የዓርብ ጨዋታ፡- ሃይማኖት ታመመ…ዓለም ዘማ ሆነች!


(በአማን ነጸረ) #1

በአማን ነጸረ

ርእሳችን ከጌቴ ገሞራው መወድስ ተወሰደች፡፡ እምነት/እውነት አንድ ብቻ ሆኖ ሳለ በዓለም ላይ የእምነት መብዛት (አሄሄ! መተማመን ሳይኖር የእምነት በያይነቱ መራባት! ግሩም! ) ቢደንቃቸው እንዲያ ተቀኙ፡፡ ግእዛችን ‹‹እምነት››ና ‹‹ሃይማኖት›› ለሚል አከፋፈል አይጨነቅም፡፡ ‹‹ሃይመነ–አሳመነ››፣ ‹‹ሃይማኖት–ማመን››፤ወይም‹‹አምነ–አመነ››፣ ‹‹አሚን/እምነት›› ብሎ ሲያበቃ በየመጻሕፍቱ እያቀያየረ ይጠቀማቸዋል፡፡ ግእዙ ‹‹ሃይማኖትክ አሕየወተከ›› ሲል ‹‹እምነትህ አዳነህ›› ማለቱ ነው፡፡ ‹‹አሚንሰ መሠረት ይዕቲ›› ሲልም እንዲሁ ስለ እምነት ነው፡፡ ባሕላችን ሃይማኖትን ከሀቀኝነትና ከምግባር አደላዳይነት ጋር ያያዘዋል፡፡ ‹‹ሃይማኖት ዘይብሉ ሰብን፣ ልጓም ዘይብሉ ፈረስን ሐደ–ሃይማኖት የሌለው ሰውና ልጓም የሌለው ፈረስ አንድ ናቸው፤›› ይላሉ ትግራውያን የሃይማኖትን ምግባር አደላዳይነት ለመግለጽ፡፡ ‹‹እከሌ እኮ በሃይማኖቱ የቆመ ነው፤›› ከተባለ ሀቀኛ ነው ማለት ነው–ታማኝ፡፡ ማመንና መታመን የአፍና የተግባር ሥያሜዎች ናቸው፡፡ ‹‹ማመን በልብ፣ መታመን በተግባር›› ይላል በዚህ በኩል http://www.mekrezetewahdo.org/2014/09/blog-post_15.html#more ወንድማችን ገብረ እግዚአብሔር ኪደ፡፡ ‹‹ ‹ማመን› [to believe God] ማለትም ይኾንልኛል ይደረግልኛል ብሎ መቀበል፤ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ተስፋ ማድረግ፤ አለመጠራጠር ማለት ሲኾን፤ ‹መታመን› [to believe in God] ማለት ደግሞ ያመኑትን እውነት በሰው ፊት በአንደበት መመስከርና በተግባራዊ ሕይወት መግለጥ ማለት ነው፡፡ ››

ማመን ከእውቀትና ከምክንያት በላይ መልካም ፈቃድና ፍላጎት ይጠይቃል፡፡ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ ‹‹የማምነው ለማወቅ እንድችል ነው–I believe in order that I may know›› ይላል፡፡ ሮማዊው ቅዱስ ኦገስቲን በበኩሉ ‹‹በነገረ ሃይማኖት ረገድ ዕውቀት በምክንያት አትወሰንም፤በልብ መሻት እንጂ…እምነትን የተመለከተ አመክንዮ በነጠላ ግለሰብ አይደመደምም (በማዕከላዊት) ቤተ ክርስቲያን እንጂ-- [to believe] is an act of intellect determined not by the reason, but by the will….the final authority for the determination of the reason in faith lies not with the individual, but with the Church itself.›› ይላል፡፡ የቅ/ኦገስቲን ፍራቻ ሃይማኖታዊት እውነት/ጽድቅ (በግእዝ ‹‹እውነት›› =‹‹ጽድቅ››) ግለሰባዊ በሆነች ቁጥር የማኅበረ-ምዕመናን አንድነት በግለሰቦች ፍላጎት ተቦርቡሮ ይላላል ይመስላል፡፡ (የሃይማኖትንና የአመክንዮን ተዛምዶ ከፈረንጅ ሐተታ ተነሥቶ በመጠኑ ገፋ አድርጎ ለማገናዘብ http://www.iep.utm.edu/faith-re/ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ ).የኛም ሊቃውንት የኦገስቲንን ፍራቻ ይጋሩዋታል፡፡ ሐሳቦቻቸውን በተራ እንይ፡፡

##1. ሃይማኖት ታመመ…ዓለም ዘማ ሆነች!

ሀ. ሃይማኖት ታመመ!

የጌቴ ገሞራው መወድስ 2 አጫጭር ግን ጥስ…ቅ ያሉ ሐሳቦችን ታነሳለች፡፡ የመጀመሪያው ሐሳብ ‹‹ሃይማኖት ታመመ፡፡ ለሞት ደረሰ፡፡ ሊቃውንቱም ያክሙት ዘንድ ከግራ ቀኝ ተሰባሰቡ፡፡ ጠዋትና ማታ በአንብቦ-መጻሕፍት እየጸለዩ በትርጓሜ-ውሃ አጠመቁት፡፡ ሕይወት አልዘራም፡፡ ባለሥራዮች (መድኃኒተኞች) ዕቡያን ካሕናት በአስማት አጥፈተውታልና›› ይላል፡፡ ኅብሩ ‹‹አስማት›› የሚለው ቃል ነው፡፡ በግእዝ ‹‹ስም›› ወደብዙ ቁጥር ሲቀየር ‹‹አስማት›› ይባላል፡፡ በዚህ አምሳል ሁሉም ለየሃይማኖቱ መጽሐፍ በማገላበጥ አዳዲስ ሥሞችን እየሰጠና በትርጓሜ እያበዛ ሃይማኖትን ታማሚ አደረገው፤‹‹ሐኪም በዝቶ በሽተኛ ሞተ›› ነው ምስጢሩ፤‹‹ተርጓሚው በዝቶ ሃይማኖት ታመመ››፡፡ ይላሉ’ኮ! በዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ›› ውስጥ ያሉ አንዲት ገጸ ባሕሪ ‹‹ወትሮም ሃይማኖትና መጣፍ አጥፊና ጠፊ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ ሊቁም…

ሊቃውንተ-ጽግም፡ወይምን፤እለ-ተጋብኡ፤
በእንተ-ሃይማኖት፡ዘሐመ፤ወበጽሐ፡ለመዊት፣
በጽባሕ፡ወሠርክ፤እንበለ-እረፍት፣
እንዘ-ያነብቡ፡መጻሕፍተ፤
አጥመቅዎ፤በማየ-ትርጓሜ፤ወአልቦ፡ሕይወት፣
እስመ-ዘይትኤበዩ፡ካሕናት፣
ዐቀብተ-ሥራይ፡ንባብ፤አጥፍእዎ፡በአስማት፡፡

… ይላሉ፡፡

###ለ. ዓለም ዘማ ሆነች!

2ኛው የመወድሱ ሐሳብ ‹‹ቆንጅዬዋና ጉረኛዋ ዘማዊት ዓለም የወለደችውን ልጅ/ሃይማኖት አባት ማንነት ማወቅ አልቻለችም፤ቀሳጥያን ሌሊቱን አድረውባት ሲወጡ፣ መሸተኞቹ የሥጋ ሊቃውንት ይገባሉና›› ትላለች፡፡ ማብራሪያ ይታከልባት፡፡ ሴተኛ አዳሪ የሆነች ሴት ከየ<ፍትወተኛ>ው ስትተኛ (እንትን ካልተጠቀመች) ልጇን ከማን እንዳረገዘች ለመረዳት ችግር ይገጥማታል፡፡ የልጇን አባት ለማወቅ ፈተና ይሆናል፡፡ (የጎጃሙ አጎቴ ለጥየቃ መጥቶ ‹‹በቀለ›› የሚል የአባት ሥም ቢበዛበት ‹‹አንተዬ! ከምድር የወጣ ይመስል ውሪውን ሁሉ እከሌ ‹በቀለ› የሚሉት የአባቱ ሥም ተዘንግቷቸው ነው? ወይስ እናቲቱ ከማን እንደጸነሰች ጠፍቷት ነው?›› ብሎ አስደንግጦኛል፡፡ ሆ! አጎቴ’ኮ የሚናገረውን አያውቅም! የስንቱን ጀግና አባት መጠሪያ! )፡፡ ህም! ሊቃችንም፡- ‹ከወጭ ወራጁ ጋር አሸሼ ከምትለው ዓለም ጋር ዳንኪረኛው በዝቶ በእሷ ውስጥ የሚፈለፈሉ ሃይማኖቶችን መገኛ አባት ለማወቅ አወከን› ነው እሚሉ፡፡ ይቀጥሉማ ጌትዬ…

…ዓለምሂ፡ዘማ-ተዝህሮ፤ዘአርአያሃ፡ሠናይት፣
ኢያእመረት፡ወላዲሁ፤ለዘወለደቶ፡ሃይማኖት፣
እንዘ-ይወጽኡ፡ነግህ፤ዘበውሳጤሃ፡ሰረቅት፣
እስመ-ሠርክ፡ይበውኡ፤ነጋድያነ-ባሶር፡ሊቃውንት፡፡

ለዚች ቅኔ ማጀቢያ መዝሙር ይፈለግላት ቢባል የሊቀ ዲያቆናት ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ መዝሙር ልክክ ይላል፡፡

መጽሐፍ ቅዱሱንስ፣ ሁሉም ያነበዋል፣
በዚህ ብቻ አይበቃም፣ ተርጓሚ ያሻዋል፡፡ …

የተርጓሚ አስፈላጊነትማ አይጠረጠርም፡፡ ችግሩ መተርጉማን አልስማማ እያሉ፡፡ ቃላትን ሞጭጨው ወዲህና ወዲያ ሲጓተቱ ‹‹አሐቲ›› ሃይማኖት እንደ ጨርቅ ተበጣጠሰች፡፡

##2. የቄርሎስ ሃይማኖት የዕብድ ጨርቅ ሆነች!

እንዲህ የሚለው ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ነው፡፡ እንዲህ ማለቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁ ከመጋቤ ብሉይ ሠይፈሥላሴ ዮሐንስ ነው፡፡ በ1990ዎቹ ‹‹ዘመቻ ፊልጶስ›› የተባለ ለተሐድሶዎች አጸፋ የተዘጋጀ ሥልጠና በሰጡን ጊዜ የነገሩን ነው፡፡ በንግግሮቻቸው መካከል ቅኔ ጣል ማድረግ ይወዳሉ፡፡ ይጣፍጥላቸዋል፡፡ እና ነገሩን፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡- ንጉሥ ሰሎሞን ሲፈጥረው መፍቀሬ-አንስት ነው፡፡ የሴት ነገር አይሆንለትም፡፡ ሀገርና ሃይማኖት ሳይለይ ይሄዳል፤ያዳርሳል፡፡ እንደ አጋፋሪ እንደሻው ሲሄድ-ሲሄድ-ሲሄድ ጭራሽ ከፈጣሪው ርቆ ቁጭ አለ፡፡ በሴት ፍቅር ተነድፎ ለጣዖት ማሳጠኛ፣ መሠውያ፣ መስገጃ ሠራ፡፡ ለፈጣሪውና ለሕዝቡ የገባውን ቃል ዘነጋ፡፡ ቀናኢው አምላክ ቀና፡፡ ቁጣው ነደደ፡፡ ነደደ፡፡ ‹‹ሰሎሞንን አለው፡- ይህን ሠርተኻልና፣ ያዘዝኹኽንም ቃል ኪዳኔና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትኽን ከአንተ ቀድጄ ለባሪያኽ እሰጠዋለኹ፡፡ /1ኛ ነገሥት 11/፡፡ ››፡፡ (ቀ.ኃ.ሥ እና መንጌ መካከል እንዲህ ያለ መንግሥት የመቅደድ ትንቢት ይኖር ይሆን? እንጃ! ) እሱ የተናገረውን አያስቀር! ከሰሎሞን ኤፍሬማዊ ባሪያ የሚወለደው ኢዮርብዓም በጌታው ሰሎሞን ላይ አመፀ፡፡ ኢዮርብዐምና ነቢዩ አኪያ በመንገድ ተገናኙ፡፡ ነቢዩ የለበሰውን ዐዲስ ልብስ ለ12 በጣጠሰው፡፡ ትርጉሙ ‹‹የሰሎሞን መንግሥት ለ12 ተበጣጠሰች›› ማለት ነበር፤ያው የግዛት መገንጠል ጥንተ-ታሪክ የተወጠነው ከዚህ ጀምሮ ነው፤አንቀጽ 39 የምታጠኑ ከዚህ ጀምሩማ! /1ኛ ነገ.12/፡፡ (የሰሎሞን ነገር ሲታሰብ ሀገር ከመገነጣጠል ጀርባ ብዙ ቆነጃጅት፣ አንድ ቃሉን ያጠፈ ዘማዊ መሪ፣ አንድ በአስተዳደር የተበደለ ሕዝብ፣ አንድ ለመቅሰፍት የተላከ ‹‹ባሪያ››ና አንድ የተቆጣ እግዚአብሔር አይጠፋም ብሎ መጠርጠር ያስቀስፍ ይሆን?ሆ! ምኑን አሳሰበኝ አያ?! )፡፡ ነገሩ በሃይማኖትም ያው ነው፡፡ አንድ ከምግባርና ሃይማኖት ያዳጠ (faith እና ፌዝ ያልለየ! ) ካሕን፣ ለስሑቱ ካሕን ውዳሴ ከንቱ ደርዳሪ ደባትር፣ በእነሱ የተማረረ ምዕመን፣ ለመጽሐፍ ቁንጸላ የተላከ ቀሳጢ፣ ብሶት ተተግኖ ለሚጮኽ ቀሳጢ የምታጨበጭብ ዘማዊት ዓለም ከያንዳንዱ የሃይማኖት ክፍፍል ጀርባ ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ ጠርጥር!

ክፍለዮሐንስ ይሕን ጠርጥሯል፡፡ ለጥርጣሬው የብሉዩን ታሪክ ሰም፣ በተረፈ-አርዮሳውያን የተፈተነችውን ርትዕት የቄርሎስ ሃይማኖት ወርቅ አድርጎ ተቀኘ፡፡ የቄርሎስን ሃይማኖት በሰሎሞን ምድራዊ መንግሥት መሰላትና ራራላት፡፡ በጉባዔ-ኬልቄዶን ማግስት ለ12 ስትከፋፈል ታይታው ‹‹የቄርሎስ ሃይማኖት የዕብድ ጨርቅ ሆነች፤እንደ ነቢዩ አኪያ ልብስ ንጉሥ (ዳኛ) በሌለበት ተበጣጠሰች፤›› ሲል ተቀኘባት፡፡ እንዲህ…

ሃይማኖተ-ቄርሎስ፡ኮነት፡ግማዳተ-ዐብድ፤
ወኁልቈ-ተመትሮ፡አብዝኃት፤ኀበ-ኢሀሎ፡ንጉሥ፣
ካህነ-ደብረ-ኤፍሬም፡ቅድመ፤እምዘመተራ፡ነኣስ፣
ወአመ-ኢዮርብዓም፡ለምሳሌ፤
በእደ-ነቢይ፤ዘተሰጠት፡ልብስ፡፡ …

ሃይማኖት መበጣጠሷ እንደ ሰሎሞን ተረግማ እማደል፡፡ ሁሉ በየራሱ እየተረጎማት እንጂ፡፡ በራሱ ለሐሳቡ እንድትስማማ አድርጎ ተርጉሟት ሲያበቃ ‹‹ሠለስቱ ምዕት እንዳሉት…›› ይላል፡፡ ጸጋውም፣ ቅባቱም፣ ተዋሕዶውም፣ ካቶሊኩም ‹‹ሠለስቱ ምዕት እንዳሉት…! ››

##3. ሠለስቱ ምዕት እንደ ሽፋን!

የቅኔውን ባለቤት አላወቅነውም፡፡ ምንጩ ግን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ናቸው፡፡ እሳቸው የጸጋ ሃይማኖትን በተረኩበት ‹‹ሃይማኖተ አበው›› የተሰኘ መጽሐፋቸው ቅኔውን ‹‹ስለካራና ቅባት›› የተነገረ በሚል ወስነው አስቀምጠውታል፡፡ ሆኖም የቅኔው ምስጢር ሲታይ ተግሳጽነቱ ለዚህና ለዚያ ተብሎ አልተወሰነም፤ለሁሉም ይሆናል፡፡ የትርጓሜው መንፈስ፡- ‹‹አርዮስና መምህሩ ወልድ በቀዳማዊ ልደቱ ፍጡር ነው የሚል ቅዠታቸውን በሐዋርያት አመካኙ፤ዛሬም የነሱን አመጻ ይፈጽም ዘንድ ሰው ሁሉ በቤቱ ቁጥር ልክ የሸነሸናትን ሃይማኖት እውነት ለማስመሰል የሠለስቱን ምዕት ሥም ይቀባባታል፤›› ማለት ነው፡፡ ሥላሴዋ ቅኔ ትምጣ…

አርዮስ፡ወመምህሩ፤
ላዕለ-ሐዋርያት፡አመክነዩ፤
ብሂለ-ፍጡር፡ወልድ፤በቀዳማዊ፡ልደቱ፣
ለአጽድቆ-ህልም፤ነገሮሙ፡ከንቱ፣
ዮምኒ፡ይፈጽም፤አመጻ፤በመስፈርተ-እሉ፡ክልኤቱ፣
እንዘ-ፍናዊሃ፤በኁልቈ-ቤቱ፣
ሰብእ፡ኵሉ፤ለሃ ይማኖቱ፣
ይቀብዕ፤ሥመ-ምዕት፡ሠለስቱ፡፡

ትላለች ቅኔዋ፡፡ እርግጥ ይቺ ቅኔ የምትመለከተው በትውፊትና ሥልጣ ክሕነት የሚያምኑ የሚያምኑ የክርስትና ዘውጎችን ነው፤‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ›› የሚሉማ ስለሠለስቱ ምዕት የ325 ዓ.ም ጉባኤ፣ ዶግማና ቀኖና ምን ገዷቸው?! አይገዳቸውም፡፡ ሁሉ ካሕን ነዋ! ብለው አልነበር?! ‹‹አቶ ለውጤም፣ አቶ ሸንቁጤም ቄስና አጥማቂ ሆነው አረፉት፤›› ብለው ነበር ሊቁ በዘመነ ቀ.ኃ.ሥ፤‹‹ሀገር የጋራ፣ ሃይማኖት የግል›› ሲታወጅ፡፡

##4. ሀገር የጋራ፣ ሃይማኖት የግል?! …ወይስ…ሀገር የግል፣ ሃይማኖት የጋራ?!

ቀስስስሰ! ዓርብ ነው፡፡ ቆ…ይ! ነባራዊው ሀቅ አልጠፋንም፤ለጨዋታ ነው፡፡ እንጫወት! ቀ.ኃ.ሥ ‹‹ሀገር የጋራ፣ ሃይማኖት የግል፤የምን ‹እኛ ብቻ ትክክል?! ›…›› እያሉ በቤ/ክ ዓውደ ምሕረት ሳይቀር ሰበኩ፡፡ በዚሁ መንፈስ ለፕሮቴስታንታውያን የሬዲዮ ጣቢያ ፈቀዱ፡፡ ‹‹ብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ›› ተከፈተ፡፡ ሬዲዮው ሲጀምር ከነቢዩ ኤርምያስ ምዕራፍ 29 ጠቅሶ ‹‹ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ›› የሚል ኃይለ ቃል ለስርጭቱ መክፈቻነት ተጠቀመ፡፡ አያችሁ?! ነገር ፍለጋ! ሆ! ሀገሪቱን እስከዛሬ ቃለ እግዚአብሔር ሳይነገር የኖረባት አድርጓት! ኧግ! ኧግ! ኧግ! ሰውየው ተቆጡ፡፡ ትግህት ልጃቸው እንደነገረችን አለቃ አያሌው ተበሳጩ፡፡ ‹‹የሬዲዮ ጣቢያው ኃላፊዎች ያሰሙት ዐዋጅ ለሺ ዓመታት በአምልኮተ-እግዚአብሔር ጸንታ የኖረችውን የአገራችንን የሃይማኖት ቅርስና ታሪክ የካደ ሥላቅ ነው፤›› ሲሉ ተቃወሙ ትለናለች የአለቃ አያሌውን የሕይወት ታሪክ የጻፈችው ልጃቸው ወ/ሮ ሥምረት አያሌው–በ‹‹አባቴና እምነቱ›› መጽሐፍ፡፡ (‹‹አዲስ እረኛ፣ ከብት አያስተኛ›› ሳይተርቱ አይቀሩም፤ስገምት! )

በወቅቱ ተቃውሞ ያሰሙት አለቃ ብቻ አልነበሩም፡፡ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሂ በአደባባይ ንጉሡን በቅኔ ሞግቻለሁ ይላሉ፡፡ ሙግቱ፡- ‹‹የአበው ሃይማኖትማ የግላችን አይደለም፤ለነባሩም ለመጤውም (ድንበር ተሻግረው የመጡትን ግብጻውያኑን ጳጳሳትና 9ቱ ቅዱሳንን፣ ወይም የኛዎቹን ድንበር ተሻጋሪዎች ሙሴ ጸሊምንና ጃንደረባውን እያሰቡ መሆን አለበት! ) የጋራችን እንጂ፡፡ ሀገር ግን (በመርህ ደረጃ ለመጤ ሳትሆን) ለዜጋዋ ብቻ ናት፡፡ አሁንም አጤ ተብለህ የምትጠራ ንጉሥ ሆይ! ቃልህን በቃልህ እንዳለ ትሽረው ዘንድ እንለምንሃለን፡፡ (ለጠላቶቿ) በተፈጥሮዋ መራር ሆምጣጤ የሆነችው ሀገራችን (ያንተን ‹ሃይማኖት የግል፣ ሀገር የጋራ›) ባትቀበል ኖሮ ጰንጠቆስጤ ባልገባብን ነበር፡፡ ለአንዳንዱም ‹ለውጤ ባይሰብክ፣ በሸንቁጤ ዳግማዊ ጥምቀት የማንጠመቅ› ባልመሰለው፤›› እያሉ መዓርግ አልባ አዳዲስ የሃይማኖት ሰባክያን በንጉሡ ፈቃድ መበራከታቸውን ተቃውመዋል፡፡ ለያኔው ዘመን ማዘከሪያ መወድሳቸው ሳይሸራረፍ ይሰማ…

ሃይማኖተ-አበው፡ኢኮነት፡ለባሕቲትነ፤
ዳእሙ፡ይዕቲ፤ለነባር፡ወለመጤ፣
ባሕቱ፡ሀገር፤ለባሕቲቱ፡ለቢጤ፣
ወእምዝ፡ንስእለከ፤ ንጉሠ-ነገሥት፤ዘትሠመይ፡አጤ፣
ቃልከ፡በቃልከ፤ኀበ-ወጽአ፡ይግባእ፤እንበለ-አሐቲ፡ውላጤ፣
መራርሂ፡ሀገሪትነ፤እንዘ-በተፈጥሮ፡ሆምጣጤ፣
እመ-ኢያክብረቶ፡ለቃልከ፤እምኢቦአ፡ጰንጠቆስጤ፣
ወዘይመስሎ፡ለዝንቱ፤እመ-ኢሰብከ፡ለውጤ፣
ጥምቀተ፡ዳግማዌ፤እምኢተጠመቅነ፡በሸንቁጤ፡፡

አደራ፡- ‹‹ሸንቁጤ››ና ‹‹ለውጤ›› የምትባሉ ዘመዶቻችን ካላችሁ በብሔር ማንነታችን የተነሣ በደባትር ተሰደብናል የሚል ፋይል እንዳትከፍቱብን አደራ፤ለጨዋታ ነው፤(ሸንቁጤና ለውጤ የአማርኛ ስሞች ባይሆኑ ቅኔዋ ‹የነፍጠኛ ሴራ› ትባል ነበር፤እግዜር አወጣት፤አወጣን! እዳ’ኮ ነው! በተናገርን ቁጥር ‹እከሌን ይከፋው ይሆን?፣ ዘመዶቻችን ‹5ኛ ረድፍ› ይሉን ይሆን?› እያልን፣ እንደ ፈንጅ አምካኝ ‹‹እንጣጥ! ›› እያልን በሰቀቀን ማውጋት ፍርጃ ነው! ሯ! )፡፡