሕግ ለታወቁት ለወራስያነ መንግሥት ፍጹም ታዛዥ ሆኜ አገለግላለሁ›› ሲል ቃል ይገባል፡፡ ግብጻዊው አቡነ ቄርሎስ አጼ ኃይለሥላሴን ቅብዐ-መንግሥት ሲቀቡ እንዲሁም አቡነ ባስልዮስ ግብፅ ሲመተ-ፕትርክና ተፈጽሞላቸው ሲመለሱ በዚህ ዐይነት የግራ ቀኙ መሃላ ተደርጓል(ዝክረ ነገር፡ገ.527 እና ዝክረ ባስልዮስ፡ገ.172)፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ሲመጡ መሃላውን የፈጸሙት የተለየ ውለታ ስለተደረገላቸው ወይም ብቃት ሳይኖራቸው በችሮታ በንጉሡ ስለተሾሙ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱ ግድ ስለሚል ነው፡፡ ያም ሆኖ አቡነ ቴዎፍሎስ ይሕን ቃል ኪዳን አፈረሱ የሚያሰኝ ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ምስክር አከታትለን እንቁጠር!

3.5.1.3. ኮ/ል ፍስሐ ደስታ ደርግ ሲመሰረት ስለነበረው ሁኔታ ‹‹አስተባባሪ ኮሚቴው ሰኔ 26 ቀን [1966 ዓ.ም] የተለያዩ መለዮ ለባሾችን የሚወክሉ አባላትን ንጉሡ ዘንድ በመላክ በኮሚቴው ሥም ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ያለውን ታማኝነት በመግለጽ አምስት ጥያቄዎችን›› እንዳቀረበ ይገልጻሉ፡፡ ንጉሡም በምላሹ ‹‹የተቋቋመው ደርግ ከአሁን በፊት ከመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር የጀመረውን ግንኙነት እንዲቀጥል ፈቅደናል›› በማለታቸው ደርግ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለውን መፈክሩን በተከታይ ቀናት ይፋ ያደርጋል (ፍስሐ ደስታ፡ገ.81)፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ትቅደም›› ዐላማዎች ተብለው በደርግ ሐምሌ 1 ቀን 1966 ዓ.ም ከተብራሩ 13 ነጥቦች ውስጥ በ3ኛነት የተቀመጠው ደርጉ ‹‹የሚያስረው በደል የሠሩትን ባለሥልጣኖች እንደሆነና የሚይዛቸውም በሕግ መሠረት(?) እንደሆነ፣ በተረፈ ሁሉም ሰው በሥራው እንዲረጋ›› የሚጠይቅ ሲሆን በዚህ ማብራሪያ በ1ኛነት የተቀመጠው የኢትዮጵያ ትቅደም ነጥብ ግን አሁንም ‹‹ደርጉ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ እንደሆነ›› የሚገልጸው አንቀጽ ነው (አንዳርጋቸው አሰግድ፡ገ.159)፡፡

3.5.1.4. ‹‹…ደርጉ…መግለጫዎች ባወጣ፣ ሰዎችን ባሰረና ንብረት በወረሰ ቁጥር የማይተማመን ባለንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንዲሉ ለግርማዊ ጃንሆይ ታማኝነቱን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ወደኋላ አላለም›› (ፍስሐ ደስታ፡ገ.86)፡፡ ‹‹ሻለቃ መንግሥቱ…አስተባባሪ ኮሚቴው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ላይ ‹ሀገሩንና ንጉሠ ነገሥቱን የሚወደው ሕዝብ…ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ የሆነው ሠራዊት …› የሚሉ ሐረጎች እንዲገቡበት አደረጉ፡፡ ‹ጅብ እስከሚነክስ፣ ያነክስ› እንዲሉ›› (ነበር፣ ክፍል አንድ፡ገ.26)፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በደርግ ያላቸው በየዋሕነት የተሞላ እምነት እስከምን ድረስ እንደነበረ ለመረዳት የወቅቱ የፖለቲካ ተዋንያን፤ ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ የፖለቲካ አስተዋይነት መዳከሙ በገሀድ የተከሠተው ባለሥልጣናት እየታፈሱ ሲታሰሩ አንዳችም ተቃውሞ ለማሰማት አለመሞከራቸው ነበር፡፡ … [ደርጎች] አንድ ሰው ባሰሩ ቁጥር እርምጃውን በንጉሠ ነገሥቱ ሥም እንዳደረጉ ወዲያውኑ ያስታውቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱን ከማስደሰቱም በላይ ልዕልት ተናኘወርቅ ሠራዊቱን በሚኰንኑበት ጊዜ ንጉሡ የወታደሩን ታማኝነት በማመስገን ተናኘወርቅን ይሳደባሉ›› ያሉትን ማመሳከር ነው(ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ-1፡ገ.164)፡፡

3.5.1.5. በወቅቱ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ ሜ/ጄነራል ታፈሰ ለማና የንጉሡ ዋና እልፍኝ አስከልካይ ሌ/ጄነራል አሰፋ ደምሴ ደርጉ ስብሰባ ላይ እንዳለ ለማሳፈን እቅድ ነድፈው ንጉሡን ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ‹‹ደርግ ለሳቸው ታማኝ መሆኑን በተደጋጋሚ ስለገለጸ›› እቅዱን ውድቅ አድርገውታል፡፡ ‹‹ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው ባለሥልጣናቱ ከጉያቸው ተወስደው ሲታሰሩ፣ ተቋሞቻቸው ሲፈራርሱ እራሳቸውን የደርግ መሪ አድርገው በመቁጠር ምንም አይነት ተቃውሞ አላሰሙም›› (ፍስሐ ደስታ፡ገ.91 እና 98)፡፡ ደርግ በዚህ መልኩ የንጉሡን ሥም ተጠቅሞ በዙፋናቸው ዙሪያ ያሉትን አዕማደ-ሥልጣን ተመልሰው እንዳይቆሙ አድርጎ ከነቀነቀ በኋላ ጳጉሜ 5 ቀን 1966 ዓ.ም ንጉሡን ለማውረድ የወሎን ረሀብ የሚያሳይ ፊልምና የንጉሡን 80ኛ ዓመት የሚያሳይ የቴሌቪዥን ፊልም አቀረበ፡፡ ትርኢቱ እንዳበቃ አዲስ አበባ ‹‹ንጉሡ ዛሬ ይውረዱ›› በሚል ሰልፈኛ ተናጠች (ገስጥ ተጫኔ፣ ነበር፣ ክፍል አንድ፡ገ.58)፡፡ ይሕ በሆነ በ3ኛው ቀን ሻለቃ ደበላ ዲንሳ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ለንጉሡ በአልጋ ወራሻቸው ተተክተው ከዙፋናቸው መውረዳቸውን ገልጾላቸው፡እሳቸው በምላሹ ‹‹…የኛ ከአስተዳዳሪነት መወገድ ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ከተባለ የተነበበውን ተቀብለነዋል…›› አሉ(ዝኒ ከማሁ፡ገ.60)፡፡ አምባሰደር ብርሃኑ ድንቄ እንዳሉት ‹‹አጼ ኃይለሥላሴ ራሳቸው ራሳቸውን ከዙፋን ገለበጡ›› (ብርሃኑ ድንቄ፣ ቄሳርና አብዮቱ፡ገ›67)፡፡ ሰፊው ሕዝብም ትናንት ‹‹የጠቅል አሽከር›› ብሎ እንዳልፎከረ ‹‹ሌባ! ሌባ! ›› ብሎ የመጨረሻውን ንጉሥ ሸኘ፡፡

3.5.1.6. እንግዲህ አቡነ መልከጼዴቅ አጽመ-ቴዎፍሎስን እረፍት የሚነሡ በዚህ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የንጉሡ ቡራኬ ባልተለየውና ባልጋ ወራሽ ሰበብ ተደርጎ በተሠራ ረቂቅና እያሳሳቀ ወሳጅ የራስ በራስ መፈንቅለ-ዙፋን ‹ፓትርያርኩ ከንጉሡ በላይ ለንጉሡ ተቆርቁረው ለምን ዙፋኑን አላዳኑም› በማለት ነው፡፡ አባታችን አቡነ መልከጼቅ ምናልባት በጊዜው ለራሳቸውም ታሳሪ ስለነበሩ የለውጡን ወላፈን መረዳት አልቻሉም፤ ወይም ለአቡነ ቴዎፍሎስ የሚሆን የርኅራኄ ልብ የላቸውም፡፡ እንጂማ ንጉሡ ራሳቸው ሂደቱን በይዋሄ መርተው የሥልጣናቸውን ውል በአደባባይ፣ ሕዝብ እየሰማ፣ እየተመለከተ ‹‹…የኛ ከአስተዳዳሪነት መወገድ ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ከተባለ የተነበበውን ተቀብለነዋል…›› ካሉ በኋላ አቡነ ቴዎፍሎስ እንዲያከብሩት የሚጠበቅ የቃል ኪዳን ሰነድ አልነበረም፡፡ ‹‹ባለውሉ ያፈረሰውን ውል ዋሱ ሊያስቀጥለው አይችልም››! ! ! መፈንቅሉ ሲደረግ የሥልጣን ወራሽ የተባለው ደርግ ሳይሆን ዋናው የንጉሡ አልጋወራሽ ነበሩ መዙፋኑ የታጩት–ኋላ ደርግ የሕዝቡን ስሜት ተከትሎ መስከረም 5 ቀን አዋጁን ቢሽረውም፡፡ ይልቅስ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ እንደ ተረት ያለ ታሪክ ነው–ብሂል፡፡ ጃንሆይ ዘውድ ሲደፉ ዙፋኑ ከልጅ ልጆቻቸው እንዳይወጣ የየጠቅላይ ግዛት ተወላጅ መሳፍንትን በእማኝነት ያስፈርማሉ፡፡ የጎጃሙ ራስ ኃይሉ ለፊርማው ዳተኛ ሆኑ፡፡ ኋላ ተወቅሰው ተጠሩና ሲሄዱ ‹‹እኔስ ለመፈረሙ እፈርምላቸዋለሁ፤ ግን እግዚአብሔር ፈርሞላቸው ይሆን?›› አሉ ይባላል፡፡ እሱ ካላለው በጳጳስና በፓትርያርክ ውግዘት ብቻ መንበር አይፀና! የወደደውን በመንበሩ የሚያስቀምጥ እሱ! ለዚህ ነበር አካል ጉዳተኛ አይነግሥም ሲባል ኖሮ ባለአንድ እጁ ዮሐንስ 2ኛ (በ1761 ዓ.ም) ለመንበር ቢታጩ፡-

…ጊዜያትሂ፡አዕላፈ፤ እመ-መከሩ፡አዕላፍ፣
አንተ፡ዘኃለይኮ፤ ወዘወሰንኮ፡ኢይተርፍ፡፡

ማለታቸው ለዚህ ነበር፡፡ በብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያት፣ በራሱ ሂደት መንበሩን ለለቀቀ ሥርዓት አቡነ ቴዎፍሎስን ምክንያተ-ድቀት አድርጎ፣ ያውም አሜሪካ ላይ ከትሞ በዚያ ነዲድ ጊዜ፣ በዚያ ኢትዮጵያዊ ምግባር በጎደለበት ዘመን በራሳቸው ወገኖች በገመድ በታነቁት አባት ላይ ፍርድ ማዥጎድጎድ ያሳምማል፡፡ ቅር ያሰኛል፡፡ በአባታችን አቡነ መልከጼዴቅ ተደጋጋሚ ዐፅመ-ቴዎፍሎስን እረፍት የነሱ ቃላት ቅር ብሎኛል፡፡ 3.5.2. የራስ ተፈሪያንስ የስሚ-ስሚ ወቀሳ-ቴዎፍሎስ! የራስ ተፈሪያኒዝም ምዕመናን/ምዕመናት ጃማይካውያን ወንድሞቻችንም የነ አቡነ መልከጼዴቅ አይነቱን ሐሜታ እየሰሙ ‹‹ቴዎፍሎስ ይሑዳ! አምላካችንን አሳልፎ ሰጠው! ›› የሚል ዶክመንተሪ እንዲህ በትነዋል፡፡ ያሳዝናል ከማለት በቀር አንወቅሳቸውም፡፡ ‹‹ሥም ይወጣል ከቤት፣ ይከተላል ጎረቤት››! እኛ ያላከበርናቸውን አባት ኦርቶዶክሳውያን መነኮሳትን ካረቢያን ድረስ ልከው ‹‹ጃንሆይ አምላክ አይደሉም›› እያሰኙ ቃለ-ወንጌል እንዲዳረስ ያደረጉባቸው ‹‹ምዕመናነ-ጃንሆይ›› እንደ አባት እንዲቀበሏቸው አንጠብቅም፡፡ ከላይ ለአቡነ መልከጼዴቅ የተጻፈውን ሐተታ ‹‹ዝኒ ከማሁ›› ብለን ለጃማይካውያኑም ከመጥቀስ በቀር ጊዜና ወረቀት አናባክንም፡፡ ባይሆን ወደሌላ የዐፅመ-ቴዎፍሎስ ወቃሽ የራሳችን ወንድም (አባት) እናልፋለን፡፡

3.5.3. የኮ/ል ፍስሐ ደስታ የተዛነፈ ትዝታ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ!

3.5.3.1. አስቀድሞ ለኮ/ል ፍስሐ ደስታና ለደርግ የድርሻቸውን…ምስጋና!

3.5.3.1.1. ኮ/ል ፍስሐ ደስታ በስክነት፣ መጻሕፍትን በጥልቀት በማጣቀስ፣ በይቅርታ መንፈስ፣ ለሰዎች የሚገባቸውን የሥራ ዋጋ በመስጠት፣ (በአንጻራዊነት) ፍትሐዊ ሆነው ለጻፉት ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› መጽሐፍ ክብር አለኝ፡፡ ለምሳሌ፡- የጄ/ል አማን ሚካኤልን በሐሜት ያልደበዘዘ ኢትዮጵያዊነት፣ የኰ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምን በሶማሊያ ጦርነት፣ በመሠረተ ትምህርት፣ በመሬት አዋጅ የታዩ በጎ አስተዋጽኦዎችን ያለስስት እውቅና መስጠት፣ ቀ.ኃ.ሥ ከዙፋን ወርደው ወደ ቮልስ ሲገቡ የሕዝቡን ‹‹ሌባ! ሌባ! ›› ማለት መተቸት፣ ለ60ዎቹ ያለፍርድ በደርግ የተገደሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት እና ለግንቦት 8 መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ግድያ ርኅራኄን መግለጽ ከእሳቸው (በጉጉት) ስጠብቅ ያገኘኋቸው ስለሆኑ ደስ ብሎኛል፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ተንበርካኪነት መስሎ በሚታይበት ሀገር ይኸን ተግባር ደፍሮ በአደባባይ መከወን ታላቅነት ነው! በመጽሐፋቸው ማንም በሐሜት ሊያደብዝዘው የማይችል ኢትዮጵያዊነት እንዳላቸው በተለያየ መንገድ ስለተረዳሁ ለዚህም አደግድጌ እጅ እነሳለሁ፡፡

3.5.3.1.2. ደርግም ቢሆን የመከልከል ሥልጣኑ በእጁ ሆኖ ሳለ ለቤ/ክ የ4 ሚሊዮን ብር ድጎማ መፍቀዱ፣ ድኻ ቀሳውስት (በተለይ በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ የነበሩ በአብዛኛው ‹ቶፋ› የነበሩ ፈላስያን ቀሳውስት) እንደ ዜጋ የእርሻ መሬት እንዲደርሳቸው በማድረጉ፣ የተወሰኑ አብነት መምህራንን በትምህርት ሚኒስቴር ስር አድርጎ ፔሮል አስገብቶ ወርኃዊ ደሞዝ ማውጣቱ፣ በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ካሕናትን ማሳተፉና ኋላም በዘመቻው ማግስት እውቅና መስጠቱ፣ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሲመታቸው እስከ ኅልፈተ-ሕይወታቸው ያሳየው አክብሮት፣ በተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ሀብትነታቸውን በመረዳት ያከናወነው የጥገናና የሙዚየም ግንባታ፣ እንደ ንሣኤ ዘጉባኤ አይነት አንጋፋ የቤ/ክ ማተሚያ ቤት አለመውረሱ፣ በሰሜን ኢትተጵያ የአጥቢያዎችን የመገበሪያ መሬት ጨርሶ አለመንጠቁ፣ በተቋቋመው የብሔረሰብ ኢንስቲትዩት ለግእዝ ቋንቋም ትኩረት ተሰጥቶ ‹‹የግእዝ ቅኔያት፡የሥነጥበብ ቅርስ›› የሚል እጅግ ጠቃሚ መድብል ኅትመት መጀመሩ፣ በነሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው አስተባባሪነትና በፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት ፈቃድ የአጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት ወር እየተካሄደ በአቡነ ቴዎፍሎስ የተቀረጸው ቃለዓዋዲ ወደ ተግባር እንዲተረጎም ሲደረግ እንቅፋት ባለመፍጠሩ፣ በአጠቃላይ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በአብዮቱ ማግሥት የንጉሥ ተቀጽላ ሆና ከመታየት ተላቅቃ በምዕመናኖቿና በካሕናቷ ኅብረት የቆመች ሆና እንድትወጣ የደርግ ዘመን በረከተ-መርገም ሆኖላታል፡፡ የተሐድሶ ጉባኤ አባላትም ከዚህ ምስጋና ዓቢይ ድርሻ አላቸው!

3.5.3.1.3. የት እንዳነበብኩት የተዘነጋኝ ጸሐፊ በእንግሊዝኛ “The far sighted Patriarch Abune Theophilos was prevented from effective administrative organization, until the events of the Revolution produced the required incentive.” ይላል፡፡ መቼውንም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ለኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ መንፈሳዊ ነጻነት የተደረገ አኩሪ ተጋድሎ ችላ ብሎ ቃለ-ዘለፋ መሰንዘር ቢከብድም ቀ.ኃ.ሥ የተወሰኑ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ለእሳቸው ተጠሪ እንዲሆኑ በማድረጋቸውና በሃይማኖት ጉዳዮች ተጠሪ ልዩ ካቢኔ በኩል በሚያደርጉት አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አቡነ ቴዎፍሎስ ደስተኛ አልነበሩም የሚል ሐሜት ይስሰማል፡፡ በመሆኑም አቡነ ቴዎፍሎስ ‹‹ከስኬታማ አስተዳደራዊ መዋቅር ተገቱ›› የምትል የአፈ-እንግሊዝ ንባብ ቁርጥራጭ እውነት አታጣም፡፡ ይኸው ፀሐፊ በመቀጠል “A hopelessly compromised E.O.T.C
had become the object of student discontent and risked mariginalization. The Church could not have shed the negative baggage of its feudal past and regained wide support without revolution” ማለቱም ጭርሱን ሐሰት ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በዘመነ-ደርግ የተራማጁን የማያቋርጥ ዘለፋና መሪዎቿን የማራከስ ዘመቻ ተቋቁማ የበለጠ ሕዝባዊት ሆናለች፡፡ ምዕመኑ ‹‹እናት ቤ/ክ ካለኛ ማን አላት! ›› በሚል መንፈሳዊ ቅንዐት ማንንም ውጫዊ ኃይል ለተራድኦ ተስፋ ሳያደርግ ከጎኗ ቆሟል፡፡ በነገሥታቱ ከታነጹት የላቁ እንደ መርካቶዎቹ አዲሱ ሚካኤልና አማኑኤል የመሳሰሉ ካቴድራሎች በሕዝብ መዋጮ ባስደማሚ ጥበብ ተገንብተው ቤ/ክ ያለ መንግሥታዊ እርጥባንና የሲሶ መንግሥት ተረታ-ተረት በገዛ ልጆቿ መቆም እንደምትችል አሳይተዋል! የዘመነ-ደርግ በረከተ-መርገም!

3.5.3.2. የቅሬታ ነጥቦች…በደርግና በኮ/ል ፍስሐ ደስታ ላይ!

3.5.3.2.1. ዘመነ ደርግ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እንደ ሀገር በተለይም በሃይማኖት በኩል (በሁሉም ተራማጅ ነን ባዮች ዘንድ) አባቶችን በጥቅል ማሳነስ የተንሰራፋበትና ተከባብሮ የመነጋገር ባህል ሳይወለድ ጨንግፎ ‹‹መደባዊ›› ትግል የተባለ ጭፍን ሃይማኖት-አከል ቡድናዊነት የተስተዋለበት ዘመን ነበር፡፡ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በደርግ ዘመን ነው ቀኖና ተጥሶ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ የተሾመው፣ ታላላቅ የቤተ ክህነት ኃላፊዎችንና ሊቃነ ጳጳሳትንና በየሚዲያው መዝለፍና ከያሉበት አንቆ ማሰር፣ ማሸማቀቅ፣ የዜና ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅ እንደ ነበሩት እንደ ብላታ ደምሴ ወርቅአገኘሁ ያሉትን ገድሎ በቆሻሻ ገንዳ መጣል፣ በጉባኤ ቤቶች አፈሳ ማካሄድ፣ ካሕናትን የነቁ (ተራማጅ) እና ያልነቁ ወይም በዝባዥና ተበዝባዥ አድርጎ መከፋፈል፣ ኢ-አማኒነትን መጫን፣ ሆን ብሎ በሰንበታት ከቅዳሴ ጋር በሚጋጭ መልኩ አስገዳጅ ስብሰባዎችን በነግኅ መጥራት፣ ሰሎሞናዊ ሥርዓትን በመተቸት ሽፋን የመካከለኛው ዘመን ኦርቶዶክሳውያን ትውፊቶችንና ታሪኮችን ደርቦ ማነወር፣ በገጠር ያሉ መሪጌቶችን (ማንበብና መጻፍ የሚችሉ በብዛት እነሱ ስለነበሩ) በገፍ ለካድሬነት መመልመል፣ መንፈሳውያን ኮሌጆችን መዝጋት፣ የቅ/ሥላሴ ካቴድራልና የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳማት በሮችንና ድምጸ ማጉያ ሳይቀር መዝጋት፣ የቤ/ክ ት/ቤቶችን በጅምላ መውረስ፣ የበዓላትና የአጽዋማትን ቀኖና በኃይል መጣስ፣ ጳጳሳትንና የቤተ ክህነት ኃላፊዎችን (በዘመኑ የነበሩትን 2 ፓትርያርኮች ጨምሮ) የሸንጎ አባል እንዲሆኑ አደርጎ ሕዝባዊ አመኔታ ላይ ግርታ መፍጠር፣ እንደ መስቀል ዓደባባይ አይነቶችን በዓላት ማክበሪያ መካናት በአብዮታዊ ሥያሜ ለውጦ በዓሉም ወደ ጃንሜዳ እንዲዞር ማድረግ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅነት ሹመትን ቀጥታ በደርግ ደብዳቤ የሚከናወን ማድረግ፣ … የደርግ በደሎች ሁሉ ማሳያ የሆነውን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍልስን መግደል የተካሄደው በዘመነ-ደርግ ነው!

3.5.3.2.2. ደርጎች ፓትርያርኩን ያለፍርድ በሰቆቃ መግደላቸው ሳያንስ ኮ/ል ፍስሐ ደስታ በመጽሐፋቸው ለጄ/ል አማን አንዶም፣ ለአክሱሙ ንቡረዕድ
ገ/ሥላሴ ፀሐዩ፣ ለ60ዎቹ የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ ለጃንሆይና ለግንቦት 8ቱ መፈንቅል አስተባባሪዎች እንግልትና ግድያ ያሳዩትን ርኅራኄ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ግድያ ነፈጉ፡፡ ይልቁንስ በዐፅመ-ቴዎፍሎስ ላይ ክስ ደረደሩ፡፡ የሲሶውን ተረክ ትቼ የተወሰኑ የኮለኔሉ ክሶችን ለመዳሰስ ልሞክር፡፡ ክሶቹ፡-

 1. አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ወዳጆች ብቻ በመሾም ደርግ ላይ ውስጥ ውስጡን አሳድመዋል፣
 2. ጳጳሳትን ጨምሮ 90 ከመቶ ካሕናት እንዲወርዱ ፈርመውባቸዋል፣
 3. በጣሊያን ጊዜ አባ መልእክቱ በሚባሉበት ወራት ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ እንዲገደሉ በግብር አበርነት ተሳትፈዋል የሚሉ ናቸው፡፡

ሌጣ ክሶች! የሰውና የሰነድ ማስረጃ አላያያዙልንም፡፡ ከራሳቸው ከጸሐፊው ትዝታ በቀር፡፡ ለዚህ ነው ትዝታቸው ተዛነፈ ማለታችን፡፡ መዛነፉን እናሳይ!

3.5.3.2.3. ‹ወዳጆቻውን ሾሙ› የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ያገር ልጆቻቸውን ሾሙ ለማለት ከሆነ ለሞታቸው ምክንያት ከሆኑት 3 አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ውስጥ አቡነ ጳውሎስና አቡነ ጴጥሮስ ሳልሳይ ከፓትርያርኩ የትውልድ አካባቢ የተሰየሙ አልነበሩም፤ እንደራሴያቸው ሆነው በወቅቱ የተሰየሙት ጳጳስና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ተደርገው የተመደቡት ግለሰብም ከአቡነ ቴዎፍሎስ ጋር የተለየ የአካባቢና ከቤ/ክ የወጣ ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ ኮ/ል ፍስሐ ‹‹ፓትርያርኩ ወዳጆቻቸውን ሾመዋል›› ያሰኛቸውን አጋጣሚ ከነማስረጃው ሳያቀርቡ በስሚ ስሚ ትዝታ ታሪክ ማዛነፋቸው ቅር ያሰኛል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ በዚህ መልኩ የሚገለጹ አባት እንዳልነበሩ ደቀመዛሙርቶቻቸው፣ አብረዋቸው የሠሩ ሊቃውንትና ጳጳሳት ይመሰክራሉ፡፡ እነሱን በቦታቸው ስለምናመጣቸው በተዛነፈ ትዝታ ላይ ጊዜ አናባክንም፡፡

3.5.3.2.4. ሌላኛው የኮ/ል ፍስሐ የክስ ነጥብ ፓትርያርኩ ‹በደርግ ላይ ውስጥ ውስጡን አሲረዋል› የሚል ነው፡፡ ይገርማል፡፡ ኮ/ል ፍስሐ ደጋግመው የነገሩንን የደርግ የብልጠትና እያሳሳቁ ሥርዓት የመለወጥ ተግባር መልሰው ዘነጉት፡፡ ደርግ ቀ.ኃ.ሥን ያወረደበት መንገድና ከሰኔ 22 ቀን 1966 ዓ.ም እስከ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የሄደበት የወራት ጉዞ ረቂቅ ነበር፡፡ እውነተኛ ባሕርይው በሕግ፣ በንጉሥ በትረ ሥልጣን፣ በተቋማት፣ በራሳቸው በንጉሡ ትእዛዝ (መጋቢት 17 ቀን 1966 ዓ.ም) በተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን ተከልሎ ለሁሉም ወገን አቋም ለመውሰድ ያስቸገረ ነበረ፡፡ በዚህ የደርግ የረቀቀ ጉዞ ተራማጆች ብቻ ሳይሆኑ ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስም የተሳሳተ ግንዛቤ ሳይዙ አልቀሩም፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ አስቀድሞ የሀገሪቱ አቅጣጫ ስላላማራቸው ቤተ ክርስቲያኗ ከንጉሣዊ አስተዳደሩ ጋር በተቀጽላነት ከምትታይበት አሳሳቢ አተያይ ወጥታ በቃለ ዓዋዲ ሕዝባዊትና በኢኮኖሚም ከመንግሥት የማትነካካ ነጻ ተቋም እንድትሆን ታላቅ ዘመን-ተሸጋሪ ውጥን ነድፈው በመንቀሳቀስ ላይ ሳሉ ነበር ለትንሽ አብዮቱ መጥቶ ጉዟቸውን የቀጨባቸው፡፡ ያመኑበትን ሳይለቁ ጅምር ጉዞውን ለማስቀጠልና ከአዲሱ ሥርዓት ጋር እስከተቻለ ሄደው የቤተ ክርስቲያን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆጠቡት ጉልበት አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ መስከረም 1 ቀን 1967 ዓ.ም ባስተላለፉት የአዲስ ዓመት ቃለ ምዕዳን ‹‹በጦር ኃይሉና በሕዝቡ የተጀመረው ‹የተቀደሰ እንቅስቃሴ› መልካም ውጤት እንዲያስገኝ ፈጣሪያችን ይርዳን›› ብለው ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት በተካሄደው የዕድገት በኅብረት ዘመቻ ሶሻሊዝም እንደ ርዕዮተ ዓለም ሲታወጅም ርዕዮተ ዓለሙን ከዘመነ-ሐዋርያት የማኅበር ኑሮ ጋር አስታርቀው መንፈሳዊ ትርጓሜ በመስጠት ‹‹ጥንቱንም ቢሆን በሐዋርያት ጊዜ እንደነበረው ማኅበር የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ተግባርና ዓላማ፡በሕዝቡ መካከል ችግረኛ እንዳይኖር፣ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ እንዲመገብና ሥጋ በለበሰው ፍጡር መካከል የተፈጥሮ ልዩነት እንደሌለ ሁሉ የኑሮ ልዩነት እንዳይኖር የእኩልነትን መንፈስ ማስተማር ነው›› ሲሉ የተራማጆችንና የደርግን ሶሻሊስታዊ ልቡና በመንፈሳዊ ልጓም ለመግራት ተጣጣሩ፡፡

3.5.3.2.5. የፓትርያርኩ ትውልዱን መማጸን አልሠራም፡፡ እንኳን እሳቸውን በጉያው ተቀምጠው አቡነ ቴዎፍሎስን ከመንበር አውርደው ለሰይፍ ካመቻቹ በኋላ ‹‹…በሞቱት ማርክስና ኤንጅልስ ሥም መመጻደቅ ሳይሆን በኢትዮጵያ ባህሪ፣ ባህልና ታሪክ›› የተቀረጸ ቅይጥ ሥርዓት ያስፈልገናል ያሉት እነ ኮ/ል አጥናፉም ካሳሰሯአው ፓትርያርክ ቀድመው በፈጠሩት አብዮት ኅዳር 2 ቀን 1970 ዓ.ም ተበሉ (ነበር፣ ክፍል አንድ፡ገ.293)፡፡ እየቆየ ደርግ ጠቅላላ በቤተ ክህነቱ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣትን አልሞ ከላይ በተጠቀሰው የተሐድሶ ጉባኤ ሽፋን የፓትርያርኩን አመራር መቀየድ ጀመረ፡፡ ያ ሁሉ የት/ቤትና የሕንጻዎች ውርስ ሲካሄድ ደርግ ፓትርያርኩን ለማነጋገር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ፓትርያርኩ የንጉሠ ነገሥቱን አስከሬን ለመቅበር ጠይቀው መልስ ነፈገ፤ አስፈራራ፡፡ በሥራቸው ያሉ ሠራተኞችን እንዳያዝዙ የተሐድሶ ጉባኤው ጣልቃ ገብነት አላላውስ አለ፡፡ ቅሬታው ተጠራቀመ፡፡ የፓትርያርኩ መንገስ ተናወፀ፡፡ ፕ/ር ጌታቸው እንደነገሩን ከደርግ ጋር በኮ/ል አጥናፉ አገናኝነት ቁርኝት ከነበረው የተሐድሶ ጉባኤ ጋር አቡነ ቴዎፍሎስ በግላጭ ተላተሙ፤ ‹በሥራዬ ጣልቃ አትግቡ› አሉ፡፡ መጀመሪያ በቅንነት የተቀበሉትን ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› የሚል የወቅቱ የምዕዳንና የንግግር ማሳረጊያ መፈክር ቸል አሉት፡፡ ደርግ ‹ቤ/ክ በአብዮታችን አያገባትም› ሲል ሳያማክራቸው በቤ/ክ ንብረት ላይ እንደወሰነ እሳቸውም በፈንታቸው ‹ደርግም በቤ/ክ አያገባውም› ሲሉ ሳያማክሩት ሸንጎውን
በሚጎራበተው የቅ/ሥላሴ ካቴድራል በደርግ አፍንጫ ስር 3 ኤጲስ ቆጶሳትን በማጰጰስ (በመሰየም) ምላሽ ሰጡ፡፡ ከዚያ በኋላ ባለጠብመንጃው ደርግ አፈረ፤ የመልስ መልሱን በጉልበት አደረገው፡፡ ጡንቻውን በመነኩሴው ላይ አሳየ! የሆነው ሁሉ በግላጭ ሆነ! ‹‹ውስጥ ውስጡን…›› የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ የኮ/ል ፍስሐ ደስታ ብዕር የፈጠጠውን ግፍና ታሪክ መጋፈጥ ሲሳነው ‹‹ፓትርያርኩ ውስጥ ውስጡን አድመው ስለነበር ግድያቸው አብዮቱን የማዳን ተልእኮ እንደነበረው›› ለማስመሰል ቃጣው! ሳይበድል የተገደለን ሬሳ መራመድ ግፍ እኮ ነው! ተው-ተው-ተው! አፈር እናልብስበት! ሟች ሞቱን ይሙትበት!

3.5.3.2.6. ከካሕናትና ገዳማውያን 90 በመቶ ፓትርያርኩ እንዲወርዱ ፈርመው ነበር ለሚለው የኮሌኔሉ ስሑት መረጃ ዲ/ዳንኤል ክብረት በብሎጉ የሰጠው መልስ በቂ ነው፡፡ በእሱ ላይ ለመጨመር ያህል ግን፡-

 1. ፓትርያርክ ሲወርድ ሃይማኖታዊ ወይም አካላዊ (ሥራውን የሚያስተጓጉል) ህጸጽ እንዳለበት ተረጋግጦ እንጂ በሆታ እንደማይወርድ መገንዘብ ይገባ ነበር፣
 2. ገዳማቱ እንኳንስ በዚያ የግርግር አፍታ ባሁኑ ጊዜም 90 ከመቶ ፐርሰንት ፊርማ ፈርመው የሚልኩበት የተፋጠነ የግንኙነት መሥመር የለም፤ መረጃው በተሐድሶ ኮሚቴው በየሀገረ ስብከቱ ተቀናብሮ ለድርግ አባላት ደረሰ፡፡ ኮ/ል ፍስሐ ይህን የተቀናበረ መረጃ እስከዛሬ ድረስ ሳያንጠረጥሩ ይዘው በተዛነፈ ትዝታ ‹‹ትዝታዬ››! ሲሉ ፐርሰንቱን በድፍረት አኖሩት!
 3. የ90 ፐርሰንት ስሌት በኮ/ል ፍስሐ ብቻ ሳይሆን በሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስም ትደጋገማለች፡፡ የመሬት አዋጁን የደገፈው ሕዝብ 90 በመቶ፣ ሶሻሊዝም ያልገባው ካድሬ 90 በመቶ እያሉ ጽፈዋል፡፡ ያለተጨባጭ ዳታ ፐርሰንት መደርደር የዛሬ ዘመን መጤ ልማድ መስሎኝ ነበር፤ ለካ የጥንት ነው!
 4. በኮ/ል ፍስሐ የፐርሰንት ድርደራ ውስጥ ከአዲሱ ሥርዓት የግርገህርና የሽግግር ጊዜ መጠቀም የሚፈልጉ ደጀ ጠኚዎች፣ ለፓትርያርኩ ቀና ያልሆነ አመለካከት ያላቸው አኩራፊዎች፣ መንበሩን የሚመኙ፣ ለአዲሱ ሥርዓት የሰገዱ የቤተ ክህነት ሰዎች አድር ባይነት፣ በብሔራውያን ሚዲያዎች ያለማቋረጥ ከሚነዛው ጸረ-ፓትርያርክ ወሲኖዶስ ዘመቻ ጋር ተዳምሮ የተፈጠረው ‹‹የስቅሎ! ስቅሎ! ›› መንፈስ አልተጤነም፡፡ አይ 90%!

3.5.3.2.7. ሌላኛው የኮ/ል ፍስሐ ደስታ ያላንዳች ማስረጃ የቀረበ ዘግናኝ ክስ ‹‹አቡነ ቴዎፍሎስ አባ መልእክቱ በሚባሉበት ጊዜ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊ በፋሽስት እንዲገደሉ›› አድርገዋል የሚል ነው፡፡ በመሰረቱ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የተቀበሉ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ከሰላሌ አርበኞች ጋር በተደረገው ፀረ-ፋሽስት ዘመቻ አርበኞችን በማበረታታት ላይ ሳሉ ተይዘው ነው(ዲ/መርሻ አለኸኝ፡ገ.75-80)፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ማዕረገ-ምንኵስና ከደ/ሊባኖስ ገዳም ተቀብለው ‹አባ መልእክቱ› የተሰኙ አቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት ጽዋ ከተቀበሉ ከ2 ዓመት በኋላ በ1930 ዓ.ም ነው፡፡ ስለዚህ አቡነ ቴዎፍሎስ ከጦር ግንባር ተይዘው በተሰውት ታላቅ አባት አቡነ ጴጥሮስ ኅልፈት ላይ ‹አባ መልእክቱ› ተሰኝተው ተሳተፉ የሚባልበት የፍሬ ነገርም ሆነ የማስረጃ መሰረት የለም፡፡ በፍጹም የለም! በወቅቱ በጥላቻ የተዛመቱ የፀረ-ቴዎፍሎስ መበለታዊ ወጎችን ሁሉ ኮ/ል ፍስሐ ሳያደቁ፣ ሳይፈጩ፣ ሳያጣሩና ሳያንጠረጥሩ እንደወረደ አኑረው፣ እንደወረደ በማስፈር ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› ማለታቸው የተዋበ ትዝታቸውን ‹‹እብለቱና ትዝታዬ›› ወደሚል ስላቅ እንዳያወርደው በዳግም ኅትመት ጊዜ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ ያሰፈሩትን ከእውነታው ጋር አስታርቀው ቢያቃኑት መልካም ነው፡፡

3.5.3.2.8. እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ አንስተን ርእሱን እንደምድመው፡፡ ፓትርያርኩ ሲወርዱ፣ ሲታሰሩ፣ በላያቸው ላይ በሕይወት እያሉ ፓትርያርክ ሲሾም፣ ሲገደሉ ለምን ተናጋሪ አባት ጠፋ?ለጥያቄው በተራ ቁጥር 3.5.3.2.6. በ3ኛነት የተጠቀሱ ነጥቦች ምላሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የተወሰኑ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት ኃላፊዎች ተጠሪነት ለፓትርያርኩ ብቻ ሳይሆን ለቀ.ኃ.ሥ ጭምር የነበረ በመሆኑ ‹‹የንጉሡ›› እና ‹‹የፓትርያርኩ›› የሚል ቡድናዊ መንፈስ በቤተ ክህነቱ መኖሩም የራሱ ድርሻ አለው፡፡ ሌላው ምክንያት ተቋማዊ ፍራቻ ነው፡፡ የዚህን ሐሳብ ዝርዝር ሐተታ ከዳንኤል ክብረት ‹‹አራቱ ኃያላን››
እንዋስ፡፡ በመጽሐፉ ከገጽ 64-66

‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች በሃይማኖታዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ከነገሥታቱ ጋር በሚጋጩ ጊዜ በሌሎች አባቶች ዘንድ ሁለት አይነት አቋሞች መንጸባረቃቸው የተለመደ ነው፡፡ ‹ነገሮችን በዝምታ ማለፍ›ና ‹በተቃራኒው መቆም›፡፡ ለምሳሌ በንግሥት አርቃንዴዎስ ምክንያት ዮሐንስ አፈወርቅ ከባዛንታይን ነገሥታት ጋር በተጋጨ ጊዜ በወቅቱ የነበሩት አባቶች በሁለት መስመር ቆመው ነበር፡፡ በምዕራብ የነበሩት አባቶች የዮሐንስ አፈወርቅን ወደ ግዞት መላክ ተቃውመው ለንጉሡ ደብዳቤ እስከመጻፍ ሲደርሱ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ታላቁ ኤጲፋንዮስ ዮሐንስ አፈወርቅ ንግሥቲቱን ማውገዙን አልደገፈውም ነበር፡፡ ኤጲፋንዮስ የዮሐንስ አፈወርቅ አይነት አቋም በቤተ ክርስቲያን ላይ ስደትና መከራ ያመጣል፣ ስለዚህ አለሳልሰን መያዝ አለብን የሚል አቋም ነበረው››

ይለናል፡፡

አስከትሎም ተመሳሳይ ታሪኮች አባ ፊልጶስ በአጼ ሰይፈአርዕድ ሲሳደድ መስተዋሉን፣ አቡነ ሺኖዳ በ1981 ዓ.ም ከመንበራቸው ሲገፉ የተወሰኑ ጳጳሳት ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቃቸውን ጠቅሷል፡፡ በአብዮቱ ዘመን የነበሩ ውስን ኢትዮጵያውያን አበው በአቡነ ቴዎፍሎስ ሰቆቃ ጊዜ በአርምሞ መዋጥም ደርግ ጨርሶ የቤተ ክርስቲያኗን ተቋማዊ ሕልውና አደጋ ላይ እንዳይጥልና ቃል የገባውን 4 ሚሊዮን ብርም ከልክሎ ካሕናቱ በረሀብ እንዳያልቁ ከመስጋት የተነሳ ሊሆን ይችላል ብለን መላ ብንመታ የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡ አጽመ-ቴዎፍሎስ በግፍዕ ከወደቀበት ፈልሶ ወደተዘጋጀለት ማረፊያ በክብር ሲገባ ያነበብኳቸው ተከታዮቹ የጳጳሳትና የሊቃውንት ምስክርነቶች ናቸው እንዲያ እንድል የሚገፋፉኝ፡፡

4. ዝክረ-ቴዎፍሎስ በአፈ-ጳጳሳት ወሊቃውንት!

በ1989 ዓ.ም በፍልሰተ-አጽመ-ቴዎፍሎስ 5ኛ ዓመት መታሰቢያ በወጣው ‹‹ዝክረ ቴዎፍሎስ›› መጽሔት አያሌ ጳጳሳትና ሊቃውንት ስለአቡነ ቴዎፍሎስ ባሕርይ፣ እውቀት፣ ትሩፋት፣ ሰማዕትነትና ያለዘረኝነት ሁሉን እኩል ተመልካችነት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ቃላቸውን በየተራ እንደወረደ እንየው!

4.1. አቡነ ቴዎፍሎስ በአፈ-ጳጳሳት!

4.1.1 አቡነ ቴዎፍሎስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) አንደበት!

‹‹…ገና ከገዳም እንደመጣሁ እንዲሁ ተመልክተው እንድማር ያደረጉኝ እሳቸው ናቸው፤ የነበርኩበት ገዳም አበምኔት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሊወስዱኝ ሞክረው ነበር፤ ‹እሱን እኛ እንጠብቀዋለን፤ ከዚያ ያሉትን ጠብቅ› ነበር ያሏቸው፡፡ … የሚወጣውንና የማይወጣውን ተማሪ ለይቶ ለማወቅ ልዩ ጸጋ ነበራቸው፤ ጥሩ ተማሪ ነው ተብሎ ከተነገራቸው በዚያ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ …ሁሉንም በእኩልነት የሚመለከቱ፣ ዘረኝነት የሌላቸው ታላቅ አባት ነበሩ፤ አስተምረው ለዚህ ደረጃ ያበቁኝም በዚህ መልኩ ነው፤ አርቆ ማሰብ፣ ትእግሥት፣ መራቀቅ፣ የተፈጥሮ ሀብታቸው ነበር፤ በሥራም እሳቸው ያልቀየሱት የቤተ ክርስቲያን ሥራ የለም፤ ነገር ግን ወቅቱ ስላልፈቀደላቸው አንድ አንዱ አልተፈጸመም፡፡ …እሳቸውን የማያውቅ፣ ትዕግስታቸውን፣ ሐሳበ ሰፊነታቸውንና ጥልቀታቸውንም የማያውቅ አይገኝም አውቆ አፉን ካልዘጋ በቀር፤ ያ! አስከፊ ሥርዓት ሲመጣ ወደ ውጭ ለመሄድ ሰፊ እድል ነበራቸው፤ ብዙዎቹም እንዲወጡ መክረዋቸው ነበር፤ እሳቸው ግን መከራውን ከዚሁ ለመቀበል መዘጋጀት እንጂ ወደ ውጭ ለመውጣት አልፈቀዱም፤ በሽሽታቸውም የአባቶችቸውን ታሪክ ለማጉደፍና የቤተ ክርስቲያናቸውን እንቅፋት ለመሆን አልወደዱም፤ አስተዋዩ አይሰማቸውም እንጂ ያልታደሉ ግን ብዙ ይላሉ፤ ለዚህም ነው የአባቶቻቸው የእነ አቡነ ጴጥሮስን ዐሠረ ጽድቅ በመከተል በትውልድ ሀገራቸው የሰማዕትነትን እድል አግኘተው የሞቱ፡፡ ››

4.1.2. በብፁዕ አቡነ ገብርኤል(ዶ/ር)!

‹‹…ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በዓለም ከነበሩና ካሉት ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡ በግሪክ ልሳን ‹ቲኦፊሎስ› ማለት ‹መፍቀሬ እግዚአብሔር› ማለት ነው [Theophilus=lover of God]፡፡ በዚህ መሠረት አባቶቻችን ሲናገሩ ‹እስመ ሥሙ ይመርሆ ኀበ ግብሩ፣ ሥሙ ግብሩን ይገልጣል› ይላሉ፡፡ … ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ እንደ ስማቸው መፍቀሬ እግዚአብሔር ነበሩ፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ ከየትም ይምጣ ከየት አባታችን ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚወዱ ነበሩ፡፡ … አባታችን… ለእኛ ለልጆቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትምህርታቸው፣ በጣዕመ ስብከታቸውና በንግግራቸው በእውነት የሚጣፍጥ ጨው ነበሩ፡፡ ››

4.1.3 (በረከታቸው ይደርብንና! ) አቡነ አብርሃምና አቡነ ሚካኤል!

ሀ. ነፍሰ ኄር አቡነ አብርሃም (ዘሐረር)፡-

‹‹…ከሠሯቸው ሥራዎች አንዱን አስታውሳለሁ፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ በመላ ኢትዮጵያ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ከገበዞች በቀር ማንም የማያውቀው የነበረውን የስእለት ገንዘብ ከምዕመናን 3 ሽማግሎች ተመርጠው ከገበዙ ጋር እንዲቆጣጠሩ የሚል መመሪያ በቅጽ መልክ አሳትመው ለየአብያተ ክርስቲያናት አስተላልፈዋል፡፡ … ይሕም…ዳብሮ በቃለ ዓዋዲ ተቀርጾ ለሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት መሠረት ሆኗል፡፡ ››

ለ. ነፍሰ ኄር አቡነ ሚካኤል (የኤርትራ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ)፡-

‹‹…በቆሙበት አደባባይ ሁሉ ተናግረው የሚያሳምኑ፣ አስተምረው የሚያረኩ፣ ለተጠየቁት ሁሉ የተሟላ መልስ የመስጠት ችሎታ የነበራቸው ታላቅ አባት ነበሩ፡፡ የበደሉት ነገር ሳይኖር ከፍትሕ መጓደል የተነሣ ብዙ ፈተና፣ መከራና ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡ ››

4.1.4. (በረከታቸው ይደርብንና! ) አቡነ መቃርዮስና አቡነ ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)!

ሀ. ነፍሰ ኄር አቡነ መቃርዮስ ዘትግራይ (የአቡነ ቴዎፍሎስ እንደራሴ የነበሩ! )፡-

‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሙሉ ትምህርት፣ ሙሉ ዕውቀት፣ ላቅ ያለ፣ ጥልቅ አስተያየት ከትእግሥት ጋር አስተባብረው የተገኙ ቅዱስ አባት
ነበሩ፡፡ ስለዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለፓትርያርክነት ያደረሰቻቸው በትምህርታቸውና በዕውቀታቸው ነበር፡፡ ››

ለ. ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ (የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ኃላፊ)፡-

‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እኔ ባለኝ አስተሳሰብ ምሁር፣ ትእግሥተኛ፣ ነቢይ፣ አስተዋይ፣ ፈላስፋ፣ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያላቸው፣ ግርማቸው ከሁሉም ሰው የተለየ፣ ስብከታቸው ሰዎችን የሚማርክ፣ በጨዋ መልክ ከአንደበታቸው የሚወጣ ቃል እንደ ትምህርት ቤት የሚቆጠር አባት ነበሩ፡፡ ››

4.2. ዝክረ ቴዎፍሎስ በአፈ ሊቃውንት!

4.2.1. ቅዱስነታቸው በነፍሰ ኄር ሊቀ ካሕናት ክንፈገብርኤል አልታየ!

በአቡነ ቴዎፍሎስ መሪነት ቃለዓዋዲ ሲረቀቅ የአርቃቂ ኮሚቴው ፀሐፊ ሆነው የቅዱስነታቸውን እንቅስቃሴና ራዕይ በቅርበት የታዘቡት ታላቁ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ተጠያቂ ሊቅ ሊቀ ካሕናት ክንፈገብርኤል አልታየ የፓትርያርኩን ፈተናዎችና ዘመን የተሻገሩ ትሩፋት ዘርዘር ባለ መልኩ እንደሚከተለው አቅርበዋል፡፡

‹‹…በ20ኛው መቶ ምዕት ዓመት የቤተ ክርስቲያን መብትና ክብር ለማስከበር (1) ከደርግ አባላት፣ (2) ከጊዜያዊ ጉባኤ አባላትና ከቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች፣ (3) ከኮከብ ቆጣሪ መሰግላን፣ (4) አንካሴ ከሚሸከሙ ባሕታውያን መሰሎች፣ (5) መሻሻልንና ለውጥን ከማይፈልጉ ወግ አጥባቂዎች ጋር (እዚህ ላይ መሻሻል ሲባል አስተዳደራዊና ቀኖናዊ እንጂ ተሐድሶዎች በሚያራግቡት መልኩ ሃይማኖታዊ ወይም ዶግማዊ መሻሻል እንዳልሆነ ልብ ይባል! ) ሲታገሉ ከመንበራቸው ተወስደው በእስር ቤት ለተሰቃዩት፣ በሰማዕትነት ለተገደሉትና አስከሬናቸው በአልባሌ ቦታ ለተጣለው አባት … አቡነ ጳውሎስ ሙዚየም ማሠራታቸውና ሐውልት ማቆማቸው እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ (ኢሳ. 56 ቁ. 7 ‹ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ›) ያለውን መሠረት በማረግ ነው፡፡ ››

‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የጎጠኝነትና የዘረኝነት ጠባይ አልነበራቸውም፣ በአንድ ወቅት ከቤተ ክህነት ሠራተኞች ውስጥ ምሁራንን መርጠው አምስት ያህል አለቆች ሲሾሙ አንዱ ‹ለምን ከሀገርዎ ልጆች አንድ ሰው እንኳ አይጨምሩም ነበር?› ቢላቸው ‹ይህ ሹመት የሚሰጠው ካሕን ሆኖ ለተገኘ እንጂ በሀገር ልጅነት አይደለም› ብለው በመናገር እንደአሳፈሩት ይነገራል፡፡ ቅዱስነታቸው በስብከተ ወንጌል ማስፋፋት፣ በሰበካ ጉባኤ ምስረታ ብሎም ማቋቋምና ማደራጀት፣ በት/ቤቶች ማጠናከር፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት፣ ቤተ ክርስቲያን የተማረ ትውልድ እንድታፈራ በማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉና ይህንንም መሠረት ጥለው የገነቡ፣ ያዋቀሩና የጎለሉ(ጉልላት ያበጁ)፣ ይሕ ቀረዎት የማይባሉ ምልዓተ-ጥበብ የተሰጣቸው ታላቅ መንፈሳዊ አግኝታ ቤተ ክርስቲያን የሥራ ገበታዋን በዘረጋችበት ወቅት ነበር ደርግ ገበታዋን በማንሳት ያሳቀቃት፡፡ ››

4.2.2 አቡነ ቴዎፍሎስ በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ብዕር!

ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ በተለያየ አጋጣሚ አቡነ ቴዎፍሎስን በአካል የሚያውቁ፣ አብረው የሠሩ፣ በተሐድሶ ጉባኤ አባል ስለነበሩ ፀረ-ቴዎፍሎስ እንቅስቃሴውን በቅርበት የታዘቡና በዚሁ ሂደት ባራመዱት የልዩነት አቋም በደርግ ጥርስ ውስጥ ገብተው ለስደት የተዳረጉ የቋንቋ በተለይም የአማርኛ ቋንቋና ጥንታውያን የግእዝ መዛግብት ሊቅ ናቸው፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ መጽሐፋውያን ሴሜቲክ ቋንቋዎችም ያበጥሯቸዋል! በአንዳንድ ፖለቲካዊ በሆኑና በደቂቀ እስጢፋኖስ ዙሪያ ባራመዷቸው ሐሳቦቻቸው ተዐቅቦ ቢኖረኝም በተቻለኝ መጠን ሥራዎቻቸውን ከምከታተልላቸው ታላላቅ ብሔራውያን ሊቃውንት አንዱ ናቸው፡፡ እሳቸው በ‹‹ግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ፡አንዳፍታ ላውጋችሁ›› በተሰኘ ውብ የሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸው ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ ሰብእናና መሥዋዕትነት የሚከተለውን ይላሉ፡፡

‹‹የአባታችን ሰማዕትነት ያኩራን እንጂ በእሳቸው ሞት ቤተ ክርስቲያኗ አንድ ትልቅ ሰው አጥታለች፡፡ አንድን ሀገር ትልቅ የሚያደርገው የሚደነቅ ሰው ሲወጣበት እንጂ መሬቱ ብቻውን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡ያለ አቡነ ፊልጶስ ደብረ ሊባኖስ ምንድን ነች?ያለ አቡነ ኢየሱስ ሞአ፡ያለ አቡነ ክርስቶስ ሞአ ደብረ ሐይቅ ምንድን ነች? ያለ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፡ያለ አቡነ ፊልጶስ ደብረ ቢዘን ምንድን ነች?ያለ አጼ ቴዎድሮስ፡ያለ አጼ ዮሐንስ፡ ያለ ራስ አሉላ፡ ያለ አጼ ምኒልክ፡ ያለ ራስ ጎበና፡ያለ ራስ መኰንን፡ ያለ አጼ ኃይለሥላሴ፡ ያለ ራስ አበበ አረጋይ፡ ያለ በላይ ዘለቀ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ምንድን ነች? ሲኖዶሱ ‹እስመ፡አኮ፡መካን፡ዘይቄድሶ፡ለሰብእ፤ አላ፡መካን፡ሰብእ፡ይቄድሶ፡ለመካን› (ሰው ቦታውን ይቀድሰዋል እንጂ፡ቦታ ሰውን አይቀድሰውም) የሚለው ይኸንኑ ለማስተማር ነው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ከግርማቸውና ከጀግንነታቸው ሌላ ዕውቀታቸው የተሟላ የተተርፈረፈ ነበር፡፡ በተገናኘን ቁጥር አዲስ ትምህርት ሳላገኝ የቀረሁበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ ግርማቸው ተራራን ድቡሽት ያደርጋል፡፡ ››፡፡

በፕ/ር ጌታቸው መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ያካሄዱት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹‹አንድ ሶቅራጥስ ቢኖረን እሱንም ገደልነው›› ብለው ነበር! አረግፍነው!

4.2.3. መርገፍ (ድኅረ-ታሪክ)!

4.2.3.1. የሰቆቃው አይነት፡-

የአቡነ ቴዎፍሎስ ሰቆቃ 6 ክፍሎች አሉት፡፡

 1. በቁም የተፈጻመባቸው ቅትለተ-ሰብእና፣
 2. ከመንበራቸው ከቀኖና እና ከሕግ ውጭ ተገፍቶ መውረድ፣
 3. በጭካኔ የተሞላና ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ፍጹም ያፈነገጠ እስራት! ‹‹እባካችሁ አትሰሩኝ አልልም፤ ግን ገዳም ወስዳችሁ እሰሩኝ›› የሚለው አራኅራኂ ቃላቸው ካነበብኩት ጀምሮ ይረብሸኛል!
 4. ስቃይ! በባዶ እግር ማስኬድ፣ በደረቅ መላጨት፣ አስኬማ መግፈፍ፣ መስቀልና ስዕል መቀማት፣ ቁምጣ አስለብሶ ስፖርት ካልሰሩ እያሉ መሳቂያና መሳለቂያ ማድረግ፣ ጸያፍና መደዴ ስድቦች፣ …!
 5. ግድያ! የገዛ ወንድሞቻቸው ለአቡነ ቴዎፍሎስ ጥይትነፈጓቸው! ፓትርያርኩ በገመድ ታንቀው በጻዕር አለፉ!
 6. ዝክረ-ስምዕ ማጥፋት! ገዳዮች ከገደሉ በኋላ የአቡነ ቴዎፍሎስ ሥም በጸሎተ ፍትሐት ለ13 እንዳይነሳ አደረጉ! ዛሬም ገፊዎቻቸው አላረፉ! ሞት ርስት ነውና እነሱም እስኪጠሩ የሰማዕቱን ዐፅም የሚያሳርፉት አይመስሉም!
4.2.3.2. አላስፈላጊ ጉርምርምታ-1!

መባል ባይገባውም አለመባሉ ዘላቂ ጉዳት እንዳያድርስ ከመፍራት የተባለ ነው አሁን የምለው ጉዳይ! አዝናለሁ! ማለት እንደሌለብኝ እያወቅሁ አለመባሉን ተጠቅመው የሚያወናብዱ ወገኖችን (እንዲያው) ለማስታገስ ያህል ነው የምለው! ነገሩ እንዲህ ነው…! ነፍሱን ይማረውና ከአባቴ ጋር ባላቸው ቅርርብ የተዛመድኳቸው አንዳንድ የጎጃም ካሕናት የአቡነ ቴዎፍሎስን ሰቆቃ ‹‹ጎጃሜ ስለሆኑ ብቻ በጥላቻ የተፈጸመባቸው›› የሚል (በእኔ እምነት) ደካማ ሐሜት ይሰነዝራሉ፡፡ ሐሜቱን ልዩነት መዝራትና ማስፋት የሚወዱ ቀሳጥያን ተሐድሶዎችም ቀስጠው ያራቡታል፡፡ ስህተት ነው! ባጭሩ ምክንያቶቼን ልደርድር፡፡

 1. ለአቡነ ቴዎፍሎስ መውረድ ትልቁን ሥራ የሠራው የደርጉ ምክትልና የተሐድሶ ኮሚቴው የበላይ ኮ/ል አጥናፉ አባተ የጎጃም (ብቸና) ሰው ነው፡፡ በቤተ ክህነቱ ያሉ እንደ ሊቄ ብርሃኑ እና ታላቁ አባት አቡነ አብርሃም ሳይቀሩ ፓትርያርኩ እንዲወርዱ ከፈረሙት ወገኖች ስለመሆናቸው የሰውና የሠነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 2. በአቡነ ቴዎፍሎስ ከመንበር መገፋት ትልቅ ሚና በተጫወተው የተሐድሶ ጉባኤ አባልነት ደረጃ ከተሳተፉት መካከል (ፓትርያርኩ እንዲወርዱ ድምጽ ባይሰጡም) የዲማው አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩበት፡፡ ደርግም ሆነ የተሐድሶ ጉባኤ የአንድ ብሔር ተዋጽዖ አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ፡- ከጎንደር ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው፣ ከሸዋ ፕ/ር ጌታቸው፣ ከወሎ አቶ መርስዔ ኀዘን አበበ(ተሐድሶዎች ሆን ብለው ታላቁን ‹‹ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ››ና ‹‹አቶ መርስዔ ኀዘን አበበ›› በማምታት ያወናብዳሉ)፣ ከኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ንቡረዕድ ድሜጥሮስ ነበሩ፡፡ ስለዚህ የየክፍለ ሀገሩ ተወካይ የተሳተፈበትን ተግባር አንደኛው አካባቢ አንደኛውን ለማጥቃት ያደረገው ማስመሰል ታላቅ በደል ነው፡፡ አ-ያ-ን-ጽ-ም! ! !

 3. በደርግ ዘመን ከቤተ ክህነቱ ወገን እጅግ ዘግናኙን ሰቆቃ የተቀበሉት አቡነ ቴዎፍሎስ ቢሆኑም ከታሠሩት ውስጥ የሁሉም ክፍለ ሀገር ካሕናትና ጳጳሳት አሉ፡፡ ከሸዋ አቡነ ጴጥሮስ፣ ከትግራይ አቡነ ጳውሎስ፣ ከጎንደር ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ (የአሁኑ አባ መልከጼዴቅ)፣ የአክሱሙ ንቡረዕድ ፀሐዩ በአብዛኛው ለ7 ዓመታት እየታሠሩ ከወጡት ወገን ናቸው፡፡ ተለይቶ አንድ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ዒላማ አልተደረገም!

 4. በደርግ ጭፈጨፋዎች ላይ ያለን መመረር እንዳለ ሆኖ ‹‹ደርግ አንድን ብሔር ለይቶ ያጠቃል›› የሚል ሐሜታ አይዋጥልኝም! ማንም ጳጳስና ፓትርያርክ የትም ቦታ ይወለድ አቡነ ቴዎፍሎስ እንዳደረጉት ደርግ ላስቀመጠው የተሐድሶ ኮሚቴ ተብዬ ኢ-መዋቅራ ጣልቃ ገብነት ካልተመቸ እድል ፈንታው ከአቡነ ቴዎፍሎስ የተለየ ይኾናል ብየ አልገምትም!

 5. ለአቡነ ቴዎፍሎስ ደግ የዋሉ አብዛኞቹ ሰዎች የጎጃም ሰዎች እንዳልነበሩ ማስተዋልም ይገባል፡፡ የአቡነ ቴዎፍሎስ መምህርና የአዲስ ዓለም ማርያም ንቡረዕድ (ሐዲስ) ተክሌ (ኋላ አቡነ ዮሐንስ) የሸዋ ሰው ናቸው፣ ፓትርያርኩ እንዳይወርዱ የታገሉት ፕ/ር ጌታቸው የሸዋ ሰው ናቸው፣ ፓትርያርኩ ከምንኩስና እስከ ፕትርክና በደረሱበት የ33 ዓመት የሲመት ጉዞ የተጓዙት በጎጃሞች ብቸኛ ድጋፍ አልነበረም! ዘመን አልፎ ዐፅመ-ቴዎፍሎስ ሲፈልስ መቃብራቸውን የጠቆሙት ሐኪም ቀነዓ ኢብሳ ጎጃሜ አይደሉም፡፡ ዐፅሙን ከሙታን መካከል የለዩት የትግራዩ አቡነ መቃርዮስ ናቸው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስን ‹‹ሰማዕተ ጽድቅ›› ያሏቸው በ1984 ዓ.ም የሽግግር ወቅት ዐቃቤ መንበር የነበሩት ትውልደ-ኤርትራዊውና ኋላም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትለይ የመጀመሪያው ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ያዕቆብ ነበሩ፡፡ በአቡነ ቴዎፍሎስ ዙሪያ ታላላቅ አስተዋጽዖቻቻውን በመዘከርና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያለስስት በመግለጽ የሸዋውን ሊቀ ካሕናት ክንሀገብርኤል አልታዬ የሚወዳደር ሰው አላጋጠመኝም! ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ አስተዋጽዖ የመሰከሩ ጳጳሳትንና ቀሳውስትን ከነትውልድ አካባቢያቸው መጥራት አይከብደኝም፡፡ ሆኖም ከዚህ በላይ መሄድ ዶግማና ቀኖናዋ ዜግነት ከቀለም፣ ብሔር ከቋንቋ፣ እድሜ ከጾታ፣ ነገድ ከጎሳ ለማይለየው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ክብር አይመጥንምና ልለፈው! ባጭሩ የጎጃም አጉረምራሚ ዘመዶቼ፤ ‹‹ባልሆነ ወግ ለተሐድሶ ትጥቅ አናቀብል›› ብቻ ልበል!

4.2.3.2. አላስፈላጊ ጉርምርምታ-2!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ውስጡና በውጩ የቤተ ክህነት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ‹‹አቡነ ቴዎፍሎስ የተገደሉት በማኅበረ ቅዱሳን ሴራ ነው›› ይላሉ፡፡ ስሁት አነጋገር ነው! በመርህ ደረጃ ከማኀበረ ቅዱሳን ራዕያትና ግቦች ጋር አንዳች ተዐቅቦ ኑሮኝ ባያውቅም በተወሰኑ ተቋማዊ አካሄዶቹና በአንዳንድ የማኅበሩ አባላት ዘንድ በምታዘባቸው (በእኔ እምነት) የማያንጹ የሚዲያ ዘመቻዎች በተደጋጋሚ ምንታዊ ውስጥ እንደምገባ መደበቅ አልፈልግም! ይሕ እንዳለ ኾኖ የአቡነ ቴዎፍሎስን አሟሟት ካነሱ ወዲያ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን አቡነ ቴዎፍሎስን አስገደለ›› የሚለውን ምውት ክስ እንዳላዩ ማለፍ ከብዶኛልና አለመስማማቴን ለማስረዳት የሚረዱ ምክንያቼን ላምጣ!

 1. በማኅበረ ቅዱሳን ምስረታ(ግንቦት 1 ቀን 1984 ዓ.ም?) እና በአቡነ ቴዎፍሎስ ከሥልጣን መውረድ(የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ.ም) መካከል ከ16 ዓመት በላይ ልዩነት አለ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የተመሠረተው አቡነ ቴዎፍሎስ ባረፉ በ16ኛው ዓመት ነው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ሲወርዱ እንኳንስ ማኅበረ ቅዱሳን ሊመሰረት ለማኅበሩ ምስረታ ቡራኬ የሰጡት አቡነ ጎርጎርዮስም አልተጰጰሱ፤ ግሪክ በትምህርት ላይ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የሌለን ተቋም ባልነበረበት ጊዜ ለተደረገ ድርጊት ኃላፊ ማድረግ ነውር ነው!

 2. ለአቡነ ቴዎፍሎስ መውረድ ምክንያት የሆኑ ቡድኖች (1) የደርግ አባላት፣ (2) የጊዜያዊ (ተሐድሶ) ጉባኤ አባላትና የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች፣ (3) ኮከብ ቆጣሪ መሰግላን፣ (4) አንካሴ የሚሸከሙ ባሕታውያን መሰሎች፣ (5) መሻሻልንና ለውጥን ከማይፈልጉ ወግ አጥባቂዎች ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡ በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ይታወቃሉ፡፡ የተወሰኑት ከፓትርያርኩ ቀድመው በደርግ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ ኮ/ል ዳንኤል ፓትርያርኩን ሲያሰቃይ ከርሞ ከእሳቸው ቀድሞ ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም መገደሉ፣ ኮ/ል አጥናፉም ኅዳር 2 ቀን 1970 መገደሉ ከላይ ተወስቷል፡፡ የተሐድሶ ጉባኤ አባላትም ቢሆኑ ያሉትም፣ የሞቱትም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ንክኪ ያላቸው አይደሉም–እኔ እስከማውቀው፡፡

 3. ወሬዎችን አገጣጥሞ ሴራ ፈጥሮ ከማጮኽ ውጭ ተጨባጭ የሰውና ሰነድ ማስረጃ ለዚህ አሉባልታ ማጠናከሪያ ሆኖ ሲቀርብ አላጋጠመኝም! የውሸት ጥይት መተኮስ ደግሞ ጥይቱ ባያልቅም ያስተዛዝባል፡፡ እንዲያ አይነት ሰዎች ሲበዙባቸው ነው መሰል ፕ/ር ጌታቸው ‹‹መሳሪያው ውሸት የሆነ ሰው የጥይት
  ችግር አይኖርበትም›› የምትል ወርቃማ ገለጻ አለቻቸው!

 4. በደርግ ጊዜ የነበረው አጠቃላይ አመለካከት እከሌ ከእከሌ ሳይል ጠርዘኛ የኢ-አማኒነት መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህ በሂደቱ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ፓትርያርክና ተቋሙ ላይ የተከሰተው ምስቅልቅልና ሰቆቃ ብርቱ ቢሆንም ሌሎች የሃይማኖት መሪዎችም ተገድለዋል፤ ታስረዋል፡፡ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበሩት ቄስ ጉዲና ቱምሳ ተገድለዋል፤ ዐፅማቸው የወጣው የአቡነ ቴዎፍሎስ ዐፅም በፈለሰበት ጊዜ ነው፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርሰቲያን መሪና የምስራቅ አፍሪካ ካርዲናል የሆኑት አባ ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በደርግ ጅማ ላይ ከታሰሩት ወኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህ በደርግ ጊዜ በነበረው የጀብደኛነትና የኢ-አማኒነት መንፈስ ምክንያት የተሰውት አባት ሰቆቃዊ ግድያና ከሥልጣን መውረድ ከሌሎች ሃይማኖቶች በተለየ በኛ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ህዋስ በ1960ዎ ስለነበረ ነው ብሎ አምኖ፣ ይሕንኑ ጽፎ፣ አስነብቦ ለማሳመን መሞከር ኃጢአትም፣ ነውርም፣ ወንጀልም ነው! ማኅበረ ቅዱሳንን ለመውቀስና ለመተቸት ያለፉት 24 ዓመታት ጉዞው፣ ያም ካልበቃ መስራች አባላቱ ከአቡነ ጎርጎርዮስ ጋር ግንኙነት ካደረጉበት ጊዜ ወዲህ ያለው ተግባሩና አካሄዱ የበቃ አርእስት ፈጥሮ ለመከራከር ስለሚያስችል ያልሆነ ወግ እየመዘዙ መተረክ ‹ለአመክንዮ ምክንያት ለኃጢኣት›› ያስጠቅሳልና ቢቀር ወይም ቢቀየር ይሻላል፡፡

ርእሱን ከመጠቅለሌ በፊት ግን መሠወር የማልችላትን ቅሬታ ልግለጽ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ሆነ ቤተ ክህነት፣ እንዲሁም መንፈሳውያን የቤተ ክርሰቲያኗ የትምህርት ተቋማት ባለፈው መቶ ዓመት ስለተሠውት አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሚካኤልና አቡነ ቴዎፍሎስ ዝክረ-ስምዕ የሚገባቸውን ሠርተዋል ብዬ አላምንም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በእነዚህ አበው ሥም ተቋማቱን ሲሰይም ዐይተነው አናውቅም፡፡ የአቡነ ቴዎፍሎስን ሰቆቃና የዝዋይ ካሕናት ማሰልጠኛ በእሳቸው መመስረቱን በቅጡ የማያውቁ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ሰንበት ተማሪዎች በብዛት ያጋጥሙኛል፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ በደርግ ዘመን (በ1974 ዓ.ም) በጻፉት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ የግራ ቀኝ አንጓጣጮችን ታግሰው አቡነ ቴዎፍሎስን በፕትርክና ክብር ጠቅሰዋቸዋል(ስለ ኅልፈታቸው ያልጠቀሱት ደርግ የአቡነ ቴዎፍስን ሞት ይፋ ባለማድረጉ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም! )፡፡ ከአቡነ ጎርጎርዮስ ኅልፈት በኋላ የአቡነ ቴዎፍሎስም ሆነ ሌሎች ቅርብ ጊዜ ግፉዓን የተሟላ የሰቆቃ ታሪካቸው ተጽፎ በመንፈሳውያን ተቋማት ሥርዓተ-ትምህርትና ኮርሶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አካል መሆን ሲገባው ሁሉም እንዳላየ ያልፈዋል፡፡ እስካሁን አልሆነም፡፡ ለወደፊቱ ግን እነዚህ የ20ኛው ክፍለ ዘመን አብሪ ከዋክብት የሆኑ አበው የሚገባቸውን ክብር እንዲያገኙ እመኛለሁ፡፡ ምኞቴን ከጸሎት ጋር እየገለጽኩ ይህንኑ ሐሳቤን በሚሸከምልኝ የመጋቤ ብሉይ ሠይፈሥላሴ ዮሐንስ ቅንጭብ መወድስ ልቋጭ!

ሊቁ መጋቤ ብሉይ ሠይፈሥላሴ ዮሐንስ በመወድሱ የ3ቱን የ20ኛዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት መሥዋዕትነት፡- ‹‹ገበሬው ጴጥሮስ አርሶና አለስልሶ ባዘጋጃት የኢትዮጵያ የደም (የመሥዋዕትነት) ማሳ የወደቀች የተገፍዖ ስንዴ 100፣ 60ና 30 አፈራች፤ ምክንያቱም ሚካኤል ተከታትሎ እቅፍ-ድግፍ አድርጎ ማየ(-ደም) አጠጥቶ ሞገስ ሆኗታልና፤ ከነሱ ቀጥሎም ቴዎፍሎስ በፈንታው ለ3 በተገመዱ ገመዶች የመሥዋዕትነት ነዶዋን ሸብ አድርጎ አዝመራውን ጠቅልሎታል…›› ሲል በመወድሱ ይራቀቅበታል፡፡ ንሳማ! የምወድህ መጋቤ ብሉይ…ከመወድሱ…!

ሥርናየ-ተገፍዖ፡ዘወድቀት፤ በኢትዮጵያ፤
ፈረየት፡ምዕተ፤ ምስለ-ሠላስ፡ወሥሳ፣
ድኅረ-መስተገብር፡ጴጥሮስ፤ ለገራህተ-ደም፡ሐረሳ፣
ሚካኤል፡ከመ-ይስቅያ፤
ማየ-ደም፤ እስመ-ተሳተፈ፤ ወኮነ፡ሞገሳ፣
ወድኅረ-እሉ፡ቴዎፍሎስ፤ ከላስስቲሃ፡አሰረ፤ በማዕሠራት፡ዘይሤለሳ፡፡ …

ልመርቅ፡- አባቶቻችንን ዳግም በግፍ ወደ መቃብር ከማውረድ ይሠውረን! በማወቅና ባለማወቅ በግፉ የተሳተፉትን የንስሐ ልብ ይስጥልን! ይቅር ይበላቸው! ይቅር ይበለን! የአባትና የልጅ ወግ አይፋለስብን! ያለፉትን በቀኙ ያኑርልን! የግፉዐን አበው በረከታቸው በኛ በሁላችን ላይ ይሁን! ያሉትን አበው በቀደሙት ጎዳና የሚራመዱ ያድርግልን! ሀገራችንን ወንድም የወንድሙን ደም የሚያፈስስባት ከመሆን ይታደግልን! የሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን! ! ! ! ! ! !

፡፡ ፡፡ ፡፡ ፡፡ ፡፡ ፡፡ በአማን ነጸረ፤ ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም፡፡ ፡፡ ፡፡ ፡፡ ፡፡ ፡፡

_ማጣቀሻዎቼ! _

ሀ. መጻሕፍት፣መጽሔቶችና ጋዜጦች

 1. መጽሐፍ ቅዱስ፣‹‹የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት››፡፡1980 ዓ.ም፡፡አ.አ፡፡ብ/ሰ/ማ/ድ፡፡
 2. ፍስሐ ደስታ (ሌ/ኮ)፣‹‹አብዮቱና ትዝታዬ››፡፡ኅዳር፣2008 ዓ.ም፡፡ፀሐይ አሳታሚ፡፡
 3. ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር)፣‹‹በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ፡አንዳፍታ ላውጋችሁ››፡፡2ኛ ዕትም፣2006 ዓ.ም፡፡ግራፊክ አታሚዎች፡፡
 4. ጌታቸው የሮም (ሻለቃ)፣‹‹የለውጡ ረመጥ የታሪክ ማስታዋሻ››፡ከ1966 እስከ 1968 ዓ፣ም፡፡እ.ኤ.አ 1990፡፡
 5. ኪዳነ ማርያም ጌታሁን(መምህር)፣‹‹የሐሰት ምስክርነት››፡‹‹የቋሚ ምስክርነት›› ለተሰኘው የአባ መልከጼዴቅ መጽሐፍ፡፡1994 ዓ.ም፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
 6. በኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትና ጳጳሳት፣‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000 ዓ.ም)››፡፡2000 ዓ.ም፡፡ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡
 7. ገብረ ዮሐንስ ገብረ ማርያም(M.T)፡፡‹‹ክርስትና በኢትዮጵያ››፡፡1995 ዓ.ም፡፡
 8. ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል(ባላምባራስ)፡፡‹‹ዝክረ ነገር››፡፡1942 ዓ.ም፡፡ነጻነት ማተሚያ ቤት፡፡
 9. ክንፈ ገብርኤል አልታየ (ሊቀ ካሕናት)፣‹‹ከሊቀ ካሕናት እስከ ፓትርያርክ፡ለአቡነ ባስልዮስ 9ኛ ዓመት በዓለ-ሲመተ-ፓትርያርክ የተዘጋጀ›› መጽሔት፡፡
 10. ‹‹ነቅዕ ንፁሕ››፡፡ግንቦት 1 ቀን 1966 ዓ.ም፡፡አዲስ ሕይወት፣ቁጥር 4፡፡
 11. ‹‹የቅዱስ ፓትርያርኩ የአዲስ ዓመት መልእክት››፡፡ግንቦት 1 ቀን 1967 ዓ.ም፡፡አዲስ ሕይወት፣ቁጥር 5፡፡
 12. ዳንኤል ክብረት(ዲያቆን)፣‹‹አራቱ ኃያላን››፡፡2006፡፡አግዮስ ኅትመት፡፡
 13. ‹‹ማርክሲስት ሌኒንስት መዝገበ ቃላት››፡፡1978 ዓ.ም፡፡ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፡፡
 14. ‹‹የ3ኛው ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ሲመት›› መጽሔት፡፡ነሐሴ 23 ቀን 1968 ዓ.ም፡፡
 15. ዮሐንስ አድማሱ፣‹‹እስኪ ተጠየቁ››፡፡1990 ዓ.ም፡፡ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፡፡
 16. አንዳርጋቸው አሰግድ፣‹‹በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ፡መኢሶን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ››፡፡1992 ዓ.ም፡፡ሴንትራል ማተሚያ ቤት፡፡
 17. ክፍሉ ታደሰ፣‹‹ያ ትውልድ፣ቅጽ አንድ››፡፡3ኛ ዕትም፣2007 ዓ.ም፡፡ዴርቶጋዳ ማ/ድርጅት፡፡
 18. ገስጥ ተጫኔ፣‹‹ነበር፣ክፍል አንድ››፡፡9ኛ ዕትም፣2007 ዓ.ም፡፡
 19. አስማማው ኃይሉ፣‹‹ኢሕአሠ፣ቅጽ ሁለት››፡፡2006 ዓ.ም፡፡አሳታሚ የ‹ያ ትውልድ ተቋም›፡፡ፋር ኢስት ትሬዲንግ፡፡
 20. ‹‹የተሐድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ሕዳሴ››፡፡2006 ዓ.ም፡፡
 21. ዲሞክራሲያ፣ቅጽ-1፣ቁጥር-1፣11/11/1966 ዓ.ም፡፡
 22. ብርሃኑ አስረስ፣‹‹ማን ይናገር የነበረ…የታሕሳስ ግርግርና መዘዙ››፡፡2005 ዓ.ም፡፡አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፡፡
 23. መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (ብላታ)፣‹‹ዜና ባስልዮስ ሊቀ ጳጰሳት ኢትዮጵያዊ››፡፡ሰኔ 10 ቀን 1950 ዓ.ም፡፡ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡
 24. ከጃርሶ ሞት ባይኖር ኪሩቤል ጋር የተረደገ ቃለ መጠይቅ፡፡የካቲት 1993 ዓ.ም፡፡ሩሕ መጽሔት፣ቅጽ-1፣ቁጥር-3፡፡
 25. ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣‹‹እኛና አብዮቱ››፡፡3ኛ ዕትም፣ሚያዚያ 2006 ዓ.ም፡፡ፀሐይ አሳታሚና አከፋፋይ፡፡
 26. Aregawi Berhe,A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991) , Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam
 27. ጸጋዬ ገብረመድኅን፣‹‹እሳት ወይ አበባ››፡፡2ኛ ዕትም፣1999 ዓ.ም፡፡ግራፊክስ ማተሚያ ቤት፡፡
 28. ‹‹ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት››፣ለ5ኛ ዓመት ፍልሰተ ዐፅማቸው፡፡ሐምሌ 4 ቀን 1989 ዓ.ም፡፡ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡
 29. ‹‹ሐመር›› መጽሔት፡፡ኅዳር/ታሕሳስ 1998 ዓ.ም፡፡
 30. ራዕየ ቴዎፍሎስ መጽሔት፡፡ሐምሌ 2002 ዓ.ም፡፡በጎፋ መካነ ሕያዋን ካቴድራል የተዘጋጀ፡፡
 31. መርሻ አለኸኝ(ዲያቆን)፣‹‹ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን››፡፡1996 ዓ.ም፡፡
 32. ‹‹ጦቢያ›› መጽሔት፣7ኛ ዓመት፣ቁጥር 3፣1992 ዓ.ም
 33. ‹‹ድምጸ ተዋሕዶ›› ጋዜጣ፣ሐምሌና ነሐሴ 1983 ዓ.ም
 34. ‹‹የገጠርን መሬት የሕዝብ ሀብት ለማድረግ›› የወጣ አዋጅ ቁጥር 31/1967
 35. ብርሃኑ ድንቄ (አምባሳደር)፣‹‹ቄሳርና አብዮቱ››፡፡

ለ. ከኢንተርኔት የተገኙ ልዩ ልዩ ማጣቀሻዎች(ቀጥታ ያልተጠቅምኳቸውም አሉ)!

 1. አዘጋጆች ብዙ መረጃዎችን የማገኝበት አድራሻ ነውና ባላውቃቸውም ውለታቸው ሲከብደኝ እንደሚኖር በአደባባይ እናገራለሁ፡፡
 2. ‹‹ለራስ ሲቆርሱ…›› ነውና ይህቺ https://www.facebook.com/firdna.kunene/posts/1646944692221431 ወይም በዚህ የምትገኘው የራሴ ክታብም ስንቅ ሆናኛለች
 3. እነዚህም
 1. https://www.facebook.com/firdna.kunene/posts/1454580061457896
 2. https://www.facebook.com/firdna.kunene/posts/1454880741427828
 3. https://www.facebook.com/firdna.kunene/posts/1455914964657739
 4. https://www.facebook.com/firdna.kunene/posts/1455915354657700
 5. https://www.facebook.com/firdna.kunene/posts/1455915927990976 ቀላል አልነበሩም!
 1. ዊኪፒዲያ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ የሚለው አለው
 2. ይቺ ሊንክም ደኅና ናት
 3. ይሕ የዓለምህ ዋሴ አስገምጋሚ ድምጽ አጽመ-ቴዎፍሎስ እንዲወጣ ስለተጋደሉት አባት መልአከ ሕይወት አባ ይትባረክና የፓትርያርኩ ጽም ስለወጣበት ሂደት ይተርካል
 4. የኢሕአፓዋ ‹‹ዲሞክራሲያ›› በዚህም ትገኛለች
 5. ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለኮ/ል ፍስሐ ደስታ መልስ የሰጠበት አጭር ጽሑፍ–የኔም አስተያየት በውስጡ አለ
 6. ይህች ጽሑፍ የራሲያ ቢልሼቪኮች በሀገራቸው ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ ያሳደሩትን መሪር ጫናና ኢ-አማኒነትን የማስረጽ ዘመቻ ትተረካለች፤ በጽሑፌ ባላካትተውም እነሱን ሳይ ኛዎቹን አብዮታውያን አመሰገንኩ! ሆ! እዩትማ!
 7. ዶ/ር ዳኛቸው የፕ/ር ጌታቸውን የሕይወት ታሪክ የሚተርክ መጽሐፍ ሲዳስሱ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስም አንስተው ነበር