የዓርብ ጨዋታ፡- በፈራጁ የሚፈርዱ ቅኔያት…‹‹እንኳን ሰቀሉት፤የጁን አገኘ!››


(በአማን ነጸረ) #1

ወጋችን ከምናኔ ጋር ትገናኛለች፡፡የተቀሰቀሰችው በካኽሊል ጂብራን ‹‹ኢየሱስ፡ወልደ እጓለ እመሕያው›› (JESUS: THE SON OF MAN) በተሰኘው ምጥን የምናብ ሥራ ውስጥ ካለች ወግ ነው፡፡በተራ ቁጥር 2 ተተርጉማ የምትቀርበው ሚጢጢ ወግ 3 ሰዎችን አስታወሰችኝ፡፡

##1. የሦስት መናንያን ወግ

  1. የአቡነ ቴዎፍሎስ አባት ዓለማዊ ሥማቸው ‹‹ጀምበሬ ውቤ›› ይባል ነበር፡፡ለዓመታት የናፈቋቸውና አዲስ ዓለም ማርያም የመጻሕፍት ትርጓሜ ይማሩ የነበሩት ልጃቸው ተማሪ መልእክቱ (የኋላው አቡነ ቴዎፍሎስ) ከጉባኤ ቤት ተመልሰው ይጠይቁኛል ብለው ሲጠብቁ ደ/ሊባኖስ መንኩሰው ‹‹አባ መልእክቱ›› መባላቸውን ሰሙ፡፡በጆሮ የሰሙትን በፎቶ አረጋገጡ፡፡ወዲያውኑ ወሰኑ፡፡‹‹በቃ!ልጄ በናቀው ዓለም አልኖረም፤›› ብለው እሳቸውም ጠፉ፡፡አድራሻቸውን አጠፉ፡፡መነኑ፡፡ሥር ኢየሱስ በተባለ ገዳም መነኰሱ፡፡ስማቸውን ቀየሩ፡፡‹‹ጀምበሬ›› መባላቸው ቀርቶ በምንኩስና ስማቸው ‹‹ወልደ ማርያም›› ተባሉ፡፡ቤተሰብ 5 ዓመት ፈልጎ አጣቸው፡፡በ5ኛው ዓመት መቃብራቸው በመነኑበት ገዳም ተገኘ፡፡መርዶ ለቤተሰብ ተነገረ፡፡ልጅዬው አባ መልእክቱ ይሕን ሲሰሙ ልባቸው ተነካ፡፡ለአባታቸው ምናኔ መታሰቢያ እንዲሆን የአባት መጠሪያቸውን ከ‹‹ጀምበሬ ውቤ›› ወደ ‹‹ወልደማርያም ውቤ‹‹ አዙረው የመዝገብ ሥማቸውን ‹‹አባ መልእክቱ ወልደማርያም ውቤ›› አሰኙ፡፡ባላገር፡-

እረ ልጅ፡እረ ልጅ፤እረ ልጅ ገመዱ፣
ቤትማ ምን ይላል፤ዘግተውት ቢሄዱ፡፡

ይላል፡፡ልጅ የወላጅን ልብ ይከፍላል ለማለት፡፡ብሂሉ ለአቶ ጀምበሬ አልሠራም፡፡ልጃቸው ቀድመው ቆብ ጫኗ!በልጃቸው ምናኔ ከዚህ ዓለም እስራት ተፈቱ፤ለክርስቶስ ታሰሩ፡፡በየመልእክቱ መግቢያና መደምደሚያ ‹‹ዘእምጳውሎስ ሙቁሑ ለክርስቶስ–ከክርስቶስ እስረኛው ጳውሎስ›› የሚላት ነገር አለችው ቅ/ጳውሎስ፡፡

  1. ስለ አባትና ልጅ ሲነሣ እስከ ፍጻሜ-ሕይወቴ ፍቅሩ የማይወጣልኝ አባቴ ታወሰኝ፡፡አባቴ ለአባቱ አንድ ወንድ ልጅ ነው፡፡ሕልሙ መናኝ መነኩሴ መሆን ነበር፡፡ሊመነኩስ ጠፍቶ ሄደ፡፡አያቴ ሰማ፡፡ካለበት ሄዶ አመጣው፡፡ድጋሚ ጠፋ፡፡አያቴ ድጋሚ ፍለጋ ወጣ፡፡ባዶ እጁን አልነበረም፡፡ረጅም ምንሽር ይዞ አባቴ ካለበት ገዳም ሄደ፡፡አስጠራው፡፡መጣ፡፡ነገረው፡፡ሁለት ጥይቶችን አውጥቶ ነገረው፡፡‹‹ያለኸኝ ወንድ ልጅ አንተ ብቻ እንደሆንህ ታውቃለህ፤ፍሬህን ማየት አለብኝ፤የወላድ መካን መባል አልፈልግም፤ስለዚህ ተመለስ፤አግባ፤ሚስት አጭቼልህ ድግስ እያሰናዳሁ ነው፤እምቢ ካልህ በዚች ጥይት አንተን፣በዚችኛዋ ራሴን እሸኛለሁ፤‹አባቴ ይሙት!› ብያለሁ፤ቃሌን እንደማላጥፍ ታውቃለህ፤ቀጥል…ወደፊት…›› አለና ልጁን ከገዳም ማርኮ ለኛ መወለድ ምክንያት ሆነ፡፡እዚህ ላይ የልጅ ገመድነት ቀርቶ ወፍራምና እቡይ የአባት ፍቅር ሰንሰለት ሆነ ማለት ነው–እረ አባት ገመዱ!

  2. በእድሜ ከኛ ቢበልም ጓደኛችን ነው፡፡ለእናቱ አንድ ነው፡፡አባቱን ስለማያውቅ በመምህራችን ነው የሚጠራ፡፡ጎበዝ ዜማ ተማሪ ነበር፡፡ቅኔም ተቀኝቷል፡፡ተክሌ አቋቋም እማራለሁ ብሎ ገዳም ወረደ፤ደብረ ሊባኖስ ሄደ፡፡በ3ኛው ዓመት የኔታንና እናቱን ጥየቃ መጣ፡፡አስቀድሞ የኔታ ቤት ደረሰ፡፡እናቱ ይሕን ሲሰሙ አላስቻላቸውም፡፡ዕለቱን የኔታ ዘንድ እንዳለ ልጃቸውን ለማየት መጡ፡፡አዩት፡፡ትክ ብለው አዩት፡፡አናቱ ላይ አስኬማ ጭኗል፡፡መንኩሷል፡፡ማን ይያዛቸው?! ‹‹እ…ሪ!ኡኡኡኡኡኡኡ…ልጄን…ልጄን!..መከንኩ!መከንኩ!..››ባለንበት ክው አልን፡፡ልብሰ-ምንኩስና ተጎናጽፎ እናቱንና የኔታን ሊጠይቅ የመጣው ጓደኛችን በብስጭት መንፈስ ግንባሩን ከስክሶ ፀጥ አለ፡፡‹‹አጽፉን/መጎናጸፊያውን ተርትሮ አለቀሰ…›› የሚሉ ገለጻዎችን በመጽሐፍ ነበር የማውቃቸው፤የዛ ቀን ባይኔ ዐየሁ፡፡የጓደኛችን እናት ነጠላቸውን ለሁለት በቅጽበት ሰንጥቀው ታጠቁት፡፡ጮኹ!ጮኹ!የኔታ እንደምንም ያዟቸው፡፡በግዝት አስፈራሯቸው፡፡ነጠላቸውን በአፋቸው ጭነው ተንሰቀሰቁ፡፡ተንሰቀሰቁ፡፡በስንት ብርታትና ማስፈራራት የኔታ ፀጥ አሰኙዋቸው፡፡እሳቸው ፀጥ ሲሉ ደግሞ ቀድም ተኮሳትሮ የነበረው መነኰስ ልጃቸው በጥልቅ ዝምታ ውስጥ እንዳለ ዕንባው ያለማቋረጥ ይፈስ ጀመር፡፡እናቱን ሳያማክር በመመንኮሱ ሳይስሰማው አልቀረም፡፡የኔታ ጎበዝ ናቸው፡፡እመቤታችን አንድ ልጇን በከብቶች በረት ወልዳ የግብፅ ስደቱን መጋራቷን፣ስቅለቱን ዐይታ መሳቀቋን አስታውሰው ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ በዳግም ትንሣኤ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዳለን መክረው አጽናኑዋቸው፡፡የ12ቱን ሐዋርያትና 120ው ቤተሰቦች ከቤትና ንብረት ተነጥሎ ጌታን መከተል እያብራሩ አረጋጓቸው (በማረጋጋቱ መካከል ግን የጓደኛችን እናት ‹‹የኔታ!ጌታ 120 ልጆችን ከእናቶቻቸው ነጠለ ነው የሚሉኝ?አሀ…! ለካ 120 እናቶች አልቅሰውበት ነው የአንድዬ ስቃዩ የበዛ!አያችሁ የእናት ጡር?!›› ብለው ድንጋጤና ፍርሃት ያለበት ሳቅ አስቀውናል)፡፡የክርስትና ትርጓሜ አንዱን ለማመን ሌላውን መካድ ሆኖ ይስሰማኛል፡፡ነፍስን ለማዳን ሥጋን መካድ፣የሰማዩን ለማግኘት የምድሩን መመነን (መናቅ) ግድ ይላል፡፡እግዚአብሔርን ስታምን ‹‹እክህደከ ሰይጣን!›› ብለህ ነው፡፡እሱን ስትከተል እናትና አባትህን ሁሉ ትተህ ነው፡፡አብርሃም ‹‹ጻእ፤ወተፈለጥ፤እምአዝማዲከ…›› እንደተባለው፡፡ይሕን መወሰን ቀላል አይደለም፡፡ውሳኔው በራስ ላይ ብቻ አይደለማ!በሚወዱት ወላጅ ላይም መጨከንን ይጠይቃል፡፡በዚያውም ላይ የራስ ብቻ ሳይሆን የወላጅ አንጀትም እንዲጨክን መጸለይ ግድ ነው፡፡ካልሆነ የገሊላዋ መበለት ታሪክ ይከሰታል፡፡

2. “ጨካኙ ኢየሱስ - Jesus the Cruel” የምትለው የገሊላዋ መበለት (A widow in Galilee)

ካኽሊል ጂብራን ሊባኖሳዊ ክርስቲያን (ካቶሊክ) ደራሲ ነው፡፡ጌታን በዘመነ-ሥጋዌው በነበሩ ሕያውና የፈጠራገጸ ባሕሪነት ከተለያየ አንጻር እያየ ሲያቀርበው ያስደምማል፡፡ከነዚህ ነጻርያን/ርያት ገጸ ባሕርያት አንዷ የገሊላዋ መበለት ናት፤አንድ ልጇ የናዝሬቱ ኢየሱስን ተከትሎ ጥሏት የሄደ መበለት፡፡የጌታ ፍቅር ምን ያሕል ጥልቅና ጥብቅ እንደሆነ ለማሳየት ደራሲው መበለቷን በብእሩ ያስተክዛታል፡፡ምስኪኗ መበለት በመጽሐፉ ገጽ 65 ወይም በዚህ http://4umi.com/gibran/jesus/widow እሷን ትቶ ጌታን ስለተከተለው ልጇ እንደሚከተለው ታንሾካሹካለች፤በአማርኛ እንስማት…

‹‹ልጄ፣የበኵር ልጄ ለኔ ለእናቱ አንድ ነው፡፡የኢየሱስን ድምጽ እስኪሰማ ድረስ በአትክልታችን ሥፍራ ይባትል ነበር፡፡ልጄ ድንገት መንፈሱ ተቀየረ፡፡አዲስ፣ከዚህ ዓለም ያልሆነ ልዩ መንፈስ ተሞላ፡፡ማሳችንንና የአትክልት ቦታችንን እርግፍ አድርጎ ተወው፡፡እኔንም ዘነጋኝ፡፡ከንቱ የጎዳና ከርታታ ሆነ፡፡ያ!የናዝሬቱ ኢየሱስ ጨካኝ ነው፡፡ርኅሩኅ ቢሆንማ እንዴት ልጅን ከእናቱ ይለያል?ልጄ ለመጨረሻ ጊዜ ‹ከደቀመዛሙርቱ መካከል ካንዱ ጋር ሀገረ-ሰሜን መጓዜ ነው፤ሕይወቴ በናዝሬት ይሆናል፡፡ወልደሽኛል፡፡ውለታሽ አለብኝ፡፡ግን ደግሞ መሄድ አለብኝ፡፡ለም መሬት፣ወርቅ፣ብር ይዤብሽ አልሄድም፡፡ምንም አልወስድም፡፡› አለኝ፡፡ይሕን ተናግሮ ሄደ፡፡አሁን ሮማውያንና ሊቃነ ካሕናት ኢየሱስን ያዙት፡፡ሰቀሉት፡፡ደግ አደረጉ፡፡እናትና ልጅ የሚያቆራርጥ እሱ መለኮታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ልጆቻችንን ወደ አሕዛብ ከተሞች የሚያሰማራ ወዳጃችን ሊሆን አይችልም፡፡ልጄ እንደማይመለስ አውቃለሁ፡፡ዐይኑ ነግሮኛል፡፡በዚህ የተነሣ ባልታረሰ ማሳ፣ባልተኮተኮተ የአትክልት ሥፍራ መካከል ብቻዬን እንድኖር ያደረገኝን የናዝሬቱ ኢየሱስ አልወደውም፡፡የሚያወድሱትን ሁሉ እጠላቸዋለሁ፡፡በቅርቡ ‹የኔ እናት፣አባትና ወንድሞች ቃሌን ሰምተው የሚከተሉኝ ናቸው› ማለቱን ነገሩኝ፡፡ለምንድን ነው የእርሱን አሠረ-ፍኖት [መንገድ] ለመከተል ልጆች እናቶቻቸውን የሚተውት?ለምንድን ነው ገና ላልተጣጣመ [የሕይወት] ምንጭ የጡቶቼ ወተት ሙቀት የሚዘነጋ[ብኝ]?ለቀዝቃዛና ለማይመች ሰሜናዊ [የናዝሬት] ምድር ሲባል የጉያዬ [የጉንፌ/የእቅፌ] ሙቀት ለምን ይዘነጋል?አዬ!ያን ናዝራዊ አልወደውም፡፡እስከ ፍጻሜ-ሕይወቴ እጠላዋለሁ፡፡የበኵር ልጄን፣አንድያ ልጄን ቀምቶኛልና!››

ትላለች፡፡

መበለቷ ተቆጥታለች፡፡ንዴት ውስጥ ናት፡፡ባገራቸው ማሲንቆ ያለ አልመሰለኝም፡፡እናጽናናት፡፡በኛው መሪጌታ ፍቅሩ መዲናና ዘለሰኛ እንጽናናት፡፡ይቀጥሉ መሪ ማሲንቆውን ይይገዝግዙት፤ኧኸ…ኸኸኸኸኸኸ…ምነው ወዳጄ ምነው ብለው ይቀጥሉ… …

በርባን ቢሰቀል፤ኢየሱስ ቀርቶ፣
ምን ይጠቅመናል፤ሽፍታ ሞቶ፡፡
እንኳን ኢየሱስን፤ሰቀሉት፣
የሞቱን፤መድኃኒት፡፡…

##3. የእጁን አገኘ!

የገሊላዋን መበለት ድፍረት አድንቀን ሳንጨርስ የኛም ሊቃውንት በፈራጁ ላይ ፍርድ ሲያዥጎደጉዱ አገኘናቸው፡፡እንዲህ እያሉ፡- ‹‹ሰው እንደበደለ አይኖርም፤የጁን ያገኛል፡፡የበደሉን መስቀል ይሸከማል፡፡ከነቢዩ (ኤልያስ) ጋር የነቢዩ ጠላት (ኤልዛቤል) ተጣላች ብሎ ሰማዩን ለጉሞ ፍጡራንን በውሃ ጥም የቀጣው አምላክ (ባስጠማቸው ሰዎች) ልጆች መካከል (ቀራንዮ) ቆሞ ‹ተጠማሁ› አለ፡፡የኖኅን ዘመዶች በጥፋት ውሃ እንደቀጣ በውሃ ጥም ‹ተጠማሁ› እያለ ሞተ፡፡አዳምን አንግሦት ሲያበቃ የበለስ ፍሬ እንዳይበላ የከለከለው አምላክ ከበለስ ፍሬ አጥቶ ልምላሜዋን ተራገመ፡፡አዳምን በምድር አሜከላ ያሰቃየ አምላክ ስለአዳም በደል በአናቱ የእሾህ አክሊል ደፋ›› እያሉ በፈጣሪያቸው ላይ አንጋጠው ሲቀኙ (በቅኔ መጻሕፍት) አገኘናቸው፡፡ይሄው መወድሳቸው ኤግዚቢት ሆኗል፤ይሰማ…

ኢይተርፍ፡ሰብእ፤በከመ-ጌገየ፤
ዳእሙ፡ይጸውር፤ጌጋየ-ርእሱ፡መስቀለ፣
ፍዳ-በጽምዐ-ማይ፡ወልድ፤ጸላኢተ-ነቢይ፡አኅጐለ፣
አምጣነ-አስምዐ፡ጊዜ-ሞቱ፤
ኀበ-ደቂቆሙ፤‹ጸማዕኩ›፡ብሂለ፣
ወበማየ-አይኅ፡አዝማደ-ኖኅ፤ ሚ-ዘቀተለ፡ወልድ፤በምክንያተ-ማይ፡ተቀትለ፣
ለአዳምኒ፡አመ-አንገሦ፤ከመ-ኢይብላዕ፡አስካለ፣
ፍሬ-ዕፀ-በለስ፡ኢረከበ፤እስከነረገመ፡ሐመልማለ፣
እመኒ፡አሥዋክ፤በከርሠ-አዳም፡አብቆለ፣
በጌጋየ-አዳም፡ልሳነ-ሦክ፤ላዕለ-ርእሰ-ወልድ፡ተለዐለ፡፡

ብለው አንዱን የድንግል ልጅ አሙት፡፡ለነገሩ አንድዬን ባለቅኔዎቹ ሲያሙት ‹‹ሐሜት አይፈራም›› ይሉታል፡፡

##4. ወልድ ሐሜት አይፈራም!

‹‹ሐሜት ቢፈራማ ከሰማይ ድረስ ሁለቱን ጓደኞቹን ጥሎ ሥጋ ፍለጋ አይመጣም ነበር፡፡አሄሄ!አይ ስስት!ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል–ባሕቲቶ፡ዘበልዐ፣ይመውት፡ባሕቲቶ!››ይሉታል፤ይፈርዱበታል፡፡አብና መንፈስ ቅዱስስ ለምን አብረው አልሞቱም እኮ ነው!እንዴት ተወብርቶልናል አያ! ይሄን ሐሜት ያመነጩ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ ተሰደው በኢየሩሳሌም ያረፉት አለቃ ተክለጽዮን ናቸው፡፡እሳቸው ጭርስ ያሉ ሊቅ ናቸው፡፡ትውልዳቸው አንኮበር ነው፡፡ሙያቸው ከዚህ እስከዚህ አይባልም፤ጭርስርስ ያሉ ሊቅ ናቸው፡፡የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበቃላት ቅድመ-አያቱ እሳቸው ናቸው ይባላል፤አያቱማ አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስ ናቸው፤አባቱ ኪዳነወልድ ክፍሌ(ኪዳነወልድ ክፍሌ የአባት ሥም አድርገው የሚጠቀሙት የመምህራቸውን ሥም ነው፤በተመሳሳይ ፓትርያርካችን አቡነ ማትያስም የመምህራቸውን ሥም በአባት ሥምነት ይጠቀማሉ–ተክለማርያም ዓሥራት!)፡፡ታዲያ አለቆቻችን ተክለጽዮን፣ክፍለ ጊዮርጊስ፣ኪዳነወልድ ሁሉም በጸጋነት ይታማሉ፡፡እውቀታቸው ግን አይጠረጠርም፤በተለይ ተክለጽዮን ብዙ የተመዘገቡ ቅኔያት አሏቸው፡፡ ከነሱ አንዷ በቅኔ ቤት የሚበዝኁ ዜማ ማጥኛ የሆነችው ተከታዩዋ ጌታን የምታማ ሚበዝኁ ናት፡፡ይቀጥሉ አለቃ ተክሌ…

ሐሜተ-ክልኤቱ፡አኃው፤ዘኢፈርሀ፡ወልድ፤በልዐ፡በተከብቶ፣
ሥጋ፡ጥዑመ፤እንዘ-የዐፁ፡ኆኅቶ፣
ወፍሉጠ-ሞት፡ኮነ፤ባሕቲቶ፡ዘበልዐ፤እስመ-ይመውት፡ባሕቲቶ፡፡

ሊቃውንት ወልድ ብቻ ሳይሆን አብና መንፈስ ቅዱስም ለፍርድ መቅረብ ነበረባቸው ይላሉ፡፡ለዚህ ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነበረ ባይ ናቸው፡፡ግና ‹‹ምን ያድርጋል!አብርሃም ጉድ ሠራን!›› ሲሉ ይፀፀታሉ፡፡

##5. ሰዶምን ጉድ የሠራት አብርሃም ነው!

‹‹እህሳ!ሥላሴን ሸሽጎ እየመገበ አጥግቦ ነዋ ጉድ የሠራት፡፡ለሰዶም ሰዎች ምስክር ቆጥሮ አብርሃምን ማሳሰር ይገባቸዋል፡፡ሦስት ጎልማሶች ቤቱ አስገባ፡፡አበላቸው፡፡ጠገቡ፡፡መዐት(ፀብ) አነሱ፡፡እነሱ ባይጠግቡ በሰዶም ሕይወት ባልጠፋ!›› የሚሉት አቡነ ጴጥሮስ ዘጎንደር ናቸው፡፡እሳቸው የጳውሎስ፣የሐዋርያት መልእክታትና የሐዋርያት ሥራ አንድምታ ትርጓሜ ኅትመቶች ባለቤትም ናቸው፡፡አጫጭር መጻሕፍትም አሏቸው፡፡አድርጌ እንደምኮራባቸው፡፡የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሊቀ ሊቃውንት ነበሩ–አስተዳዳሪ፡፡ትውልዳቸው ጎጃም ነው፤ደብረ ኤልያስ፡፡በሥላሴ ላይ የፈረደች ደፋር ዋዜማ ቅኔ አለቻቸው፡፡ይቻትና(ታዲያ ፍርዱ በሰሙ እንጂ በወርቁ እንዳልሆነ መቼም መናገር አይጠበቅብኝም!)…

ለእደወ-ሰዶም፡እምደለወ፤
አሲረ-አብርሃም፡አብ፤እመ-ረከቡ፡ሰማዕተ፣
አብርሃም፤እምድኅረ-አጽገበ፤እደወ፡ሠለስተ፣
ጽጉባኒሁ፡እደው፤እስመ-አንሥኡ፡መዓተ፣
እመሰ፡ኢጸግቡ፤አሐደ፡ዕለተ፣
እምርኢነ፤በሰዶም፡ሕይወተ፡፡