ህየንተ ዓርብ:- ሐተታ-ሥልጣን በቅኔያት!


(በአማን ነጸረ) #1

ስለ ሥልጣን እናውጋ! ሥልጣን ‹‹ሠለጠ›› ከሚለው የግእዝ ቃል ይወጣል፤ ‹‹ሠለጠነ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ሥልጣን››ና ‹‹ሥልጣኔ›› ጎረቤት ኖረዋል ለካ! ምንጫቸው አንድ ቃል ነው፡፡ ሥልጣን የእንግሊዝኛ አቻው authority መሆን አለበት፡፡ ሥልጣን አሰልጣኝ (ቀቢ/መራጭ/አንጋሽ/ጉልበት) ይፈልጋል፤ ምንጭ አለው–ሥልጣን፡፡ አይሑድ ጌታ ድውያንን ሲፈውስ ‹‹በአይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ?! ›› ይሉት ነበር፤ የሥልጣንህ ምንጭ (validity) ከየት ነው ለማለት!

ባገራችን የሥልጣን ምንጮች 3 ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ (1)አጥንትና ደም፣ (2)ጉልበት፣ (3)ምርጫ፡፡ ምርጫ ለሰበካ ጉባኤ፣ ለገዳ ሥርዓት፣ ለእድርና እቁብ ለመሳሰሉት ታገለግላለች፤ ሌላው እንኳ ተከድኖ ይብሰል! አጥንትና ደም ከጉልበት ጋር ተዋሕዳ ከሀገራችን በትረ-ሥልጣን ጋር ከቆረበች ብዙ ሺ ዘመኗ ነው ይባላል፡፡ ‹ክንዱን ሳይንተራስ› መንበረ ሥልጣኑን ማን ለማን ሊለቅ! ባለሥልጣን ‹‹በጋርድ›› እንጂ ‹‹በካርድ›› አይተማመንም፤ በፖለቲካ ባህላችን፡፡ ብቻ ለአመል አሉ፡፡ እነ ካሌብ አሉ፤ ሥልጣን በቃን ያሉ (5ኛ ክፍል ሳለሁ ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን በፈቃዱ የለቀቀ አፍሪካዊ መሪ›› ሲባል እውነተኛ መልሱ ‹‹ካሌብ›› መሆኑን እያወቅሁ አስተማሪያችን ‹‹ማንዴላ›› ብለው ስላስተማሩ ኤክስ እንዳይገባብኝ ካሌብን ለማንዴላ ሠዋሁት! አርጎ እንደሚጸጽተኝ! )፡፡ ከካሌብ ወዲህም ሥልጣን ትተን ገዳም ካልገባን ብለው የተገለገሉ ‹ጥቂቶች ቆራጦች› ነበሩ፤ በተራ ምክር አልመለስ ሲሉ በቅኔ ተከለከሉ፡፡ ‹ካወቃችሁባት፣ ገረገራም ዋልድባ ናት፤ › ተባሉ፡፡

##1. ካወቁባት፣ ገረገራም ዋልድባ ናት፤ ከተውትም፣ የማይተው የለም!
###ሀ. ካወቁባት፣ ገረገራም ዋልድባ ናት!

ቅኔው የተደረገው ለመስፍኑ ራስ ዓሊ ነው ይላሉ መ/ብርሃን አድማሱ፤ ሆኖም ይዘቱ ለፍጻሜ መንግሥት ተ/ሃይማኖት ይመስላል፡፡ መልእክቱ መስፍኑ/ንጉሡ መንግሥታቸውን ትተው ለመመነን ያላቸውን ሐሳብ እንዲቀይሩ የሚማጸን ነው–በሥልጣን ቆዩልን፡፡ ‹‹(መስፍን/ንጉሥ) ተክለ ሃይማኖት ሆይ! የጽድቅን ነገር ከላሊበላ ዐይተህ ተረዳ፡፡ ከዚህች ዓለም ተለይተህ ለብቻህ አትሁን፤ ላንተም ሆነ ለላሊበላ ምድር አንድ ናት፡፡ ልብህ ያለዕረፍት በዋልድባ ወአብረንታቲ (ገዳም) የምናኔ ፍላጎት አይታወክ፤ ካወቅህበት ገረገራም (የገጠር አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንም) ዋልድባ ናትና፤ ›› የሚል ነው፡፡ ባጭሩ፡- ‹ክቡር ሆይ! የጽድቅ ቦታ ገዳም ብቻ አይደለም፤ በዙፋን ተቀምጦም የጽድቅ ሥራ መስራት እንደሚቻል ከቅ/ላሊበላ ተማር› ማለት ነው፡፡

ተክለ-ሃይማኖት፡ዜና-ጽድቅ፤
ተሰአል፡እምላሊበላ፤
ወዕራቀከ፡ኢትቁም፤ እምንዋየ-ዓለም፡ዛቲ፣
ዚአከ፤ ወዘላሊበላ፤ እስመ-ምድር፡አሐቲ፣
ወልቡናከ፡ኢይድክም፤ ኵለሄ፤ በእግረ-ልቡና፡ሐታቲ፣
በፍቅረ-ዋልድባ፡ወአብረንታቲ፣
እመሰ፡ተአምር፤ ባቲ፣
ገረገራ፤ ዋልድባ፡ይእቲ፡፡

መስፍኑ/ንጉሡ ተማጽኖውን ተቀብለው በሥልጣን ይቆዩ/አይቆዩ እናጣራለን፡፡ ልቡናቸው ጨክኖ ከመነኑ እንደ አድያም ሰገድ ኢያሱ እናደንቃቸዋለን፡፡

###ለ. ከተውት የማይተው የለም!
አድያም ሰገድ ኢያሱ የአማርኛ ባለውለታ ናቸው፤ ትርጓሜ-መጻሕፍት በአማርኛ እንዲሠራና አንድምታ እንዲስፋፋ የደከሙ የዘመነ-ጎንደር ንጉሥ፡፡ ሊቃውንቱን አሰባስበው የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ሲሰሙ ዓለምን ናቁት፡፡ ለምናኔ ተነሡ፡፡ ሊቃውንቱ ግርምትና ሐዘን ተቀላቀለባቸው፡፡ ኀዘን ለቅኔ ትመቻለች፤ ልብ ሲሰበር የምስጢር ልቡና ወለል… ትላለች፡፡ ወለል አለች፡፡ ለንጉሡ ተቀኙለት፡፡ እንቆንጥር ከመወድሳቸው…

ኵሉ፡ይትኀደግ፤ እመ-ኀደግዎ፤
ምሳሌ-ዝኒ፡ነገር፤ እምኀልዮ-መንበር፡ምጡቅ፣
አምጣነ-ኢያሱ፡ኀደገ፤ ተድላ-መንበሩ፡ዘወርቅ፣
ወከዊኖተ-ነግድ፡በብሔሩ፤
ኢያስተዐጽብ፤ ያዕቆብ፡ልሂቅ፣
በአንጻረ-አብርሃም፡ወይስሐቅ፤
ትሩፋነ-እሉሰ፡ንህነ፤ ሐለፍተ-ፍና፡እንበለ-ስንቅ፣
ለጽድቅ፡ኢንዜከራ፤ ወኢትዜከረነ፡ጽድቅ፣
እስመ-ጊዜ-ብዕልነ፡ንትዔበይ፤ ወጊዜ-ንዴትነ፡ንሰርቅ፡፡ …

አሉ፤ አድያም ሰገድ ኢያሱን ዐይተው፡፡ ትርጓሜው፡- ‹‹ከተውት የማይተው የለም፡፡ ለዚህ ምሳሌ የወርቅ መንበሩን ትቶ የመነነው (አድያም ሰገድ) ኢያሱ ነው፡፡ በአብርሃምና በይስሐቅ አንጻር የሚኖር የያዕቆብ ስደትም አይገርምም፤ (ከተውት የማይተው የለም! )፡፡ ስንቃችንን ሳንሰንቅ የምንጓዝ እኛ የነሱ ተከታይ ተጓዦች ግን ጽድቅን አላሰብናትም፤ እሷም አላሰበችን፡፡ በባለጸጋነታችን ጊዜ እንታበይልንና፤ በድኻነታችን ጊዜም እንቀስጣለንና፤ (ጽድቅን አላሰብናትም)፤ ›› ይላል በወቀሳ፤ አድያም ሰገድ ኢያሱን አብነት አድርጎ፡፡

ይሕን የሰሙት ሌላው ባለቅኔ ‹መስሎት እኮ ነው፡፡ ከጥንትስ ቢሆን! አብርሃም ቢሰደድ ለእንጀራ ነው፤ ያዕቆብም እንደዚያው፡፡ ዳዊትም ለሥልጣኑ ነው፡፡ ባይሆን የንጉሥ ክርሰቶስ ግብጽ ለግብጽ መንከራተት ቢያስደንቅ እሺ! › ሳይሉ አልቀሩም!

##2. ኢየሱስ ፡ ሀገር አልባው ሀገር ገዥ፣ የሕይወት እንጀራው የእንጀራ ራብተኛ! !

እንዲህ የሚሉት ወለጌው የቅኔ ሰው ናቸው፡፡ የንታ ገ/ሥላሴ ሀገራቸው ወለጋ ነው፤ ወንበራቸው ጎጃም ኤልያስ፡፡ ተማሪዎቻቸው እነ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ…! በ1939 ዓ.ም አካባቢ ዐረፉ፡፡ ደጋግሜ ተናግሬያለሁ! በኔ ንባብ በእሳቸው ልክ ቅኔው በየመጻሕፍቱ የተመዘገበለት ክቡር መምህር የለም፡፡ ክቡር ናቸው፡፡ በእመቤቲቱ ልጅ እንዲህ ይቀኛሉ፤ ‹‹እህ! ዳዊት ቢሰደድ መንበሩ በሳዖል ስለተፈተነ ነው፡፡ አብርሃም ቢሰደድ እንጀራ ፍለጋ ነው፡፡ መቼስ! ሥልጣንና እንጀራ ከጥንትም ምክንያተ-ስደት ናቸው፡፡ አንቺ ሆይ! ! ድንግል ሆይ! የልጅሽ ስደት ከቶ ምን ፍለጋ ነው? ምክንያቱ አልገባንም፡፡ እንጀራ ፍለጋ እንዳይባል ራሱ የሕይወት እንጀራ ነው፤ ለሥልጣን እንዳይባል ሥልጣን ሁሉ በእጁ ነው፡፡ ሆ…! ››፡፡ ከመወድሱ እንደወረደ ያንበልብሉለትማ ገብርዬ፤ ተቀበል…

ስድተ-ነጋሢ፡ዳዊት፤ እንበይነ-መንግሥት፤
ወስደተ-አብርሃም፡አብ፤ ለኀሢሠ-እክል፤ ውእቱ፣
ኀሢሠ-መንግሥት፡ወእክል፤ እስመ-ሰዳዲ፡እምጥንቱ፣
ባህቱ፡ድንግል፤ ሀገሪትነ፤
ኢተዐውቀ፤ ነገረ-ስደቱ፤ ለወልድኪ፡ዝንቱ፣
ወከመ-ወኢምንት፤ ምክንያቱ፣
አምጣነ-ለሊሁ፡ኅብስት፤ ወመንግሥት፡እስመ-ሎቱ፡፡ …

እንግዲህ ቃል አለብን! ንጉሡን አንስተን ንግሥቲቱን ችላ አንላትም–ያውም በፍልሰታ ዋዜማ–እንዲያ ብናደረግ To ignore The Mother means, to misinterpret The Son የሚለው ከቅዱስነታቸው (አቡነ ጳውሎስ) መመረቂያ ጽሑፍ ያገኘነው የእሷን ቦታና ማዕረግ አመላካች ቃል ይቃወመናል! እሷ እንደ ሔዋን ንግሥትነትን ሳትመኛት በምግባሯ የተነሣ ንግሥትነት ራሷ ፈልጋት መጣች፡፡ ሥልጣን ሲሸሹዋት አደል የምትከተል!

##3. የሁለት ሔዋኖች የንግሥትነት ወግ!

ቀዳሚቷ ሔዋን ‹‹ሰላም ለኪ ሔዋን! ንግሥተ ሰማያት ወምድር! ›› ስትባል ልቧ በሐሴት ቀለጠ (የሴቶች የቁልምጫ ፍቅር ከዚህ ይጀምራል እንላለን ስናማቸው–አድናቆትና ውዳሴ ከንቱ ያጠቃቸዋል እንላለን–prejudice ባንባል! )፡፡ አዳም በበኩሉ ‹‹ሰላም ለከ አዳም! ንጉሠ ሰማያት ወምድር! ›› ሲባል በመጠኑ ተግደረደረ፡፡ የምድርን ንግሥና የከለከላቸው አልነበረም፡፡ ልቡና አይረካ! ተመኙ! የሰማዩ ሥልጣን አማራቸው፡፡ የሥልጣኑን መሰላል እስከመጨረሻ ወጥተው በ3ቱ ሥላሴ መንበር በ4ኛና 5ኛነት ለመደረብ ተመኙ፡፡ ‹‹ንዷቸው! ግዟቸው! ›› ተብለው የተሰጡዋቸውን ፍጥረታት ዘንግተው ወደላይ ወደፈጣሪያቸው መንግሥት አንጋጠጡ፡፡ ሰው ያለውን ሳይሆን የሌለውን አደል የሚያስብ! ሊቁ ይሕን ታዝቦ ህም! ልብ አይሞት፤ ‹‹ኵሉ፡ለእመ-ሞተ፤ አምጣነ-ልቡና፡ኢይመውት›› ይላል፡፡ ምክንያቱም…

…አዳምሂ፡ለእመ-ነግሠ፤ መልእልተ-ኵሉ፡ፍጥረት፣
መንግሥቶ፡ለፈጣሪሁ፤ ተመነየ፡በገነት፣
ኵሉ፡ለእመ-ሞተ፤ አምጣነ-ልቡና፡ኢይመውት፡፡

ክፋቷ! ክፋቷ ሥልጣን ሲፈልጓት ትርቃለች፡፡ ከመለኰት መተካከል የፈለገችው ሔዋን የሰማይ ንግሥት መሆንን ተመኘች፤ አልተሳካላትም፡፡ ዳግሚት ሔዋን እመቤታችን ግን ምኞቷ በኢሳይያስ 7 ትንቢት የተነገረላትን እመቤት ማገልገል ነበር፤ ንግሥትነቱን መች አስባው! ያላሰበችው ለእሷ ሆነ፡፡ ባለቅኔው ይሕ የ2ቱ ምኞት ፍጻሜ ገረመው፡፡ ተገርሞ ‹‹ሔዋን የክብር ዙፋን ተመኘች፤ ድንግል በበኩሏ ትንቢት የተነገረላትን እመቤት ደርሳባት ለማገልገል ተመኘች፡፡ ምኞታቸው አልቀረም–የ2ቱም! (ለጊዜው) ሔዋን (የሰማይ ንግሥትነት ባይቀናትም) ዘግይታ ከባርነት ወጣች፡፡ ድንግልም ለሰዎች ሰላምና ምሕረት (ለማስሰጠት) በባለሥልጣኑ ልጇ ቤት አገልጋይ ሆነች፤ ደከመች፡፡ መለኰት የ2ቱን ምኞት ዐየ፡፡ ለአገልጋይዋ እመቤት ተራዳእያን መላእክትን ላከ፡፡ እሱም አልበቃው፡፡ በታዥነቷ ተመሰጠ–በአማን ነጸረ፡፡ መለኰት (ልጇ በሥጋዌው) ታዘዛት፡፡ በስተመጨረሻ ለታዛዡዋ እመቤት የድካሟ ውለታ በ4 እጥፍ ተመለሰላት፤ ›› ይላታል ሊቁ፤ ለመታዘዝ ተመኝታ መላእክት ታዘዙላት!

ተመነየት፡ሔዋን፤ መንበረ-ልዕልና፤
ወድንግል፡አብደረት፤ ውስተ-ቤተ-ድንግል፡ተራድኦተ፣
ባሕቱ፡ኢይኩን፤ ተምኔተ-ክልኤሆን፡ሀሰተ፣
ሔዋን፡ግዕዘት፤ እምግብርናት፤
ወድንግል፤ ውስተ-ቤተ-ወልዳ፤ ተሰምየት፤ ዓመተ፣
አምጣነ-ብዙኀ፡ትሰርኅ፤
በአስተዳልዎ፡ለሰብእ፤ ሰላመ፡ወምሕረተ፣
መለኮትሂ፡ሶበ-ነጸረ፤ ግብራተ-ዚአሃ፡ክልኤተ፣
ፈነወ፡እምላዕሉ፤ ዘይትራደእዋ፡መላእክተ፣
አኮኑ፡አልጸቀ፤ ፍዳ-ተባርዮ፡ትርብዕተ፣
መጠነ-ብዙኅ፡አዝዞታ፤ እስከነ-ትኤዝዝ፡መለኮተ፡፡

ነገሩማ እሷም ‹‹ገዢዎችን፡ከዙፋናቸው፡አዋርዷል፤ ትሑታንንም፡ከፍ፡አድርጓል፤ ›› ብላ መጻኢ ጸጋዋን ተንብያለች፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እንዲያ የተደረገላቸው አባት አሉ፤ ሥልጣንን ሲሸሹት የተከተላቸው!

##4. ሥልጣንን ሲሸሹት የተከተላቸው አባት፤ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት!

አቡነ ተ/ሃይማኖት ከምንኩስና ተነስተው ባንድ ጊዜ ጵጵስና እና ፕትርክና የተሾሙ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ሥልጣንን ሲሸሹዋት ተከተለቻቸው–እንደ እመቤታችን፡፡ በ1968 ዓ.ም የቤተ ክህነት ጥቂት የሥልጣን ተምኔተኞች አቡነ ቴዎፍሎስን ለሰቆቃ ዳርገው ለመንበሩ ሲመቻቹ የሰማዩ ጌታ ካልታሰበ ቦታ ያልታሰበ ሰው በመንበሩ አስቀመጠ! ያን ጊዜ ባለቅኔው አጋጣሚውን ‹‹ባለጸጎችን ባዶ እጃቸውን ሰደደ፤ ትሑታኑን ከፍ ከፍ አደረገ! ›› ከሚለው የድንግል ትንቢት ምስጢር አስተባብሮ ተቀኘበት! ቅኔው የሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው ነው! ሊቀ ማዕምራን በተወለዱበት (ትውልዳቸው ደብረ ታቦር) ጎንደር ክፍለ ሀገር ለ5 ዓመታት የሻለቃ መላኩ ተፈራ ምክትል ነበሩ፤ በአቡነ ቴዎፍሎስ ሰቆቃም ችንካር ካቀበሉት ነው ቁጥራቸው፡፡ ይሕ አንድ ገጽታቸው ነው፡፡ በሌላ ገጽታቸው ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅነታቸው ዘመን ምስጉን ንግግር አዋቂ፣ ጽሑፍ አሳማሪ፣ አስተዳደር አዋቃሪ፣ ሥርዓት አስጠባቂ ነበሩ፡፡ ቅኔውንም ያሳምሩታል፡፡ እንዲህ…

ትንቢተ-ድንግል፡ፈክር፤ ተክለ-ሃይማኖት፣
በዘተዐብዮ፡ነፍስከ፤ ለእግዚአብሄር፡መድኅን፣
ርዕሰ-ማዕዘንት፡እምኮነት፤ ለሕንጻ-መለኮት፡ሥልጣን፣
ነደቅት፤ ዘይሜንንዋ፤ አስኬማከ፡ዕብን፣
እንዘ-ዕራቆሙ፡ለብዑላን፣
አኮኑ፡አጽገበ፤ እምበረከቱ፡ለርኁባን፣
ንግርሂ፡ምሕረቶ፤ ለእግዚአ-ሐዲስ፡ዘመን፣
እምድኅረ-ሰበረ፡ወቀጥቀጠ፤ መናሥግተ-ዘሐጺን፣
በወላይታ፡ቅድስት፤ ደብረ-ሕያዋን፣
ሥርዓተ-ክሕነት፡ቅኔ-ደብተራ፤ አምጣነ-ተተክለ፡ለጻድቃን፡፡

ትርጉም፡- ‹‹ተ/ሃይማት ሆይ! መድኅን እግዚአብሔርን ከፍ-ከፍ በምታደርግ ነፍስሕ የድንግልን ትንቢት ተርጉምልን፡፡ ግንበኞች የናቋት ድንጋይ/አስኬማህ ለመለኮት ሕንጻ/ሥልጣን የማዕዘን ራስ በሆነች ጊዜ፡ (እግዚአብሔር) ባለጸጎችን ራቁታቸውን ሰዶ የተራቡትን አጥግቧልና፡፡ ላዲሱ ዘመን ጌታም ምሕረቱን ተናገር፤ የብረት መሸንጎሪያውን ከሰበረና ከቀጠቀጠ በኋላ የሕያዋን ተራራ በምትሆን ወላይታ ሥርዓተ-ክሕነት/የምስጋና ድንኳን ለጻድቃን ተተክሏልና፡፡ ››

ምስጢሩ፡- ቀደም ሲል እንደተገለጸው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ቁጥር 53 እመቤታችን በኤልሳቤጥ ቤት ተገኝታ ‹‹የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤ ›› ስትል የተናገረችውን ትንቢት የሚያስታውስ ሲሆን መልእክቱም ከጳጳሳቱ ወገን በትምህርትና በአስተዳደር ልምድ ብዙ ከፍ-ከፍ ያሉ ሳሉ እግዚአብሔር ካልተጠበቀው የወላይታ ምድር ዝቅ ያለውን መናኙን ተ/ሃይማኖት ለሹመት መረጠው ማለት ነው፡፡

ጾማችንን በትህትናችን ሰይጣንን ድል ነስተን ልዕልና የምናገኝበት ያድርግልን፤ መልካም ጾመ ማርያም ለኦርቶዶክሳውያንና ካቶሊካውያን ጸዋምያን! በትንሣኤዋ ያገናኘን!